|
Wednesday, 05 March 2008 |
|
ረዘም ብሎ የእንቁላል ቅርጽ ጥፍር ያላቸው ሰዎች አጫጭር ጥፍር ካላቸው ይልቅ ቀዝቀዝ ያሉና በቀላሉ የማይበሳጩ ናቸው፡፡ ጥፍር ረዥም ከሆነ አንጓዎችም ረዣዥም ስለሚሆኑ እነዚህ ሰዎች በኅሊናቸው የሚመሩ ሀሳባውያን ናቸው፡፡ ከልምድ እንደታወቀው የምኞትና የምቾት ሰዎች ሲሆኑ፣ በተቃራኒው ረዣዥም የጥፍር አንጓ ያላቸው ደግሞ ተጨባጭም ባይሆን በኅሊናቸው ተቀባይነት ያገኘውን ሁሉ ይቀበላሉ፡፡ ባለ አጭሮቹን በሚያከራክር ጉዳይ የሚያክላቸው የለም፡፡ በቅጽበት የክርክር ሀሳብ የሚያመነጩ ፈጣኖች ናቸው፡፡ ነገር ግን እንዲበሳጩ ለማድረግ በቀላሉ መቀስቀስ ይቻላል፡፡
ጥፍሮች ከመርዘም ይልቅ ሲሰፉ ጠበኝነትን፣ ብስጩነትን፣ ወዲያው መበቀል የሚፈልጉና በትንሽ ምክንያት የሚናደዱ እንደሆኑ የሚያመለክት ነው፡፡
በጥፍር ላይ ስለህመም የተገለፀውን ለማረጋገጥ በመዳፍ ላይ ከሚታዩት የአንጐልና የሕይወት መስመሮች ላይ ስለወደፊት በሽታ ከሚገልፀው ጋር ማመሳከር በጣም ጠቃሚ መሆኑን በቅድሚያ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
(ኃይለሚካኤል ለቴራ፣ መዳፍ እንደ መጽሐፍ (ትርጉም"፣ 1984")
እኔነት
አንድ የቴሌፎን ኩባንያ በስልክ ንግግሮች ውስጥ በከፍተኛ መጠን የሚደጋገመውን ቃል ለማወቅ አንድ ጥናት አካሄደ፡፡ ተደጋግሞ የሚነገረው "እኔ" የሚለው ቃል ነው፡፡ "፣እኔ፣፣ በአምስት መቶ የቴሌፎን ንግግሮች ውስጥ 3990 ጊዜ ተደጋግሞ ተነግሮ ነበር፡፡ "እኔ፣ እኔ፣ እኔ፣ እኔ" በዚህ ጥናት መሠረት ሰው ሁሉ ማንን እንደሚወድ አወቅህ?
ከብዙ ጓደኞችህ ጋር የተነሳኸው ፎቶግራፍ ቢቀርብልህ ቀድመህ የምታየው የማንን ምስል ነው? ሰዎች ይወዱኛል ብለህ የምታስብ ከሆነ ይህን ጥያቄ መልስልኝ፡፡ ዛሬ ማታ ብትሞት ነገ እቀብርህ ላይ ስንት ሰው ይገኛሉ?
ካልወደድካቸው ሰዎች አንተን የሚወዱበት ምን ምክንያት አለ? እርሳስ ፈልግና መልሱን ፃፍ፡፡
ሩጫችን ሁሉ ሰዎችን በማስደነቅ እንዲወዱን ለማድረግ ከሆነ የልብ ጓደኛ ልናገኝ አንችልም፡፡ የልብ ጓደኛ እኮ እንዲህ በቀላሉ አይገኝም፡፡ ታላቁ ናፖሊዮን ሞክሮት ያልተሳካለት ነገር ነው፡፡ ኮዦሴፊን ጋር በመጨረሻ ባደረጉት ንግግር ላይ ናፖሊዮን፡-
"ዦሴፊን እኔ በዓለም ላይ መልካም እድል ካጋጠማቸው ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ሆኖም በዚች ቅፅበት ከልቤ የምተማመነው ባንቺ ብቻ ነው" ብሏት ነበር፡፡ ታሪክ አዋቂዎች እሷንስ በርግጥ ያምናት ነበር? የሚል ጥርጣሬ አላቸው፡፡
(ዋሴ ሀብቴና ደምሴ ጽጌ፣ ጠብታ ማር (ትርጉም"፣ 1981")
ፍርሀት አዶከብሬ
ፍርሀት አዶከብሬ አያ እናት አይምሬ የቁም መቃብሬ የቅዠት ሀገሬ፡፡ ከሥጋ ከነብሴ ከደሜ ቆንጥሬ ከአጥንቴ ሰንጥሬ፤ ምስህን ሰጥቼህ ላመልህ ገብሬ፤ ያው ነህ አንተ ግና ልጓምህ አይላላ፡፡ ትጋልበኛለህ በእሾህ በቆንጥር ላይ ጨለማ እንደግራር በቅሎበት በሚታይ አንዲት ዘሀ - ጮራ በማትደፍርበት እውነት - ፍቅር - ውበት በተቀበሩበት፡፡
(ደበበ ሠይፉ፣ ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ፣ 1992)
ፍርድ
ለማንም ሕዝብ ልዩነትና አድልዎ የሌለበት ትክክለኛ ፍርድ ያለብዙ ችግር ማግኘት ካይነተኛ የነፃነት ዓምዶች አንዱ ነው፡፡ የፍርድ ቤት ደረጃ ያለልክ በዝቶ የመጨረሻ ፍርድ የሚገኝበት መንገድ ከመጠን ያለፈ ሲረዝም የመጨረሻ ፍርድ የማያገኙ የገንዘብና የዕድሜ ድሆች ያልሆኑ ብቻ ይሆናሉ፡፡ በብዙ ኪሣራና በብዙ ድካም እመጨረሻው ፍርድ ቤት ከሚደርሱት እንኳ አንዳንድ ጊዜ ተሙዋግተው ከሚያገኙት ይልቅ ኪሣራቸው በልጦ፣ ትዳራቸው ተጐሳቁሎ ያገኙትና በቀረብን የሚሉ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሚበዛውን ጊዜ የተረቱ ተሙዋጋቾች የበላይ ፍርድ ቤት መኖሩን ካወቁ ፍርድ እናስገለብጣለን ብለው ተስፋ በማድረግ እመጨረሻው ድረስ ደርሰው ቁርጥ እስኪያውቁ ሽቅብ ሲሄዱ መኖርን ይመርጣሉ፡፡
(ሐዲስ ዓለማዬሁ፣ ኢትዮጵያ ምን ዐይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?፣ 1966)
ማዕበሉ ብቻ ይለፍ
ጋብሮቮዬውና ልጁ፣ ጀልባቸውን እየቀዘፉ ሲዝናኑ ከፍተኛ ማዕበል ይነሣል፡፡ ማዕበሉ ጀልባይቱን ሽቅብ አጉኖ ቁልቁል ሲመልሳት የተመለከተው አባትም በሁኔታው ተደናግጦ፣ "አምላኬ ሆይ" ከዚህ መከራ ካወጣኸን የጀልባዬን ተራዳ የሚያክል ሻማ አበራልሃለሁ" ብሎ ይሳላል፡፡
በፍራቻ ተውጦ ጭብጦ አክሎ ጭብጥ ብሎ ተቀምጦ የነበረው ልጁ ይህን ሲሰማ ተገርሞ፣ "አባዬ" ሻማ ሠሪዎች ተራዳ የሚያክል ሻማ ይሠራሉ?" በማለት ቢጠይቀው፣
"አፍህን ዝጋ፣ አንት ክልፍልፍ" ማዕበሉ ብቻ ይለፍ እንጂ ሌላውን በኋላ እናስብበታለን" አለው ይባላል፡፡
(ዐረፈ ዓይኔ ሐጐስ፣ ቀልዶች ከጋብሮቮ ምድር፣1979)
አጭሩ ጦርነት
በዓለም ታሪክ አጭሩ ጦርነት፣ በእንግሊዝ ጦር ኃይልና በዛንዚባር መካከል የተካሄደው ነው፡፡ ጦርነቱ ነሐሴ 27/1896 የተከናወነ ሲሆን፣ የፈጀው ጊዜ 38 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡
ሱልጣን ሰዒድ ካህሊድ የተባለው የዛንዚባር ተወላጅ በራሱ አነሳሽነት ንጉሥ ነኝ ብሎ ዘውድ ይደፋል፡፡ ሁኔታው በወቅቱ የሀገሬው ቅኝ ገዥ የነበረውን የእንግሊዝን መንግሥት በማስቆጣቱ በሪር አድሚራል ራውሰን የሚመራው የባህር ኃይል ፍሊት ወደ ስፍራው ተልኮ አዲሱ ንጉሥ ቤተ መንግሥቱን አፍርሶ እጁን እንዲሰጥ ይጠይቃል፡፡ ካህሊድ ግን አሻፈረኝ በማለቱ የባህር ኃይሉ መርከቦች ለ38 ደቂቃ ቤተ መንግሥቱንና አካባቢውን በመድፍ ጥይት ይደበድባሉ፡፡ በዚህም የንጉሡና የቤተ መንግሥቱ ታሪክ አከተመ፡፡ የሚገርመው ነገር፣ ቤተ መንግሥቱን ለማፍረስ የተተኮሰው ዋጋ በልጦ ተገኝቷል፡፡ አድሚራል ራውሰንም በዚሁ የ38 ደቂቃ ጦረንት የዛንዚባርን አንደኛ ደረጃ ባለኰከብ ሜዳይ ተሸልመዋል፡፡
(ሻለቃ አባይነህ አበራ፣ ጭላሃ ወግ (ትርጉም"፣ 1981)
የሌሊት ወፍ ለምን የሌሊት ወፍ ተባለች?
የሌሊት ወፍ እንደ አይጥ ጥርስ አላት፣ እንደወፍም ክንፍ አላት፡፡ አንድ ጊዜ ወፎችና የዱር እንስሳት ተጣልተው አምስት ቀን ሙሉ ጦርነት አደረጉ፡፡ የሌሊት ወፍ ግን ገለልተኛ ሆና ትመለከትና የዱር እንስሳት ሲያጠቁ ስታይ ወደነሱ ትሄድና እኔ እኮ ዘሬ ወደ እናንተ ነው፣ እዩት ጥርሴን እዩት ጡቴን፣ እስቲ ከወፎች እንደኔ ጥርስና ጡት ያለው ማነው? ትላቸዋለች፡፡ ደግሞ ወፎች ሲበሩ ስታይ ወደነሱ ትሄድና እኔ እኮ የእናንተ ወገን ነኝ እዩት ክንፌን እስቲ ከዱር እንስሳት ወገን እንደኔ በክንፍ እየበረረ በአየር ላይ የሚሄድ ማነው ትላቸዋለች፡፡ እንዲህ እያለቻቸው ወደ ጦርነቱ ግን አትገባም፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ እርቅ ተደረገና ጦርነቱ ቆመ፡፡ እርቁን ምክንያት በማድረግ ትልቅ በአል ተደረገ፡፡ የሌሊት ወፍም ወደ ወፎቹ ድግስ ስትሄድ እኛ እንደ አውሬ ጥርስ የለንም ብለው አባረሯት፡፡ ወደ ዱር እንስሳትም ስትሄድ እኛ እንደወፎች ክንፍ የለንም ለምን መጣሽ አሉና አባረሯት፡፡ ከዚህ በኋላ አፈረችና ወፎችም የዱር እንስሳትም እንዳያዩዋት ቀን ቀን ተደብቃ እየዋለች ማታ ማታ ምግብዋን ለመፈለግ ትወጣ ጀመር፡፡ የሌሊት ወፍም የተባለችው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
(ዘሪሁን አስፋው፣ የስነጽሁፍ መሰረታውያን፣ 1992)
ገ ራ ገ ር
ሕፃኑ የቤተሰቦቹን መኪና ሰርቆ አሽከረከረ
ሚሮስቫል ኖባክ የተባለ የአምስት ዓመት ሕፃን ከሚኖሩበት ሚሞን ከተማ የቤተሰቦቹን መኪና ሰርቆ በማሽከርከር አንድ ማይል ያህል ከተጓዘ በኋላ ግጭት ሳይፈጠር ሊያዝ መቻሉን የቼክ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ሚሮስቫል የተያዘው አንድ ፓርክ ውስጥ ሲሆን ከፊት ለፊት ማየት እንዲችል ከአሽከርካሪው መቀመጫ ላይ ሁለት ትራሶችን ደራርቦ ነበር፡፡ ፖሊስ ሕፃኑን ሕግ ፊት ለማቆም እድሜው ያልደረሰ በመሆኑ ትቶታል፡፡ ነገር ግን ይህን ያህል ርቀት እንዴት ሊያሽከረክር እንደቻለ እንደሚያጣራ አስታውቋል፡፡
ሰውየው በሀያ ዓመት ልዩነት አባትና ልጅን አዳነ
ዋንግ ዌከን የተባለ የአምሳ ስምንት ዓመት ቻይናዊ በሃያ ዓመት ልዩነት አባትና ልጅን ከጥልቅ የውሀ ጉድጓድ በማውጣት ሕይወታቸውን ማትረፉን ዘ ያንግተስ ኢቭኒንግ ኒውስ የተባለ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
ከውኃ ጉድጓድ ውስጥ ያወጣው ሕፃን የሰባት ዓመት እድሜ አለው፡፡ ሕፃኑን ይዘው ወደዚያ አካባቢ የመጡት አያቱ የልጃቸው ልጅ መሆኑን ሲገልፁለት ሕፃኑ ከሃያ አመት በፊት ከጉድጓድ ያወጣው ጐልማሳ ልጅ መሆኑን ለመረዳት ችሏል ዋንግ ዌከን፡፡
"የልጅ ልጄን ይዤ በዚያ አካባቢ እያለፍኩ ነበር፡፡ ሕፃኑ ከጉድጓድ ለመውጣት ሲታገል ተመለከትኩ ብሏል ዋንግ ዌክን፡፡ የሕፃኑ አያት ደግሞ የልጃቸውንና የልጅ ልጃቸውን ሕይወት የታደገውን ሰው አመስግነዋል፡፡
የሁለት ልጆች እናትና የ44 ዓመቷ ቦክሰኛ
የሁለት ልጆች እናትና የ44 ዓመቷ ጃፓናዊት በዕድሜ ትልቋ ጃፓናዊት በመሆን የጃፓንን የቦርድ ፈቃድ አገኘች፡፡
ከዙሚ ኢዛኪ ዕድሜያቸው 14 እና 21 የሆኑ ሴት ልጆች እናት ስትሆን በሚቀጥለው ሳምንት 45 ዓመቷን ትሞላለች፡፡
በዚህ እድሜ የጃፓንን የቦክስ ኮሚሽን ፈቃድ ያገኘች ብቸኛ ቦክሰኛ ሆናለች፡፡ በኮሚሽኑ ሕግ መሠረት የቦክስ ፈቃድ የሚሰጣቸው ዕድሜያቸው ከ32 ዓመት በታች መሆን አለበት፡፡ ካዙሚ ይህን ፈቃድ ያገኘችው ከዚህ ቀደም ባገኘችው የሀገሪቱ ታላቅ የቦክስ ሰው ማዕረግ ምክንያት ነው፡፡
ከሥራ ለመቅረት ትከሻውን በጥይት አስመታ
በዋሽንግተን ነዋሪ የሆነው የሃያ አንድ ዓመቱ ዳንኤል ኩች ከመሥሪያ ቤቱ ለመቅረት የሴት ጓደኛውን በጥይት ተኩሳ እንድታቆስለው ማድረጉን ዴይሊ ቴሌግራፍ አስታወቀ፡፡
ዳንኤል ከሥራ መቅረት የፈለገው በዕለቱ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ የሠራተኞች የአደንዛዥ እፅ ምርመራ ይደረግ ስለነበር መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ዳንኤል ለመቁሰሉ የሰጠው ምክንያት ግን ከጓደኛው ጋር መንገድ ላይ እየተጓዘ ከመኪና ላይ የተተኮሰ ጥይት መሆኑን ነው፡፡
የዚህ ዓይነት የተሳሳቱ የአደጋ ሪፖርቶች በብዙ መልኩ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ፖሊስ ጠቁሞ የዳንኤል ጓደኛ በዚህ ዓይነት ድርጊት ተባባሪ ሆና በመገኘቷ በቁጥጥር ስር እንደዋለች አስረድቷል፡፡ |