| ክቡር ሚኒስትር |
|
|
| Wednesday, 05 March 2008 | |
|
/ሕገ ወጥ የሆኑ ሥራዎችና ግንባታዎች በዝተዋል፤ ሥራ የሚሰራው በሙስና ነው የሚል ተደጋጋሚ ሪፖርት ስለቀረበ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ይህን እየተከታተለ መፍትሔ የሚሰጥ በክቡር ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ በኮሚቴው ውስጥ ባለሙያዎችና ሌሎች ኃላፊዎች አሉ፡፡ በአንዱ ስብሰባ የሞቀ ክርክር እየተካሄደ ነው/ - ወለም ዘለም ማለት የለም፤ ይፈርሳል ይፈርሳል፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ሰውየው መፍረስ የለበትም ብሎ እየተከራከረ ነው፡፡ - ተከራከረ፣ አልተከራከረ ለውጥ የለውም፡፡ ሕገ ወጥ ግንባታ ነው ይፈርሳል ማለት ይፈርሳል ይፈርሳል ነው፡፡ - ቀበሌኮ ፈቅዶለታል ክቡር ሚኒስትር፡፡ - በሙስና የተዘፈቀ ቀበሌ ነዋ፡፡ ከተማው ቢሰማ ኖሮ የቀበሌ ሃላፊዎቹ ይባረሩ ነበር፡፡ - ክፍለ ከተማውም ፈቅዶለታል ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ክፍለ ከተማው ከፈቀደለት ሙሰኛው ክፍለ ከተማ ነው ማለት ነው፡፡ አስተዳደሩ እንዲያውቀው አድርግና በክፍለ ከተማው ላይ እርምጃ ይወሰድ፡፡ - ከንቲባውም ፈቅደውለታል፡፡ - እሳቸው”. አላልኩህም፡፡ የከተማው ሥራ አስኪያጅ ቢሰሙ ኖሮ ዝም ብለው አያዩም ነበር፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ክፍለ ከተሞቹን ስንጠይቅ ሥራ አስኪያጁ ስላዘዙን ነው የፈቀድነው ብለዋል - (ሌላ ተናጋሪ) ነገሩ ሕገ ውጥ ነው፡፡ ነገር ግን አንዲት ትንሽ ኬክ ቤት ላይ ይህን ያህል ከመረባረብ ሌላ ትላልቅ ሕገወጥ ሥራዎች አሉ፡፡ ለምን በእነዛ አንጀምርም፡፡ በትላልቆቹ ብንጀምር ሕዝቡ መንግሥት ቆርጦ ተነስቷል ብሎ ያምናል ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እንዲያውም በትናንሾቹ ብንጀምር ነው መንግሥት ቆርጦ ተነስቷል ብሎ ሕዝቡ የሚያምነው፡፡ - ክቡር ሚኒስትር አሁንኮ ሕዝቡ እየሳቀብን ነው፡፡ - ደግሞ ምን ብሎ ነው የሚስቀው? - ስንት ሕገ ወጥ ሃብታም እያለ ኑሮን ለማሻሻል በሚፍጨረጨረው ላይ ያተኩራሉ ብሎ፡፡ - እኛ ሕገወጥ ስንል ሕገ ወጥ ማለታችን ነው፡፡ ትልቅ ትንሽ አንልም፡፡ - ሕዝቡ ግን ሁለት ኢትዮጵያውያን በሁለት ዓይን ይታያሉ እያለ ነው፡፡ ተፈርተው የሚተውና ተንቀው የሚደፈሩ፡፡ - በእርግጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል ዓይን አይታይም፡፡ ልማታዊና ልማታዊ ያልሆኑ አሉ፡፡ ልማታዊውን እናበረታታለን፡፡ - (ሌላ ተናጋሪ) ክቡር ሚኒስትር ዳር ዳር እያልን ነው መሰለኝ፡፡ ለግንባታ ተብሎ የተወሰደ መሬት ፒያሳ ታጥሮ ተቀምጧል፡፡ መቻራ ሜዳም እንደዚሁ፡፡ ለመናፈሻ ተብሎ ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት የተሠራውም ይኸው እስከ ዛሬ ሕዝብ አልተጠቀመበትም፣ የተረከበውም የለም፡፡ - በአንተ ቤት ደፍረህ መናገርህ ነው? ይህ የማዘጋጃ ቤቱ ሥራ ነው፡፡ - እንዴት የማዘጋጃ ቤት ክቡር ሚኒስትር? - ታዲያ መሬት ማስተዳደር የእኛ ሥራ ነው? - ቤት ማፍረስ የእኛ ሥራ ነው እንዴ ክቡር ሚኒስትር? - ሕገወጦችን ለማስተካከል ሃላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ - (ሌላ ተናጋሪ) ክቡር ሚኒስትር ይህ ይፍረስ የተባለው ሥጋ ቤት ነው ሻይ ቤት ሰውየው እየከሰሰ ነው አሉ፡፡ እንዲያውም ፍርድ ቤቱ ፈርዶለታል፡፡ - ይግባኝ ማለት ነዋ፡፡ - ይግባኝ ተብሎ ተፈርዶለታል፡፡ - ሰበር ድረስ እንሄዳለን እንዲያውም ሌላ መፍትሔ አለ፡፡ - ምን ሌላ መፍትሔ አለ ክቡር ሚኒስትር? - ከቀበሌ ውላችን አቋርጠናል ተብሎ እንዲፃፍ እናደርጋለን፡፡ - (ሌላ ተናጋሪ) ጎሽ ክቡር ሚኒስትር ሌባን መለማመጥና ፍርድ ቤትን ማጓተት አያስፈልግም፡፡ በኪራይ ቤቶች ካልሆነ በፖሊስ በአስቸኳይ መጨረስ ነው፡፡ - (ሌላ ተከራካሪ) ክቡር ሚኒስትር በፖሊስ በኩል የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ - ለምን አይመስልህም እባክህ? ለነገሩ አንተ ሁሌም መስሎህ አያውቅም፡፡ ሕግ ሕግ ነው የምትለው፡፡ - አዎን ክቡር ሚኒስትር ፖሊስም ያለው ሕጉ አይፈቅድም ነው፡፡ - ለምንድነው የማይፈቅደው? - ከቀበሌና ከክፍለ ከተማ አስፈቅዶ ስለሰራ ሕገወጥ ግንባታ ማለት አይቻልም፡፡ - የፈቀደው የቀበሌና የክፍለ ከተማ ሹም በሙስና ማንሳት ማባረርና ማሰር ነዋ፡፡ - ክቡር ሚኒስትር እነሱ ቢታሰሩም የሰጡትን ፈቃድ ሕገ ወጥ አያደርገውም፡፡ - ለምን አያደርገውም? - ክቡር ሚኒስትር የፈቀዱለት ከተነሱና ከታሰሩ በኋላ ሳይሆን ስልጣን ላይ እያሉ ስለሆነ ፈቃዳቸው ሕጋዊ ማረጋገጫ ነው፡፡ - እኛ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ የተቋቋምን ስለሆንን ከሌላው ሁሉ የበላይ ነን፡፡ - እንዴ ክቡር ሚኒስትር ኮሚቴው የአገሪቱን ሕግና መመሪያ ተከትሎ እንዲሰራ ነውኮ የታዘዘው፡፡ - እኔምኮ ሕግ ይጣስ አላልኩም፡፡ አሰራርና መመሪያ ይጣስ አላልኩም፡፡ ምን እያልኩ እንደሆነ ገብቷችኋል? - እኔ አልገባኝም፡፡ - እንቅፋት የሚሆኑ ሕጎችና አሰራሮች ካሉ እንቀይራቸው ነው ያልሁት፡፡ እንቀይራቸው እንጂ እንጣሳቸው አላልኩም፡፡ - እስኪቀየሩ ድረስ ግን እናክብራቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡ - መቀየራቸው ስለማይቀር የተወሰነው ውሳኔ ተግባር ላይ ይዋል ነው የምለው፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ገና ለገና ሕጉን እንቀይራለን ተብሎ እርምጃ እየተወሰደ ሊቆይ ነው፡፡ - አዎን ፈርሜ ደልድዬ እልካለሁ፡፡ ለሁሉም፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ባይፃፍ ጥሩ ነው፣ ከተፃፈም በእርስዎ ፊርማ ባይሆን - ለምን? - ከላይ ሆነው ለየቀበሌዎች በፊርማዎ ለምን ትዕዛዝ ይልካሉ? - ሌላው በአገር ጉዳይ ቸልተኛ ሆኖ ካልፈረመ ማን ይፈርም ታዲያ? - እርስዎ ለማዘጋጃ ቤት ይፃፉ፣ ማዘጋጃ ቤቱ ደግሞ ለሰውየው ይፃፍ፡፡ - ይህ ልፍስፍስ ማዘጋጃ ቤት እያለ ሥራ አይሰራም፡፡ በቀጥታ ራሴ እፅፍለታለሁ፡፡ ለሰውየው ለባለ ሥጋ ቤቱ፡፡ (ዝም”. መግባባት ላይ አልተደረሰም፡፡ ክቡር ሚኒስትር ድልደላው እንዲዘጋጅ አዘዙ፡፡ ከውጭ የመጣ ዘመድ እንግዳ ስላላቸው ወደ ቤት ሄዱ) - አስጠበቅኩህ አይደል፡፡ ስብሰባ እየመራሁ ስለነበረ ነው፡፡ - ኢሕአዴግና ስብሰባ፡፡ - እንዴት ሆነልህ? - አስቸጋሪ ነው፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ ውስጥ ትናንሽ መንግሥታት አሉ፡፡ የከንቲባው አስተዳደር ሌላ ነው፡፡ የሥራ አስኪያጁ አስተዳደር ሌላ ነው፡፡ - አንተ ስለነሱ ምን አገባህ መሬት ፈልገህ ነው የሄድከው፡፡ መሬት አስተዳደር አትሄድም? - እኮ አራት፣ አምስት ሃላፊዎች አሉ፡፡ አንድም ውሳኔ መስጠት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ - ችሎታም ያላቸው አይመስለኝም፡፡ - አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡ የችሎታ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንዲያውም ብዙ የሠራ ነው፡፡ አንደኛው በሌላ መሥሪያ ቤት ብዙ ሠርቷል፡፡ የተመረቀውም በዚሁ ሙያ ነው፡፡ ችግሩ የተደራጀ አመራር አለመኖሩ ነው፡፡ ሌላ ችግርም አለ፡፡ - ሌላ ምን? - በብጥስጣስ ወረቀት የምትፅፉዋቸው መመሪያዎች ችግር እየፈጠሩ ናቸው፡፡ - እንዴት? - አንዱ ጨረታ እንጂ ድርድር ቀርቷል ብሎ ይፅፋል፡፡ ሌላው ከዚህ ካሬ ሜትር በላይ እንዳትሰጡ ብሎ ይፅፋል፡፡ ሌላው አቁሙ የሚል መመሪያ ይልካል፡፡ - ለጊዜው ነው ግድ የለም፡፡ - በኢንቨስትመንት ለጊዜው የሚባል ነገር የለም፡፡ ይህን የሰማ ይሸሻል በቃ” - ይሸሻል ብለህ ነው? - ክቡር ሚኒስትር እኔ ራሴ ከአዲስ አበባ ሸሽቻለሁ፡፡ - ሸሽተህ የት ሄድክ? እዚሁ ነው ያለኸው፡፡ - ኦሮሚያ ክልል ጥሩ ስለሆነ ወደዚያ ሄጃለሁ፡፡ - ያሰሩሃል ብለህ ነው? - ክቡር ሚኒስትር እንዴት እንደተባበሩኝ ብታይ ይገርምሃል፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ተካሂዷል ከተባለ እዚያ ብቻ ነው፡፡ - ይቅናህ - ቀንቶኛል፡፡ ከቢሮ ከፀሃፊያቸው ተደወለ - ሃሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እሺ ምን ሆንሽ ደግሞ? - እየተከታተላችሁ ሪፖርት አቅርቡልኝ ባሉት መሰረት እዚያ ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ አንድ ቤት አፍርሰናል ብለዋል፡፡ - የማን ቤት? - የአቶ ዳንኤል፡፡ - ዳንኤል ያ ከውጭ የመጣው? - አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ለምን ያፈርሱታል? - ሕገወጥ ግንባታ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ቢሆንስ እኛን አምኖ ከውጭ የመጣ ዲያስፖራ ነው፡፡ ስንት