|
Sunday, 02 March 2008 |
|
በሒልተን ሆቴል አንደኛው የመሰባሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ በሃገር ባህል የተሸመኑ ጨርቆች በተለያዩ ዲዛይንና በዘመናዊ መልኩ ለቤት ማስጌጫነት ተሰርተው ለእይታ ቀርበዋል፡፡ ሸማዎቹ በተለያየ ቀለምና በተለያየ ዲዛይን የጠረጴዛ ልብስ፣ የአልጋ ልብስ፣ ሻርኘ፣ ቦርሳ፣ ፎጣና ሌላም አይነት ምርቶች ተሰርተውባቸዋል፡፡
ለእይታ የቀረቡት የቤት ማስጌጫና አልባሳት ከጥጥ ብቻ የተሰሩ ሲሆን ከሃር ብቻ የተሰሩ ጌጣጌጦችንም አስተውለናል፡፡ እነዚህን አልባሳትና ጌጣጌጦች ለውጭ ገበያ ጭምር የሚቀርቡ ሲሆን የሚሌኒየሙ ተሸላሚ በሆኑ ሴት ላኪዎች የተመረቱ ናቸው፡፡
ያለፈው ረቡዕ የሽልማቱ አሸናፊ የሆኑት ስድስት ሴቶች በብሔራዊ ቤተመንግሥት ሽልማታቸውን ተረክበዋል፡፡ የሽልማቱ አሸናፊ የሆኑትን ሴቶች አነጋግረናቸዋል፡፡
ወ/ሮ ሣራ አበራ የሙያ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ባለቤት ናቸው፡፡ በዕለቱ የዋንጫ ሽልማት ያገኙት አንደኛ በመውጣት ነበር፡፡
ወ/ሮ ሣራ የፋሽን ዲዛይነርነት ተምረው በአልባሳት ዲዛይነርነት ለበርካታ ዓመታት እንደሰሩ ይናገራሉ፡፡ ሣራ ጋርመንት በሚል በሚታወቀው ድርጅታቸው አማካይነት ለኢትዮጵያ አየር መንገድም ለ14 ዓመት ዩኒፎርም እየሰሩ በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡
ለሽልማት የበቁት ግን በአልባሳት ዲዛይን ሳይሆን ከሁለት ዓመት በፊት ባቋቋሙት ድርጅት "ሙያ ኢትዮጵያ" በሚሰሩዋቸው በባህል ልብስ የተሰሩ የቤት ውስጥ ማስጌጫዎች የፋሽን አክሰሰሪዎች ነው፡፡ "በልብስ ዲዛይን ሥራ በዓለም ገበያ ውስጥ ገብቶ ተወዳዳሪ መሆን ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ እጅግ በርካታ ዲዛይኖች ይቀርባሉ፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ሳስብ በሽመና የተሰሩ ነገሮችን ምርጫዬ አድርጌያለሁ፡፡ ምክንያቱም ባህላዊ ሽመና ከዓለም ላይ እየጠፋ በመሆኑና ከምርቱም ባሻገር በእጅ የተሰራ ነው መባሉ ገበያውን ሰብሮ ለመግባት ስለሚያስችል" ብለዋል፡፡
ወይዘሮዋ ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓና ጃፓን የሚልኩት ከጥጥ የተሰሩ የቤት ውስጥ ማስጌጫዎችን ብቻ አይደለም፡፡ በሸክላ የተሰሩ ድስቶችንና የለያዩ ቁሳቁሶችንም ነው፡፡ "ፈረንጆቹ የሚያዩት ሸክላን ተሰባሪነት ሳይሆን በእጅ የተሰራ መሆኑን ነው፡፡ ጥበቡን ያደንቃሉ፡፡ የሸማ ሥራውንም የኢትዮጵያ ሸማኔዎች በእጃቸው ቆጥረው የሰሩት ጥበብ መሆኑ ስለሚገርማቸው ገበያው ጥሩ ነው" ይላሉ ወ/ሮ ሣራ፡፡ በውጭው ዓለም ስላለው የገበያ ውድድር በተመለከተም የሚያቀርቧቸው የሸማ ሥራዎች በውጭው ዓለም ተቀባይነት እንዳላቸውና እንዲያውም ተፈላጊነቱ እያለ ምርቱ እያነሳቸው መቸገራቸውን ነው የገለፁት፡፡
የተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ከባድና ፈታኝ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ሣራ ደከመኝ ሳይሉ ከሰሩት ግን ውጤታማ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ "በተለይ በእኛ ሃገር የኑሮ ጫናው የሚከብደው በሴቶች ላይ ነው፡፡ የቤተሰብ ኃላፊ ሆኖ ቤትን ማስተዳደር አለ፣ ሴት መሆን በራሱ በእኛ ሃገር ሁለተኛ ያደርጋል፡፡ በዛ ላይ በውጭ ንግድ ላይ ስትሰማሪ በቀን 16 እና ከዛ በላይ ሰዓት ሥራሽ ላይ ማሳለፍ ይጠበቅብሻል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ይፈትናሉ ግን ደከመኝ ማለት አያስፈልግም" ብለዋል፡፡
በዕደ ጥበብ ሥራ ተሰማርተው የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ በሁለተኛነት የተሸለመው ድርጅት ሣባ ሃር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ከሃር ብቻ የተሰሩ የአንገት ልብሶች፣ የአልጋ ልብስና የተለያዩ የቤት ውስጥ ማስጌጫዎችን እያመረተ ለገበያ በማቅረብ ይታወቃል፡፡ በዕለቱ ያገኘናቸውን የድርጅቱን ማርኬቲንግ ኤንድ ኘሮዳክት ዲቨሎኘመንት ማኔጀር የሆኑትን ወ/ሪት ሳሳሁልሽ ሽብሩን አነጋግረናቸዋል፡፡
የሃር ልብሶች በድሮ ኢትዮጵውያን ነገስታት ይለብሱ ነበር፡፡ ያኔ ግን ታሪክ እንደሚያስረዳው የሃር ምርት ኢትዮጵያ ውስጥ አይመረትም፡፡ ከቻይና በሃር ተሰርቶ የመጣን ልብስ በመተርተር በኢትዮጵያውያን ሸማኔዎች እንደገና ተሸምኖ የተለያዩ አልባሳት ተሰርተውበት ለዓለም ቤተክርስቲያናት እንደስጦታ ያበረክቱት ነበር፤ ነገስታትም ይለብሱት ነበር፡፡
ወ/ሪት ሳሳሁልሽ እንደሚሉት ዛሬ ግን ሣባ ሃር የሚያመርታቸው የሃር አልባሳትና ጌጣ ጌጦች የሃሩ ክር በኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ተመርቶ፣ በኢትዮጵያውያን ሴቶች ተፈትሎና በሸማኔዎች ተሸምኖ በዘመናዊ መልኩ በተለያየ ዲዛይን ተሰርቶ ነው ለዓለም ገበያ የሚቀርበው፡፡
ከሃር የሚሰሩት የአልጋ፣ የትራስ፣ የጠረጴዛና የአንገት ልብሶችን ድርጅቱ ወደ አሜሪካ፣ ዴንማርክ፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ካናዳና ሌሎችም ሃገሮች ገበያ ያቀርባል፡፡ በዚህ ሥራው ውጤታማ በመሆኑም ድርጅቱ ሁለተኛ ሆኖ ተሸልሟል፡፡
ወ/ሮ መንበረ አለማየሁ ደግሞ የመንቢስ ዲዛይን ድርጅት ባለቤት ናቸው፡፡ ሦስተኛ በመውጣት የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ድርጅታቸው እንደሌሎቹ ተሸላሚዎች ሁሉ በባህል አልባሳት የተሰሩ የተለያየ ዲዛይን ያላቸው የቤት ውስጥ ማስጌጫዎችና እንደሻርኘና ቦርሳ ያለ አልባሳትን ያመርታል፡፡ ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከጀመረ አራት ዓመት እንዳለፈው ገልፀውልናል፡፡
ድርጅቱ ሥራ ከተጀመረ ጀምሮ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡ የድርጅቱ ባለቤት እንደሚሉት ወደ ውጭ ገበያ ንግድ ከመጀመራቸው በፊት የልብስ ስፌት ኩባንያ ነበራቸው፡፡ በዚሁ ኩባንያ የተለያዩ ልብሶችን በተለያየ ዲዛይን በመስፋት ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርቡ ነበር፡፡ ወደ ውጭ ገበያ መላክን ሲያስቡ ግን በአዲስ ድርጅት ወደ ሽመና ሥራ ውጤቶች እንዳተኮሩ አጫውተውናል፡፡ ሥራውን እንደጀመሩም በዓለም ገበያ ላይ ከባድ ውድድር እንደገጠማቸው አልሸሸጉም፡፡
"ምርታችንን ይዘን ወደ ውጭ ሃገሮች ስንሄድ ውድድሩ ከባድ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ከተለያዩ ሃገራት የሚመጡ ጥሩ ጥሩ የሆኑ ብዙ ዓይነት ዲዛይኖች አሉ፡፡ በተለይ ከእስያ የሚመጡት ደግሞ ዋጋቸው ርካሽ በመሆኑ ከነሱ ጋር መወዳደር ይከብደናል"
ወይዘሮ መንበረ እንደሚሉት ሲጀምሩ የዓለምን ገበያ ሰብሮ ለመግባት ውድድሩ የከበዳቸው ቢሆንም የተሻለ ጥራት ያለው እቃ እያመረቱ የተሻለ ክፍያ መጠየቅ የሚለውን ዓላማ አድርገው መንቀሳቀስ ከጀመሩ በኋላ የተሻለ ውጤት አይተዋል፡፡ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው እቃዎችን እያመረቱ በአሜሪካ አውሮፓና አውስትራሊያ ለሚገኙ ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ተጠቃማዎች በውድ እየሸጡ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ሴቶችና ሌላ ተጨማሪ ሦስት ሴቶች የሚሌኒየሙን ሽልማት እንዲያገኙ ያስተባበረው ሴንተር ፎር አፍሪካን ውሜን ኢኮኖሚክ ኢምፓወርመንት ነው፡፡ የድርጅቱ ኃላፊ ወይዘሮ ንግሥት ኃይሌ የሴቶቹ መሸለም እነሱንም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን እንደሚያበረታታ ገልፀዋል፡፡
የተሸለሙ ሴቶች የተመረጡበት መስፈርት ምን እንደሆነ ጠይቀናቸው ነበር "ዋናው በተሰማሩበት የውጭ ንግድ ዘርፍ ያስመዘገቡት ምንዛሬ (ኤክስፖርት ፐርፎርማንስ) ነው፡፡ የእኛ ድርጅት ድጋፍ ሲሰጣቸው ከቆየ በኋላ አዳዲስ ምርቶችን ይዘው ቀርበዋል ወይም አዳዲስ ምርቶቻቸውን በገበያቸው ላይ ያሳደሩት አዎንታዊ ተፅእኖ አለ ወይ? የሚሉትን አይተናል፡፡ ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ የሴቶቹ የመፍጠር ችሎታ ነወ፡፡ አዳዲስ ዲዛይኖችን በመፍጠር የመሥራት ችሎታቸው ወሳኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ባሉበት የሚቆሙ ከሆነ ከገበያ ውጭ ይሆናሉ፡፡ በእነዚሁ መስፈርቶች አወዳድረን ተሸላሚዎቹን መምረጥ ችለናል" የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
በትዕግሥት ዘሪሁን |