| “ጨዋታ” የማያውቁ የዴሞክራሲ ፖለቲካ እሴቶች |
|
|
| Wednesday, 05 March 2008 | |
|
(ከአብርሃ ዘያሬድ)
አገራችን ስፖርት መጫወት፣ ስፖርት ማጫወት፣ የተዋጣላት የስፖርት መልካም አስተዳደር ማየት ብቻ ሳይሆን ሌሎች የተዋጣላቸው፣ የተዋጣላት የሚባል የስፖርት አስተዳደር ያላቸው አገሮች፣ ማኅበሮች፣ ቡድኖች/ክለቦች ጥሩ እና ጨዋ ስፖርታቸውን ሲያሳዩ እንኳን ጥሩ ተመልካች ሆነን ማየት ያልቻለችበት አገር እየሆነችብን በእጅጉ የተቸገርን ይመስለኛል፡፡ ይህ የጨዋታ ጉዳይ ግን የጨዋታ ብቻ ነው የሚባል አለመሆኑ ችግሩን ከሌሎች ችግሮችና የአገር ሕመሞች እኩል ቦታ እንድንሰጠው አድርጎናል፡፡ ጉዳዩ የሚወዳደርና የሚነጻጸር በየዘርፉና በየመስኩ ችግሩ በየቦታው ያለ ነው የሚባልም በዚህ የሚያበቃም ብቻ አይደለም፡፡ በፖለቲካውና በቁም ነገሩ የምናየው የአገር ሕመምና ጠንቅ ያለበትና የተጠናወተው በሽታ በተመሳሳይ ሁኔታ በስፖርቱም “ጨዋታ” በሚባለውም የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚታየውና ያው ተመሳሳይ ቫይረስ የለከፈው ነው፡፡ በድርብ ጥንድ ትርጉሙ በተለይም በአገራችን ውስጥ “የተመልካች ስፖርት” ከዚህም መካከል የተመልካችና የተመልካች ብቻ ስፖርት እየሆነ የመጣውን እግር ኳስ እንደ ተመልካች ብቻ እንኳን ጥሩና ጨዋ ተመልካች መሆን አልቻልንም፡፡ ይህንን የሚያመለክቱ ሁለት ዓይነት አብነቶችን ላቅርብ፡፡ አንደኛው ለምሳሌ አርሰናልና ቸልሲ ሲጫወቱ በአንድ የአርሰናል ወይም የቸልሲ (ብቻ) በሆነ ማሳያ ቤት ደጋፊው የሳሳውን ቡድን ለሚደግፍ ሰዎች መናገር ሃሳብን መግለጽ እንደ ሰው ጮክ ብሎ ተስፋን፣ ስጋት፣ ደስታን፣ ሀዘንን ለመግለጽ እጅግ በጣም የተነወረ የተከለከለ ነው፡፡ በሌላው መስክ እንደሚታየው “የብቃት ማረጋገጫ ወይም ፈቃድ” የሚሰጠው ጉዳይ እንኳን አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ ከስልጣን ተወገደ የሚባለው በውጭ አገር የስፖርቱ አስተዳዳሪና ገዥ አካል በኩል ደግሞ የአገሪቱ የእግር ኳስ ጨዋታ ብሔራዊ ሕጋዊ ወኪል ተደርጎ የተወሰደው አመራር ሥልጣን ላይ (እውቅና አግኝቶ) በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ የእግር ኳስ እድገት ለማምጣት የተመልካችን ወደ ስታዲየም መምጣት በውጤትነት ለማስከተል ዘየደ የተባለው መፍትሄ ያኔ እንደተወራው “ዲኤስቲቪ”ን መከልከል ወይም መኩርኮም ነበር፡፡ “ህዳሴ” አገኘ የተባለው አዲሱ ነገር ግን የፊፋን እውቅና ያላገኘው አስተዳደርም ወደ ዙሪክ ከመሄዱ በፊት እግረመንገዱን ጎራ ያለው ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው የአመራሩ በእቅድ የተያዘ እርምጃ አድርጎ የወሰደው ለንደን ላይ የአገሪቱን የፕሪሚየር ሊግ ኃላፊዎች አንድ በሉን ብሎ ለመማጸን መፍትሄ ለመፈላለግ ነው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ስታዲየሞች በአውሮፓ/በእንግሊዝ ጨዋታ ምክንያት ሰው ዞር አልልባቸው ስላለ አዲሱ የሚባለው የእግር ኳስ አስተዳደር በዘየደው መላ መሰረት እንግሊዞች የራሳችንን ኳስ ጨዋታ እያየን ወዲያውም የእንግሊዝንም እንድንመለከት ትልልቅ ስክሪኖች ሊተከልልን ነው ተብለናል፡፡ የአገራችን የእግር ኳስ አስተዳደር በሚደንቅ ሁኔታ አሁን የደረሰበት ችግር ውስጥ የገባው ጨዋታ መመልከትን በመሰለ ተራና “ትንሽ” ከሚባል ነገር ጀምሮ ትልቁ እሚባለው ፖለቲካ ውስጥ ድረስ ያለው የአገር “ሶፍትዌር” በተመሳሳይ ሁኔታ ጨዋጨዋታም ሆነ የህግ የበላይነት የሚባሉት እስቶች ያለመሆኑ ነው፡፡ በትልቁ የፖለቲካ መስክ የአንድ ፓርቲ አባል ወይም ደጋፊ የመሆን ጉዳይ በዚያውም ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ተቃዋሚም ሆነ ገዥ ፓርቲ ዘንድ ሌላውን ያገለዋል፣ ጠላት አድርጎ ይፈርጀዋል፡፡ ከዜግነት ትርጉም ውጭ ያወጣዋል፡፡ ይህ የአግላይ ፖለቲካ (ኤክስኩሉዠነሪ ፖለቲክስ) የላቀን የመጠቀን በሚሉት ሁሉ የሚታይ ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ላሳይ “ህዳሴ” በሚባል የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ልሳን ልዩ እትም የኢሕአዴግ የምርጫ ምልክት ትርጉም “ይበራል” የሚል ርዕስ በተሰጠው አንድ ግጥም ተብራርቷል፡፡ በዚህ ግጥም መሰረት ችቦው (የኢሕአዴግ የምርጫ ምልክት) “የአንደኛው ጫፍ የሕዝቦች ጧፍ መብራት”. የጎህ ፍንጣቂ . . . ጨረሩ የሰፋ የወደፊት ተስፋ”. ችቦውን አንድዶ ነጻነት ያመጣ” ነው፡፡ ችቦው በሌላኛው በኩል “እንቅፋት አስወጋጅ” ብቻ አይደለም፡፡ ችቦው እንዳይበራ ለሚያሰናክሉ ከድህነት ጋራ”“ ተሳስረው ላደሩ የሀገር ክብር እድገት”. ሞታቸው ለሆነ ተስፋቸው ተሟጦ”. ነትቦ ለበነነ ውርደት ከጫንቃቸው፣ አብሮ ለተሰፋ ስፍር ቁዝማቸው . . .ሞልቶ ለተደፋ የችግርን ክምር”. ለመናድ ለፈሩ መንገድ ላይ ተጋርጠው፣ እንቅፋት ለሰሩ ከዚህም ከዚያም ለቅመው”. ወሬን እየገዙ ትርፍ የለው ኪሳራን፣ ደራርበው ላበዙ ለእንደዚህኞቹ”. ችቦው ያቃጥላል መሞቅ አይቻልም”. ወደፊት ይፋጃል ያሳሳል ይጠርጋል”. ግን ደግሞ ይበራል” ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር ይህ ግጥም “በሌላኛው ጫፍ በኩል” ላሉት የሚያስተላልፈው መልዕክት በግጥሙ መጨረሻ ላይ ስማቸው/የብዕር ስማቸው የተጠቀሰው ሰው ይሁን የፓርቲው የኢሕአዴግ የመመረጫ ፕሮግራም በአብላጫ ድምፅ ቢያሸንፍ ችቦው እየመረጠ የሚበራበት፣ እየለየ ደግሞ በወላፈኑ እየተፋጀ “መሞቅ አይቻልም” እያለ እያሰሰ፣ እየጠረገ “ያሳሳል፣ ይጠርጋል” የሚልበት የዴሞክራሲ ፖለቲካ እሴት በጭራሽ የለም፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ በየአምስት ዓመቱ በሚደረግ ምርጫ/መቀያየር የሚለዋወጥ መንግሥት የወቅቱን ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ወይም ሥልጣን ላይ ለመውጣት ፕሮግራሙን አቅርቦ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርግ የፖለቲካ ፓርቲ አልደገፍክም አልመረጥክም፣ ፕሮግራሙን ራዕዩን ትቃወማለህ፤ ተብሎ “የሀገር ክብር እድገት”. ሞታቸው ለሆኑ” በሚል ክስና ወቀሳ የሚወገዝበትም ሆነ የሚታማበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ ትልቅ በሚባለው “ፖለቲካ” ውስጥ የሚታየው ይኸው “እኛ እና እነሱ” ጥበብ ስፖርቱ አስተዳደርም ጨዋታውም ውስጥ ያው አለ፡፡ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የመልካም አስተዳደር ችግር ጉዳይ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ እንዴት እንዲህ እያደረገ አሁን ወደ 2000 እንደተሸጋገረ ያየነውና የሰማነው ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በነበረው ውዝግብ በአንድ በኩል አቶ ተዘራ ወዳጆ በሌላ በኩል ዶክተር አሸብር ነበሩ፡፡ አሁን በአንድ በኩል ዶክተር አሸብር በሌላ በኩል አቶ አህመድ ያሲን ናቸው፡፡ ሁለቱም ጊዜ ፊፋ አንዱን አላውቅም ሌላውን አውቃለሁ ብሏል፡፡ ተመሳሳይ አሰራርና አቋም ወስዷል፡፡ ይህ ጸሐፊ ዛሬ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ገብቶ ብዙ የሚለው ነገር የለም፡፡ የእግር ኳስም ሆነ የየትኛውም የግልም ሆነ የግል ያልሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በተለይም የስልጣን ሽግግር አያያዝና መተላለፍ ጉዳይ በጥፋትና ጥፋት መሰረት አይነተኛው የሥልጣን ጉዳይ ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም፡፡ የዶክተር አሸብር የፕሬዚዳንትነትና መላው አስተዳደራቸው ምንም የማይታበል፣ የማይካድ ከባድና ብርቱ ጥፋት አጥፍቷል እንበል፡፡ እንዲያ ስለሆነ ግን ጥፋተኛውንና በደል የፈጸመውን የስፖርት አስተዳደር ለመቀየር የስፖርቱን ሕግ አላግባብ መቀየር በተቋቋመው የስፖርቱ የአስተዳደር ሕግ ላይ ጥፋት መፈጸም ትክክለኛው መንገድ አይደለም፡፡ አንድን ጥፋት በሌላ ጥፋት አነስተኛም ሆነ ከባድ ጥፋት ማረም አይቻልም፡፡ አይገባም፤ ዴሞክራሲያዊም አይደለም፡፡ ከዚህ የባሰውና የከፋው ደግሞ እውነተኛ ነገር ትክክለኛ መንገድ ይዞ እንኳን ቢሆን በዚህ ምክንያት የአንዱን “ዜግነት” ወይም “የሀገር ክብር እድገት ተቆርቋሪነት” ጉዳይን ለጥያቄ ማቅረብ “ሞታቸው ለሆነ”“. ብሎ ማወጅ የዴሞክራሲ ፖለቲካ ወግና ባህል አይደለም፡፡ በተለያዩ መድረኮች ሲባል የሰማነው ግን ይህንኑ ነው፡፡ ከፊፋ የፌብርዋሪ 22 ውሳኔ ይፋ መሆን በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው አዲሱ አስተዳደር (ወይም ፊፋ “ተብየው” የሚለው) በደርግ ዘመን የረሳነውን የሚያስታውስ፣ እያስተዛዘነ ዜግነትን የሚጠይቅ መግለጫ ነው የሰጠው፡፡ ኢትዮጵያ ተወልዶ አድጎ ንግድ ፈቃድ አግኝቶ አገሩን መክሰስ ሲል የሰጠው የአዲሱ አስተዳደር መግለጫ “የእናት ጡት ነካሽ”ን ያስታውሰናል፡፡ በተመሳሳይ ቅኝት የአንድ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ “ዶክተሩ በልማቱ ጅምር መንገድ ላይ ቆመዋል” በሚል ርዕስ ጽፏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በዚህ ጉዳይ ላይ ጋዜጦች የሕዝቡን ስሜት ብቻ ሳይሆን የዋና ባለጉዳዮን በተለይም የአዲሱን አስተዳደር (መፀነስና መወለድ ጨምሮ) አረማመድ የውሃ ቦይ እየቆፈሩ መርተውታል የሚል ጥርጣሬ አለ፡፡ ፖለቲካችን ከጨዋታ ማወቅ ቢጀምር በሁሉም ዘርፍ የማያምርበት ምክንያት የለም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |