Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow የኢኮኖሚ ጭንቅላት ናቸውና...
የኢኮኖሚ ጭንቅላት ናቸውና... Print E-mail
Sunday, 09 March 2008
Imageየኢኮኖሚ ጭንቅላት ናቸውና ልዩ ትኩረት ለፋይናንስ ተቋማት!

የተዛባና የተነካ ጭንቅላት ያለው ሰው አይ ቁመት፣ አይ መልክ፣ አይ ጥርስ፣ አይ ጠጉር፣ አይ እግር፣ አይ ዳሌ እያሉ ቢያደንቁት ትርጉም የለውም፡፡ እንደ ስሙ ሊያንቀሳቅሰውና ሊያኖረው የሚያስችለው ወሳኙ የሆነው ጭንቅላቱ ተዛብቷልና፡፡
 
ኢኮኖሚም እንደዚያ ነው፡፡ የኢኮኖሚው ጭንቅላት የሆኑት የፋይናንስ ድርጅቶችና ተቋሞች ከቀወሱ ልማትም፣ እድገትም፣ መሠረተ ልማትም፣ ንግድም፣ ኮንስትራክሽንም፣ አገልግሎቱም ይበላሻሉ፡፡ እነዚህ ከተበላሹ ደግሞ አይ የአየር ጠባይ፣ አይ ተራራ፣ አይ ሸንተረር፣ አይ ዘፈን፣ አይ መዝሙር፣ አይ ባህል፣ አይ ታሪክ". እያልን ብናደንቅና ብናወድስ ትርጉም የለውም፡፡ አጉል ማስተዛዘኛ ነው የሚሆነው፡፡

የፋይናንስ ድርጅቶች ስንል ብሔራዊ ባንክ፣ ሌሎች ባንኮችና ኢንሹራንሶች ማለታችን ነው፡፡ የመንግሥትም ይሁኑ የግል የፋይናንስ ተቋሞች በጋራ የኢኮኖሚው ጭንቅላት ናቸው፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል ገንዘብና ንብረት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ኢምፖርትና ኤክስፖርት፣ ኮንስትራክሽንና መሠረተ ልማት የሚንቀሳቀሰው በእነዚህ ተቋማት ዙሪያ ነው፡፡ እነሱ ከቀወሱና ከተናጉ ጠቅላላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ይናጋል፣ ይቃወሳል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ያሉት የፋይናንስ ድርጅቶች፡- እጅግ ከፍተኛ ትኩረት፣ ዳግም መደራጀት፣ አዲስ አወቃቀር አዲስ ፖሊሲ፣ አዲስ ራዕይና እምነት ያለው የሰው ኃይል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህን እውን ለማድረግ መንግሥት ቆራጥና አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ እርምጃውን ለመውሰድ የሚያስችለው በቂ መረጃም በእጁ ይገኛል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ብቃት ያለው አመራር እንደሌለው ገሃድ ወጥቷል፡፡ የአገር ሃብትና መጠባበቂያ የሆነው ወርቅ መሣቂያና መቀለጃ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ተባባሪ ሆኗል ወይም ተጭበርብሯል፡፡ በሁለቱም በኩል ሲታይ ብቃት የሌለው ለመሆኑ በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡ ልማት ባንክ ከሰረ ብሎ ብሔራዊ ባንክ ያቀረበው ሪፖርትም የልማት ባንኩን ደካማነት ብቻ የሚያሳይ ሳይሆን የብሔራዊ ባንክንም ደካማነት ያረጋግጣል፡፡ ምክንያቱም ይህ ኪሳራ የአንድ ዓመት ሳይሆን ቢያንስ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲከማች የመጣ ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ በጊዜው ለምን አልገለፀም? አልተቆጣጠረም? የሚያሰኝ ነው፡፡

ለአበባ የተሰጠው ብድር ከስድስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ሆኖ የተገኘው ገቢ ግን ሰባ ሚሊዮን ብር ብቻ በነበረበት ወቅትም ብሔራዊ ባንኩ እንኳን ሊቆጣጠርና መፍትሔ ሊሰጥ "እንዴት ነው ነገሩ?" የሚል መገረምም አላሳየም፡፡ ሥራ ላይ ሊውል የሚችል ብር ሲቃጠል የሚታይበት ብሔራዊ ባንክ ብሔራዊ ባንክ ሊባል አይገባውም፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዢና ምክትል ገዢ ብቻ ሳይሆኑ ብሔራዊ ባንኩን የሚቆጣጠረው ባለሥልጣንም የሚጠየቅበት ጉዳይ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የራሱን ሥራ  ማካሄድ አቅቶት የበላይ አካል ሥራውን እንዲሠራለት ሲጠብቅና ሲማጠን የበላይ አካልም የባንኩን ችግር አይቶ ከመፍታት ይልቅ የባንኩን ሥራ "በአደራነት" እያካሄደ መቆየቱ ያስጠይቀዋል እንጂ አያስመሰግነውም፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኤጄንሲ ኃላፊ አጥቶ ለሦስት ዓመታት ተዘግቶ መክረሙም ተገቢ አልነበረም፡፡ ብዙ መሥራትና ማስተካከል ይችል የነበረ አካል ኃላፊ አጥቶ ሥራ ፈት ሆኖ መቆየቱ ሌላው የፋይናንስ ድርጅቶች ትኩረት የሚያስፈልጋቸው መሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኤጄንሲው እያደረገው ያለው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ቀደም ብሎ ቢጀምር ኖሮ ብዙ ችግር ማስወገድ በተቻለ ነበር፡፡

የልማት ባንክ ችግር ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ችግር ነው፡፡ ኃላፊዎች ተብለው የተቀመጡ ሰዎች በሚያበድሩት ድርጅት ቦርድ አባላት ሆነው ሲሰሩና ያበደሩት ድርጅት ሊሸጡና ሊለውጡ እንደሚችሉ ውክልና እንዲሰጣቸው ሲጠየቁ እየተስተዋለና እየተነገረ፣ በመገናኛ ብዙሃን እየተላለፈ እያለ ሥራ ጠፍቶ አሁን ልማት ባንክ ችግር ውስጥ ገብቶ ቢገኝ የሚገረም ሰው ካለ ራሱ የሚያስገርም ሰው ነው፡፡ አምስት ቢልዮን ብር አበድሮ ከአምስቱ አራቱ ቢልዮን መሰብሰብ አቅቶት ቢገኝ ችግር ለመኖሩ የሚሰጠው ተጨማሪ መረጃ አይኖርም፡፡ የታወቀ ነውና፡፡ ስለአሟሟቱ የሬሳ ምርመራ ዘዴው እውቀት ይሰጥ እንደሆነ እንጂ፡፡

የባንኮችና ኢንሹራንሶች ፖሊሲ ምን ይመስላል? ኤንትሬና አሮጌ ቪላ አለህ እያሉ ዋስትና (ኮላትራል) ማፈላለግ የዘመናዊ ባንክ አሰራር ነው ወይ? ባንኮች በሃራጅ በሚሸጡት ንብረት ላይ ነው ማተኮር ያለባቸው ወይስ ቢዝነሱ የተሳካ ሆኖ በሚከፈለው ወለድና ብድር? ባንኮች በሚሸጥ ንብረት ላይ እያተኮሩ የሚያበድሩ መሆናቸው ራሱ አሳዛኝ ነው፡፡

በሚሸጠው ንብረት ላይ ያለው ፖሊሲ ምን ይመስላል? መኪኖች (ትናንሽ የቤትና የቢሮ እንዲሁም የጭነት መኪኖች) በባንኮችና በኢንሹራንሶች ተወርሰው ከአዲስ አበባ እስከ አቃቂ ባለው ዋና መንገድ ዳር ተጥለው ዝገው፣ ሣር በቅሎባቸው ይታያሉ፡፡ የፎርክሎዣር ሕግ ውጤቱ ይህ ነው ወይ? ንብረት ወርሶ መጣል፤ ንብረቱም ለኪሳራ፣ ገንዘቡም ለኪሳራ ማድረግ መዳረግ? ከመውረስና ከመጣል ይልቅ ጤናማ ገንዘብ ሰጥቶ በሽተኛውን ገንዘብ ማዳን አይሻልም?

የግል ባንኮች የሚመረቱት አትራፊ ሆነው መስራቾች ከትርፉ እንዲጠቀሙ ሳይሆን ለመበደር እንዲመቻቸው ብለው በመስራቾች ሲመሰረቱ ምን ይባላል? ከእድርና ከእቁብ ያነሰ አደረጃጀትና አመኔታ ያላቸው የግል ባንኮችስ ባንኮች ናቸው? ልማት ላይ ከማተኮር ይልቅ "ገልባጭ" መኪና መግዣ ለማበደር የሚቋቋሙ ባንኮችን ባንኮች እንበላቸው? ጥሩና በልማት ላይ የሚንቀሳቀሱ የሚባሉ ጥቂት የግል ባንኮች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን ለስርቆትና ለዝርፊያ እንዲመቻቹ የሚቋቋሙ ባንኮች አሉ፡፡ ይህም የፋይናንስ ድርጅቶችን ችግር የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ብዙ ለማለት የማስረጃ ችግር የለም፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በወርቅም፣ በባሌስትራም፣ በኪሳራውም፣ በትርፉም፣ በገንዘብ እጥረቱም፣ ባልተሰበሰበ ገንዘብ ብዛቱም አንፃር ሲታይ በፋይናንስ ድርጅቶች ዙሪያ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ሆኗል፡፡ አሳሳቢ ነው፡፡ በተለይም ከአሁኑ አሳፋሪ አካሄዳቸው አንፃር ሲታይ እነዚህን ባንኮች ይዞ ልማት አይታሰብም፡፡

ይህ ችግሩን በግልፅ ወደ አደባባይ እንዲወጣ ያመቻቸ ስለሆነ መንግሥት ይህ ሁኔታ ሳያመልጥ በአስቸኳይ እርምጃ ይውሰድ፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ደመወዝ ለመጨመር ኤጀንሲው የቦርድ አባላትም ማኔጅመንቱም እየተነጋገሩ ሠርተዋል፡፡ ይህ ከተቻለ፣ እየተነጋገሩ ብዙ ችግር መፍታት ይቻላል ማለት ነው፡፡ ይህ አካሄድ ተሳክቶ ብሔራዊ ባንክን የማስተካከል ሥራ ካልተሰካ ግን ታጥቦ ጭቃ ነው፡፡

ስለዚህ፣ መንግሥት ለፋይናንስ ድርጅቶች ጥንካሬና መሻሻል ልዩ ትኩረት ይስጥ፡፡ አሁኑኑ!!
 
< Prev   Next >