| የአንዳንድ የኮንስትራክሽን እቃዎች ዋጋ... |
|
|
| Wednesday, 05 March 2008 | |
|
የአንዳንድ የኮንስትራክሽን እቃዎች ዋጋ ከሁለት እጥፍ በላይ እየጨመረ ነው
ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ዋና ግብአት የሚባሉ እቃዎች ዋጋ በሁለት እጥፍ እንደጨመረ ተጠቆመ፡፡ የኮንስትራክሽን እቃዎች ዋጋ መጨመርን በሚመለከት ያነጋገርናቸው የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለሙያዎችና ኃላፊዎች እንደጠቆሙት ከጥቂት ወራት ወዲህ እየጨመረ የመጣው የኮንስትራክሽን እቃዎች ዋጋ መወደድ ሥራዎቻቸው ላይ እክል እየፈጠረ መምጣቱንና የአንዳንድ ምርቶች ዋጋ በሁለት እጥፍ መጨመሩን ይጠቅሳሉ፡፡ በግንባታ ሥራ ዋና ዋና ግብአቶች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የብረት፣ የፌሮ ብረት ማሰሪያ ሽቦ (ብላክዋየር"፣ ድንጋይ ላሜራዎች የመሳሰሉት በሁለት ወራት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋቸው እያሻቀበ መምጣቱንና አመልክተዋል፡፡ እንደ ሲሚንቶ ያሉት ምርቶች 30 በመቶ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን በሁለት ሳምንት ውስጥ 30 ብር ጭማሪ ታይቶባቸዋል፡፡ ሲሚንቶ ከፋብሪካም እንደልብ ማግኘት አለመቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ስምንት ብር ይሸጥ የነበረ የፌሮ ማሰሪያ ሽቦ ዋጋው እየጨመረ መጥቶ ባሳለፍነው ሳምንት መግቢያ ጀምሮ 28 ብር፣ በተመሳሳይ 250 ብር ይሸጥ የነበረ ባለሁለት ሚ.ሜ ስፋት ላሜራ 500 ብር ገብቷል፡፡ 800 ብር ይሸጥ የነበረውም ባለ 5 ሚ.ሜ ላሜራ 1050 ብር ደርሷል፡፡ የሲሳይ ኮንስትራክሽን ሳይት ማናጀር አቶ ቢኒያም ነጋ እንደገለጹት ደግሞ ከፋብሪካ ውጭ በነጋዴዎች 150 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል የሙገር ሲሚንቶ 190 ብር፣ የውጭ ሲሚንቶ ደግሞ ከ145 ብር ወደ 180 ብር ከፍ ብሏል፡፡ 350 ብር ይሸጥ የነበረ አንድ መኪና ድንጋይ 700 ብር ደርሷል፡፡ ይህ ትልቅ ጭማሪ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ኮንትራክተሮቹ ገለጻ ከኮንስትራክሽን እቃዎች ዋጋ ጭማሪ ሌላም ባለሙያዎች የሚከፈላቸውን ጭማሪ በማሳደጋቸው ለግንባታ የሚያወጡትን ጭማሪ እያሳደገባቸው ነው፡፡ እንደ ምሳሌ ያነሱት ለአንድ ግንበኛ ቀደም ብሎ በቀን በአማካይ 40 ብር ይከፈል ነበር አሁን ግን ዋጋቸው በአማካይ 65 ብር አድርሰውታል፡፡ ሌሎች የቀን ተከፋይ ሠራተኞችም ክፍያቸው አድጓል፡፡ የኮንስትራክሽን እቃዎች የዋጋ ጭማሪውና ሠራተኛው እየጠየቀ ያለው የክፍያ መጠን ማደግ ተደማምሮ በጨረታ ያሸነፉበትን አንድ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ገንዘብን እንደሚጠይቅና ይህም ተጨማሪ ወጪ አሁን ካለው ገበያ አኳያ ሲታይ በአነስተኛ ግምት ከ30-40 በመቶ ተጨማሪ ወጪን የሚጠይቁ እንደሆነም እየገለጹ ነው፡፡ እንደ አቶ ቢኒያም ገለጻ ይህ ችግር በዚህ የሚገታ ብቻ አለመሆኑን የገለጹት ኮንትራክተሮች የተቀበሉትን ሥራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለመጨረስ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ያሉ ግንባታዎች በሙሉ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ይጨርሳሉ የሚል እምነት የሌላቸው ኮንትራክተሮች ያጋጠሙን ሲሆን መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የሚታየው የኮንስትራክሽን ግንባታ አሁን ባለው ፍጥነት ለመቀጠል ከታሰበም የኮንስትራክሽን እቃዎች በበቂ ሁኔታ መቅረብ እንዳለባቸውና አሁን ያለው ሰፊ የዋጋ ልዩነት ለማካካስም መንግሥት ትኩረት እንዲያደርግ ጠቁመዋል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |