| የአሜሪካ አየር ኃይል በሶማሊያ ጥቃት ሰነዘረ |
|
|
| Wednesday, 05 March 2008 | |
|
የአሜሪካ የአየር ኃይል በሶማሊያ የእስልምና አክራሪ ቡድን ላይ ጥቃት መሰንዘሩን የአይን እማኞችን በመጥቀስ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ደሆብል ከተማ ላይ በተሰነዘረው በዚሁ ጥቃት ከስድስት በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከሀያ በላይ ሰዎች ቆስለዋል፡፡ የሶማሊያ አክሪሪ ቡድን የደሆብል ከተማን ሰሞኑን ከመንግሥት ኃይል በማስለቀቅ መቆጣጠራቸው አይዘነጋም፡፡ የከተማዋ ነዋሪ ፋጡማ አብዱላሂ በአየር ጥቃቱ በአካባቢው ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ገልፃለች፡፡ የቡድኑ ቃል አቀባይ ሼህ ሙክታር “አሜሪካኖች በሰነዘሩት ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ ሆነዋል” በማለት ጥቃቱ ኢላማውን መሳቱን አስታውቀዋል፡፡ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጥቃቱን በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የፀረ-ሽብርተኝነት ዘመቻውን ለማሳካት እገዛ የሚያደርግ ልዩ ኃይል ጅቡቲ ላይ ማቋቋሙ ይታወቃል፡፡ በኬንያ የአናን ተልዕኮ ተጠናቀቀ የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ኮፊ አናን በኬንያ የጀመሩት የሰላም ድርድር ተልዕኮ በድል ተጠናቀቀ፡፡ በኬንያ የኘሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ተከትሎ የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት ጥረት ያደረጉት አናን ተልዕኳቸውን አጠናቀው ወደ ኡጋንዳ አቅንተዋል፡፡ በሰላም ድርድሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ የጠቅላይ ሚኒስትርነት የስልጣን መንበር ተረክበዋል፡፡ አናን ኬንያውያን የሀገራቸውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በንቃት መከታተል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ “ኬንያውያን በሀገራችሁ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላችሁን ኃላፊነት መዘንጋት የለባችሁም፤ ፖለቲከኞች ብቻ እንዳስፈለጋቸው እንዲያካሂዱ መፍቀድ የለባችሁም” በማለት ለህዝቡ መልስ ማስተላለፋቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል፡፡ የአረብ ዘላኖች በሱዳን ግጭት ተገደሉ ከሰባ በላይ የታጠቁ የአረብ ዘላኖች በደቡብ ሱዳን ውስጥ በተቀሰቀሰ ግጭት መገደላቸውን አሶሲየትድ ኘሬስ ዘገባ አመለከተ፡፡ በደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ንቅናቄና በመሰሪያ ጐሣ አባላት መካከል ሰሞኑን በተቀሰቀሰ ግጭት በአካባቢው የሚኖሩ ከሰባ በላይ አረብ ዘላኖች ሲገደሉ ስድስት የአማፂው ቡድን ወታደሮች ተገድለዋል፡፡ የሱዳን የዜና ማዕከል በበኩሉ የመሰሪያ ጐሣ አባላት የአማፅያኑ ካምኘ ላይ ከፍተኛ ጥቃት መሰንዘራቸውን ዘግቧል፡፡ በጥቃቱ አማፅያኑ አካባቢውን ጥለው ለመውጣት መገደዳቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ በነዳጅ ሀብት የምትታወቀው የአበዬ አካባቢ በተቀሰቀሰው በዚሁ ግጭት ውጥረት መንገሱን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ የአማፅያኑ ቡድን የሱዳን ማዕከላዊ መንግሥት የመሰሪያ ጐሣ አባላትን በማስታጠቅ ጥቃት እየሰነዘረ መሆኑን ገልጿል፡፡ የእስራኤል የጦር ኃይል ከጋዛ ወጣ የእስራኤል የጦር ኃይል የጋዛ አካባቢን ለቆ መውጣቱን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡ በእስራኤል የጦር ኃይልና በጋዛ ታጣቂዎች መካከል ሰሞኑን በተካሄደ ግጭት ከመቶ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል፡፡ የእስራኤል የጦር ኃይል በአካባቢው በሰነዘረው ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን በመጥቀስ የአረብ ሀገራት ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡ ሀማስ በበኩሉ በእስራኤል ላይ ድል መቀዳጀቱን ገልጿል፡፡ የእስራኤል የጦር ኃይል ከጋዛ የተሰነዘረበትን የሮኬት ጥቃት አፀፌታ መመለሱንና በዚህም በሀማስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል፡፡ የእስራአል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሀም ራሞን “የእስራኤል መንግሥት ዋነኛ ተልዕኮ ከጋዛ የሚሰነዘረውን የሮኬት ጥቃት ማስቆም ነው፤ ይህንንም አሳክተናል” በማለት አብራርተዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |