| አደጋ መከላከል የትራንስፖርት ድርጅቶች... |
|
|
| Sunday, 09 March 2008 | |
|
አደጋ መከላከል የትራንስፖርት ድርጅቶች አመራረጥ ሥርዓቱ ለሙስና የተጋለጠ ነው
የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ ዕርዳታ ለማጓጓዝ በሚያወጣው ጨረታ ከአምስት ድርጅቶች በታች እንደሚያሳትፍ የጨረታ ኮሚቴ አባላት ከሕግና ሥርዓት ውጪ እንደ ቋሚ የሥራ መደብ ማስቀመጡ፣ አዳዲስ የትራንስፖርት ድርጅቶችን የሚያሳትፍ አሠራር አለመዘርጋቱን በመጥቀስ ይኸንኑ ለሙስናና ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ሥርዓቱን እንዲፈትሽና እንዲያስተካክል የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባካሄደው ጥናት ጠቆመ፡፡ ከሚሽኑ በኤጀንሲው የዕርዳታ እህል አጓጓዥ ድርጅቶች አመራረጥ ሥርዓት ላይ በቅርቡ ባካሄደው የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ ጥናት ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው በኤጀንሲው የበላይ ኃላፊ ሳይፀድቅ የመንግሥትን የጨረታ ሕግና መመሪያ ሳይከተል "ሥራው አስቸኳይ ነው" በሚል ብቻ ከአጓጓዥ ድርጅቶች ጋር ጊዜያዊ ውል ይፈፅማል፡፡ አሸናፊው ድርጅት ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ቋሚ ውልና ክፍያ እንዲሰራ ሲጠየቅ ከፍተኛ (ጉቦ) ጥያቄ ይቀርባል፡፡ በመንግሥት ግዢ መመሪያ መሠረት የጨረታ ኮሚቴ አባላት የሥራ ዘመን ሁለት ዓመት መሆን እንዳለበት ቢደነግግም የኤጀንሲው ሦስት የጨረታ ኮሚቴ አባላት ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ እንደ ቋሚ የሥራ መደብ እንዲሠሩ መደረጉ በጨረታ አፈፃፀም ወቅት አላስፈላጊ ግንኙነቶች እንዲፈጠሩ መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ አሰራሩንም ህገወጥ ብሎታል፡፡ በተጨማሪም በኤጀንሲው የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች ዝርዝር ወይም ዳታ ቤዝ የሌለው መሆኑ ብቃት ያላቸውን የዕርዳታ እህል አጓጓዥ ድርጅቶች በተገቢው መንገድ በመምረጥ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዳይገኝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ጠቁሟል፡፡ ኤጀንሲው የውስን ጨረታ ተብሎ ከመንግሥት ግዢ መመሪያ አንቀጽ 11 ቢያንስ አምስት አቅራቢ ድርጅቶችን መጋበዝ የሚለውን ድንጋጌ በመጣስ ከአምስት በታች አጓጓዥ ድርጅቶችን መጋበዝ ግዢ መፈፀምና በተደጋጋሚ የተለመዱ ድርጅቶችን ብቻ አሸናፊ አድርጎ መምረጡ አዲሶቹን አጓጓዥ ድርጅቶች የማያሳትፍ አሠራር እንዲከተል ምክንያት መሆኑ በጥናቱ ጠቁሟል፡፡ በሌላም በኩል ኤጀንሲው ለረዥም ጊዜ ለተረጂዎች እህል ሲያመላልሱ የነበሩና እህል በመስረቅ፣ በማሰረቅና በአግባቡ ለተረጂው ባለማድረስ በወንጀል የተጠየቁ የትራንስፖርት ድርጅቶችን ከጨረታው እንዲገለሉ አያደርግም ሲል በተደጋጋሚ ክስ የተመሰረተበትን የትራንስፖርት ድርጅት ስም በመጥቀስ አሰራሩን ወቅሷል፡፡ የፌዴራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማን፣ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሲሞን መቻሌና አግባብ ያላቸው የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የካቲት 13 ቀን 2000 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ኤጀንሲው የመንግሥትን የግዢ መመሪያ ከመከተል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ታምኖበታል፡፡ ኮሚሽኑ በጥናቱ ለጠቀሳቸው ችግሮች ባሰፈረው መፍትሄም ኤጀንሲው በዋንኛነት የመንግሥት ግዢ ሕግና መመሪያ አክብሮ እንዲሠራ መክሯል፡፡ በተጨማሪም ኤጀንሲው የዕርዳታውን ዓይነት መደበኛ እና አስቸኳይ በሚል በመለየት ለመደበኛ ዕርዳታ አጓጓዥ ድርጅቶች የግልፅ ጨረታ ዘዴ የተከተለ ግዢ መፈፀም እና ለአስቸኳይ ዕርዳታ ደግሞ አስቸኳይ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመመዘኛ መስፈርት በማስቀመጥ እንዲተገብር አሳስቧል፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |