| ብሔራዊ ባንክ ለሽያጭ የቀረበ ወርቅ... |
|
|
| Sunday, 09 March 2008 | |
|
ብሔራዊ ባንክ ለሽያጭ የቀረበ ወርቅ ሳይሸጥ ተመለሰ
- ወርቅ በፍተሻ እየተገኘ ነው - የዋው ፋሽን ሱቆች ታሸጉ ለብሔራዊ ባንክ ለሽያጭ የቀረበ ወርቅ ከተመረመረ በኋላ ማህተም ለማድረግ በተፈጠረ አለመግባባት ሊታሸግ ባለመቻሉ ባለቤቱ ወርቁን ሳይሸጡ ወደ ቤታቸው ይዘው መመለሳቸው ተሰማ፡፡ በአራት ግለሰቦች የተመመዘበረ ወርቅ በምርመራ ይፋ ሆነ፡፡ በወርቅ ማጭበርበር ዙሪያ የሚደረገው ምርመራ እየሰፋ መምጣቱና ንፁህ ወርቅ በግለሰቦች ቤት እየተገኘ መሆኑ ታወቀ፡፡ የብሔራዊ ባንክ ምንጮች እንዳስታወቁት የካቲት 27 ቀን 2000 ዓ.ም ብሔራዊ ባንክ የቀረበው የነጋዴ ወርቅ ሳይሸጥ የቀረው የጂኦሎጃኮል ሰርቬይ ማህተም ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው፡፡ ከአስራ አምስት ቀናት በፊት የጂኦሎጂካል ላቦራቶሪን የወርቅ መመርመሪያ መሳሪያ የተረከበውና ወደ ራሱ ህንፃ የወሰደው ብሔራዊ ባንክ የነጋዴው ወርቅ እንደቀረበ ከላቦራቶሪው ሁለት ኬሚስቶች ምርመራ እንዲያካሂዱ ጠርቷቸው ነበር፡፡ ኬሚስቶቹ ለሽያጭ የቀረበውን ወርቅ ከመረመሩ በኋላ ትክክለኛነቱን አረጋግጠዋል፡፡ ወርቁ ትክክለኛነቱ ከታወቀ በኋላ ታሽጐ ማህተም ይደረግበት ሲባል አለመግባባቱ እንደተፈጠረ ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡ "ብሔራዊ ባንክ ህንፃ ውስጥ ለተመረመረ ወርቅ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ላቦራቶሪ እንዴት ማህተም ያደርጋል?" በማለት የባንኩ ኃላፊዎች ላቦራቶሪው ማህተም እንዲያደርግ ያቀረበውን ጥያቄ እንዳልተቀበሉት የገለፁት የዜናው ታማኝ ምንጮች በዚሁ "በማህተም አድርግ፣ አላደርግም" ክርክር ሳቢያ ወርቁ ሳይታሸግ ቀርቶ ባለቤቱ ይዘውት ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡ ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉ ሁለት ወንድማማቾች መኖሪያ ቤት በተካሄደ ፍተሻ የተደበቀ ንፁህ ወርቅ መገኘቱ ታውቋል፡፡ ሙዳሲር መሐመድ የተባሉ የሶፋም ኢንተርፕራይዝ ባለንብረት መኖሪያ ቤት የካቲት 1ዐ ቀን 2000 ዓ.ም 70 ኪሎ ግራም ከ445 ግራም 22 ካራት ወርቅ ሲገኝ፣ ወንድማቸው ሱልጣን መሀመድ መኖሪያ ቤት 8 ኪ.ግ ከ433 ግራም 21 ካራት ወርቅ የካቲት 12 ቀን 2000 ዓ.ም እንደተገኘ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ክፍሎች የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ለአቶ ሙደሲር መሐመድ፣ ለአቶ ሱልጣን መሐመድና አቶ መሐመድ አወል ላቀረቡት ወርቅ የጂኦሎጂካል ጥናት ዋና ላቦራቶሪ የሰጠውን ሰርተፊኬት በተመለከተ ማብራሪያ መጠየቁን አንድ መረጃ አመልክቷል፡፡ ላቦራቶሪው በተጠየቀው ማብራሪያ መሠረት 1. በክብደት (ግራም) በካራትና በፐርሰንት አንድ ዓይነት የሆኑ የወርቅ ጥፍጥፎችን በሚመለከት፡- ሀ/ በሙደሲር መሐመድ ስም በፋይል ቁጥር 0621/08ሓሞማ ላቦራቶሪ ቁጥራቸው 0622፣ 0623፣ 0635፣ 0638፣ እና በመሐመድ አወል ስም ፋይል ቁጥር 9347/08ሓሞማ፣ 9347/07 9561/2007 የላቦራቶሪ ቁጥር 6335፣ 9183፣ 9369፣ 9569 የሆኑ የወርቅ ጥፍጥፎች ላይ በተደረገው ንጽጽር በተለያዩ ጊዜያት ከመምጣታቸው ውጭ እና ላቦራቶሪው ሊቀበለው በሚችል የድጋሚ ምዘና የክብደት ልዩነት (0.1 ግርማ) የተለያዩ ጥፍጥፎች ለመሆናቸው ለማመን በጣም ይከብዳል፡፡ ለ/ በሱልጣን መሐመድ ስም ከተመዘገቡት ውስጥ ፋይል ቁጥር 0994/08ሓሞማ ላቦራቶሪው ቁጥር 0997 ከዚህ በፊት ለመሐመድ አወል ከተሰጠው ሰርተፊኬት ፋይል ቁጥር 9561/07ሓሞማ ላቦራቶሪ ቁጥር 9571 አንድ ናሙና መሆናቸውን ማየት ይቻላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ፌዴራል ፖሊስ እንዲመለሱለት የጠየቃቸው ጥያቄዎች ከዚህ በፊት የካቲት 11 ቀን 2000 ዓ.ም ከተሰጠው ሙያዊ ማብራሪያ የተለየ እንዳልሆነ ጠቅሶ መረጃው እንደሚከተለው አቅርቦታል፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መመሪያ ጥር 13 ቀን 2000 ዓ.ም በቁጥር ወ/ም/መ/ኢኮ 6447/2000 በብሔራዊ ባንክ በወርቅ ግዥ ስም የተፈፀመውን ወንጀል በሚመለከት መ/ቤቱን ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጠው በጠየቀው መሠረትና መ/ቤቱም ማብራሪያውን እንድሰጥ ባዘዘኝ መሠረት አስተያዬቴን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ ጥር 27 ቀን 2000 ዓ.ም በጽሁፍ የሰጠሁት ሙያዊ አስተያየት ለሁለቱ ግለሰቦች ማለትም ለአቶ መሐመድ አወል እና ለአቶ ሙደሲር መሐመድ (ሶፋም) ላቦራቶሪው የሰጣቸው የወርቅ ጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ባልደረሰኝ ሁኔታ ስለነበር ከዚህ በፊት የሰጠሁት በዚህ እንዲተካ ስጠይቅ በትህትና ነው፡፡ 1. በክብደት፣ በካራትና በፐርሰንት አንድ ዓይነት የሆኑ የወርቅ ጥፍጥፎችን (Gold Bars) በሚመለከት ፌዴራል ፖሊስ ከላይ በርዕሱ የተገለጹትን የወርቅ መገለጫዎች ጥርጣሬ በሚመለከት የጂኦሎጂ ጥናት ዋና ላቦራቶሪ ለብሔራዊ ባንክ የላከውን የውጤት ማረጋገጫ (በአቶ መሐመድ አወል ስም 6 ገጽ እና በአቶ ሙደሲር መሐመድ ስም 13 ገጽ ለማየት ተሞክሯል፡፡ የሚዘጋጀው የወርቅ ጥፍጥፍ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ታግዞ ንፁህ ወርቁን ከሌሎች ወርቅ ካልሆኑ (impurities) ነገር ግን ከወርቅ ጋር አብረው የሚገኙ እንደ ብር (Ag) እና መዳብ (Cu) ያሉ ባልተለያዩበትና ትክክለኛ ይዘታቸው ባልተለካበት (በማይታወቅበት) ሁኔታ ሲሆን ለግለሰቦቹ የተሰጡ ሰርቲፊኬቶች በተናጠል ብናይ ይህንኑ እውነታ ይገልፃሉ፡፡ በእያንዳንዳቸው የተሰጡት ሰርቲፊኬቶች የወርቅ ጥፍጥፎች ክብደት ከመጠጋጋት ባሻገር አንድ ዓይነት ክብደቱ (similar weight) ያላቸው የወርቅ ጥፍጥፎች የሉም፡፡ ይህም የሚያመለክተን አንድ ዓይነት የወርቅ ጥፍጥፎች ማዘጋጀት እንደማይቻል ሲሆን በሌላ በተሰጠ ሰርቲፊኬት ወይም ለአንዱ ግለሰብ የተሰጠ ተመሳሳይ የወርቅ ጥፍጥፎች በሌላው ላይ ለማየት የቻልነው ጥፍጥፎቹ እየተዘዋወሩ (በተደጋጋሚ) ወደ ላቦራቶሪ ከመምጣታቸው ውጭ ሌላ ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ ሁለት የወርቅ ቁርጥራጮች በክብደት ተለያዩም አንድ ዓይነት ክብደት ኖሯቸውም አንድ ዓይነት ጥራት ሊኖራቸው የሚችለው በመጀመሪያ ወርቁ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከሌሎች ወርቅ ካልሆኑ (impurities) ተለይቶ የወርቅ ጥራቱ 24 ካራት መሆኑ ከተረጋገጠ ብቻ ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀ ወርቅ 5 ግራም ወስደን 20 ግራም የወርቁ ጥራት ያው 24 ካራት ነው፡፡ እኛ አሁን እያየነው ያለነው የወርቅ ጥፍጥፎች ግን ወርቅ ያልሆኑ ነገሮች (impurities) ጋር ውሁድ (alloy) ሆነው የሚገኙትን ስለሆነ ተመሳሳይ ክብደት ስላላቸው የግድ በጥራት አንድ ይሆናሉ ወይም ክብደታቸው ከተለያዩ ጥራታቸውም ሊለያይ ይችላል (የግድ ይላል) ማለት አንችልም፡፡ 2. በክብደት አንድ ሆነው መጠነኛ የሆነ የካራት ወይም የፐርሰንት ልዩነት መኖርን በሚመለከት፣ በላቦራቶሪ ውስጥ በጥፍጥፎች ምዘና ከተካሄደ በኋላ የወርቁን ጥራት በካራት ወይም በፐርሰንት ለመግለጽ የተለያዩ የሂሳብ ስሌቶች ይካሄዳሉ፡፡ በዚህም ወቅት ቁጥሮችን የማጠጋጋት (Round-off) ወይም እንዳሉ መጠቀም ሊኖር ይችላል፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ጥርጣሬ ያሳደሩበትን ሰርቲፊኬቶች ብንመለከት ተመሳሳይ ክብደት ኖሯቸው ልንቀበለው የምንችል የካራት ልዩነት የመጣው ከላይ በገለጽኩት ምክንያትና አንድ መሆን የግድም ስለማይሆን ነው፡፡ 3. በክብደት ልዩነት ኖሮ በካራት እና በፐርሰንት አንድ መሆንን በሚመለከት - ከላይ በተራ ቁጥር 1 እና 2 በተጠቀሱት ምክንያቶች ሁለት የወርቅ ጥፍጥፎች ሀ/ በክብደት ተለያይተው አንድ ዓይነት የወርቅ ጥራት ሊኖራቸውም ወይም ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ለ/ በክብደት ተቀራርበው አንድ ዓይነት የወርቅ ጥራት ሊኖራቸው ወይም ላይኖራቸው ይችላል፡፡ እያንዳንዱ የወርቅ ጥፍጥፍ የራሱ የግል ፀባያትን እንጂ ከሌላው ጋር ማወዳደር ተገቢ አይሆንም፡፡ በአጠቃላይ በመሐመድ አወልና በሙደሲር መሐመድ (Sofam enterprise) በተደረገው ንጽጽር የወርቅ ናሙናዎቹ ተመላልሰው ላቦራቶሪ የገቡ መሆኑን ከዳታው መረዳት እንደምንችል እገልፃለሁ፡፡ በተመሳሳይ ዜና ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የዋው ፋሽን ምርቶች መሸጫ ሱቆች ታሸጉ፡፡ የድርጅቱ ባለቤት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ሰነባብተዋል፡፡ በፌዴራል ስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ጠያቂነት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት የዋው ፋሽን ሱቆች እንዲታሸጉ ያለፈው ሐሙስ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን ባገኘነው መረጃ መሠረት የሱቆቹ መዘጋት ከወርቅ ዝርፊያው ጋር ለሚደረገው ምርመራ አጋዥ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከዋው ፋሽን ሱቆች መካከል አንዳንዶቹ ከንግድ ፈቃድ ጋር በተያያዘ የተዘጉ መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የዋው ኢንተርፕራይዝ ኃ/የተ/የግ/ማ የሥራ አመራር አባላት ገልጸዋል፡፡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተዘጉት የድርጅቱ ሱቆች ብቻ ሲሆኑ የዋው ኢንተርፕራይዝ ፋብሪካ የተለመደ ስራውን እያከናወነ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ከዚሁ ከወርቅ ማጨበርበር ጋር በተያያዘ የመኪና መለዋወጫ ቤቶችም መታሸጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሰግድ ተፈራ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |