| መንግሥት የጀመረውን የደመወዝ... |
|
|
| Wednesday, 05 March 2008 | |
መንግሥት የጀመረውን የደመወዝ ጭማሪ ሁሉም ይከተለውየመንግሥት የገንዘብ ድርጅቶች፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የቢዝነስና ኮንስትራክሽን ባንክ፣ የልማት ባንክና የመድን ኢንሹራንስ ሠራተኞች በቅርቡ የደመወዝ ጭማሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ መንግሥት ካለአንዳች ግፊት የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉና አራት ወር ወደ ኋላ ተመልሶ እንዲጀመር ማድረጉ ያስመሰግነዋል፡፡ ይህ ለሦስት ዓመታት ተዘግቶ ሳር በቅሎበት የነበረው ኤጀንሲ ሥራ እየሰራ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ የኑሮ ውድነት በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ቤት ተዳርሷል፡፡ ብዙ ደመወዝ ያገኛል የሚባለውም አሁን ካለው የዋጋ ንረት አንጻር ያ ብዙ የተባለው ደመወዝ ሲነኩት ጦሽ የሚል ሆኗል፡፡ ይህ የኑሮ ውድነት ሁኔታ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄን በሁሉም መሥሪያ ቤት እያስነሳ ነው፡፡ ያለው ችግር በፋይናንስ ድርጅቶች ብቻ ስላልሆነ መንግሥት በሌሎች መሥሪያ ቤቶችም ተመሳሳይ ጥናት እያደረገ ተመሳሳይ የደመወዝ እድገትና ጭማሪ እንደሚያደርግ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘትና የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የሚለው መመዘኛ ሁሉንም የመንግሥት ድርጅቶች የሚመለከት ነው፡፡ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ የመንግሥት ድርጅቶችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ የግል ኩባንያዎችና ድርጅቶችም ተመሳሳይ ጥያቄ ተደቅኖባቸዋል፡፡ ከኑሮ ውድነት ጋር የማይጣጣም የደመወዝ ሁኔታ ፊት ለፊት የተደቀነ ጥያቄ ነው፡፡ ስለሆነም የደመወዝ ጭማሪና እድገቱ ተግባር ላይ ሊውል ይገባል፡፡ ትራንስፖርቱ፣ ወተቱ፣ ሙዙ፣ ዳቦው ወዘተ. ሁሉ በየቀኑ እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ሰዓት እንደ ዱሮው ቀጥል ማለት አስቸጋሪ ነውና ደመወዝ የመጨመር አጀንዳ ሁሉም ሊያነሳው ይገባል፡፡ በአንድ በኩል አሠሪዎችና ቀጣሪዎች የደመወዝ መጨመር እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ሲገባ በሌላ በኩል ደግሞ ሠራተኛው ሊያደርገው የሚገባ ነገር አለ፡፡ የድርጅቱን ገቢ እንዲጨምር በርትቶ መሥራትንና የደመወዝ ጭማሪውን ከድርጅቱ አቅም በላይ አለመጠየቅን ነው፡፡ ምክንያቱም በደመወዝ ጭማሪ ምክንያት ድርጅቶች ተዘግተው ወደ ሥራ አጥነት ማምራት እንዳይኖር መጠንቀቅ ነው፡፡ በአሠሪና በሠራተኛ መካከል ይህ ሚዛን መጠበቅ አለበት፡፡ መጨመር ከአሰሪ" መረዳትና ማመዛዘን ከሠራተኛ" ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ጉዳይ ግን የኑሮ ውድነት በደመወዝ ጭማሪ ብቻ የማይፈታ መሆኑን ነው፡፡ ኑሮ ውድ ቢሆንም ግድ የለም ደመወዝ እጨምራለሁ እየተባለ መኖር አይቻልም፡፡ ዋጋ የሚቀንስበት ስልት መፈለጉም ጎን ለጎን ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በኅብረተሰቡ ላይ እየቀለዱ ያሉ ነጋዴዎችም የነፃ ገበያ መንፈስ ሳይረበሽ ቁጥጥርና አመራር ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ በከተማው ዙሪያ ያሉት መጋዘኖች ችግር ፈቺ እንጂ ችግር ፈጣሪ መሆን የለባቸውም፡፡ ስግብግብነት፣ ሸፍጥና ተንኮል የሚደረደርባቸውና የሚሸረብባቸው መጋዘኖች መሆን የለባቸውም፡፡ በአቋራጭ ብልፅግናን ለመፍጠር እንቅልፍ የሚታጣባቸው ሳይሆኑ፣ የልማትና የሚዛናዊ ግብይት አጥር ሆነው ኅብረተሰቡን የሚያገለግሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ መደረግ ያለበት ይህ ብቻም አይደለም፡፡ የኑሮ ውድነትን ለመፍታት ምርት መጨመርም ሌላው መፍትሄ ነው፡፡ የበርበሬ ዋጋ እንዳይሰቀል የበርበሬ ምርት መጨመር፣ የስንዴ የማሽላና የጤፍ ዋጋ ከተሰቀለበት ለማውረድም የምርት መጨመር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ሦስት መንገዶች አስቀምጠናል፡፡ አንደኛው የደመወዝ ጭማሪ፣ ሁለተኛው በነጋዴ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እና ሦስተኛው ምርት መጨመር ናቸው፡፡ በእነዚህ መንገዶች እየናረ ያለውን የሸቀጦች ዋጋ መቋቋምና ጉዳቱን መቀነስ እንችላለን፡፡ እነዚህን ለማድረግ ግርግር መፍጠርና ሰላምን ማደፍረስ አያስፈልግም፡፡ በመረዳዳት መደረግ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ሠራተኛው እስኪለምንና እስኪጠይቅ መጠበቅም አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ገሃድ የወጣ የኑሮ ውድነት አለና፡፡ የድል አጥብያ አርበኛ ለመሆን መሞከርና ካልተጨመረ ዋ የሚል እንቅስቃሴም አያስፈልግም፡፡ ውይይት ያስፈልጋል ባለሙያዎች ስለጉዳዩ ሊያስረዱ፣ ሕዝብ ያሰበውን ሊጠይቅ መድረክ መከፈት አለበት፡፡ ይህም የሁላችንም የመገናኛ ብዙሃን ሥራ ነው፡፡ ከነዳጅ ጋር የተያያዙ የዋጋ ጭማሪዎች ከቁጥጥራችን ውጭ ናቸው፡፡ በእነዚህ እየተመካኘ የሚደረጉ አላስፈላጊ ጭማሪዎች ግን መቆም አለባቸው፡፡ ከነዳጅ ጋር የተያያዙና ያልተያያዙ ጭማሪዎችን ለመለየትም ውይይት ያስፈልጋል፡፡ የሱር ታክስ ጉዳይስ? በቅንጦት ዕቃዎች ላይ ብቻ የሚደረግ ነው ተብሎ የተጀመረው ወተትንም አካትቷል፡፡ በሱር ታክስ ዙሪያ አንዳንድ ማስተካከያና ስረዛ ቢደረግ በአስፈላጊ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ቅነሳ ሊደረግ ይችላል፡፡ ሁሉም መፍትሄ ይፈልግ፣ ሁሉም ይወያይበት፡፡ መንግሥት ችግሩን በመገንዘብ የደመወዝ ጭማሪ ጀምሯልና ሌላውም ይከተለው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |