Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow "ኢዴኅ... አገር ባይመራም አሁን ያለው...
"ኢዴኅ... አገር ባይመራም አሁን ያለው... Print E-mail
Wednesday, 05 March 2008
Image"ኢዴኅ... አገር ባይመራም አሁን ያለው የዴሞክራሲ ጅምር የእርሱ ፍልስፍና ነበር"
አቶ ግርማይ ሃደራ፣
የኢትዮጵያ ፍትሕና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር ሊቀመንበር

አቶ ግርማይ ሃደራ በ1967 ዓ.ም በትግራይ ክልል ተመስርቶ ፀረ ደርግ በትጥቅ ትግል ውስጥ የቆየው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዲዩ) በ18 ዓመታቸው (በ1968 ዓ.ም) ተቀላቀሉ፡፡ በኢትዮጵያና በሱዳን የድርጅቱ አገናኝ መኮንን ሆነው ሠርተዋል፡፡ በ1984 ዓ.ም ወደ አገር ውስጥ ገብተው እስከ 1992 ዓ.ም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የድርጅቱን ቅርንጫፎች መርተዋል፡፡ ከ1992 ጀምሮ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በቅርቡ የተመሠረተው የኢትዮጵያዊ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር ሊቀመንበር ናቸው፡፡
 
አቶ ግርማይ በቅርቡ የተመሰረተውን ግንባርና በወቅታዊ የምርጫ ሁኔታ አስመልክተን አነጋግረናቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፈጠራችሁት ጥምረት ግንባር ነው ወይስ ውህድ?

አቶ ግርማይ፡- ግንባር ነው፡፡ ህብረት ውስጥ የነበሩት ፓርቲዎች እየወጡ ሲበታተኑ መልሶ መሰባሰቡ አስፈላጊ መሆኑ አምነን ተሰባስበን ነው ይህን ግንባር የፈጠርነው፡፡ የግንባሩ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት (ኢዴኃአ"፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ"ና የኦሮሞ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ (ኦነብፓ) ነን፡፡ ብዙ ጊዜ ወስደን መክረናል፡፡ ለዚች አገር ይበጃል በምንለው ላይ አብረን እንሰራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ግንባር ስትፈጥሩ ተቀናጅተው ከነበሩና አሁን ከተለያዩት ምን ተማራችሁ?

አቶ ግርማይ፡
- ከእነሱ ይህን ተምረናል ብለን እንደ መነሻ የምንወስደው ምንም ዓይነት ትምህርት የለም፡፡ ከውድቀትና መበታተን ምን መማር ይቻላል፡፡ በጋራ መሥራት እንዳለብን እናምናለን፡፡

ህብረት ነበር፤ ከዚያ በፊትም አማራጭ ፓርቲ ነበር፡፡ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራሙ ከሚመሳሰል ጋር ህብረት ፈጥሮ የመንቀሳቀስ ሁኔታ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ህብረቶች ይፈጠራሉ ነገር ግን ግባቸውን ሳይመቱ ይፈርሳሉ፡፡ እኛ ከዚያ የምንማረው ነገር የለም፡፡ ህብረት ፈጥሮ ግቡን የመታ ስለሌለ የምትማረው ውሱን ነው፡፡ ተባብረን መሥራት ከማንም በላይ የምናምንበት ጉዳይ ስለሆነ ትምህርት አያስፈልገውም፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል ከነበሩት በምን ትለያላችሁ?

አቶ ግርማይ፡-
ህብረትና ቅንጅት የተፈረካከሱበት ዋና ምክንያት በፓርቲያቸው መካከል ዴሞክራሲያዊ፣ ግልፅነት የሰፈነበትና የእርስ በርስ መተማመን ስላልነበረ ነው፡፡ ይህ በእኛ ግምገማ ነው፡፡ እኛ ግንባር ስንፈጥር ካለፉት ህብረቶች የምንማረው ነገር አለ ከተባለ እነዚህን ማስወገድ ነው፡፡ በእኛ ግንባር አንዱ በሌላው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ወይም አንዱ ሌላውን ለመዋጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አይኖርም፡፡ በግንባሩ የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ በግለሰቦች ፍላጎትና ውሳኔ ሳይሆን በአሰራርና በህገ ደንቡ መሠረት መሆን እንዳለበት ተማምነናል፡፡

ሌላ ትልቁ ጉዳይ፣ እኛ ግንባር ስንፈጥር የእያንዳንዱ ተናጠል ድርጅት ህልውናና ነፃነት በጠበቀ መልኩ ነው፡፡ ይህ ሌላ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚያ ድርጅቶች መብት ኖሯቸው፣ ለስራቸው ስኬት ደግሞ ጠንካራ ኃይል እንዲኖራቸው ሌላ የጋራ  መድረክ ፈጥረዋል፡፡ የእያንዳንዱ ድርጅት ህልውና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጋራ መስራት ያለባቸው ደግሞ አምነን ተግባብተን ለመሥራት እንድንችል ሰፊ ጊዜ ወስደን መርምረነዋል፡፡ በዋናነት እገሌ ጥሩ ነበር፣ እገሌ መጥፎ ነበር ብለን ሌሎች ድርጅቶች ውስጥ የምንገባበት ነገር አይኖርም፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ወስደን መርምረን ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረስነው፡፡ በተገቢ መልኩ ለመቀጠልም እንሰራለን፡፡ የእኛን ጥንካሬ አይተው ብዙ ድርጅቶች ይቀላቀሉናል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ ኃይል መጨመር ነው፡፡ ወደ ኋላ ይመልሰናል የምንለው ነገር አይኖርም፡፡ በምክክር፣ በመተማመንና በግልፅነት የተመሰረተ ነገር ከመጠራጠርና ከፈላጭ ቆራጭነት አመለካከት የፀዳ ነው የሚሆነው፡፡ የግንባሩ ህልውና በዚህ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሚያዚያ ወር የማሟያና የአካባቢ ምርጫ ሊካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በግንባሩ ስም ነው የምትወዳደሩት ወይስ በተናጠል?

አቶ ግርማይ፡-
የምንወዳደረው በግንባሩ ስም ሳይሆን በተናጠል ነው፡፡ ምክንያቱም ግንባሩ የተፈጠረው ቆየት ብሎ ነው፡፡ ፍቃድ የጠየቅነው በመጨረሻ በመሆኑ ለዝግጅት ጊዜ የለንም፡፡ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ግን በተናጠል ለመወዳደር ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል፡፡ ግንባሩ ለእነሱ አስፈላጊ ድጋፍ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምርጫ ዝግጅት ስታደርጉ የገጠማችሁ መሰናክል አለ?

አቶ ግርማይ፡-
በምርጫ ለመወዳደር ስታስብ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሊሆን አይችልም፡፡ በየክልሉ ድብቅ የሆኑ መሰናክሎች አሉ፡፡ ችግሮቹ በግልፅ የሚታዩ አይደሉም፡፡ ህብረተሰቡን የሚያሸማቅቁ ችግሮች ይፈፀማሉ፡፡ ዛሬ ተመዝግበው ነገ አልወዳደርም ይሉሃል፡፡ ይህ በሁሉም የግንባሩ አባላት ፓርቲዎች ውስጥ እየታየ ያለው ነው፡፡ ከፍተኛ መሸማቀቅ አለ፡፡

በአዲስ አበባ ደግሞ አንድ ከፍተኛ ችግር እየታየ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩዎች ስም አያወጡትም፡፡ ኢህአዴግ ያሸማቅቅሃል፡፡ የተቃዋሚ ዕጩዎች ስም ዝርዝር አለመለጠፍ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቁርጠኛ ድፍረት የለህም ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ያንተ የነበረው አባል ነገ አንተ ጋር አይሆንም፡፡ ምክንያቱም አይነግርህም፡፡ ይህ የሚያሳይህ የማይታይ ውስጣዊ የሆነ ዘመቻ አለ ማለት ነው፡፡ በ59 የምርጫ ጣቢያዎች  እንወዳደራለን፡፡ ይሁን እንጂ የሕዝብ ብዛት ባለባቸው አካባቢዎች የኢህአዴግን ዕጩዎች ብቻ ነው የምታየው፡፡ አሁንም የዴሞክራሲ ባህላችን ገና ያላደገ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን እስከ መጨረሻ በትዕግስት እንጠብቃለን፡፡ ዴሞክራሲ ሂደት በመሆኑ ቀስ በቀስ የሚመጣ ለውጥ ይኖራል፡፡
 
ሪፖርተር፡- የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች አንዳንድ ቦታ ላይ ተለጥፎ አይቻለሁ፣ የእናንተ ብቻ ነው ያልተለጠፈው?

አቶ ግርማይ፡-
አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ስም ዝርዝራቸው ወጥቷል፡፡ ለምን እንደሆነ ግልፅ አለሆነልንም፡፡ ሙከራው ሕዝብን ለመሸወድ ይመስለኛል፡፡ ሕዝብን አትሸውድም፣ ሕዝብን ሸውደህ የምታመጣው ለውጥም አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- ከ97 ምርጫ ምን ተማራችሁ?

አቶ ግርማይ፡-
እኛ ብቻ አይደለንም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ብዙ ይማራል፡፡ ነገሮች በሰከነ መንፈስ መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ አብረህ በምትሰራበት ጊዜ በመጀመሪያ በዓላማ መተማመን አለብህ፡፡ ለጊዜያዊ ጥቅምና ድምፅ ለማግኘት ወይም አንድን አካል ለመጉዳት መሆን የለበትም፡፡ የራስህን ዓላማ ለማሳካት መሆን አለበት፡፡ ዴሞክራሲን ለሕዝብ አሰፍናለሁ ስትል የድርጅትህ የውስጥ አሰራር ራሱ ዴሞክራሲያዊ ፅንሰ ሃሳብ የተከተለ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ያላደረገ ድርጅት ማሸነፍ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የዴሞክራሲ ምንጭ ሊሆን አይችልም፡፡ እኛ ከዚህ ዓይነቱ ሁኔታ መሸሽ ነው የምንፈልገው፡፡ ማንኛውም ልዩነት ሲፈጠር ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማጥበብ ነው የምንፈልገው፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢዴኅ (EDU) ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት አባል ነበር፡፡ በህብረት የነበራችሁ ቆይታ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ግርማይ፡-
ህብረት ሲመሰረት (95 ዓ.ም መጨረሻ) የበርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብሰብ ሆኖ ነው፡፡ ከ14 ድርጅቶች በላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ኢዴኅ ነው፡፡ ህብረቱን መፍጠር ያስፈለገበት ምክንያት በውስጥም በውጭም የነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ተበታትነው፣ የተበታተነ አቋም ይዘው ክፍተት ከሚሰጡ አንድ ሆነው የጋራ ጥያቄና መድረክ ፈጥረው ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ለማቅረብ ተባብረን እንስራ ብለው ስለወሰኑ ነው፡፡ በወቅቱ ተሰብስቦ የነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ ፍላጎት፣ አንዱ የኢህአዴግ የፖለቲካ መስመር ሲሆን ሁለተኛው ህበረት የሚለውን ነገር ብዙ ድርጅቶችን አሰባስቦ በሁለት መንገዶች አቅጣጫ ተለይተው ነበር፡፡ ህብረቱ ከተመሰረተ በኋላም በርካታ ሥራዎች ሰርቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ህብረቱ ይህን ያህል አስፈላጊ ከነበረ ለምን ወጣችሁ?

አቶ ግርማይ፡-
ከህብረት መውጣት የጀመርነው እኛ አይደለንም፡፡ እኛ የወጣነው በመጨረሻ ነው፡፡ በምርጫ 97 ትልቅ ፓርቲ ሆኖ የመጣው ቅንጅት ከህብረት የወጡ ፓርቲዎች የመሰረቱት ነው፡፡ ለምሳሌ ኢዴፓ መድህን፣ መኢአድ፣ መኢሀድ እንዲሁም ኦብኮ እነዚህ ሁሉ በተከታታይ ወጥተዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ከህብረቱ የወጡበት ምክንያት እዚያ ቤት ውስጥ ያለው ችግር ሊያስኬዳቸው ስላልቻለ ሌላ አማራጭ መፍጠር ነበረባቸው፡፡ ስለዚህ እኛም ከህብረት ለመውጣት የተገደድነው ሰበቡ የእኛ ሳይሆን የህብረቱ ነው፡፡ ሌሎች እየወጡ ሲሄዱ ኢዴኅ ለመጨረሻ ጊዜ በርካታ ጥያቄዎችን አቅርቦ ከህብረቱ ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ኢዴኅ ህብረቱ አስፈላጊ ሆኖ ስላላገኘው ለመውጣት ተገዷል፡፡

ደቡበ ህብረት የሚባለውም ከህብረቱ መስራቾች ዋና ተዋናይ የነበረ ቢሆንም እሱም አስፈላጊ ሆኖ ስላላገኘው ከዚህ ወጥቶ እንደገና ተሰባስቦ የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች አንድነት በሚል ተመሠረተ፡፡ ቀጥሎ ኢዴኅ ከእነዚህ አንድነት ከመሰረቱትና ሌሎችንም ጨምሮ ግንባር ለመፍጠር ድርድር ጀመረ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዴኅ በአገራችን ቀዳሚ ከሚባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ እስከ አሁን ምን ለውጥ አምጥቷል?

አቶ ግርማይ፡-
የኢዴኅ ጥያቄ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውስጥ በመጀመሪያ ፀረ ፊውዳል ሥርዓትና ቀጥሎም በደርግ ሲንቀሳቀስ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ በደርግ የፖለቲካ መታገያ ክፍተትም ስላልነበረው፣ ትግል ረየትጥቅሪ ያዋጣል ብሎ ለዴሞክራሲ ለመታገል በ1967 ዓ.ም ተመሠረተ፡፡ ዓላማውም ደርግ የነጠቀውን የኢትዮያ ሕዝብ ስልጣን ለማስመለስ ነበር፡፡

ኢዴኅ ከተመሰረተ ጀምሮ ያስመዘገበው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ነው፡ ኢዴኅ የስልጣን ባለቤት ሆኖ አገር ባይመራም፣ አሁን ያለው የዴሞክራሲ ጅምር መጀመሪያ የኢዴኅ ፍልስፍና ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ኮሚኒስቶች ወይም ጠባቦች ነበሩና ብቸኛ የዴሞክራሲ መስመር ይዞ ሲታገል የነበረው ኢዴኅ ነው፡፡ ዴሞክራሲ በማይታሰብበት ጊዜ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ይዞ የመጣው ኢዴኅ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ኢህአዴግ ስልጣን ይዞ ሰላማዊ ጥሪ ሲያደርግም ለዴሞክራሲ ቅድሚያ ሰጥቶ በሰላም አምኖ በአገሪቱ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ከወሰኑት ቁጥር አንድ ሆኖ ነው የገባው፡፡ ቀጥሎም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብዙ ቅርንጫፎችን ከፍቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲያዊ ስልጣን ባለቤት እንዲሆን ሲታገል ቆይቷል፡፡ አሁንም እየታገለ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ የዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ቡድኖችም ነበሩ?

አቶ ግርማይ፡
- በእርግጥ በትግሉ ላይ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ዓለም በሁለት ተከፍላ ስለነበር ሁሉም የኮሚኒስት/ማርክሲስት ርእዮተ ዓለም ተከታዮች ነበሩ፡፡ የምዕራባውያን ዴሞክራሲ አምኖበት በወቅቱ አቋሙ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኢዴኅ ብቻ ነው፡፡ ህወሓት፣ ኢህአፓ የመሳሰሉ ሁሉም ጠባብ ኮሚኒስቶች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሚኒስት ሆነው ዴሞክራሲያዊ የሆኑ አልነበሩም?

አቶ ግርማይ፡-
ኮሚኒስት ሆነህ ዴሞክራሲያዊ መሆን አይቻልም፡፡ አይገናኙም፡፡ እሣትና ጭድ ናቸው፡፡ በመሬት ዙርያ፣ በፆታ እኩልነት፣ በዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች፣ በፕሬስ ነፃነት ወዘተ. ሁለቱም ተቃራኒ ናቸው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነኝ ስላልክ ሳይሆን የምትከተለው መስመር ነው የሚመራህ፡፡

ሪፖርተር፡- በመሬት ላይ የነበራችሁ ፖሊሲ አሁንስ ቀየራችሁ?

አቶ ግርማይ፡-
እኛ በነፃ ኢኮኖሚ እናምናለን፡፡ መሬት የሕዝብ ነው፡፡ መንግሥት ከሕዝብ ይወለዳል፣ በሕዝብ አገልግሎት ይኖራል አገልግሎቱ ሲጨርስ ደግሞ ለቆ ይሄዳል፣ በሌላም ይተካል፡፡ ስርዓት ይለዋወጣል እንጂ የመሬት ባለቤትነት መለዋወጥ የለበትም፡፡ በሕዝብ ንብረትና ጥቅም ላይ ጣልቃ የሚገባ "ዴሞክራሲ የለም፡፡ አሁንም ኢህአዴግ በመሬት ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ከዚያ የመነጨ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መሬት የመንግሥት ነው በሚለው የኢህአዴግ አቋም ትክክል አይደለም?

አቶ ግርማይ፡-
አይደለም፡፡ በምን መስፈርት? መንግሥት ማለት በሕዝብ በተወሰነ ጊዜ ስልጣን ተሰጥቶት የሚያስተዳድር ነው፡፡ ሕዝብ ግን ነዋሪ ነው፡፡ መሬትም ነዋሪ ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥትን የሚያገናኙ ነገሮች አሉ እንጂ መንግሥትና ሕዝብ አንድ ናቸው የሚባል ነገር አይገባኝም፡፡ ለማደናገር ነው፡፡ መንግሥት የተወሰነ መሬት ለተለየ ዓላማ ሊጠቀም ይችላል እንጂ የመሬት ባለቤት ሆኖ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያከራየው ያሳፍራል፡፡ የመሬትና የምርቱ ተጠቃሚ መሆን ያለበት ሕዝቡ ራሱ ነው፡፡ መንግሥት ይቺ ትበቃሃለች፤ እስከ ብሎ የሚሰጠው ነገር ኢ-ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ሕዝቡ በመሬት ላይ ተጠቃሚ ነው፤ ሲኖር የሚያመርትበት፣ ሲሞትም የሚቀበርበት፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ከሕዝብ መጣ እንጂ ሕዝብ ከመንግሥት አልመጣም፡፡

ሪፖርተር፡- መሬት ይሸጥ ይለወጥ እያሉን ነው?

አቶ ግርማይ፡-
ሕዝብ ለራሱ የሚጠቅመውን ያውቃል፡፡ መሬት ተሰጥቶህ የራስህ መሆኑ መጀመሪያ መረጋገጥ አለበት፡፡ የፈለግከውን ማድረግ ትችላለህ ተብሎ ይፈቀድለት፡፡ ቢፈልግ ይሸጠዋል፡፡ የሚሸጠው ግን ቁማር ሊጫወትበት አይደለም፤ ሌላ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ሲያስብ ነው፡፡ ለሕዝብ ተቆርቋሪ ሆነህ "ሸጦ ሸጦ ያልቅበታል" ብለህ የምትናገርበት ምንም ዓይነት መረጃ ወይም ጥናት የለህም፡፡ መጀመሪያ የመሸጥም የመንከባከብም መብት ይሰጠው፡፡ ከዚያ ማስተማር፣ ግንዛቤ ማስጨበጥና አቅጣጫ ማስያዝ ትችላለህ እንጂ ይሻለኛል ብሎ ሲወስን ግን ንብረቱ ነው፣ መብቱ ነው፡፡ ከተሞክሮም በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ነኝ በሚል አገር "መሬት የመንግሥት ነው" የሚል በጭራሽ የለም፡፡ አይደለም መሬት ተቋማትም የሉም፡፡

ይህን ስንል ይህማ ፊውዳሎች ሲያደርጉት የነበረ ጥንሰስ ሃሳብ፣ የኢትዮጵያ መሬት ሊያራቁት የሚችል፣ ሕዝቡ ለድህነት ሊያጋልጥ የሚችል፣ ሕዝብ ደግሞ መሬቱን ሸጦ ወደ ከተማ በመግባት ለልመና ይዳረጋል የሚሉን፡፡ አሁንስ መሬት እንክብካቤ እየተደረገለት ነው? ሕዝቡ ለልመና እየተዳረገ አይደለም? በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን እንኳ መሬት የለኝም የሚል ዜጋ አልነበረም፡፡ የመሬቱ ይዞታ፣ ምርታማነት ከቦታ ቦታ ሊለያይ ይችላል እንጂ የራሴ መሬት የሚለው ግን ነበረው፡፡ አሁን እኮ የእኔ የሚለው የለውም፡፡ መንግሥት ነገ ይውሰደው ከነገ ወዲያ አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የኢህአዴግ ጭሰኛ ነው፡፡

16 ዓመት እንድትጠቀምበት ሰጥቸሃለሁ ብሎ ኮንትራት መስጠት የሚችል ባለቤቱ ራሱ ነው፡፡ መንግሥት ማነውና መስጠትና መከልከል የሚችል? ከየት አመጣው?    

በየማነ ናግሽ
 
< Prev   Next >