| "ልውጥ ህያው የሆኑ ምርቶች ከገቡ... |
|
|
| Wednesday, 05 March 2008 | |
![]() ሻምበል ገብረመድኅን ሻምበል ገብረመድኅን ቢረጋ የኢኮ ሸማቾች ማኅበር ዳይሬክተር ልውጥ ህያው ምርቶችና የምርት ውጤቶችን በተመለተ ከትናንት በስቲያ በግዮን ሆቴል አውደ ጥናት ተደርጐ ነበር፡፡ በዚህ አውደ ጥናት ላይ ልውጥ ህያው ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፈቀድ አለበት፣ መፈቀድ የለበትም በሚል ክርክር ተካሂዷል፡፡ ልውጥ ህያው ምርቶችን በመጠቀም ፈጣን እድገት ሊመጣ ይችላል የሚል አመለካከት ያላቸው ወገኖች በአሁኑ ጊዜም 23 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆን መሬት በልውጠ ህያው በሆኑ ምርቶች የተሸፈነና በርካታ አገሮች እየተጠቀሙበት በመሆኑ ይህ እየተስፋፋ የመጣው ጉዳይ ወደድንም ጠላንም በአገራችን መተግበሩ ግድ ነው ይላሉ፡፡ ሕግ ወጥቶ እንደሌሎች አገሮች መጠቀም ከቻልን ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ በህጋዊ መንገድ የልውጥ ህያው ምርቶች እየገቡ ባይሆንም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በብዛት እየገቡ መሆናቸውን የሚጠቁሙም አሉ፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይ ልውጥ ህያው ምርቶች መግባት የገበሬውን የሸማቹንና የአገሪቱንም ጥቅም ይነካል በማለት ሲከራከሩ ከነበሩት ግለሰቦች መካከል አንዱ ሻምበል ገብረመድህን ጌራ ናቸው፡፡ ሻምበል ገብረመድኅን ቢረጋ የኢኮ ሸማቾች ማህበር ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በልውጥ ህያው ምርቶች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ልውጥ ህያው ምርቶች ወደኢትዮጵያ እንዳይገቡ የምትከላከሉት ለምንድነው? አቶ ገብረመድኅን፡- ይሄ ጉዳይ በጣም ስላሳሰበን ከማህበራችን አሥር ዋና ዋና ዓላማዎች አንዱ ልውጥ ህያዋን Genetically Modified Organism (GMOs) የሚባሉ አዲስ የባዮ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ምግቦች ሰብሎችና ሌሎችም ምርቶች በሸማቹ መብት፣ ጤና እንዲሁም በገበሬው መብት ላይ በአካባቢ ተፅእኖዎች የምግብ ዋስትናን በመፃረርና በመሳሰሉት ላይ ያላቸው አሉታዊ እንድምታ በጣም ስላሳሰበን ይህንን አሉታዊ እንድምታ እየታወቀ አንዳንድ ወገኖች ምንም ችግር እንደሌለ በመቁጠር እነዚህን ባእድ ምርቶች እንድንቀበልና እንድንመገብ ያልሆነ ምክንያት እየሰጡ ነው፡፡ እኛ ህዝባችንን አስተምረን ሁሉም አውቆ እንዲጠነቀቅ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ወደ አገራችን እንዳይገባ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የልውጥ ህያው ምርቶች ወደ አገራችን ገብቷው፡፡ እየተጠቀምን ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ስለሆነም የልውጥ ህያዋን ምርቶች ወደ አገራችን አይግቡ ብለን መከራከር አንችልም እያሉ ነው፤ ሻምበል ገብረመድኅን፡- ይህንን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት ጂ.ኤም.ኦ ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ማናቸውም ህይወት ያላቸው ነገሮች ከሚገዙበትና ከሚባዙበት ከተለምዶ ስርዓት ውጭ በሆነ መንገድ በተፈጥሮ የማይገናኙ ዝርያዎችን እንዲገናኙ በማድረግ (በሳይንስ ጥበብ) የሁለት የተለያዩ ዝርያዎችን ለምሳሌ የበቆሎን ዝርያ የበቆሎነት ምንም ዓይነት ባህሪ ከሌለው ከተሃዋሲ ወይም መሬት ውስጥ ካለ ትል ዘረመል በመውሰድ የዛን ነፍስ ተዋሲ ዘረመል በበቆሎ ዘር ላይ በመውጋትና በማጣበቅ በቆሎው በተፈጥሮው ያልነበረውን ልዩ ባህሪ ይዞ እንዲበቅል የሚደረግ ዘዴ ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳያቆም በአሁኑ ሠዓት ሁኔታው እየተስፋፋ በጣም ሲያሳስበን ወደ ነበረው ደረጃ ደርሷል፡፡ ይህም አሜሪካኖች የሰው ዘረመል በሩዝ ዘረመል ላይ ወግተው አዲስ የሩዝ ምርት እያመረቱ ነው፡፡ ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት የአፍሪካ ልጆች በተቅማጥ በሽታ እየተጠቁ ስለሆነ ይህ የሰው ዘረመል ያለበትን የሩዝ ምርት ለመስጠት ነው እያሉ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- አሁን የተጠቀሰውን ምርት አሜሪካውያኑ እየተጠቀሙበት ነው? ሻምበል ገብረመድኅን፡- አይጠቀሙበትም፡፡ ሪፖርተር፡- ሰሞኑን በተደረገ አንድ አውደ ጥናት ላይ ይህንን ምርት አሜሪካውያን ራሳቸው እየተጠቀሙበት ነው ተብሏል እኮ? ሻምበል ገብረመድኅን፡- አሜሪካ ይህንን ድርጊት እንዲስፋፋ በማድረግ ቀዳሚ ነች፡፡ አሜሪካ ይህንን ባዮ ቴክኖሎጂ በምታስፋፋበት ጊዜ አንዳንድ ተቃውሞ ሲገጥማት ይህንን የምንሠራው ለአሜካውያን አይደለም፡፡ የምንሠራው አፍሪካውያንን ለመመገብ ነው ይሏቸዋል፡፡ እዚህ አገራችን ያሉና ይህንን ቴክኖሎጁ የሚደግፉ ወገኖች ትምህርት ሲሰጡ ደግሞ አሜሪካውያን በዚህ ቴክኖሎጂ የሚመረቱ ምግቦች መመገብ ከጀመሩ አሥር ዓመት ሆኗቸዋልና ምንም አልሆኑም ይሉናል፡፡ ሪፖርተር፡- እነዚህ የዘረመል ምርት ውጤት የሆኑ ምግቦችና ሌሎች ሰብሎች ወደ አገራችን ገብተዋል ብላችሁ ታምናላችሁ? ሻምበል ገብረመድን፡- በዚህ ጉዳይ የሚከራከሩ ወገኖች ኢትዮጵያ ብዙ የተራቡ ወገኖች ስላሉ ከአሜሪካ ወይም ከካናዳ የገባ እህል በእርዳታ የምትቀበል ከሆነ ጂ.ኤም.ኦ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዓለም ላይ በልውጥ ህያው የሚመረቱ ምርቶችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ስምምነት አለ፡፡ "ካይታይና ኘሮቶኮል" ይባላል፡፡ አገራችን ይህንን ስምምነት ፈርማለች፡፡ ከዚህ ፊርማ በኋላ እያንዳንዱ አገር የራሱ ብሔራዊ ህግ ማዘጋጀት አለበት ይላል፡፡ ይህ ህግ ከተዘጋጀ በኋላ በዚህ ቴክኖሎጂ የሚመረቱ ምርቶች ድንጋጌው መሠረት አስገብቻለሁ ማለት ይችላል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ለማምታታት ሲፈልጉ እየገባ ነው ይላሉ እንጂ ህግን ተከትሎ የገባ ዘረመል ምርት የለም፡፡ ሪፖርተር፡- በህገ ወጥ መንገድ ገብቶስ ከሆነ? ሻምበል ገብረመድን፡- በህገ ወጥ መንገድ አልገባም ብሎ መከራከር አይቻልም፡፡ ገብቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን አነስተኛ እንደሚሆን እንገምታለን፡፡ አንዳንድ የምግብ ውጤቶች ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ውስጥ አንዷ የልውጡ ምርት አምራች አገር ናት፡፡ በደቡብ አፍሪካ በትልቁ የሚመረቱ በቆሎ፣ አኩሪ አተርና የጐመን ዘር የመሳሰሉት ሲሆኑ አዲስ የመጡ ደግሞ እንደ ስኳር ድንችና ፍራፍሬዎችም እየተመረቱ ናቸው፡፡ እኛን በጣም የሚያሳስበን ትልቁ ነገር የበቆሎ ምርት ነው፡፡ የበቆሎ ስርጭት በንፋስ የሚሄድ በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቆሎ በእርዳታ ትቀበላለች፡፡ በምትቀበልበት ጊዜ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩት ይህ ዘረመል ምርት አገር ውስጥ ገብቶ የኛን በቆሎ እንዳይበክል እየተፈጨ የገባበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሪፖርተር፡- በዚህ መንገድ የተመረቱ ምርቶችም ሆኑ ሌሎች እቃዎች ወደአገር ውስጥ መግባታቸው የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው? ሻምበል ገብረመድኅን፡- ዋና ጉዳት እና ሁላችንንም የሚያሳስበን ልውጥ ሕያው ያልሆኑና ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅባቸው የተለያዩ ዘሮች አሏት፡፡ ለምሳሌ ማሽላን ብንወስድ ከ80 በላይ የማሽላ ዘሮች አሉ፡፡ ጤፍም ከ1ዐዐ በላይ ዝርያዎች አሉት፡፡ ሌሎችም ምርቶች እንደዚሁ ናቸው፡፡ ልውጥ ህያው የሆኑ ምርቶችና ዘሮች ወደ አገራችን ከገቡ ወይም አስፈላጊው ቁጥጥርና ፍተሻ ሳይደረግ፣ ሊያስከትሉት የሚችሉት ጉዳት አስቀድሞ ተጠንቶ ጠንቁን እንዴት አድርጐ ማስወገድና መቀነስ እንደሚቻል ጥንቃቄ ሳይደረግ ማስገባት የነበሩን የዘር ዓይነቶች እንዲጠፉ ያደርጋል፡፡ ልውጥ ህያው የሆነ ማሽላ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገባ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ዘሮቻችን አጥፍቶ በላቦራቶሪ የተሠራው ዘር ብቻ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ልውጥ ህያው የሆኑ ምግቦችን የተመገቡ ሰዎችና አይጦች ላይ የተደረገ ጥናት አለርጂክ እንዲነሳ አድርጓል፡፡ ከአሁን በፊት ያልነበረ በሰውነት ውስጥ በሽታ የመቋቋም ባህሪ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ሪፖርተር፡- በሽታ የመቋቋም ባህሪ በሸውነት ውስጥ እንዲፈጠር አድርጓል ማለት ምን ማለት ነው? ሻምበል ገብረመድኅን፡- አንቲ ባዮቲክስ የምንላቸው መድኃኒቶች አሉ፡፡ ልውጥ ህያው የሚባሉ ምርቶች በላቦራቶሪ ሲሰሩ ከባክቴሪያ ወይም ከተዋህሲያን ዘረመሎች በውስጣቸው ያለው ባህሪ አንቲባዮቲክስ እንዲቋቋሙ ተደርገው ነው የሚመረቱት፡፡ ይህ የሚፈለገው የሚያመርቷቸው የሰብል ውጤቶች በአብዛኛው በሽታ ተባይ ውርጭና የመሳሰሉትን የሚቋቋም እንዲሆን ለማድረግ የአንቲ ባዮቲክስ ሬዚስት የሚያደርጉ ክፍሎችን ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ ቢ.ቲ. የተባለውን ተዋሲ የተወጋው በቆሎ አጠገቡ ሌሎች ተዋስያን መጥተው በሽታ እንዳያጠቁት ይከላከላል፡፡ የዚህን ምርት ውጤት የተመገበ ሰው ደግሞ ጉዳት እንደሚያስከትል ታይቷል፡፡ ከመመገብ አልፈን ደግሞ ዘሩ በፋብሪካ በሚመረትበት ጊዜ በምርምር የተገኘ እንደመሆኑ መጠን የፓተንት ጥበቃ መብት ይዞነው የሚወጣው፡፡ የፓተንት መብት ይዞ የሚወጣ ከሆነ አንድ ጊዜ ገዝቶ የሚዘራው ገበሬ ዘሩን በቤቱ ማቆየት አይችልም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ገበሬ ልምድ የሚፈልገውን ዘር ከምርቱ ላይ አስቀርቶ አስቀምጦ ይዘራል፡፡ በልውጥ ህያው የተገኘ ዘር ግን ለዘር ብሎ ምርቱን በቤት መቆየት ወንጀል ነው የሚሆነው፡፡ ሪፖርተር፡- ለምንድነው? ሻምበል ገብረመድኅን፡- ወንጀል የሚሆነው የማንኛውም በልውጥ ህያው የተገኘ ዘር በምርምር የተገኘ በመሆኑና ሳይንቲስቶች ለረዥም ዓመት የለፉበት በመሆኑ እንዲሁም ይህንን ምርት እንዲመረት ያደረጉት ኩባንያዎች ለአመታት ገንዘባቸውን ያፈሰሱበት በመሆኑ ምርምሩ ላይ ያዋለትን ኢንቨስትመንት መልሰው ለማግኘት ሮያሊቲ ወይም መከፈል የሚገባውን ክፍያ ይጠይቁበታል፡፡ ገበሬው ይህንን ዘር በተጠቀመ ቁጥር ክፍያ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ይህንን ክፍያቸውን ለመሰብሰብ ደግሞ በህግ መብት አግኝተዋል፡፡ ሪፖርተር፡- አሁን ይህንን ዘረመል ምርቶች የሚጠቀሙ አገሮች ተበራክተዋል፡፡ ልውጥ ህያው የሆኑ ዘሮችን የሚጠቀሙ ገበሬዎች ይከፍላሉ ማለት ነው? ሻምበል ገብረመድኅን፡- የኢትዮጵያ ገበሬ አሁን ልውጥ ህያው የሆኑ ዘሮችን ከሚጠቀሙ ገበሬዎች ማነፃፀር አይችልም፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ገበሬ የሚባሉት ከጠቅላላው ህዝብ አንድ በመቶ አይሆንም፡፡ ግን እጅግ ትላልቅ እርሻዎች አሉዋቸው፡፡ እነዚህ እርሻ ላይ የሚዘሩት ገበሬዎች ደግሞ ሞንሳንቶ (ዘረመል ምርቶችን በማቅረብ የሚታወቅ የአሜሪካ ኩባንያ ነው) ከእርሱ ጋር ኮንትራት በመፈራረም ዘሩን ይገዛሉ፤ ይዘራሉ፡፡ ብዙ ስለሚያመርቱ አትራፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ከኩባንያው ዘሩን የመግዛት ግዴታ አለበት፡፡ ዘሩን መልሶ ያልወሰደ ገበሬ ማሳው ላይ ሰብል አብቅሎ ቢገኝ ይከሱታል፡፡ ለዚህ አገላለፅ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነውን የአንድ ካናዳዊ ገበሬ የገጠመውን ማንሳት ይችላል፡፡ ይህ ገበሬ ዘረመል ምርት ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት የለውም፡፡ ሰፊ የጐመን ዘር እርሻ አለው፡፡ ሚስተር ሱማይዘር ይባላሉ፡፡ የራሳቸውን ዘር እየዘሩ የኖሩ ናቸው፡፡ መጨረሻ ላይ የሰው የሆነ ማሳ ጠርጥሮ በፍርድ ቤት አስፈቅዶ ማሳውን ያስፈትሻል፡፡ ማሳ ውስጥ ጥበቃ የሚደረግለት የሞንሰንቶ ጐመን ዘር ተገኘ፡፡ ተከሰሰና ማሳው እንዲወድም ተደረገ፡፡ ይህም የሆነው ፓተንት ያለው ዘር በማሳ ውስጥ ስለተገኘ ነው፡፡ በኋላ ላይ ግን ፍርዱ ከተፈረደ በኋላ ሁኔታው ሲጣራ የምንሳንቶ ዘር ማሳ ውስጥ የተገኘው የሞንሳንቶ ዘር የያዙ ተሽከርካሪዎች በአካባቢው ቆመው በነበሩበት ጊዜ ዘሩ ፈሶ ወደ ማሳው በመግባት በመስፋፋታቸው እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ ግን ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ ሪፖርተር፡- ነፍስ ላለው ነገር ፓተንት ይሰጣል እንዴ? ሽምበል ገብረመድኅን፡- በአሜሪካን ህግ ይፈቀዳል፡፡ ደስ የሚለው ነገር በኢትዮጵያ ህይወት ላላቸው ነገሮች የፓተንት ጥበቃ አይሰጥም፡፡ አብዛኛው አፍሪካ አገሮችም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ማለት ማንኛውም እፅዋትም እንስሳትም ሆነ የእነርሱ ውጤት የሆኑ ምርቶች አይሰጥበትም፡፡ በህግ ተከልክሏል፡፡ ነገር ግን ወደ WTO ለመግባት ኢትዮጵያ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ይለወጣል ብለን ከምንሠጋባቸው ህጐች መካከል አንዱ ይህ ህግ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ ብዙ ከውጭ የመጡ የታሸጉ ምግቦች አሉ፡፡ በልውጥ ህያው ምርት መሠራት አለመሰራታቸው በምን ይታወቃል? ሻምበል ገብረመድኅን፡- በሌላ አገር ህግ አለ፡፡ ከልውጥ ህያው የተሠራን ምግብ ልውጥ ህያው እንደሌለው ተደርጐ መሸጥ ወንጀል ነው፡፡ ነገር ግን የአሜሪካን መንግሥት የያዘው አቋም ይህንን የሚለይ ምልክት አናረግም ብለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ አገሮች በተለይ አውሮፓውያን ይህ መጠቀስ አለበት ብለው ይከራከራሉ፡፡ ሸማቹ ይህንን ለይቶ ለመጠቀም ይችላል፡፡ ሳያውቀው ምርቶችን መግዛት የለበትም የሚል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በአገራችንም ለእነዚህ ቁጥጥር የሚሆን ረቂቅ ህግ ተዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ እስካሁን ያለውን ለማፅዳት ፍተሻ መደረግ አለበት፡፡ መሳሪያዎቹ መግባት አለባቸው፡፡ የአቅም ግንባታ መደረግ አለበት፡፡ በዘረመል ምርቶች የተመረቱ ምግቦች ከተገኙ እንዲወገዱ ይደረጋል፡፡ እስካሁን የምንጠቀምባቸው ምርቶች ግን ይኑራቸው አይኑራቸው አይታወቅም፡፡ ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተደረገ አወደ ጥናት ላይ 3.6 ቢሊዮን ህዝብ በሚኖርባቸው አገሮች ወይም 23 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆን መሬት በልውጥ ህያው ምርቶች ተሸፍኗል ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ ማምለጥ ትችላለች? ሻምበል ገብረመድኅን፡- የልውጥ ህያው ምርትን በተመለከተ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ባደረገው በቂ መረጃ አለ፡፡ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ባቀረቡት ሪፖርት የልውጥ ህያው አቀንቃኞች ገበያ ለማግኘት ሲሉ መረጃዎቻቸውን ያሳድጋሉ፡፡ ይህንን ለመሳቢያ ይጠቀሙበታል፡፡ የሚያቀርቡት ቁጥር ተጋንኗል፡፡ እነርሱ የማጠቅሱት ቁጥር ትክክል ካለመሆኑም የሚያሳይ መረጃዎችም እየቀረቡ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በልውጥ ህያው በሆኑ ምርቶች ወይም ዘሮች መጠቀም ምርትን ያሳድጋል፡፡ በእነርሱ መጠቀሙም ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ነው እየተባለ ነው፤ ሻምበል ገብረመድኅን፡- በእኛ አገር ያሉ ሳይንቲስቶች በተለይ የታወቁት የአዲስ አበባ ዩኒቭርሲቲ ምሁር ሳይቀሩ በዚህ መጠቀም ምርታማ ያደርጋል የተባለው ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምርታማ የማይኮነው በዚህ ቴክኖሎጂ መጠቀም ብዙ ግብአቶችን ይጠይቃል፡፡ ብዙ ማዳበሪያ ኬሚካል ውሃ . . . ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁሉ ወጪ ወጥቶበት ከምርቱ የሚገኘው ትርፍ አጥጋቢ አይሆንም፡፡ እንደውም ይከሰራል፡፡ በጥቂት መሬት ላይ ብዙምርት ይገኛል ይባሉ እንጂ አጠገባችን ኬንያና አጋንዳ ውስጥ በስኳር ድንች ላይ በተደረገ ሙከራ ልውጥ ህያው የሆነው ምርት በተፈጥሮ ከተራው ምርት ያነሰ ምርት ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ምርታማ አይዳለም ባይ ነኝ፡፡ በጥቅሉ ግን ይህንን ቴክኖሎጂ ያስፋፉት በአንደኛወና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የጦር መሳሪያ አቅራቢ የነበሩ ኩባንያዎች ናቸው፡፡የመድኃኒትና የኬሚካል ትርፍ ሲቀንስ ወደ ዘረመል ስራ ውስጥ የገቡ ናቸው፡፡ በፋብሪካቸው የሚያመርቱትን ዘር መጀመሪያ በዱቤ ይሰጣሉ፡፡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ምርቱ ጥሩ ይሆንላቸውና ነባር ዘራቸውን ያጠፋሉ፡፡ በእነርሱ ምርት መጠቀም ሲጀምሩ ብዙ ግብአት እየጠየቃችሁ ነው፡፡ ችግሩም በእጃቸው የነበረው ነባር ዝርያ ከእጃቸው ሲወጣ ፓተንት ያለው ዘርን እየገዙ ሲጠቀሙ ቆይተው አንድ ቀን ቢከለክሏቸው የሚዘሩት ነገር እንዲያጡ ያደርጋል፡፡ ዘር በመቆጣጠር ብቻ አገሮችን ሊቆጣጠሩበት ይችላሉ፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |