| የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚዲያ አጠቃቀም... |
|
|
| Wednesday, 05 March 2008 | |
![]() ኘሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ![]() አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ![]() ዶክተር መረራ ጉዲና በሚያዚያ ወር ለሚካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ቅስቀሳን አስመልክቶ ለፓርቲዎች የተሰጠው የመገናኛ ብዙሀን የአየር ሰዓት ድልድል ፍትሀዊ አለመሆኑን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በሰጡት አስተያየት የመንግሥት መገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ አለመቻላቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚህም ገዢው ፓርቲ በበላይነት መገናኛ ብዙሀኑን የሚጠቀምበትን መንገድ አመቻችቷል በማለት ወቅሰዋል፡፡ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሃፊ አቶ ሳሳሁልህ ከበደ የቅስቀሳ የአየር ሰዓት ድልደላ ፓርቲዎች ባቀረቧቸው እጩዎች ቁጥር ብዛት መሆኑ አግባብ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ዋና ፀሃፊው "ገዢው ፓርቲ ለራሱ ጠቀሜታ ሲል በእጩዎች ብዛት የአየር ስዓት ድልደላ ቀመር እንዲወጣ አድርጓል" ብለዋል፡፡ አቶ ሳሳሁልህ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅንጅት በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ያቀረባቸውን የእጩ ተወዳዳሪ ብዛት ብቻ ከግንዛቤ በማስገባት ሊሰጣቸው የሚገባው የአየር ሰዓት መቀነሱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም "በፓርቲያችን ላይ ከፍተኛ ሸፍጥ ተካሂዷል" ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ይህንንም በተመለከተ የቅሬታ ደብዳቤ የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እንዲሁም ለብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ ማቅረባቸውንና ምላሽ እንዳላገኙ አብራርተዋል፡፡ ዋና ፀሃፊው "የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሆን ብሎ ትክክለኛውን የእጩዎቻችንን ቁጥር ለሚመለከተው አካል ሳይልክ ቀርቷል" ሲሉ አማርረዋል፡፡ በማያያዝም የአየር ሰዓት ህብረ ብሔራዊ ፓርቲዎቻችንና የጐሳ ፓርቲዎችን በመለየት እንዳልተከናወነ አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሰያዊ ኃይሎች ህብረት ሊቀመንበር ኘሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ፓርቲያቸው በፓርላማ 51 መቀመጫ እንዳለው፣ ነገር ግን የአየር ሰዓቱ የተሰላው በ12 መቀመጫ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዚህም በኦሮሚያ ውስጥ ያላቸው መቀመጫ በሙሉ ተነጥቆ ከህብረት እራሱን ላገለለው ለአብኮ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ ኘሮፌሰሩ "ይህ ፍፁም ህገወጥነት ነው" ሲሉ አማርረዋል፡፡ ሊቀመንበሩ ፓርቲያቸው ማግኘት ከነበረበት አምስት ሰዓት የአየር ጊዜ መቀነሱንና አንድ ሰዓት ብቻ የተፈቀደላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አብኮ ለውድድሩ እጩ አለማቅረቡንና ከኢህአዴግ ቀጥሎ ከፍተኛ የአየር ጊዜ የተመደበለት መሆኑን በመጥቀስ ፓርቲያቸው ላይ ሸፍጥ መሠራቱን ገልፀዋል፡፡ ኘሮፌሰሩ ፓርቲያቸው በዚህ ሁኔታ በምርጫው ለመሳተፍ እንደሚቸግር አስታውቀዋል፡፡ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው የአየር ሰዓት ድልድሉ "ፍትሐዊ ብቻ ሳይሆን የሕፃን ጨዋታ ሆኗል" ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ዶክተር መረራ የተለመደው የሸፍጥ ጨዋታና የኢህአዴግ ገታራ አቋም መቀጠሉን አብራርተዋል፡፡ ይህ አካሄድ በኢትዮጵያ ህዝብና በታሪክ ፊት የሚያስጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶክተር መረራ የምርጫውን ሂደት ከምርጫ ቦርድ ይልቅ የመንግሥት አስተዳደር እያከናወነው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በምርጫው ሂደት መቀጠሉም ሆነ መውጣቱም ጥቅም እንደሌለው ገልፀዋል፡፡ የኦሮሞ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከተሰጣቸው የቅስቀሳ የአየር ጊዜ ውስጥ ዘጠና ከመቶው በኦሮምኛ መሆኑ አግባብ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ "የአየር ሰዓቱ ድልደላ ፍትሀዊ ያልሆነና ያልተስማማንበት ነው" ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ መስፍን ሽፈራው ፓርቲያቸው ከኢህአዴግ እኩል የእጩ ብዛት ማቅረቡን ጠቁመው የአየር ሰዓት ድልደላው፤ ከኢህአዴግ ጋር ሲነፃፀር 57 ለ 1 መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ድልድሉ ለገዢው ፓርቲ ያደላ መሆኑን አቶ መስፍን አብራርተዋል፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |