| በአጭር ጊዜ ፎቆችን ለመገንባት የሚያግዝ... |
|
|
| Wednesday, 05 March 2008 | |
|
በአጭር ጊዜ ፎቆችን ለመገንባት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊሆን ነው
ኮንክሪትንና ብረትን አንድ ላይ በማጣመር ክብደቱ የቀለለ፣ በአጭር ጊዜ ፎቆችን ለመገንባት የሚያግዝና የቋሚዎችን ብዛት የሚቀንስ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ ማሩ የብረት ኢንዱስትሪ ኃ.የተ.የግ ኩባንያ ከጣሊያኑ አርቶ ስካን ኩባንያ ጋር መፈራረሙንና ፕሮጀክት ለመስራት ጥናት እያካሄዱ መሆናቸው ተገለፀ፡፡ የኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ፓርትነርሺፕ ፕሮግራም ትናንት የካቲት 25 ቀን 2000 ዓ.ም በቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ባዘጋጀው የግማሽ ቀን የውይይት ስብሰባ ላይ የአርቶስካን ኩባንያ ተወካዮች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ቴክኖሎጂው ፎቆችን በአጭር ጊዜ የመስራት አቅምን ለመፍጠር ያስችላል፡፡ በኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ፓርትነርሺፕ ፕሮግራም ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ኢንጂነር ዳንኤል ቅጣው ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት በፕሮግራሙ በአገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ እያመቻቹ ሲሆን ቴክኖሎጂውን ኮንትራክተሮች አይተው ሊመዝኑት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር አንድን ቴክኖሎጂ አውቆና አሻሽሎ ወደ ኢኮኖሚው የማስረጽ አቅም ሲሆን ማሽኖችን መግዛት ብቻ በቂ እንዳልሆነና ሌሎችን በማየት በቴክኖሎጂና በትምህርት ያለንበትን ደረጃ በማወቅ ለመለወጥ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በፕሮግራሙ ከጀርመን፣ ጣሊያን፣ ቻይናና ሕንድ ኩባንያዎች ጋር በመስራት ኢንዱስትሪዎች አቅማቸውን ለማሳደግ በሚችሉበት ሂደት ላይ እየሰሩ መሆናቸውንም ዶክተር ኢንጂነር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ዘላለም ኃይሉ በበኩላቸው በኮንስትራክሽን ሴክተር ብዙ ጊዜ የሚፈለገው ገንዘብ እያለ ሕንፃዎችንና ድልድዮችን በሚፈለገው ፍጥነት የመሥራት ችግር እንዳለ ጠቁመው የአርቶ ስካን ኩባንያ አይነት ቴክኖሎጂዎችን የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚጠቀሙበትን አቅም መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን በፍጥነት የመጨረስ አቅም ወሳኝ መሆኑ በዚህ ኩባንያው ብዙ የሥራ የመስራር ልምዳቸው በአጭር ጊዜም ትልልቅ ሕንፃዎችን ለመጨረስ የሚያስችል ቴክኖሎጂን መያዛቸውን ተናግረው የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ የማድረግ ፈቃደኝነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ፓርትነርሺፕ የኢትዮጵያን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አቅም ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት መሃንዲሶች ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ጎን ለጎን በተግባር የታገዘ ትምህርት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በዚሁ መሠረትም ከአገር ውስጥም ሆነ ውጪ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንና ጤናማ ግንኙነትን በመመስረት በተግባር የታገዘ ትምህርት የሚያገኙበት ፕሮግራም መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ከአሁኑ የትምህርት ለውጥ በኋላም የተሻለ አቅም ያላቸው መሃንዲሶች የኮንስትራክሽን ዘርፍን እንደሚቀላቀሉ ያላቸውን እምነት ዶ/ር ዘላለም ገልፀዋል፡፡ የማሩ የብረት ኢንጂነሪንግ ኃየተ.የግ.ኩባንያ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳያን ማሩ በበኩላቸው አርቶ ስካን ቴክኖሎጂ ብረትን አንድ ላይ በማጣመር በአጭር ጊዜ ፎቆችን የመገንባት አቅም እንዳለው ገልፀው ሰፋፊ ቤቶችን ለመገንባት በሲኒማ ቤት፣ አዳራሾች፣ ጣሪያውን ለመሸከም የሚያገለግሉ ቋሚዎች በብዛት መጠቀምን በመቀነስ ልቅ የሆኑ ሰፋፊ ቦታዎችን ለመስራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡ ቴክኖሎጂው በብዛት ብረትን መጠቀሙ ከዋጋ አንፃር የሚኖረውን ልዩነት በተመለከተም ሥራን በአጭር ጊዜ የመጨረስ አቅም መፍጠር በዋጋ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚፈጥር ገልፀው 16ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር ለመገንባት 1 ዓመት ከሰባት ወር አካባቢ የሚፈጅ ሲሆን በዚህኛው ቴክኖሎጅ በስምንት ወር ለማጠናቀቅ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጠር፤ ይህ በቢዝነስ እንቅስቃሴ አንድ አመት ቀድሞ መገኘት ማለት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ቴክኖሎጂው በአገር ውስጥ አገልግሎት ላይ ባይውልም በውጪ አገር ለረዥም ጊዜ የተሰራበት በመሆኑ ከድርጅቱ ጋር በጋራ ለመስራት ተፈራርመው ለዚህም ፕሮጀክቶችን ለመስራት ጥናት እያካሄዱ መሆናቸውን አቶ ዳያና ተናግረዋል፡፡ በቤዛዊት ስዩም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |