Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ወርቅ ቤቶች "ወርቅ" ያሉት ጉዳይ...
ወርቅ ቤቶች "ወርቅ" ያሉት ጉዳይ... Print E-mail
Wednesday, 05 March 2008
ወርቅ ቤቶች "ወርቅ" ያሉት ጉዳይ እንደገና ምርመራ ሊካሄድበት ነው

ፀረ ሙስና በብሔራዊ ባንክ ላይ የጀመረውን የአሰራር ማሻሻያ አቋረጠ


የፌደራል የስነምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽን ተጭበረበረ በተባለው 38 ኪሎ ግራም ወርቅ ላይ እንደገና ከመነሻው ጀምሮ ለጥልቅ ምርመራ ሊያካሂድ መሆኑ ተሰማ፡፡
 
ከሶስት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ በደህንነት ኃይሎች የተያዘውን 38 ኪሎ ግራም ወርቅ ኮሚሽኑ ወደ ኋላ ተመልሶ መመርመር ያስፈለገው ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤት ብይን ከተላለፈባቸው ሁለት ተከሳሾች መካከል አንዱ የተገኙት ወርቁ ተመርምሮ ብረት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ መሆኑን የኮሚሽኑ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የኮሚሽኑ ምንጮች እንዳስታወቁት ወርቁ በህገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ ሲል እንደተያዘ እማኝ የፖሊስ አባላት በተገኙበት በአንድ የግለሰብ ወርቅ ቤት ተመርምሮ ወርቅ እንደሆነ ተረጋግጦ ነበር፡፡ የፌደራል ፖሊስ ኤግዚቢት ኦፊሰር በአደራ የተረከቡት ይሄው ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ የፌደራል የስነምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽን በተደጋጋሚ ፌደራል ፖሊስን በደብዳቤ ጠይቋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ጥያቄው ከቀረበለት ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ በአደራ ያስቀመጠው ወርቅ እንዲመረመር ሲደረግ ብረት ሆኖ መገኘቱን ያስታወቁት ምንጮች ይሄው ወርቅ እንዴት ብረት ሆነ? የሚለው ጥያቄና በወንጀሉ ከተፈረደባቸው በኋላ በቅርቡ ፍርዳቸውን ለመፈፀም ከተሰወሩበት መጡ የተባሉት ወንጀለኛ ጉዳይ የማጭበርበር ሂደቱን ውስብስብ ስለሚያደርገው ምርመራው ከስር እንዲጀመር ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

በወቅቱ ወርቁ በግለሰብ ወርቅ ቤት ተመርምሮ ወርቅ ነው ከተባለ በኋላ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ ባንክና የፖሊስ ታዛቢዎች ባሉበት ካዝና ገብቶ መታሸጉን የጠቆሙት ውስጥ አዋቂዎች "ወርቁ የትና እንዴት ተጭበረበረ" የሚለውን ለማጣራት ኮሚሽኑ ምርመራውን እንደ አዲስ እንዲያካሂድ ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የፌደራል ፖሊስ የኤግዚቢት ኦፊሰር ብቻ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በሌሉበት የተፈረደባቸውና ፍርዴን ልፈጽም በማለት ሰሞኑን እንደመጡ የተነገረላቸው የወንጀሉ ተባባሪ በእስር ላይ ይሁኑ ተመልሰው ከአገር ይውጡ የኮሚሽኑ ምንጮች የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤት በቁጥጥር ሥር በዋሉት አንድ ተከሳሽና በጠፉት ሌላኛው ተከሳሽ ላይ 10 ዓመት እስራት ፈርዶ ነበር፡፡

በሌላ የወርቅ ዜና በብሔራዊ ባንክ ያለው ወርቅ እንዲመረመር በታዘዘው መሰረት ከተመረመሩት በአደራ የተቀመጡ ወርቆች መካከል በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ የአውሮፕላን የውስጥ አካል ተደብቆ ከሦስት ዓመት በፊት የተያዘው 25 ኪሎ ግራም ወርቅ ተመርምሮ ወርቅ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በወቅቱ ከአዲስ አበባ ወደ ዱባይ ይጓዝ በነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የውስጥ አካል የተደበቀው ወርቅ ሲመነዘር ከ1.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነው ብር የተያዘው በዱባይ ፖሊስ ነው፡፡

አውሮፕላኑ ዱባይ አየር ማረፊያ እንደደረሰ ወርቅና ብሩ ከተደበቀበት የአውሮፕላኑ የውስጥ አካል ሲወጣ ፖሊስ እንደያዘው ያስታወሱት ምንጮች ወንጀለኛውን መንግሥት ከዱባይ ፖሊስ ጋር በመነጋገር በወቅቱ ወደ አገር ቤት እንዲመጣ አድርጎት ነበር፡፡

ወርቅና ብሩን ለማስመለስ በተደረገ ተደጋጋሚ ጥያቄ መስማማት ላይ ተደርሶ ወርቅና ብሩን ወደ አገር ቤት እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ በቅርቡ በተካሄደ ምርመራ ትክክለኛ ወርቅ መሆኑ እንደተረጋገጠ የገለፁት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ክፍሎች "በሰው አገር ተቀምጦ የመጣ ወርቅ ትክክለኛ ወርቅ ሆኖ ሲገኝ እዚሁ አገር ቤት በአገር ልጅ እጅ የተቀመጠ ወርቅ ብረት ሆኖ መገኘቱ አሳዛኝ ነው" ሲሉ በዝርፊያው ማዘናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ ዜና የፌደራል ስነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን በብሔራዊ ባንክ ላይ ጀምሮት የነበረውን የአሰራር ማሻሻያ ጥናት ማቋረጡ ታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ ጥናቱን ያቋረጠበትን ምክንያት ይፋ ባያደርግም ባንኩ ከገባበት ውስብስብ ችግር የተነሳ እየተካሄደበት ያለው ምርመራ ቀድሞ መጠናቀቅ ስላለበት እንደሆነ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሁለት ግለሰቦች በከፍተኛ ደረጃ ያጭበረበረው ሲሆን እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር ያልዋለው ከፍያለው ኡመታ 29 ጊዜ ማጭበርበሩ ተጠቅሶ ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡

ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ካሉት ላይ በፍተሻ፣ በጥቆማና በተለያዩ መንገዶች የተዘረፈው ከፍተኛ ገንዘብና ወርቅ እንደተገኘም ለማወቅ ተችሏል፡፡  

በአሰግድ ተፈራ
 
< Prev   Next >