|
Wednesday, 05 March 2008 |
|
“ተማሪዎች ብቁ መሆናቸውንና መማራቸውን ሳናረጋግጥ የምናድለው ዲግሪና ሰርተፍኬት አይኖርም” ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን ታምራት የቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት
ቅድስተ ማርያም ዩኒቨሪሲቲ ኮሌጅ በሀገራችን ውስጥ በትምህርት ዘርፍ ተሰማርተው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ከፍተኛ የግል ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ጊዜ ውስጥ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ሃያ ሦስት ሺህ ተማሪዎችን በተለያየ የሙያ ዘርፎች አስመርቋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከስምንት መቶ በላይ ሰራተኞች በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ ተቀጥረው ይሰራሉ፡፡ ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ባከናወናቸው ሥራዎች ዙሪያ የዩኒቨሪሲቲ ኮሌጁን መስራች እና ኘሬዚደንት የሆኑትን ረዳት ኘሮፌሰር ወንድወሰን ታምራትን ሪፖርተራችን ኃይሌ ሙሉ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የትምህርት ጥራትን በመጠበቅ መልኩ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች ምንድናቸው?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- የትምህርት ጥራት ሥራ ከተቋማት ህልውና ጋር የተያያዘ ሥራ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ሥራ ውጫዊና ውስጣዊ የሆነ ገጽታ አለው፡፡ በየትኛውም ዓለም የሚሰራበት ስርዓት ነው፡፡ በአንድ በኩል መንግሥት ለዜጐች የሚያዳርሰው ትምህርት በሚመጥን መልክ መሆኑን የሚቆጣጠርበት ውጫዊ የቁጥጥር ስርዓት አካሄድ አለ፡፡ አንድ ተቋም ከውጭ የሚደረግበትን የጥራት ቁጥጥር ብቻ ጠብቆ መንቀሳቀስ አይኖርበትም፡፡ የራሱን የጥራት ሥራ የሚያስጠብቅበት ስርዓት በውስጥ ሊያሳድግ ይገባል፡፡ ይህንን በተመለከተ ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከምስረታው ጀምሮ በተቋሙ የሚካሄዱ ትምህርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የዘረጋቸው ስርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህ ስርዓቶች ዋና መነሻቸው በአገር አቀፍ ደረጃና በዓለም አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማሟላት ያለባቸውን ጉዳዮች በመለየት የተሰራ ነው፡፡ የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ይህንኑ ሥራ ብቻውን የሚሰራ አንድ የጥራትና የምርምር ማዕከል አቋቁሞ ላለፉት ዓመታት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ይሄ የጥራትና የምርምር ማዕከል ከመቋቋሙ በፊት ተቋሙ ትምህርት ሚኒስቴርን ሲያግዙ ከነበሩ ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ራሱን የማስገምገም ስርዓት አከናውኗል፡፡ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር አንድ የፉል ብራይት ስኮላር ከአሜሪካ በማስመጣት ለሁለት ወር ያህል አርባ ለሚሆኑ መምህራንና የዲፓርትመንትና የፋኩልቲ ኃላፊዎች በጥራት ሥራ ዙሪያ ስልጠና በመስጠት በመጨረሻ ማዕከሉ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ራሱን የቻለ ዳይሬክተር አለው?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- ይህ ማዕከል ራሱን የቻለ ዳይሬክተር አለው፡፡ ራሳቸውን የቻሉና ሰፊ ጊዜያቸውን ለጥራትና ቁጥጥር ተግባር የሚያውሉ ባለሙያዎች የተመደቡበት ቢሮ ነው፡፡ የዚህ ቢሮ አይነተኛ ዓላማ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ህግጋትን በመከተል በግቢያችን ውስጥ የሚካሄድ የትምህርት ስርዓት በተለየ ሁኔታ እየተካሄደ ነው ወይ? ድክመታችን ምንድን ናቸው? ጥንካሬዎቻችን ምንድን ናቸው የሚሉ ሥራዎችን ይሰራል፡፡ አነስተኛ ምርምሮችን ያካሂዳል፡፡ ማዕከሉ በየጊዜው የሚደርስባቸውን ውጤቶች ከማኔጅመንቱ ጋር በመሆን ለመምህራን ለየትምህርት ክፍሎች እንዲቀርቡ ያደርጋል፡፡ የማኔጅመንቱና የመምህራን ካውንስል የሚገናኙበት ስርዓት ይፈጥራል፡፡ በዚያ ዙሪያ ያሉ ተግባራትን በመለየት በመምህራን የሚደረጉትንና በማኔጅመንቱ በኩል ሊደረጉ የሚገባቸውን ተግባር በመለየት ዘወትር የለውጥ ሥራ ለማካሄድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያካሂዳል፡፡
ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች አስመርቆ ለማውጣት ከምልመላ ጀምሮ የሚከተለው አሰራር ምንድን ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- ምልመላን በተመለከተ የቅበላን መስፈርቶች የሚያወጣው የትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ከዚያ ውጭ በክልል ደረጃ ለምንሰራቸው ሥራዎች የክልል ትምህርት ቢሮዎች ናቸው መስፈርቶቹን የሚያወጡት፡፡ እነዚህን አገር አቀፍና ክልላዊ ሕጐች አጥብቀን እንከተላለን፡፡ ከዚህ የቅበላ መስፈርት በኋላ የምንቀበላቸው ተማሪዎች ለስልጠና ባለሙያ የሚያበቃቸው ስርዓተ ትምህርት በተገቢው ሁኔታ መዘጋጀቱን ዘወትር እንፈትሻለን፡፡ በየጊዜው የትምህርት ስርዓታችን ለውጥ እንዲኖረው፣ ተግባር ተኮር እንዲሆንና ተማሪዎቻችንን ተወዳዳሪ እንዲያደርግ ሰፊ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ብዙዎቹ ተማሪዎቻችን በመንግሥት የትምህርት ተቋማት እድል ሳያገኙ ወደ እኛ የመጡና በተወሰነ ደረጃም ነጥባቸው ወደ መንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማያስገባቸው በመሆኑ ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ ተማሪዎች ካሉ ለእነዚህ ተማሪዎች ልዩ የቲቶሪያል ድጋፍ እናደርጋለን፡፡
ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸው የላይብረሪና የተለያዩ ቁሳቁሶች በተገቢው ሁኔታ መሟላታቸውን በየጊዜው እንከታተላለን፡፡ በትምህርቱ ሥራ ላይ ወሳኝ የሆነው አካል መምህሩ በመሆኑ መመህራን ከምልመላ ጀምሮ በአጠቃላይ ሥራቸው ላይ ሰፊ ጥንቃቄ አድርገን ብቃታቸውን ለማረጋገጥ እንሞክራለን፡፡ ምልመላችን ከማኔጅመንቱና ከዲፓርትመንቱ ያሉ ኃላፊዎችን በጋራ ይዞ የሚከናወን ነው፡፡ መምህራኑ በሥራ ላይ ሲሰማሩ ተከታታይ የሆነ ግምገማ ይካሄዳል፡፡ የተማሪዎች ግምገማ አለ፡፡ መምህራንም የራሳቸው ግምገማ አላቸው፡፡ የትምህርት ክፍሎችና የማኔጅመንቱ ግምገማ አለ፡፡ እነዚህን ግምገማዎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚሰራልን የምርምርና የጥራት መቆጣጠሪያ ማዕከላችን ነው፡፡ በእነዚህ ዙሪያ ያገኘናቸውን መረጃዎች ይዘን የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንሞክራለን፡፡ በክፍል ተማሪዎች ከሚሰሯቸው ሥራዎች በተጨማሪ ተጓዳኝ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በተማሪዎች ህብረትና በተማሪዎች ጉዳይ ቢሮ አማካኝነት እንሰራለን፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ተማሪዎችን የአካዳሚ እውቀት ብቻ የጨበጡ ሰዎች ሳይሆኑ ከሌሎች ጋር ተግባቢነት ያላቸው ከሌሎች ጋር አብረው መሥራት የሚችሉ ተማሪዎች እንዲሆኑ የሚረዱበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ረገድ የባህል ቡድኖች፣ በየሳምንቱ ለተማሪዎች የሚቀርቡ የቶክ ሾው ዝግጅቶች ይካሄዳሉ፡፡ በቅርቡ ደግሞ ተማሪዎች የራሳቸውን ጋዜጣ የማሳተም እንቅስቃሴዎች የጀመሩበት ሁኔታ አለ፡፡
ሪፖርተር፡- የውጤት አሰጣጥን በተመለከተ ቢገልፁልን፤
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- ውጤትን በተመለከተ ተማሪው የሚገባውን ማርክ ያገኛል፡፡ በዚህ ዙሪያ እንደግል ተቋማት የገንዘብ ምንጮቻችን ናቸው ብለን የተለየ የምናደርገው አስተየየት አይኖርም፡፡ ሥራውን በትክክል ለመወጣት እንደሚጥር የአንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው ራሳችንን የምናየው፡፡ በመስኩ ገቢ ለማስገባት እንደሚሞክር የንግድ ሱቅ አይደለም የተቋቋምነው፡፡ ይህም በመሆኑ የተሻሉ ሥራዎችን ለመሥራት በየጊዜው በምናደርገው ጥረት ተወዳዳሪ ምሩቃንን ለማፍራት ችለናል ብለን እናስባለን፡፡ በተወሰነ ደረጃ ይህንን በተለያዩ ቦታ በሚያደርጓቸው ውድድሮች ተማሪዎች በሚደርሱባቸው ደረጃዎች እየለካን አንገኛለን፡፡ በቅርቡ ደግሞ ላለፉት ዘጠኝና አስር ዓመታት በተለያዩ መስኮች ተመርቀው በየሥራ ዘርፉ የሚገኙ ምሩቆቻችን የትና በምን ሁኔታ እንዳሉ እውቀታቸው ምን ያህል ረድቷቸዋል የሚል ሰፊ አገር አቀፍ ጥናት እያከናወንን ነው፡፡ በዚህና በመሳሰሉት አሰራሮች ነው ተማሪዎቻችን የተሻሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የምንሞክረው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በቅርቡ የከፈትነው የኢንተርፕሩነርሺፕና የኢኖቬሽን ማዕከል አለ፡፡ ተማሪዎች በሥራ መስክ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው? ብሎ በምርምር የመለየት ሥራ የሚሰራ ማዕከል ነው፡፡ ቀጣሪዎች የሚፈልጉትን ክህሎት በመለየት ስርዓተ ትምህርታችን ከፍላጐቱ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው? በእርግጥ ንቁ ተወዳዳሪዎችን እያፈራን ነው? የሚለውን ለማየትና በቀጣይ የተጠናከሩ ሥራዎች ለመሥራት እየሞከርን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ የቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውጤት አሰጣጥ ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ ሊመረቁ የተዘጋጁ ተማሪዎችም የሚባረሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የተማሪዎቹን ቅሬታ እንዴት ነው የሚያየው?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- አንዳንድ ጊዜ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ የተሳሳተ አመለካከተ ያለ ይመስለኛል፡፡ የግል ተቋማት በመሆናችን ብቻ ስርዓትን ህግን ወደኋላ አድርገን ገቢያችንን የምናስቀድም አድርገው የሚመለከቱን ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ገቢያችን መቶ በመቶ በተማሪዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን የትምህርት ሥራ እንደተራ የንግድ ሥራ የሚታይ አይደለም፡፡ ገቢን ብቻ የመጀመሪያ ግቡ የሚያደርግ ሥራ አይደለም፡፡ የተቋሙ ተቀዳሚ መርህ ተማሪዎች መማራቸውንና ብቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ተማሪዎች ብቁ መሆናቸውንና መማራቸውን ሳናረጋግጥ የምናድለው ዲግሪና ሰርተፍኬት አይኖርም፡፡ ይህ ከሆነ የሰርትፍኬትና የዲፕሎማ መሸጫ ሱቆች ነው የምንሆነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ሁኔታ ተቋሙ በምንም ዓይነት መልኩ የሚደራደርበት አካሄድ የለውም፡፡ በማንኛውም ደረጃ ቢሆን ተማሪዎች በቂውን መስፈርት አሟልተው በሚጠበቅባቸው ሁኔታ ሰልጥነዋል ብለን ካላመንን ሊባረሩ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች ሰርተፍኬታቸው ትርጉም ያለው የሥራ መሳሪያ እንዲሆንላቸው በቂ ክህሎትና እውቀት ጨብጠዋል ወይስ አልጨበጡም የሚለውን በምናረጋግጥበት ጊዜ ስርዓቱን ጠብቀው እንዲመረቁ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንሰጣለን፡፡ ይሄ ግን ጥያቄ ውስጥ በሚገባበት ወቅት ከተቋም በላይ የሀገርና የሕዝብም ኃላፊነት ያለብን ይመስለኛል፡፡ የውሸት ምስክርነት ልንሰጥበት የምንችልበት ሁኔታ የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ከትምህርት ሚኒስቴርና ከክልሉ የትምህርት ቢሮ ያላችሁ የሥራ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- ከክልል የትምህርት ቢሮና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ሰፊ ግንኙነቶች አሉን፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተለያዩ አገር አቀፍ የሥራ እንቅስቃሴዎች በሚደረጉ ጊዜ ኮሌጁ የራሱን ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች በመላክ ሰፊ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ የቴክኒክና የሙያ ትምህርት የምዘና ስርዓት ለመንደፍ በተደረገ ሰፊ ስልጠናና ሴሚናር ላይ ባለሙያዎቻችን ተሳትፈው የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በሚያዘጋጃቸው የምክክርና የጋራ መድረኮች ላይ አስፈላጊውን ተሳትፎ እናደርጋለን፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በሚያወጣቸው መመሪያዎች ላይ እንደዚሁ ተገቢ የመሰለንን አስተያየትና ይጠቅማሉ የምንላቸውን ጉዳዮች ለማሳወቅ እንጥራለን፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ ከግል ተቋማት የሚመረቁ መምህራን በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዳያስተምሩ አዝዟል፡፡ ይህንን የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ እንዴት ያዩታል? በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ የፈጠረው ተፅዕኖስ ምን ይመስላል? ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- ይህ መመሪያ አግባብ ያልሆነ መመሪያ መሆኑን በመግለጽ ስንከራከርበት ቆይተናል፡፡ ወደፊትም በተለያየ ደረጃ ለመንግሥት ከማመልከት ወደ ኋላ አንልም፡፡ ይህ መመሪያ ትክክል አይደለም የምንልባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በእውቅናና በቅድመ እውቅና አልፈው የሚሰጡት የትምህርት መረጃ ከየትኛውም የመንግሥት ተቋማት የሚወጡ ምሩቃን ካላቸው ደረጃ እኩል እንደሆነ የሚናገር ስርዓት ዘርግተን በስተመጨረሻ “ከምረቃ በኋላ ከግል የሚወጡትን ልንቀበል አንችልም” የሚል መመሪያ ማውጣት በመጀመሪያ የተዘረጋውን ስርዓት የሚንድ ነው የሚመስለኝ፡፡ የተመራቂዎቹን ሕገ መንግሥታዊ መብትም እንደዚሁ የሚፃረር ነው፡፡ ይህንን መመሪያ ትክክል የማያደርገው “ሌላው ነገር መነሻዎቹና መድረሻው የሚያመጣው ውጤት ነው፡፡
ምንም ዓይነት ጥናት በግሉ ዘርፍ ሳይካሄድ ከግሉ ዘርፍ የሚወጡ ምሩቃን በበቂ ሁኔታ መዘጋጀትና አለመዘጋጀታቸው ሳይጣራ፣ ከመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ያላቸው ደረጃ ሳይመዘን የግሉን የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ አንቀጥርም የሚል ውሳኔ ላይ መድረስ በምንም መለኪያ አግባብ አይሆንም ብለን እናስባለን፡፡ ይህ መመሪያ በመውጣቱ በቀጥታ የጐዳቸው ተቋማት ብዙ ናቸው፡፡ ለዓመታት የመምህራንን የትምህርት ዘርፍ ብቻ ይዘው ሲያሰለጥኑ የነበሩ ተቋማት ከዘርፉ በቀጥታ ወጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙ ሺህ ተቋማትን መኖርና ማበብ እንፈልጋለን እያልን እነዚህን ተቋማት በቀላሉ ማጣታችን አግባብ ይሆን ወይ የሚሉ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በሌላ በኩል መድረሻው አግባብ አለመሆኑን ያረጋገጥነው ነገር መንግሥት የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን መምህራንን አልቀጥርም ካለ በኋላ ይህንን እንደ አንድ መነሻ በመውሰድና አጓጉል የሆነ ድመዳሜ ላይ በመድረስ የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሰለጠኑ ምሩቃንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እያገለሉ ያሉበት ሁኔታ አለ፡፡
ይህ መመሪያ በፈጠረው የመረበሽ ስሜት በትምህርቱ ዘርፍ ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች የሚመጡ አደጋዎችን በመፍራት የመተማመን መንፈሳቸው ተሸርሽሯል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅም እንደ ማንኛውም ተቋም በመምህራን ትምህርት ዘርፍ በሚያሰለጥናቸው የሰልጣኞች ቁጥር ላይ ይህ መመሪያ ተፅዕኖ ፈጥሮበታል፡፡ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበር አማካይነት መመሪያው አግባብ የሌለው መሆኑን ለመንግሥት የተለያዩ አካላት እያሳወቅን ነው፡፡ አንድ መፍትሄ በአጭር ጊዜ ሊገኝ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንንም ተስፋ አድርገን እየጠበቅን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ ያለው የአካዳሚክ ነፃነት ምን ይመስላል?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- የአካዳሚክ ነፃነት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ልምዶች ያሉት ጉዳይ ነው፡፡ ማንኛውም ተማሪ እውቀትን በመፈለግ ሂደት ውስጥ ሙሉ ነፃነት ኑሮት እንዲንቀሳቀስ የተቋማት አካዳሚክ ነፃነት ያዛል፡፡ በዚህ ረገድ ተማሪዎች በክፍልም ውስጥ ሆነ ከክፍል ውጭ እውቀታቸውን ለማጐልበት፣ የተሻለ ነገር ላይ ለመድረስና ለመመራመር ሙሉ ነፃነታቸውን እንዲጠቀሙ እናበረታታለን፡፡ የአንድ ወገን ሥራ ብቻ እንዳይሆን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የሚቻለውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡ የተማሪዎች ማህበር እንዲመሰርትና በተማሪዎች ማህበር በኩል የመማር ነፃነታቸውን የሚያስከብሩበት ስርዓት አንዲኖር ጥረት እናደርጋለን፡፡ እነዚህ ነፃነቶች በተገቢው ሁኔታ አልተከበሩም በሚሉበት ወቅት ተማሪዎች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ አወቃቀር ይፈቅዳል፡፡ በዋነኛነት ከተማሪዎች ህብረት ጐን የኮሌጁን አካል በመወከል የተማሪዎችን ጥያቄዎች ለማሟላት የሚጥረው የተማሪዎች ጉዳይ ቢሮ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአስተዳደራዊ መዋቅራችንም ይህንኑ በሚያቅፍ መልክ ነው የተሰራው፡፡ ተማሪዎች ከመምህራኖቻቸው ጋር ካሏቸው ግንኙነት ውጪ በዲፓርትመንት ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች አሉ፡፡ እስከ አካዳሚክ ዲንና እስከ ፕሬዚዳንት ቢሮ ድረስ ቅሬታቸውን በማቅረብ ሊሟሉላቸው የሚገቡ ነገሮችን የሚያቀርቡበት ስርዓት አለ፡፡ ለመጪው አምስት ዓመት በሰራነው የስትራቴጂክ ፕላን ውስጥ ተማሪዎች በአካዳሚክ ኮሚሽን ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ተሳትፎ የሚያቀርቡበትን ስርዓት እያመቻቸን ነው፡፡
ተማሪዎች በየደረጃው ውክልና የሚያገኙበትን ስርዓት ለመፍጠር ጥናት እያደረግን ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ መምህራንም እውቀትን በመፈለግና እውቀትን ለተማሪዎች በማስተላለፍ ዙሪያ አንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚሰጣቸውን ነፃነት በቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚያገኙበትን ሁኔታ እናበረታታለን፡፡ አስተዳደሩና መምህራን ያላቸው ግንኙነት የአለቃና የጭፍራ የፊውዳልና የሎሌ ከመሆን ይልቅ የአንድ ስርዓት የጋራ አካሎች ሆነን ለአንድ ዓላማ የምንንቀሳቀስ ግለሰቦች ሆነን የምንሰራበት ስርዓት ለመፍጠር ነው የምንሞክረው፡፡
ሪፖርተር፡- ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በትምህርቱ ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን ያስቻሉት ምክንያቶች ምንድናቸው? አጀማመሩስ እንዴት ነበር?
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመሳሳይ የመነሻ ዳራ ነው ያላቸው፡፡ አንጋፋዎቹ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኮምፒዩተር ማዕከላት፣ የቋንቋ ማዕከላት በሰርተፍኬት ደረጃ የአጭር ጊዜ ስልጠና ሲሰጡ የነበሩ ናቸው፡፡ የቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከቋንቋ ትምህርት ቤት ነው የተነሳው፡፡ የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ ሲመሰረተ በአነስተኛ ተማሪዎች ነበር ሥራውን የጀመረው፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ሰፊ ጥረትና ትግል በማድረግ ዛሬ ያለበት የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅቷል፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ሁሉንም አጠቃልሎ መጥቀስ ባይቻል ዋና ዋናዎቹን ማንሳት ይቻላል፡፡ በጥራት ላይ ያተኮረ ስልጠና ለመስጠት ጥረት ማድረጋችን አንዱ ነው፡፡ የአቅም ውስንነት ሳይገድበን የተሻለ ሥራ መሥራት አለብን የሚል መርህ አለን፡፡ ይህንን አላማችን ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ለመሄድ ትጋቱ፣ እልሁና ቁርጠኝነቱ ነበረን፡፡ ይህ ለውጤታማነታችን የረዳን ይመስለኛል፡፡ የሠራተኛውና የማኔጅመንቱ ተግባቢነት ከፍተኛ መሆኑም በብዙ መልክ ጠቅሞናል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ወጣቶችና ትጉህ የሆኑ ሠራተኞች ናቸው፡፡ ዘወትር ለመሻሻልና ለመለወጥ ያለን ጉጉት ከፍተኛ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ከምናካብታቸው ልምዶች በተጨማሪ በውጭ አገር ካሉ ተቋማት ጋር የቅርብ ግንኙነት ለመፍጠር በየጊዜው ጥረት እናደርጋለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሆላንድ ከሚገኘው ኒው ቢዝነሰ ስኩል ኦፍ አምስተርዳም ጋር በመተባበር በማርኬቲንግ ዲፓርትመንት የምናካሂደው ስራ አለ፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ተገቢውን የማስተዋወቅ ስራ በውጭው ዓለም አግኝቶ የአገራችን ገበሬዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስርዓት ለመፍጠር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከዚያ ኮሌጅ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ተማሪዎችና መምህራኖቻቸው በፈጠሩት ስራ የኢትዮጵያ ቡና ሆላንድ ውስጥ የሚተዋወቅበትን ስርዓት ዘርግተዋል፡፡ በቅርቡ እንደገና ይህንኑ ከሚሰራው ቡድን ጋር በመሆን ተጨማሪ አስራ ስድስት ተማሪዎች ይመጣሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ተጨማሪ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ በዚህ መልኩ የምንቀበለውን ሙያ ለተማሪዎቻችንና ለመመህራኖቻችን የማሳለፍ ስርዓት አለ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ እንግሊዝ አገር ኢንግላንድ አፍሪካ ፓርትነር ሺፕ በሚል ፕሮግራም ውስጥ በተደረገ ውድድር በአፍሪካ ደረጃ ከተመረጡ አስራ ዘጠኝ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሴንት ማርክ እና ሴንት ጆን ከተሰኘ የእንግሊዝ አገር ኮሌጅ ጋር በመተባበር የሰራው ፕሮጀክት ነው፡፡ በገንዘብ ደረጃም ለአገራችን ከፍ ያለ ገንዘብ እንድናሸንፍ ሆኗል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ከኢንድራ ጋንዲ ናሽናል ዩኒቨርሲቲ ጋር በፈጠርነው ቅርርብ በአገራችን ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን የማስተርስ ፕሮግራም ማካሄድ ችለናል፡፡ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ብዙ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሳተፉ ሆነዋል፡፡ በአገር ውስጥ ብቻ ሳንወሰን አጋጣሚዎች በሚፈጥሩትና ራሳችንም በምናደርገው ጥረት ከውጪ ተቋማት ጋር በምንፈጥረው ግንኙነት ውጤታማ እንድንሆን ረድቶናል፡፡
ሪፖርተር፡- በሂደት ላይ ያጋጠሟችሁ ችግሮች አሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን፡- የተለያዩ ችግሮች አጋጥመውናል፡፡ በዘርፉ ውስጥ የሚታዩ ዋና ዋና ችግሮች አሉ፡፡ በቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ብቻ የሚታዩ ችግሮች አይደሉም፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ ትልቁ የዘርፉ ችግር የነበረው ለዘርፉ ይሰጥ የነበረው አመለካከትና እምነት ነው፡፡ ዘርፉ የትርፍ ማጋበሻ እንደሆነ ተደርጐ የንግድ ዓላማ ባላቸው ሰዎች ብቻ የሚሰራ ተደርጐ ነበር የሚታየው፡፡ ይህንን አመለካከት ሰብሮ ለመውጣትና በሕዝቡ ዘንድ ተአማኒነትን ለማትረፍ በጣም ብዙ ትግልና ተግባሮች ማከናወን ነበረብን፡፡ ሕዝቡ በሂደት አማራጭ ሊኖረው እንደሚችል የሚገነዘብበት ሁኔታ አሁን ተፈጥሯል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሁለተኛውና ዋናው ችግር በመንግሥት በኩል ለዘርፉ ሊሰጡ የሚገቡ እገዛዎች አለመተግበራቸው ነው፡፡ በተለያዩ አዋጆችና ፖሊሲዎች ላይ ዘርፉ ሊያገኛቸው የሚገባው ጥቅምና እገዛ ተገልጿል፡፡ እነዚህ ነገሮች ግን በአስፈፃሚ አካላት በኩል የማግኘቱ ነገር ቀላል ሆኖ አላገኘነውም፡፡
የራሳችን መሬት ኖሮን የራሳችን ግንባታ ማከናወን ብንችል በዘርፉ ላይ አሁን ካሳየነው ውጤት በተሻለ ማስመዝገብ እንችል ነበር፡፡ ብዙ ተቋማት ከሠራተኞቻቸው እኩል ወይም በሚበልጥ ደረጃ ብዙ ወጭ የሚያወጡት በህንፃ ኪራይ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ለትምህርት ጥራትና ለትምህርት ሥራ ያላቸውን ዓላማ በተገቢው ጊዜና ቦታ ለማዋል እጃችን ተይዘናል፡፡ ይህ በሁሉም ተቋማት ላይ የሚታይ ችግር ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የሚታየው የመንግሥትና የግል ተቋማት በጋራ በመስራት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በአገራችን ውስጥ በስፋት አይተገበርም፡፡ እነዚህ እንደ ችግሮች ሆነው የቆዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ችግሮች አሉ ብለን አልተቀመጥንም፡፡ እየሰራን በሂደት ችግሮቹን ለመቅረፍ ነው የምንሞክረው፡፡ ከዚህ ውጭ ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ከተማሪው በሚገኝ ገቢ ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑ ለሌላ አደጋ ያጋልጠዋል፡፡ የተማሪዎች ቁጥር ባሽቆለቆለ ቁጥር የተቋማት አቅም እያሽቆለቆለ ነው የሚሄደው፡፡ የራሳችንን የተለያዩ የገቢ ምንጮች የማዳበርና ተቋሙ ተጠናክሮ የሚሄድበትን ስርዓት የማመቻቸት ችግሮች ነበሩብን፡፡ ይህንን ችግር አሁን ለመወጣት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ለራሳችንም የሚሆኑ ለሌሎች ከፍተኛ ተቋማትም የሚያገለግሉ መጽሐፍቶችን በማሳተም ላይ እንገኛለን፡፡ አጫጭር ስልጠናዎችንና የምክር ግልጋሎቶችን በመስጠት ተጨማሪ ገቢዎችን ለማግኘት ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ |