Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow መገደብ ያለበት አባይ ብቻ...
መገደብ ያለበት አባይ ብቻ... Print E-mail
Sunday, 02 March 2008
መገደብ ያለበት አባይ ብቻ ሳይሆን ሃሞታችንም ነው

(በነገደ ሥዩም)

ድህነታችን የሥራ ወኔአችንን አኮላሽቶ፣ ስንፍናችንን አበራክቶ የወሬና የምኞት ኢንዱስትሪ ባለቤቶች አድርጎን የማይጨበጥ ነገር እየተመኘን ነው፡፡ የተጨበጠን ነገር እየናቅንና እየተቸን ከድህነት ጋር ተለማምደን ላንላቀቅ ሞቆን መኖር ከጀመርን ቆይተናል፡፡
በዘመነ አክሱም በዓለማችን ካሉት ሃብታምና ጠንካራ ሕዝቦች አንዱ እንደነበርን ስለዘመኑ የፃፉ መስክረውልናል፡፡፡ የሚሌኒየም በዓል በማክበር፣ ንፁህ ልብስ በመልበስ፣ በመከባበር፣ በመዋደድ፣ ትልቅ የተባለ ሰልፍ በማድረግ ከድህነታችን የምንወጣ የሚመስለን ካለን ተሳስተናል፡፡

አንዱ አበባ ሲያመርት ሌላው የአበባ መያዣ  ሁሉም አበባ ላይ ይሮጣል፡፡ ችግሩን ለይቶ የመፍትሄ ኘሮግራም ነድፎ ይህንን ልስራ ልቆሽሽ ልድከም በኋላ እፀዳለሁ ብሎ ወደ ሥራ የገባ የለም፡፡ ጤነኛ የሆነ ዘመናዊነትን መልመድ አለብን፡፡ በሥራ መከበርን ከድህነት የማምለጥ ዘመናዊነትን፡፡

ከድህነት የመውጣት ህዳሴ ሳይሳካ ስንፍናው አሸንፎን ተመልሰን ድህነት በስንት ጣዕሙ እንዳንል፡፡ ከድህነት መውጣት ማለት እንዲህ እንደሚሌኒየም በዓል ተሰልፎና ዘፍኖ ነጭ ለብሶ እንደማማር ቀላል አይደለም፡፡

ኢሚግሬሽን የሚባል ወንዝ አለ፡፡ ወደ ቦሌ ፈስሶ ከዚያም ወደ ሌላ አገር ቦይንግ በሚባለው አሸንዳ ልክ አባይ አፈራችንንና ውሃችንን እንደሚወስደው ይህም ምትክ የሌለው የተማረና ጉልበት ያለውን ለአገሩ ስንትና ስንት የሚሰራውን ነው የሚወስደው፡፡ በአገሪቱ ልጅና ሽማግሌ ብቻ የሚቀር ነው የሚመስለው፡፡

የምትሄደው ለምንድነው ብትሉት ያ ጎበዝ ወይም ያቺ ቆንጆ በምሬት እዚህ እንዴት እኖራለሁ? ተምሬአለሁ ግን ደስታ የለም፡፡ ውጭ እኮ ብዙ ታገኛለህ ወዘተ. ይሏችኋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ገንዘብ ስለማግኘት እንጂ በክብሩ ላይ ስለሚደርሰው አያሳስበውም፡፡ እያጣ እየነጣ መሆኑን ልብ አይልም፡፡ የት ይደርሳል የተባለው አሜሪካ ሄዶ ወዶ ገብ ባሪያ ሲሆን ይታያል፡፡ በሀገር ከሰሩ መከበርና መክበር እንዳለና ለልጅ ልጅ ታላቅ ሥራ እንደሚሰራ አያስብም፡፡ ሃሞቱ ተንጠፍጥፎ ወደ ነጮቹ አገር ፈሷል፡፡ የአገሩ የሆነ ነገር ሁሉ ይንቃል፡፡ በፈረንጅ ነገር ይደነቃል፣ ያመልካል፡፡

መገደብ ያለበት ይህ የጎበዞችና የቆንጆዎቹ ኢትዮጵያውያን ሃሞት እንጂ አባይማ አፈርና ውሃ ነው ይዞ የሚሄደው፡፡ የእነዚህ ሃሞት ከተገደበ አባይን መገደብ አይከብድም፡፡ "ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ብከዳሽ ቀኜ ትክዳኝ" ችግርሽ ችግሬ ነው አልለይሽም የሆንሽውን እሆናለሁ የሚል ሃሞተ ቆፍጣና ዜጋ ስሜቱን ፍላጎቱን ሃሞቱን የገደበ ቆፍጠን ያለ ዘላቂ የኢትዮጵያን እድገት የሚያስብ ሃሞቱ ያልፈሰሰ በስሜቱ ያልረከሰ ማንነቱን የሚያውቅ ወደነፈሰው የማይነፍስ እርሱ ነው ግድብ፡፡

በ1929 ዓ.ም. በእንግሊዝና በግብፅ መካከል ናይልን ለመጠቀም በተዋዋሉትና በ1959 በሱዳንና በግብፅ መካከል የተፈረመው ውል የሄልሲንኪውን ዓለም አቀፍ ውል ከምንም ሳይቆጠር የተፈረመው ውል የአባይን አመንጪ አገሮች በገባር ወንዞች እንዳይጠቀሙና ውሃውን የሚቀንስ ኘሮጀክት እንዳይሰሩ ያግዳል፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል ነው፡፡ እነሱ ግን የእስራኤል  ምድረ በዳን ለማልማት የአባይን ወንዝ ለመሸጥ እየተደራደሩ በሀገራችን ውሃ ኘሮጀክት እንዳንሰራ ይዋዋላሉ፡፡ እኛ የሌለንበት ውል ሲዋዋሉ አያፍሩም፣ አይፈሩም፡፡ አቅም የለንም፡፡ ለመደራደር ለመከበርና ለመታፈር የሚያደራድር አቅም መኖር አለበት፡፡

አባይን ሳንጠብቅ ከወዲሁ ሌሎች እሴቶችን መጠቀም እንችላለን፡፡ የአፍሪካ የውሃ ማማ የምትባለው አገራችን አባይና ገባሮቹን ሳትነካ በሌሎች ተከዜ፣ አዋሽ፣ ገናሌ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ወዘተ. የከርሰ ምድር ውሃችንን በመጠቀም ነገ አባይን ለመጠቀም ለሚፈልጉ ልጆቻችን ትልቅ እሴትና መሰረት መጣል እንችላለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥቁር አባይ የሚባለው ወንዛችን 1370 ኪ.ሜ. (850 ማይል) ይረዝማል፡፡ ከ1830 ሜትር /6000 ጫማ/ ከባህር ጠለል በላይ ተነስቶ ቁልቁል የሚፈሰው አባይ በሚገባ ካስተዋልነው እስከ አሁን ድረስ ቢገደብ የሚለው ስሜታችንን ልንታዘበው እንችል ነበር፡፡ ግራና ቀኝ ያለው መሬት ተራራማ ከመሆኑም በላይ ለግብርና ለኢንዱስትሪ ወይም መስኖ ልማት እንደ ግብፅና ሱዳን ዴልታ ምቹ አይደለም፡፡ ተፈጥሮ በከፍተኛ ተራሮች ገድቦታል፡፡ ለአባይ አቅም ኖሮን እንኳን ግድብ ብንሰራለት ለልማት ምቹ የሆነ ቦታ (መሬት) እምብዛም ነው፡፡ ከአባይ ይልቅ ሌሎች ወንዞቻችን ግራና ቀኝ ለልማት ምቹ የሆነ መሬት አላቸው፡፡

በአባይ ወንዝ መገደብ ድህነታችን እንደሚፈታ የምናስብ ካለን ማስተዋል ያለብን ነገር አለ፡፡ ከባህርዳር በጭስ አባይ ቁልቁል አባይ ሲፈስ በግራ በኩል የወሎ ተራራዎች ዋድላ፣ ዳውንት፣ ሳይንት፣ ቦረና ስንመለከታቸው በአካባቢው አጠራር የአባይ ሸለቆ "አላህ በክርኑ የመታው" እንደሚሉት ተገድቦ ለመስኖ ለመጠቀም ወይም አቅጣጫውን ለመቀየር የማይመች ነው፡፡ በቀኝ በኩል ያለው የጎጃም ምድር ዳንግላ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደጀን፣ ጎሃ ጽዮንን ዞሮ እስኪሄድ ድረስ ለመስኖ የሚሆን እንደ ግብፅ ወይም እንደሱዳን የተመቸ ሰፊ መሬት እምብዛም የለውም፡፡ አባይ ተገደበ አልተገደበ አጓጊ አጀንዳ አይሆንም ማለትም ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የሀገራችን የውሃ ሃብት አስተዳደር ፖሊሲ ሌላ ሊተገበር የሚችል "SMART" ስትራቴጂ ይዞ መነሳት አለበት፡፡ አባቶቻችን አባይን በማን ያድክሙ በእህት በወንድሙ እንዳሉት፡፡ የአባይን መገደብ እኛ በሌሎቹ የውሃ ሃብቶቻችን አቅም እንፍጠርና ለልጆቻችን አቅም እናቆይላቸው፡፡ መንግሥትም ከነዲኘሎማቶቹ የአባይን ሁኔታ መስመር እያስያዘ የልማት አቅጣጫውን ያሳምር፡፡ ህዝቡ አጠገቡ ካለው ወንዝ ቢነሳ ፈጣን ልማትን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ አለበለዚያ የአጀንዳ ቅደም ተከተል ተዛብቶብን በኋላ ለሚታሰብበት ጉዳይ አሁን ናላችን እስኪዞር ብንከራከር ለፈጣን ልማቱ ብልጥ አንሆንም፡፡ አጠገባችን ያለውን የግንፍሌን ወንዝ ጥቅም ሳናውቅ ስለአባይ በርቀት የረቀቀ እውቀት ቢኖረን ላም አለኝ በሰማይ ሊሆንብን ይችላል፡፡

ግብፅ ልትሸጠው የተዘጋጀችው የተሻለ አቅም አለኝ ብላ ስለምትደፍር ነው፡፡ እኛም ልክ እንደ ሃይላንድ እያሸግን ውሃችንን ለመሸጥ የሚያስችለን አቅም ልናዳብር ይገባል፡፡ በውሃ ሃብታችን በፍጥነት ስንጠቀምበትና ገንዘብ አስገኚ (Cash Crops) ምርት እያመረትን በዓለም ተወዳዳሪ መሆን አለብን፡፡ በቤታችን አጠገብ የሚፈስሰው ጅረት በብቃት መጠቀምን ይጠይቃል፡፡

ወንዝ የሌለው የኢትዮጵያ ክፍል የለምና በውሃ ሃብት ልማት የተሰማሩ ድርጅቶች፣ መንግሥት፣ ኀብረተሰቡ፣ የትምህርት ተቋማትና ሁሉም የልማት ሀይሎች የውሃን ምስጢር ተጠቅመው ሀገራችንን ማልማት ይችላሉ፡፡ በሰው ሀገር ሄደን ጉልበት እናፈስሳለን፡፡ ሥራን ሳንንቅ እንሰራለን፡፡ በቅርቡ እየፈለሱ መጥተው በልመና የሚተዳደሩ ወገኖች ከአዲስ አበባ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ታዲያ ወደ ውጭ ከሃገር የሚኮበልሉትስ ከእነዚህ በምን ይሻላሉ?  ለእነሱም የሚሆን ሥራ ቢሰራ መልካም ነው፡፡ ከአባይ ወንዝ የበለጠ ሃብት ያለው እነዚህ ሰዎች ጋር ነው፡፡ ሀገርን ንቆ ፈረንጅን የማምለክ አባዜ ተለውጦ ወኔአችንና ሃሞታችን የራስን በመውደድና በማሳደግ ኢትዮጵያን መለወጥ በሚለው ይተካ፡፡ ወደ ውጭ የሚፈስሰው ስሜታችን፣ ፍላጎታችን እኛነታችን ሃብታችን ይገደብ፡፡

ከልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን የበለፀገች ሀገር ይረከቡ፡፡ "እኔ ከሞትኩ" እንበል፡፡  እያዋረደን ያለው አመለካከታችን እንጂ ድህነታችን ብቻ አይደለም፡፡ በቲኦሪ ሸፍተን እኛነታችንን እስኪያስንቀን ድረስ ለውጭ ባህልና እሳቤ መማረክ የለብንም፡፡ ቆም ብለን እናስብ፡፡ ሃብታችንን ሰብሰብ፣ ስሜታችንን ገታ፡፡

የሚጠጣ ውሃ በዓለማችን እያለቀ መሆኑን የጂኦሎጂካል ጥናቶች  መጪው ጊዜ የጦርነት ምክንያት የሚሆነው ውሃ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ አሁን አሁን ዘጠኙ የናይል አመንጪ አገሮች በአባይ አጠቃቀም ከፍተኛ ተቃወሞ በግብፅ ላይ ማንሳት ከጀመሩ ውለው  የግብፅ የቀድሞ መሪ አንዋር ሳዳት "የውሃ ጥያቄ ለግብፅ የድንበር ጥያቄና ጦርነት መቀስቀስ ነው" ካሉ ወዲህ ሁሉም የግብፅ ባለሥልጣኖች "ውሃ ከደም ይወፍራል" በማለት ጦርነት እንደሚቀሰቅሱ ማስፈራራታቸው የተለመደ ሆኗል፡፡

እኛ የዚህን ማስፈራሪያ ምላሽ የምንሰጠው በሌሎች ወንዞቻችን ተጠቅመን መጀመሪያ ህዝባችንን በሚገባ መመገብ ስንችልና አስተማማኝ የሀገር ሃብትና ልማት አስመዝግበን ለልጆቻችን ማውረስ ስንችል፣ ልጆቻችንም ይህንን አቅም ተጠቅመው ግብፆችን ከእናንተ ጋር ጦርነት አንገጥምም ወደ እናንተ የሚፈሰውን ወንዛችንን በኬሚካል እንመርዛለን፡፡ አለበለዚያ እናንተ በአገራችሁ ነዳጅ ሃብት ለእኛ እንደማትሰጡንና እንደምትሸጡልን ሁሉ እኛም ውሃችንን ለመግዛት ትገደዳላችሁ፡፡ አለበለዚያ ንፁህ ውሃ አታገኙም መሰል ስትራቴጂካል ማስፈራሪያ በመሰንዘር ሀገራችንን የሃብቷ ተጠቃሚ ሊያደርጓትና ሀገራቸውን ሊያለሙ ይችላሉ፡፡
 
< Prev   Next >