| ዝክረ ዓድዋ - 2000 |
|
|
| Sunday, 02 March 2008 | |
![]() አፄ ምኒልክ ከ112 ዓመታት በፊት፣ በዛሬዋ ዕለተ ሰንበት እሑድ፣ እንደ ዘንድሮ ሁሉ በዘመነ ዮሐንስ ዓድዋ ላይ የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ድል የተመታበት ቀን ነው፡፡ ዕለቱም ዘመኑም የገጠመበት ታሪካዊ መዓልት፣ ኢትዮጵያውያን እርመኛ አርበኞች በጠቅላይ አዝማቹ በንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ አማካይነት ሕያው ታሪክ ያስመዘገቡበት ዓድዋ፡፡ ሁለተኛው ሺህ በሚያበቃበት ዓመትና ወደ ሦስተኛው ሺሕ መሸጋገሪያ ዋዜማ ላይ ሆነን የምንዘክረው የዓድዋ ድል፡፡ ከዚህ ጽሑፍ መክፈቻ ላይ የሰፈረው ኃይለ ቃል ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሕዝቡንና የየአካባቢውን መኳንንትና ገዢዎች በኢጣሊያ ላይ ያነሳሱበት የክተት አዋጅ ነበር፡፡ ጸሐፌ ታሪክ ቤርክሌይ ስለ ዓድዋ ዐውደ ውጊያ የጻፈውን ጳውሎስ ኞኞ “ዐጤ ምኒልክ” ብሎ ባሳተመው መጽሐፉ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡ “ሃያ ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሉበት የአውሮጳ ጦር በአፍሪቃ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡ በእልቂቱ በኩል 25”000 ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ . . . አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የእኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው” የዓድዋውን ጦርነት ከመሩት የጦር አዛዦች መካከል እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ መኰንን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ አባተ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ይገኙበታል፡፡ አዝማሪዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት ይሰጡት የነበረው ወኔ ቀስቃሽ አዝመራ ጉልህ ነበር፡፡ ስለነዚያ አዝማሪዎች ቤርክሌይ ከጉዞው ጋር አያይዞ የጻፈው የሚጠቀስ ነው፡፡ “. . . በሠራዊቱ መሀል አዝማሪዎችም አብረው ይዘምታሉ፡፡ በዚያ ሁሉ ሁካታ አዝማሪዎቹ ዘማቹን እያጫወቱ ይሄዳሉ፡፡ አብሮአቸው የሚጓዘው ሠራዊትም ለአዝማሪዎቹ ግጥም ይነግሩዋቸዋል፡፡ አዝማሪዎቹ የደከመውን በግጥም እያበረታቱ ይጓዛሉ” ፣ወንድሜ ራበህ ወይ? ወንድሜ ጠማህ ወይ አዎን የናቴ ልጅ እርቦህ ጠምቶሃል ታዲያ የናቴ ልጅ አዳኝ ወፍ አይደለህም ወይ? ግፋ ብረር ወደፊትህ ሂደህ ጠላትህን አትበላም ወይ? ግፋ ወደፊት ከበዓሉ ቦታ ፈጥነህ ድረስ የምታርደውን ሥጋ የማቆራርጥልህ እኔ ነኝ ግፋ የናቴ ልጅ ውሃ ጠምቶሃል ጠጅ ብታጣ ደሜን እንድትጠጣ እሰጥሃለሁ፣ የዓድዋ ጦርነት ሲነሳ ሁሌም የሚነሳው ባሻዬ አውአሎም ሐረጎት ነው፡፡ በስለላ ሙያው ተጠቅሞ የኢጣሊያን የጦር እቅድ በማሳከር አኩሪ ተግባር አከናውኗል፡፡ የባዕዳኑ አገልጋይ የነበረው አውዓሎም በቁጭት በመነሳሳትና በብላታ ገብረእግዚአብሔር ጊላ አማካይነት ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር ይገናኛል፡፡ እንደ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ጽሑፍ ራስ መንገሻም ከአፄ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ይገናኙና የጦርነቱ ጊዜ ሲቃረብ የተሳከረውን እቅድ ለዤኔራል ባራቲየሪ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ አውዓሎምና ብላታ ገ/እግዚአብሔር ከኢጣሊያውያን ተለይተው ወደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ገብተው ጦርነቱ ሲፋፋም ከኢጣሊያ መኰንኖች አንዱ ነገሩን ተገንዝቦ “አውዓሎም አውዓሎም” እያለ ሲጣራ አውዓሎም ሰምቶ “ዝወአልካዮ አያውዕለኒ” ብሎ አፌዘበት ይባላል፡፡ ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም. ሌሊት ለእሑድ 23 አጥቢያ ወታደሩ እየሸለለ አዝማሪዎችም ማዘመር ጀመሩ፡፡ “ኧረ ጉዱ በዛ ኧረ ጉዱ በዛ በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ” ይሉ ነበር፡፡ ለጦር አዝማቾችም ማንቂያም ተገጥሟል፡፡ ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ፡፡ እነዚያ ጣሊያኖች ሙግት አይገባቸው አሉላ አነጣጥረህ ቶሎ አወራርዳቸው፡፡ ዳኛው ወዴት ሄዷል እስኪ ወጥተህ እይ አክሱም መንገሻዬ እስኪያዝ ነወይ፡፡ ዓድዋ ላይ ጣሊያኖች የዘፈኑለት ምኒልክ ጎራዴህ ወረደ ባንገት፡፡ የኢትዮጵያ ድል አድራጊነት የኢጣሊያ ሽንፈት ከተረጋገጠ በኋላ የኢትዮጵያ ሠራዊት ምርኮኛውን ይሻማው ጀመር፡፡ “አስካሪስ” ተብለው የሚታወቁት በኢጣሊያ ወገን የተሰለፉት የኤርትራ ተወላጅ ወታደሮች የአካል ቅጣት ደረሰባቸው፡፡ ለዚህም እንዲህ ተገጠመላቸው፡፡ “ዓድዋ ውዒለ ኣብ ሓሸዋ፣ ኢደይን እግረይን ቆሪፁ ወዲኡወን ንጉስ ሸዋ ዓድዋ ውዒለ ምስ እምበይተይ ኢደይን እግረይን ገዲፈየን መጺአ ከምዘይናተይ” (የአማርኛ ትርጉሙ) ዓድዋ ዋልኩኝ ከአሸዋ እጅና እግሬን ቆረጠው ንጉሠ ሸዋ ዓድዋ ዋልኩኝ ከእሜቴ ጋር ተጎትቼ የኔ እንዳልሆኑ እጅና እግሬን ትቼ፡፡ የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበት ዕለት በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የበዓላት ትውፊት መሠረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀን ነው፡፡ ከቀደመው ጊዜ አንስቶ እስካሁን “ጠባቂ ቅዱስ” (ዘ ፓትረን ሴንት) ተብሎ ይታወቃል፡፡ እስከነ ዝማሬውም “የዓድዋ አርበኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምኒልክ ጋር አብሮ ሲቀድስ፤ ምኒልክ በጦሩ ጊዮርጊስ በፈረሱ ጣልያንን ድል አደረጉ ደም እያፈሰሱ” እየተባለ እስካሁን ይዘመራል፡፡ የዓድዋ ድልን አስመልክቶ በተለያዩ የጥበብ ሰዎች የተሠሩ ኪነጥበብ ተኮር ሥራዎች በፊልም፣ በተውኔት፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ግጥም፣ በቅኔ ወዘተ. የቀረቡት በርካታ ናቸው፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በፊት የፊልም ዳይሬክተሩ ኘሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ “ዓድዋ” በሚል መጠሪያ የደረሰው ፊልም በበርካታ ታሪካዊ ፎቶግራፎች የታጀበ ነበር፡፡ በተውኔት ዘርፍ ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ነፍስ ኄር ጸጋዬ ገብረመድኅን “ዓድዋ” ከተሰኘውና በ1964 ከደረሰው ግጥም ሌላ አሜሪካ ውስጥ ለእይታ የበቃው “ምኒልክ” ተውኔት ዓድዋን ያጎላበት ነበር፡፡ የደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ካለፉ በኋላ የታተመው “ዓድዋ” ተውኔታቸውም ይጠቀሳል፡፡ “ዋ” . . . ያቺ ዓድዋ” የጸጋዬ ገብረመድኅን “እሳት ወይ አበባ” ከተሰኘው የሥነ ግጥም መድበሉ ውስጥ የሚገኝ ስለ ዓድዋ የዘከረበት ነው፡፡ ከፊሉ እነሆ፡፡ . . . . ዋ” ዓድዋ የዘር ዐፅመ ርስትዋ የደም ትቢያ መቀነትዋ በሞት ከባርነት ሥርየት በደም ለነፃነት ስለት አበው የተሰውብሽ ለት፤ . . . ሲያስተጋባ ከበሮዋ ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ ያባ መቻል ያባ ዳኘው ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው ያባ በለው በለው ሲለው በለው - በለው - በለው” ዋ” . . . ዓድዋ . . . ሥነ ሥዕልን በተመለከተ ድሉን የሚያሳዩ በተለያዩ ሠዓልያን የተሣሉ ባህላዊና ዘመናዊ ሥዕሎች የመኖራቸውን ያህል ኢጣሊያናውያንም የምኒልክን ታላቅነትና ድል አድራጊነት፣ የክሪስፒን ተሸናፊነትና ውድቀት የሚያሳይ የካርቱን ሥዕል አሰራጭተዋል፡፡ ሥዕሉ በ”ለ ፐቲት ጆርናል” የታተመ ሲሆን፣ ምኒልክ ክርስፒን በታላቅ ዱላ ሲጎሽሙትና ሲጥሉት ያሳያል፡፡ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ በድል አድራጊነት አዲስ አበባ እንደገቡ በቤተክህነት የተደረገላቸውን አቀባበል የንጉሡ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ጽፈውታል፡፡ የእንጦጦ ማርያምና የራጉኤል፣ የሥላሴና የዑራኤል የጊዮርጊስም ካህናት ልብስ ተክህኗቸውን እንደለበሱ በጃን ሜዳ “ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፣ ተሐጺባ በደመ ኢጣልያ” መሬቷ በኢጣልያ ደም ታጥባ ፋሲካ (ደስታ) አደረገች የሚለውን ጠቅሰው በንጉሠ ነገሥቱ ፊት አሸበሸቡ ሲሉ አመልክተዋል፡፡ አቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ “ዐፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘው መጽሐፋቸው የጐጃሙ ሊቅ መምህር ወልደ ሥላሴ እንደመልክ አድርገው ለአፄ ምኒልክ በግእዝ ደርሰው ያበረከቱት የደራሲውን ሊቅነት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካውንም የጦርነቱንም ታሪክ በትክክል የተከታተሉት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሰላም ለአፉከ ለፈጣሪ ዘየአኵቶ ኢይትናገር ስላቀ ወኢይነብብ ከንቶ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ማኅቶቶ ኃልቀ ማንጀር ረማዦርሪ ወስዕነ ፍኖቶ ዤኔራል ባራቲዬሪ ሶበ ገብዓ ደንገፀ ኡምቤርቶ፡፡ (ሰላም ፈጣሪን ለሚያመሰግነው አፍህ ስላቅ ለማይናገረው፣ ከንቱ ነገር ለማያወጋው አፍህ ሰላም ይሁን፡፡ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለኢትዮጵያ ብርሃኗ ማዦር ማለፊያ መንገድ አጥቶ አለቀ ዤኔራል ባራቲዬሪ ወደርሱ በተመለሰ ጊዜ ኡምቤርቶ ደነገጠ፡፡) ለዳግማዊ ምኒልክ ለእቴጌ ጣይቱ ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ የተደረሰው የአማርኛ ግጥም ብዙ ነው፡፡ የአብዛኞቹ ገጣሚዎች ስም አይታወቅም፡፡ ከነዚያ መካከል አቶ ተክለጻድቅ የሚከተለውን ይጠቅሳሉ፡፡ ዳግማዊ ምኒልክን ከትልቁ እስክንድር በክንፋማ ፈረስ ወደ ሰማይ ወጣ ከተባለው ጋር በማመሳሰል የተደረሰው ቅኔ እነሆ “የዳኛው አሽከሮች እየተባባሉ ብልት መቆራረጥ አንድነት ያውቃሉ ዓድዋ ከከተማው ሥጋ ቆርጠው ጣሉ፡፡ የእስክንድር ፈረስ መቼ ተወለደ የምኒልክ ፈረስ በክንፎቹ ሔደ” በሔኖክ ያሬድ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |