Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow አምባሳደር ሆቴል ታሸገ
አምባሳደር ሆቴል ታሸገ Print E-mail
Wednesday, 05 March 2008
መርካቶ አመዴ ማዞሪያ ጫፍ ላይ በሚገኘው አምባሳደር ሆቴል ውስጥ አልጋ ይዘው የነበሩና በመስተናገድ ላይ የነበሩ ሰዎችን የክፍለ ከተማው ፖሊሶችን ይዘወ በመምጣት የክፍለ ከተማው ሹሞች በኃይል በማስወጣት የካቲት 21 ቀን 2000 ዓ.ም. መታሸጉን የሆቴሉ ኃላፊ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡
የከበደና ቤተሰቡ ጠቅላላ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (አምባሳደር ሆቴል) ህጋዊ ተወካይና የሆቴሉ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ከበደ እንደገለፁት የካቲት 21 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. አምስት ሰዓት አካባቢ ከተለያዩ ክፍለ አገራት የመጡና አዲስ አበባ የሚገኙ ደንበኞቻችን ምሳ ለመብላት ሆቴሉን ሞልተውት ባሉበት ሰዓት፣ የክፍለ ከተማው ኃላፊዎች በርካታ ፖሊሶችንና አሻጊ ቡድን ይዘው በመምጣት እንግዶቻችንን በመገፈታተር አስወጥተው ሆቴሉን ማሸጋቸውን ገልፀዋል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 12 አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ባለ ሦስት ኮከብ የሆነው አምባሳደር ሆቴል፣ ከ25 ዓመታት በፊት አባታቸው ሲሰሩበት እንደነበር የሚናገሩት አቶ ዳንኤል 50 ቋሚ ሰራተኞችና ከ5ዐ የሚበልጡ ጊዜያዊ ሰራተኞች፣ እንዲሁም በርካታ ቤተሰቦች የሚተዳደሩበት የሥራ ቦታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሆቴሉ ከኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ጋር ጥቅምት 25 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. የኪራይ ውል ማደሳቸውንና በውሉ መሠረት ለአንድ ዓመት የሚቆይ (በየዓመቱ የሚታደስ) ሥምምነት ላይ ቢደርሱም፣ ያለምንም ቅድሚያ ማስጠንቀቂያና የውል ህግን በሚጥስ መንገድ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የካቲት 6 ቀን 2ዐዐዐ በተፃፈ ደብዳቤ "ቤቱ ያረፈበት ቦታ ለልማት ተግባር የሚውል መሆኑን በቁጥር መ7-1241/ሸ24/ 2/2000 በ3/6/2000 ከቤቶች ሽያጭ አፈፃፀም መመሪያ በተፃፈ ደብዳቤ ተገልፆልናል፡፡

ከኤጀንሲው ጋር የተዋዋላችሁትን የኪራይ ውል ከየካቲት 15 ቀን 2ዐዐዐ ጀምሮ የተቋረጠ መሆኑን እናስታውቃለን" የሚል ደብዳቤ እንደደረሳቸው ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው ቤቱ ያረፈበት ቦታ ለልማት ይፈለጋል ቢባልም፣ በመጋቢት ወር 1994 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሊዝ አፈፃፀም መምሪያ "የያዝነውን ቦታ ማስተር ኘላኑን በጠበቀ ሁኔታ ለቢዝነስና ሆቴል አገልግሎት መንግሥት በፈቀደው የሊዝ ዋጋ ከፍለን እናልማ" በሚል ማመልከታቸውን አስታውሰው የተሰራው ሥራ ግን አግባብነት የሌለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

"በሆቴሉ ውስጥ 32 አልጋዎች አሉ፡፡ ሁሉም ሙሉ ናቸው፡፡ ተከራዮቹ እቃዎቻቸውን አላወጡም፡፡ አንዳንድ የሚፈልጓቸው እቃዎችን በግምጃ ቤታችን ውስጥ እናስቀምጥላቸዋለን፡፡ ስለዚህ ሆቴሉ የታሸገው በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ሰዎች ላይ ጭምር ነው" በማለት አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ዳንኤል፣ በዕለቱ ለምሳ ያዘጋጇቸው ምግቦች ከመበላሸታቸውም በተጨማሪ፣ በርካታ የሚበላሹና እቃ የሚያበላሹ ነገሮች በሆቴሉ ውስጥ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

ለምን ውሉን ማቋረጥ እንዳስፈለገው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲን ጠይቀነው፣ "የአዲስ አበባ አስተዳደር ለህዝብ አገልግሎትና ለልማት የሚፈለጉ ቦታዎችን የመስጠት አሠራር ያለ በመሆኑ፣ የአስተዳደሩ ሊዝ ቦርድ ወስኖ ለኤጀንሲው ካሳ በመክፈልና ውላችንን እንድናቋርጥ ደብዳቤ በመፃፉ ውሉ እንዲቋረጥ ደብዳቤ ፅፈናል" ሲሉ የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ወልደጊዮርጊስ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ውብሸት ብርሃኑ በበኩላቸው "ቦታው ባለአደራ አስተዳደሩ ከመምጣቱ በፊት የነበረው ቦርድ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦታውን በሊዝ ሸጦለታል፡፡ ባንኩ ቦታዬን አስረክቡኝ በማለቱ የአፈፃፀም ደብዳቤ ተፅፏል፡፡ በዚህም መሠረት ኤጀንሲው የውል ማቋረጥ ደብዳቤ ፅፎ ይሆናል" በማለት ከዚህ በላይ ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

ቦታው ከጊዜያዊ ባለአደራ አስተዳደሩ በፊት የነበረው ቦርድ በሊዝ እንደሸጠው እየታወቀ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ለምን አዲስ የኪራይ ውል ተዋዋለ? በማለት ላቀረብንላቸው ጥያቄ "ይህንን እኔም አላውቀወም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በታምሩ ጽጌ
 
< Prev   Next >