| ኦዴንጋ የስልጣን ክፍፍሉ... |
|
|
| Sunday, 09 March 2008 | |
|
ኦዴንጋ የስልጣን ክፍፍሉ እየተፋጠነ መሆኑን ገለፁ
የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ በተቃዋሚዎችና በመንግስት መካከል የተደረሰው የስልጣን ክፍፍል እየተፋጠነ መሆኑን ለቢቢሲ ገለፁ፡፡ ከሳምንት በፊት በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን አደራዳሪነት የተደረሰው የስልጣን ክፍፍል ስምምነት እየተፋጠነ መሆኑን ራይላ ኦዲንጋ አስታውቀዋል፡፡ በስምምነቱ መሠረት የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እንዲሆኑ ተወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ኃላፊነት ድርሻ ክፍፍል እየተደረገ ነው፡፡ የመንግሥት ባለስልጣናትና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሰሞኑን ባደረጉት ውይይት በአገሪቱ ህገመንግስት ላይ መጠነኛ ለውጥ የሚካሄድበትን ሁኔታ አመቻችተዋል፡፡ በኬንያ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ተከትሎ በተነሳው ግጭት ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከስድስት መቶ ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ የፈረንሳይ ወታደር ሱዳን ውስጥ ተገደለ በቻድ የአውሮፓ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል አባል የሆነ የፈረንሳይ ወታደር ሱዳን ውስጥ መገደሉን የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ አመለከተ፡፡ በወታደሩ ግድያ የሱዳን መንግሥት ይቅርታ ጠይቋል፡፡ የሱዳን ወታደራዊ ባለስልጣናት ወታደሩ ሊገደል የቻለው የሱዳንን ድንበር በመሻገሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሱዳን የጦር ኃይል ቃል አቀባይ ጄነራል ኦስማን ሙሀመድ አልጋባሽ “የወታደሩ ግድያ የሚያሳዝን ነው ነገር ግን የወታደሩ በድን አካል የተገኘው የሱዳን ግዛት ውስጥ ነው፤” በማለት ወታደሩ ያለፈቃድ ድንበር መሻገሩን አስታውቀዋል፡፡ በዛምቢያ የቻይና የማዕድን ማምረቻ ድርጅት ላይ ጉዳት ደረሰ በዛምቢያ የቻይና የማዕድን ማምረቻ ድርጅት ሰራተኞች ባነሱት አመጽ በድርጅቱና በቻይናዊ የድርጅቱ ባለቤት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡ የአመፁ ተሳታፊ ከሆኑት ሠራተኞች ውስጥ ከአምስት መቶ በላይ ሠራተኞች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በግጭቱ የድርጅቱ የማምረቻ መሣሪያ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ በአመጹ ቻይናዊ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ባደረሰባቸው ጉዳት ሆስፒታል መግባታቸው ታውቋል፡፡ ያለፈው አመት በተመሳሳይ መልኩ በተነሳ አመጽ ከሃምሳ በላይ ሠራተኞች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ በዛምቢያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የአገሪቱ መንግሥት ለውጭ ድርጅቶች ከገደብ ያለፈ ነፃነት በመስጠት የአገሪቱ ሀብት እየተመዘበረ ነው ሲሉ ወንጅለዋል፡፡ ኢራን የአውሮፓ ኅብረት የኒውክሊየር ውይይትን ተቃወመች የኢራን ፕሬዚዳንት መሀመድ አህመዲነጃድ የአውሮፓ ኅብረት ያቀረበውን የኒውክሊየር ውይይት መቃወማቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ፡፡ አህመዲነጃጅ “ኢራን የኒውክሊየር ውይይት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር አታደርግም” ሲሉ አሳውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የኒውክሊየር ጉዳይን በተመለከተ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክሊየር ጉዳይ ጽ/ቤት ጋር ብቻ እንደሚወያዩ ገልፀዋል፡፡ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ጀርመን በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢራን የኒውክሊየር ቀውስ በአካባቢው መፍጠሯን አሳውቀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |