| ተመራቂ ወጣት ሥራ አጦች |
|
|
| Wednesday, 05 March 2008 | |
![]() ታጠቅ ካሳ ለውይይቱ እንደ መነሻ የሆነው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አባል፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የወጡ ወጣቶች ከተመረቁ በኋላ ሥራ ለማግኘት የገጠማቸውን ችግር በሚመለከት ያቀረቡት አነስተኛ ፅሑፍ ነው፡፡ ወጣቶቹ ያቀረቡት ፅሑፍ እንደሚያሳየው ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን የወጡ ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ከሚገጥማቸው ችግር ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያዎች ሲወጡ ከፍተኛ የሥራ ልምድ መጠየቅና የቅጥር አፈፃፀም ግልፅና ቀጥተኛ አለመሆን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በርካታ የሥራ ማስታወቂያዎች በተደጋጋሚ በተለያዩ ጋዜጣዎች ቢወጡም ለእነዚያ ክፍት ሥራዎች የሚጠየቁት የሥራ ልምድ ዓመታት በመሆናቸው የሚወጡ ማስታወቂያዎች በብዛት ከከፍተኛ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎችን ያላገናዘበ መሆኑ በጽሁፉ ተመልክቷል፡፡ ምንአልባትም እነዚያ ክፍት የሥራ ቦታዎች የተጠየቀውን ያህል የሥራ ልምድ የማይጠይቁ ናቸው፡፡ ስለሆነም ከመንግሥትም ሆነ ከግል ተቋማት የሚወጡ የአዲስ ተመራቂዎችን ሁኔታ ያገናዘበ የቅጥር ሁኔታ ሊኖር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ቀደም ሲል ከመንግሥት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ሥራ የሚመደቡበት ሁኔታ እንደነበር በማስታወስ አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ መቀየሩን፣ ተመራቂ ተማሪዎችም ይህንን ለውጥ በመረዳት የራሳቸውን አቅጣጫ መያዝ እንደሚኖርባቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ አሳስበዋል፡፡ ምን ያህል የተማረ ወጣት ሥራ እንዳጣ ለማወቅ በተለይም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የወጡ ተማሪዎችን የሥራ አጥነት ችግር ለመዳሰስ በቂ ጥናት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ መንግሥት ተመራቂዎችን ሥራ ይመድብ በነበረበት ወቅት የነበረው የሥራ ቅጥር አመለካከት ዛሬ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የማይሄድ በመሆኑ ይህ አስተሳሰብ ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህም ወጣት ተመራቂዎች በራሳቸው ራዕይ በአዲስ መንገድ ለመሄድ እንዲሞክሩ መክረዋል፡፡ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እየተደረገ ያለው የቢፒአር ጥናት በአገሪቱ ያለውን የተማረ የሰው ኃይል የሥራ አጥነት ችግርን ሙሉ በሙሉ ይቀርፈዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩን ጠቁመው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ አዲስ ተመራቂዎች ለሚገጥማቸው የሥራ አጥነት ችግር መረጃ አለማግኘት እንደ ምክንያት ሊጠቀስ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ ተመራቂዎች ሥነ ምግባር ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው በተመራቂ ተማሪዎች የሥራ አጥነት ዙሪያ ተመራቂ ተማሪዎች፣ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተደርጐ በዚህ ዙሪያ ያሉት ችግሮች በግልፅ ተለይተው እንዲወጡና የመፍትሔ ሀሳቦችን ማስቀመጥ እንዲቻል መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ኘሬዚዳንት ወጣት ታጠቅ ካሳ አስታውቋል፡፡ “ወጣቶቹ ባዘጋጁት አነስተኛ ፅሁፍ ከቅጥር ጋር በተያያዘ የገጠሟቸውን ችግሮች አቅርበዋል፡፡ ይህን ፅሁፍ እንደመነሻ አድርገን መወያየታችን ወጣት ተመራቂዎቹ ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑና ከሚመለከታቸው አካላት የሚቀርብላቸውን አማራጭ እንዲገነዘቡ፣ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲረዱ ያስችላል” ብሏል፡፡ የወጣቶች ሥራ አጥነትን በማስመልከት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ወጣቶችን በማደራጀትና የተለያዩ የሥራ ፈጠራ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና ፣የተማረ የሰው ኃይል የሥራ አጥነት ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው፣ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዲኘሎማና በዲግሪ የተመረቁ ወጣቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጿል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት አብዛኞቹ ወጣቶች የከፍተኛ ተቋም ተማሪ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አባል የነበሩ ናቸው፡፡ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አዘጋጅነት በወጣቱ ችግር ዙሪያ በርካታ ውይይት መደረጋቸውን በመጠቆም ተግባራዊ ነገሮቹ ምን እንደሚመስሉ ወጣት ታጠቅን ጠየቅነው፡፡ “በተወሰነ መልኩ ወደ ተግባር የተቀየሩ ነገሮች አሉ፡፡ በየቀበሌ ፅህፈት ቤቶች ወጣቶች ተደራጅተው የሚፈልጉትን ሥራ መስራት እንዲችሉ በጥቃቅንና አነስተኛ የብድር ተቋማት በኩል ብድር ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ በእርግጥ ከተዘጋጀው ገንዘብ በወጣቶች የተወሰደው አነስተኛ ብድር ነው” በማለት መልሷል፡፡ ባሉት ችግሮች ዙሪያ ውይይቶች መደረጋቸው ወጣቶችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ወደ መፍትሄ ለመሄድ እንደሚረዳ አመልክቷል፡፡ በምህረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |