Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ሌሎቹም የዓድዋ ተራሮች ይዘከሩ
ሌሎቹም የዓድዋ ተራሮች ይዘከሩ Print E-mail
Sunday, 02 March 2008
(እውነቱ ከሳሪስ)

አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኢንተርኔትና በሪፖርተር ጋዜጣ ስለ ዓድዋ የሚመለከቱ የተለያዩ ፅሑፎችን ለማየት ችያለሁ፡፡
በመጀመሪያ ያየሁት አምና በዚህ ወር አካባቢ ገ.ኢ.ጎርፉ በተባሉ ፀሐፊ ተዘጋጅቶ በኢንተርኔት በኣይጋ ፎረም ድረ ገፅ የተሰራጨውና አምስት ክፍል ያለው ጽሑፍ ነበር፡፡  ዓድዋ ስለሚለው ቃል በአፈታሪክ ደረጃ ከሚነገረው ጀምሮ ስለ ታሪካዊነቱና ሌላም ብዙ ጠቃሚ ጉዳዮች ያነሳሉ፡፡ የ"ጉግል" የኢንተርኔት መፈለጊያ መሳሪያ በመጠቀም ያደረጉት ንፅፅር እንደሚያሳየው (ማንም ኢንተርኔት መጠቀም የሚችል ሰው ይህንን ፍለጋ በማድረግ ማየት ይችላል) ዓድዋ ከሌሎች እውቅ የኢትዮጵያ ስሞች በላይ ታዋቂነት ያለው መሆኑን ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን፣ ይህንን ታዋቂነቱን እኛ ኢትዮጵያውያን በሚገባ እየተጠቀምንበት አለመሆናችንን ነው፡፡ ገ.ኢ.ጎርፉ የዓድዋን ታዋቂነት በሚገባ ጥቅም ላይ ቢውል ትልቅ የቱሪዝም መስህብ ከመሆኑ አልፎ ለአካባቢው ከዚያም አልፎ ለመላ አገሪቱ ትልቅ የገቢ ምንጭና የብዙ ሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሊሆን እንደሚችል ይተነትናሉ፡፡

ገ.ኢ.ጎርፉ ያነሱት ሌላው ቁም ነገር የዓድዋ ታዋቂነትና የአፄ ምኒልክ ገናናነትን ለያይቶ ለማየት የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ዓድዋ ውስጥ ይህንን የሚዘክር ምንም ነገር ያለመኖሩን በማንሳት በከተማው ውስጥ ቤተመዘክር (ሙዝየም) ቢቋቋም፣ ከከተማው ዳርቻ ከሚገኘው ሶሎዳ ከሚባለው ተራራ መሃሉ ላይ ደግሞ ለአፄ ምኒልክ አፅማቸው ያረፈበትን ቤተመቃብር የሚዘክር በላዩ ላይ ከወገባቸው በላይ ሆነው የሚያሳይ  ያረፈበት መታሰቢያ ቢሰራ የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

የገ.ኢ.ጎርፉ ጽሑፍ ካነበብኩ ከአንድ ወር በኋላ ይመስለኛል "የኢትዮጵያ ሌላው ገጽ" (The Other Face of Ethiopia) የሚባል ተቋም "ዝክረ ዓድዋ ጦርነት" ወይም "የዓድዋ ጦርነትን እናስታውስ"  ኘሮጀክት ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር በባብሮ በመቅረፅ ዓድዋ ውስጥ የባህል ማዕከልና ቤተ መዘክር ለመገንባት ማሰባቸውን አነበብኩ፡፡ በማከታተልም በተለያዩ ሚዲያዎች የመሠረት ድንጋይ የማኖር ሥነ ሥርዓት የሚያሳዩ ዜናዎችን ለማየት ችዬ ነበር፡፡

አሁን ደግሞ ገሠሠው ተብሎ  የዓድዋ ተራራ ላይ እያንዳንዱ ፊደል አንድ መቶ ካሬ ስፋት ያለው ሆኖ "ዓድዋ ሳብሮ" የሚል ጽሑፍ ለማኖር የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዊ ብቅ ማለታቸውን ረቡዕ ጥር 7 ቀን 2000 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ለማንበብ ቻልኩ፡፡

ሐሳቡ መልካም ነው፡፡ ዓድዋ ከተማ ውስጥ የባህል ማዕከልና ቤተ መዘክር ማቋቋሙና "ዓድዋ ሳብሮ" የሚል ጽሑፍ ገሠሠው ተራራ ላይ ማስቀመጡ ገ.ኢ.ጎርፉ ወዳመላከቱት ሐሳብ የሚወስዱ ጥሩ ጅምሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን "ዓድዋ ላይ ምልክት ማስቀመጥ" በሚል ርዕስ በሪፖርተር ጋዜጣ በወጣው ጽሑፍ ትንሽ የተምታታ ነገር አለበት፡፡ ". . . ገሠሠው ተራራ ላይ አድዋ የሚል ጽሑፍ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የማስቀመጥ. . . " የሚለው ላይ "ዓድዋ" የሚለው ቃል የአማርኛ ወይም የእንግሊዝኛ ቃል አይደለም፡፡ ቃሉ በትግሪኛ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ወደ ማንኛቸውም ሌላ ቋንቋ ቢተረጎምም ያው ዓድዋ ነው፡፡ ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በ"አ/አ" እና "ዐ/ዓ" የድምጽ ልዩነት ባለመኖሩ "አድዋ" ብለው ቢጽፉ "ዓድዋ" እያሉ አለመሆናቸውን ሊያወቁት ይገባል፡፡ ባልሳሳት ለማለት የተፈለገው "ዓድዋ" የሚለውን ስም በግዕዝና በላቲን ፊደላት ጽፎ ማስቀመጥን ነው፡፡

እስከ ሃያ ሚሊዮን ብር አውጥቶ ስፋታቸው እያንዳንዳቸው አንድ መቶ አንድ መቶ ካሬ የሆኑ ፊደላት በተሠራ ስም ማስቀመጡ ለዓድዋና ለአካባቢው ሕዝብ ምን ፋይዳ አለው? ሕዝቡ የእያንዳንዱን ተራራ ስምና በዓድዋ ጦርነት ወቅት የነበረው ሚና ያውቀዋል፡፡ የስሙ በገሠሠው ተራራ መተከል ደግሞ እግር ጥሎት ለሚመጣ መንገደኛ ብቻ ተብሎ ይህን ያህል ሚሊዮን ብር ማውጣት ተገቢነቱ ለሁሉም ተመልካች ግልፅ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህን ስንል የአቶ ሰሎሞንን ጥረት ለማጥላላት ወይም ዋጋ ለማሳጣት ሳይሆን፣ የእሳቸው ጥረት የበለጠ ዋጋ የሚኖረው ሌሎችም ተጓዳኝ ነገሮች ሲሠሩ መሆኑን ለመጠቆም ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ዓድዋ የሚለው ስም ካለው ገናናነት አንፃርና ለአክሱምም ካለው ቅርበት ትልቅ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን ማድረጉ ላይ ነው፡፡ ቱሪስቶች ደግሞ አንድ የተተከለ ስም ብቻ ለማየት ብለው በሺህ የሚቆጠር ኪሎ ሜትር አቋርጠው አይመጡም፡፡ ገ.ኢ ጎርፉ እንዳሉት ብዙ የሚሠሩ ተጓዳኝ ነገሮች አሉ፡፡ የዓድዋና የአካባቢው ህዝብ ለስሙ መተከል ይበልጥ ባለውለታነት ሊሰማው የሚችለው ድርጊቱ ለኑሮም መሻሻል፣ ለልጆቹም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሲያስችል ለማየት ሲበቃ ነው፡፡

የዓድዋ ተራሮች ሶሎዳና ገሠሠው ብቻ  ሌሎችም አሉ፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል፣ በዓድዋ ጦርነት ወቅት የየራሳቸው ሚና ነበራቸው፡፡ የተለያዩት የጦር አዝማቾች ጦሮቻቸውን በተለያዩት የዓድዋ ተራሮችና ጋራዎች ነበር ያሰፈሩት፡፡ አቶ ሰሎሞን እንደ ተገነዘቡት በታሪክ መፃህፍት ስሞቻቸው የተጠቀሱት ለጎብኚዎች ያለ ጥያቄና መሪ የትኞቹ እንደሆኑ መለየት የሚቻል አይደለም፡፡ አሁንም ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ፡፡ በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት ጉዳዩ ለማንም የሚተው ሳይሆን የክልሉ መንግሥት የኢንቨስትመንት ቢሮ ይህ መስክ እንደ አንድ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በመያዝ ሊንቀሳቀስበት የሚገባ ነው፡፡

ዓድዋ ለጥንታዊቷና ታሪካዊቷ አክሱም ከተማ በቅርብ ርቀት የምትገኝ ከተማ እንደመሆኗ መጠን አካባቢው ሁሉ የአክሱማውያን ሥልጣኔ ቀመስ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በመሆኑም በዚያ አካባቢ ከርሰ ምድር ሁሉ ብዙ ታሪካዊ ምስጢሮች እንደያዙ ናቸው፡፡ ማንኛውም ዓይነት ቁፋሮን የሚጠይቁ ተግባራት ከመካሄዳቸው በፊት የቱሪዝም ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ የታሪክና የአርኪዮሎጂ ጠበብትም አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ቢደረግ ዛሬ ታሪክ ለመሥራት ስንንቀሳቀስ የጥንቱን ታሪክ ሳናውቅ እንዳናጠፋ ለመጠንቀቅ ይረዳናል፡፡ አመቺ የሚሆነው ግን ከላይ እንደጠቀስነው የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ዓድዋንና አካባቢዋን ለማልማት ከስሟ ጀምሮ ተራሮቿና ሜዳዎቿ ጭምር ትልቅ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሆን የሚችሉበት ሰፊ ዕድል መኖሩን ተገንዝቦ አስፈላጊው ቅድመ ጥናት ከአካባቢና ከታሪክ ሥነ ቅሪት ጥበቃ አንፃር የት ቦታ ምን ዓይነት ልማት ማካሄድ እንደሚቻል ለይቶ ቢያስቀምጥና አልሚዎችን ቢጋብዝና ቢያስተዋውቅ መልካም ይሆናል፡፡
 
< Prev   Next >