ትልልቅ ነገር እያለ ለምን ትንንሹ ላይ እንደምታተኩሩ አይገባኝም፡፡ - ከቀበሌ ወይም ከክፍለ ከተማ ፈቃድ የሚባል ነገር የለውማ ሰውየው፡፡ - ምን ፈቃድ ያስፈልጋል? ካስፈለገም ቀስ ብሎ ያወጣው አልነበር፡፡ ሆን ተብሎ የእኛን ደጋፊዎች ለማምታት የተደረገ ነው፡፡ - ጥብቅ እንሁን አላሉም ወይ ክቡር ሚኒስትር? - በቃ በቃ አሁን ስልኩን ዝጊው፡፡ - ሌላም አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ምንድነው ሌላ? - ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መጥሪያ መጥቷል፡፡ - የምን ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው? - አንድ ቤት የፈረሰበት ሰው የከሰሰው ነው፡፡ - እኔ አይመቸኝም የኮሚቴው አባል አንቺንና እኔን ወክሎ እንዲሄድ ንገረው፡፡ - እሺ እለዋለሁ ግን እምቢ ካለኝስ? - አይልሽም እንዳንቺ ከቤተሰቦቹ የወረሰው ሃብት ያለው አይመስለኝም፡፡ - የወረስኩት ሃብት ቢኖረኝ ኖሮ በእንደዚህ አይነት ሥራ ባልተቀጠርኩ ነበር፡፡ - እኔ ግን የወረስኩት ቢኖር ኖሮም አገሬን ለማገልገል ሚኒስትር ሆኜ መቀጠሌን አልተውም፡፡ - የወረሱት ሃብት ቢኖርዎት ኖሮ ግን ከመጀመሪያውም ኢሕአዴግ ባልሆኑ ነበር፡፡ - ማን ነው ኢሕአዴግ የድሆች ነው ያለሽ? - ዱሮ ማለቴ ነው አሁን አይደለም፡፡ - በይ፣ በይ አሽሙርሽን አቁሚና እምቢ ካለሽ ትዕዛዙን በፅሁፍ ስጪው፡፡ (ስልኩ ተዘጋ፡፡ የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ቤት ገቡ) - እንደምን ዋልክ ምነው በጊዜ መጣህ ስብሰባ የለም እንዴ? - በጊዜ ገባሁ መውጣትም አልፈለግኩም፣ ተናደድኩ፡፡ - ምን አናደደህ? - አንድ ደንቆሮ ቤት ይላል፣ ሌላው ደንቆሮ ተመልሶ እኔን ይከሳል፡፡ ፍርድ ቤት ቅረብ የሚል መጥሪያ ያመጣል፡፡ የአንደኛው ዲያስፖራ ቤት በዛ በኩል ይፈርሳል፡፡ ጣጣ ነው፡፡ - ማን ነው የከሰሰህ? - አንዱ አላግባብ ቤት ገንብቶ ይፍረስ የሚል ትዕዛዝ ስፅፍለት ከሰሰኝ፡፡ - የዚህ እንኳ አላግባብ የተገነባ ነው፡፡ እኔኮ የሚያሳዝነኝ በሕጋዊ መንገድ ገንብተው፣ ቀበሌና ክፍለ ከተማ አስፈቅደው የሰሩትን ቤት ይፍረስ ሲባል ነው፡፡ - በሕጋዊ መንገድ አስፈቅደው ከሰሩ ይፍረስ ተብሎ ይታዘዛል ብለሽ ነው? - ዛሬኮ እዚያ ነው የዋልኩት፡፡ - የት? - ልደታ፡፡ - ለምን? - አንድ የዘመዳችን ቤት ይፍረስ ተብሎ ሰውየው ተጨንቆ ያለቅስ ነበር፡፡ - ማን ይፍረስ ብሎ አዘዘ? - ስም አልነገረኝም አንድ ሚኒስትር ነው ያለኝ፡፡ - እ.እ.እ - ማን ነው ሰውየው ያልሽኝ”. ዘመዳችን ነው አልሽኝ፡፡ - አላስተዋወቅኩህም፡፡ አንዴ ግን እትዬ ስርጉት ለቅሶ ላይ አይተኸው ነበር እኮ፡፡ የእሱ ቤት ነው ይፍረስ የተባለው፡፡ - ምን ቤት ነው? - ሥጋ ቤት፡፡ - ማን አልሽኝ ሰውየውን፡፡ - የተናኘ ወንድም ነውኮ፡፡ - እኮ ማን አልሽኝ፡፡ - በቄ፡፡ - “ውይ በቅዬ ነው እንዴ” |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |