| "ቅንጅት ዱሮም እንደ ድሪቶ የተሰፋ... |
|
|
| Sunday, 09 March 2008 | |
|
"ቅንጅት ዱሮም እንደ ድሪቶ የተሰፋ ነው እንጂ የተደራጀ አልነበረም"
አቶ በድሩ አደም አቶ በድሩ አደምን በቀድሞው ቅንጅትና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሰለሞን ጐሹ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በግለሰብ ፖለቲከኛና በፓርቲ ፖለቲካ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? አቶ በድሩ፡- ጥፋት ሲፈፀም ሁልጊዜ ከማልቀስ በጋራ የሕዝብ እንባ ላብስ በማለት ወደ ፓርቲ ፖለቲካ ገብቻለሁ፡፡ በወቅቱ በኢህአዴግ የግል ተወዳዳሪዎችን ሞራል የሚነካ ሕግ ወጥቶ ነበር፡፡ ለፓርቲ አባላት በምርጫ ለመወዳደር 500 ድጋፍ ድምፅ ያስፈልግ ነበር፡፡ እሱ ቀርቶ ወደ ምንም አያስፈልገውም ሲቀየር ለግል ተወዳዳሪ ግን የነበረው 1"000 ድጋፍ ድምፅ አልተቀየረም፡፡ ወደ ፓርቲ ከገባሁ በኋላ በአጭር ጊዜ ነው ትክክለኛ ቦታ እንዳልገባሁ የተረዳሁት፡፡ በወቅቱ ጉድለቱን ለመናገር ምርጫ ደርሶ ስለነበር ተፅእኖ ነበረብኝ፡፡ ከፓርቲው አባላት ጋር በፓርቲውና በአመራሩ ጉድለት ዙሪያ ብዙ ተከራክሬያለሁ፡፡ የግለሰቦች የሥልጣን ጥመኝነት ነበር፡፡ የጋራ አመራር በወረቀት ላይ እንጂ በተግባር አልነበረም፡፡ በጋራ መደራጀቱ ለሀገርም ለሕዝብም ለእኛም ጠቃሚ ቢሆንም ተመሳሳይ አላማ እውነተኛ ሕዝባዊ ፍቅርና ስሜት ያላቸው በቂ ሰዎች በቅንጅት ስላልታቀፉ ፓርቲው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ሪፖርተር፡- የእናንተ እናት ፓርቲ ቀስተ ደመና የመኢአድና የኢዴአፓ መድኀን ፓርቲዎችን ለማስታረቅ ብሎ የቀድሞውን ቅንጅትን በበላይነት ተቆጣጥሯል ተብሎ ይተቻል፤ አቶ በድሩ፡- መኢአድንና ኢደአፓ መድህንን ለማስታረቅ ብዙ ጥረት አድርጓል፡፡ አልተሳካም፡፡ የቀስተ ደመና መሪዎች የአስታራቂነት ሚና ሳይሆን የተጫወቱት አቋማቸውን መጫን ነበር፡፡ ይሄን ደግሞ ሀገሪቷ ላይም ደግመውታል፡፡ የአምባገነንነትና የገዢነት ስሜት ይንፀባረቅበት ነበር፡፡ ለዚህ በር የከፈተለት የመኢአድና የኢዴአፓ መድኀን እርስ በርስ አለመጣጣምና አለመስማማት ነው፡፡ የተወከለበት ቦታ ብቻ ሳይሆን ያልተወከለበትንም በበላይነት ይቆጣጠር ነበር፡፡ በሁሉም አይነት እንቅስቃሴዎች ሌሎቹን ፓርቲዎች ያገል ነበር፡፡ ሪፖርተር፡- ከግለሰቦች የሥልጣን ፍላጎትና ሽኩቻ ባሻገር የቀድሞውን ቅንጅት የመሰረቱት አራት ፓርቲዎች ርዕዮተ አለማዊ ልዩነት ነበራቸው? አቶ በድሩ፡- ሊበራል ቡርዥዋ አመለካከት እናራምዳለን ብለን ነው የተነሳነው፡፡ እርግጥ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እኛ ሶሻል ዲሞክራቶች ነን ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ነገር ግን ከሥልጣን ጥመኝነት በዘለለ የርዕዮተ ዓለም ልዩነቱ ችግር አልነበረም፡፡ ሪፖርተር፡- መኢአድና ኢዴአፓ መድኀን ሕብረብሔራዊ ፓርቲዎች ከመሆናቸው በፊት አማራ ተኮር ፓርቲዎች ነበሩ፡፡ የቀድሞው ቅንጅት በርካታ አባላትም አማራዎች ናቸው፡፡ የዶ/ር ብርሃኑ እና የኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ልዩነትንም ከብሔር ጋር የሚያያይዙት አሉ፤ አቶ በድሩ፡- ይህን ያየሁት ከታሰርኩ በኋላ ነው፡፡ የዘር ልዩነት በእርግጥም አለ፡፡ ዶ/ር ብርሃኑም ሆነ ኢንጅነር ኃይሉ የብሔራቸውን ሰዎች ይፈልጉ ነበር፡፡ የዘር ብቻም ሳይሆን የሀይማኖትም ልዩነት አለ፡፡ ይህን ከእስር በፊት አላየሁም፡፡ ሪፖርተር፡- የታሰሩት በግለሰብ ደረጃ ነው በፓርቲው ስም? አቶ በድሩ፡- የታሰርኩት በቅንጅት ስም ነው፡፡ ነገር ግን እኔ በቅንጅት ምክር ቤት አባልነት ተመርጬ እውነቱ እስኪወጣ ድረስ አልቀበልም ብዬ ተቀምጫለሁ፡፡ ተቃውሞዬን በፅሁፍ ባለማስቀመጤ መንግሥት ያሰረኝ በቅንጅት አባልነት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በቅንጅት ክስ ከዳንኤል በቀለና ከነፃነት ደምሴ ጋር በመሆን ይቅርታ አልጠየቁም፡፡ ለምን? አቶ በድሩ፡- እንደታሰርን እንከላከል አንከላከል በሚል ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ እኔ እከላከላለሁ አልኩ፡፡ ምክንያቱም ወደ ምርጫ ስገባ በዚህ ህገ መንግሥትና ባሉት ህጎች ወይም የፍትህ ስርዓት እዳኛለሁ ብዬ ነው የገባሁት፡፡ ከታሰርኩ በኋላ በፍትህ ስርዓቱ አላምንበትም በማለት አልዳኝም ማለት ራሴን መካድ ነው፡፡ የቀረበብኝን ፣ወያኔ ወደ በረሀ ይመለስ፣ የሚል ክስም አላልኩም፡፡ ተከራክሬ ከሰባት ክሶች ሁሉ ነፃ ሆኜ ነው የወጣሁት፡፡ "ኢሕአዴግ አንድ በፈጣሪ ሁለት በእናንተ ጡንቻ የዛሬ ሳምንት ወደ ነበረበት ይመለሳል" ነው ያልኩት፡፡ ዳኞቹም በእናንተ ጡንቻ የሚለው ስለሚያነሳሳ መብራራት ነበረበት አሉኝ፡፡ እርግጥ ሚያዚያ 3ዐ በአብዮት አደባባይ ያደረግኩት ንግግር ሕዝቡን ለግንቦት 7 ምርጫ ለማነሳሳት ነበር፡፡ የነበረው የሕዝብ ጡንቻ ካርድ ነበር፡፡ ከጥይትም ከዱላም የባሰ ገሎ የሚያነሳ የምርጫ ካርድ ነው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ 487 መሠረት የ6 ወር ቀላል እስራት ወይም 5ዐዐ ብር እንድታሰር ተፈረደብኝ፡፡ ነገር ግን ከዚያ በላይ በመታሰሬ በነፃ ተለቅቄአለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- የዶ/ር ብርሃኑና የኢንጅነር ኃይሉ ልዩነት የቅንጅት ዓለም አቀፍ አመራርና የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤትን በመመስረት የበለጠ የተባባሰበት ሁኔታ እንዳለ ተነግሯል፡፡ በእስር ቤት የነበረው ሁኔታ ምን መልክ ነበረው? አቶ በድሩ፡- እስር ቤት በነበርንበት ወቅት ብዙ ችግር ይፈጥር የነበረው ዶ/ር ብርሃኑ ነው እንጂ ኢንጅነር ኃይሉ አልነበሩም፡፡ ብርሃኑ ለቅንጅት ዓለም አቀፍ አመራር ስድስት እጩዎችን በቀጥታ ያስተላልፋል . . . ሪፖርተር፡- ኢንጅነር ኃይሉ በወቅቱ አልተሳተፉበትም? አቶ በድሩ፡- እንዲቋቋም ተስማምተዋል፡፡ ዝርዝሩ ላይ አልገቡም፡፡ እርግጥ ዶ/ር ብርሃኑ ነግሬው ተስማምተዋል ይላል፡፡ ኢንጅነሩ ግን አልሰማሁም ይላሉ፡፡ የተቋቋመው አመራር ከስድስት አባላት ውስጥ ሦስት ቀስተ ደመና ሁለት የመኢአድ ደጋፊ እና አንድ የኢዴአፓ መድኀን አባል ነው፡፡ ይህን ብዙዎቻችን ተቃውመናል፡፡ ከሦስቱም ድርጅቶች አራት አባላትን ያቀፈ (ኢዲሊ በውጭ ተወካይ አልነበረውም) የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ተቋቋመ፡፡ ሥራ ሲጀምሩ እርስ በርስ መጋጨትና መጠላለፍ ጀመሩ፡፡ አንዱ አንዱን ገንዘብ አጠፋህ በማለት መካሰስ ጀመሩ፡፡ የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ሲቋቋም ዶ/ር ብርሃኑ አይኑርበት እንጂ መነሻው ኢንጅነር ኃይሉ ብቻ አልነበሩም፡፡ መነሻ ሀሳቡን ያቀረቡት ሌሎች ናቸው፡፡ ሪፖርተር፡- የቅንጅት ዓለም አቀፍ አመራርና የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ልዩነት የዲያስፖራውን ድምፅ በመክፈል ቅንጅቱን አላዳከመም? በአሁኑ ወቅትስ የዲያስፖራው ሚና ምንድነው? አቶ በድሩ፡- የዲያስፖራው ለሁለት መከፈል ቅንጅትን አላዳከመውም፡፡ የቅንጅቱ ለሁለት መከፈል ግን የዲያስፖራውን ሚና ከፍሎታል፡፡ የችግሩ ምንጭ ከዚህ ነው፡፡ ገንዘብ ጠፍቷል ተብሎ ኘሮፖጋንዳ ተጀመረ፡፡ አንዱ አጠፋህ ይባላል፡፡ ነገር ግን መልስ አይሰጥም፡፡ ከእስር ሳንፈታ ወደዚያው ለመሄድ ወሰንን፡፡ ሐምሌ 2ዐ በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በተፃፈ ደብዳቤ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ደጋፊ የሆነው የቅንጅት ዓለም አቀፍ አመራር እና ኢንጅነር ኃይሉ ደጋፊ የነበረው የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት እንዲፈርሱ ተደርጎ በድጋፍ ሰጭነት እንዲቀጥሉ ተደረገ፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ አሜሪካ አቀናን፡፡ ሪፖርተር፡- ከኢንጅነር ጋር አብረው በመጓዝ የዶ/ር ብርሃኑን ቡድን ይቃወሙ ነበር፡፡ ምክንያትዎ ምን ነበር? አቶ በድሩ፡- እነሱ ሐምሌ 13 እኔ ሐምሌ 3ዐ ቀን 1999 ዓ.ም. ነው የወጣነው፡፡ ልጆቻቸው የተጎዱባቸውን ቤተሰቦች እየዞርኩ እፈልግ ነበር፡፡ ለሚሌኒየሙ እና ለረመዳን ወር በዓል የሆነ ነገር ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ ሲበዙብኝ ኢንጅነርን አማከርኳቸው፡፡ ተስማሙ፡፡ ለዚያ የሚሆን ብር ከመኢአድ ሒሳብ ላይ ለማውጣት አሰብን፡፡ ኢንጅነር ከፈረመ በኋላ ቀሪዎቹ ሁለት ፈራሚዎች አንዱ ውጭ ነበር ሀገር ውስጥ ያለው አልፈርምም ስላለ ተበድረን ሰጠን፡፡ ኢንጅነር ታመው ወደ አሜሪካ ሄዱ፡፡ ከዚያ ጠርተውኝ ሄድኩ፡፡ ዲያስፖራውን አብረን እንድናሳምን ነው፡፡ እኔም የተቻለኝን አድርጌአለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- ዲያስፓራው የሁለቱን ቡድን ልዩነት እንዴት ነበር የተቀበለው? አቶ በድሩ፡- ሕዝቡ ቅንጅት ለሁለት በመከፈሉ በጣም አዝኗል፡፡ መጀመሪያ የዶ/ር ብርሃኑን ቡድን አምኖ ነበር፡፡ በኋላ እውነቱን ሳስቀምጥላቸው በብዛት ተመልሰዋል፡፡ ተፀፅተዋል፡፡ ሒሳቡም ኦዲት ተደርጓል፡፡ ከ700 ሺህ ዶላር እስከ 1.2 ሚሊዮን ዶላር እንደተሰረቀ ቢገለፅም በቅንጅት ሒሳብ ይህን ያህል ብር ኖሮ አያውቅም፡፡ ይህን የፈጠራ ክስ ያሰማው የዶ/ር ብርሃኑ ቡድን ነው፡፡ በአሜሪካ ሕግ መሠረት ሒሳቡ ሲጣራ የተጭበረበረ ብር አልነበረም፡፡ ይህን ክስ ያሰሙት ላይም ክስ መስርተናል፡፡ እስራኤላዊ የሆነ በአሜሪካ ሕግ መሠረት ቻርተርድ የሆነ አካውንታንት ነው ሒሳቡን ኦዲት ያደረገው፡፡ ክሱን አምኖ የነበረው ኢንጅነር ኃይሉ ሻወልም በቅርቡ የኦዲት ሪፖርቱን ተከትሎ ድሮም ከስሼ አላውቅም ብሎ ክዷል፡፡ እንደውም ለአቶ አባይነህ ብርሃኑ በአቢሲኒያ ባንክ በኩል የተላከው 7500 ዶላር የት እንደደረሰ አልታወቀም፡፡ ሪፖርተር፡- ቡድኑ ወደ ተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተጨማሪ የልዩነት መንስኤዎች እንደተገኙ ይነገራል፤ አቶ በድሩ፡- ለመንቀሳቀስ ግብረ ኃይል ሲመሰረት ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ ምክንያቱም ተጠሪነቱ ለፓርቲው ስላልነበር፡፡ ኢንጅነር ኃይሉ ግን የግብር ኃይሉን ሰብሳቢ ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያትን አደረገ፡፡ ዶ/ር ታዬ በመስሪያ ቤቱ የተሾመውን ሻለቃ ዮሴፍን ከቢሮው ያባረረ ነው፡፡ ሐምሌ 2ዐ የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ቢፈርስም የምክር ቤቱ ኘሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ታዬ በእንቅስቃሴአችን አሁንም ምክር ቤቱ እንዳለ ያወሩ ነበር፡፡ እኔ ይህንን አልቀበልም አልኩ፡፡ በዲያስፖራው የተመረጡ ሰዎችን እንደ ሌባ ተቆጥረው አብረው እንዳይሄዱ ተደርገው (ይህም ስንታሰር ለማስፈታት ብዙ የጣሩ፣ የኢንጅነሩን ዓይን ያሳከሙ መሆናቸው ተዘንግቶ) መካሄዱ ለእኔ ክህደት ነበር፡፡ የቅንጅት አምስት የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ሲታገዱ አላውቅም፡፡ ተጨባጭ ጥፋት ከተገኘ ተወያይተን አጥፊዎቹን ማገድ ነው ያለብን፡፡ ውክልናውም በሕጉ መሠረት መሆን ነው ያለበት፡፡ አቶ ገብረፃድቅ፣ ዶ/ር በዛብህ፣ ሻለቃ አድማሱና ወ/ሮ ንግሥትም አያውቁም፡፡ እኩልነት የተጠበቀበት የብሔር ብሔረሰቦች መብት የተከበረበት የዘርና የሃይማኖት ልዩነት የማይደረግበት ስርዓት ለመፍጠር የምታገል ሰው ነኝ እንጂ ፣አቤት ጓድ ሊቀመንበር፣ እያልኩ የማጎበድድ አይደለሁም፡፡ መጨረሻ ፌብሩዋሪ 3 ሎስ አንጀለስ ላይ ከህዝብ ጋር ስብሰባ ለማድረግ አዳራሽ ከተከራየን በኋላ ኢንጂነር ሞገስ ይቅርታ ካልጠየቀኝ መግቢያ ካርዱም በቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ሥም ካልሆነ ጉባኤውም ላይ ዶ/ር ታዬ አብሮኝ ካልተቀመጠ በማለት ኢንጂነር ኃይሉ ስብሰባውን ሲሰርዘው ሁሉም ነገር በቃኝ፡፡ በቃኝ ብዬ ጥዬ ወደ ሀገር ቤት መጣሁ፡፡ ሪፖርተር፡- ፓርላማ መግባት አለመግባት ከውይይት እስከ ውጤት አጨቃጫቂ ቢሆንም የኢንጅነሩ ውሳኔ የፓርቲውን የአሁኑን ሁኔታ ይበልጥ አስቸጋሪ እንዳደረገው እየተነገረ ነው፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው? አቶ በድሩ፡- ቅንጅት በፊትም ቢሆን አልነበረም፡፡ ህዝቡ ነው የተቀናጀው፡፡ የቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት አመራረጥ ችግር ነበረበት፡፡ ወ/ት ብርቱካን ያለ ምንም ልምድ ነው የቅንጅት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆነችው . . . . ሪፖርተር፡- ከላይ እንደገለፁልኝ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሥልጣን ጥም ካለበት ወ/ት ብርቱካን እንድትመረጥ እንዴት ሆነ? አቶ በድሩ፡- አንደኛ ኦሮሞ ነች፤ ሁለተኛ ሴት ነች፡፡ በዚህ ተጠቅሞ ልደቱን ከጣለ በኋላ እሷን አሻንጉሊት በማድረግ ለመጫወት አስቦ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ ያላቸውን ድርሻ ካየን ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መሆን የነበረበት አቶ ልደቱ አያሌው ነው . . ሪፖርተር፡- ምንን ታሳቢ በማድረግ? አቶ በድሩ፡- በቁጥር ብዛት፡፡ ከመኢአድ በመቀጠል ብዙ አባላት ያሉት ፓርቲ ኢዴአፓ መድኀን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ኢድሊም ያቀረበው እጩ ዶ/ር ዓለማየሁ አረዳን እንደነበር የሚናገሩ አሉ፤ አቶ በድሩ፡- ልክ ነው፡፡ ዶ/ር አለማየሁን ጥለው ሙሉነህ እዩኤልን እንዲመረጥ ያደረጉት በተንኮል ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በወቅቱ ይህን ካወቁ ለምን አልተቃወሙም? አቶ በድሩ፡- ምርጫው ላይ አልተገኘሁም፡፡ በሌለሁበት ነው ቀስተ ደመናም ሆነ ቅንጅቱ የመረጠኝ፡፡ የቀረሁት ነገሩ ስላላማረኝ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ከአራቱ ፓርቲዎች ኢዴአፓ መድኀን ጥሎ ሲወጣ በወቅቱ ምን ተሰማዎት? አቶ በድሩ፡- ኢዴአፓ መድኀን ከሌሎቹ ፓርቲዎች የተለየ ዓላማና የፖሊሲ ልዩነት የለውም፡፡ በስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ነው የለቀቀው፡፡ የኢዴአፓ መድኀን ፍፁም አብላጫ ድምፅ በወቅቱ ልደቱን ተከትሎ አልወጣም፡፡ አቶ አየለ ጫሚሶም ሆነ አቶ ተመስገን ዘውዴ የወጡት ከኢዴአፓ መድኀን ነው፡፡ ፓርቲው አሁንም በቅንጅት ውስጥ ነው፡፡ ልደቱን ግን እንዲወጣ ያደረጉት የሌሎች ፓርቲዎች በተለይም መኢአድና የቀስተ ደመና መሪዎች ናቸው፡፡ ግን እሱም የኢድሊውን ዶ/ር አለማየሁ አረዳን ገፍተው ከጣሉት አንዱ ነበር፡፡ ይሄ ያሳዝነኝ ነበር፡፡ ሪፖርተር፡- የነልደቱ ልዩነት ሚዲያ ላይ በመውጣታቸው እንጂ አመራሩ ላይ እናንተንም በወቅቱ ቅሬታ ነበራችሁ ማለት ነው? አቶ በድሩ፡- አዎ፡፡ ልዩነታችን በሚዲያ በመውጣትና ባለመውጣት መካከል ነው፡፡ ፓርቲው ውስጡ ባዶ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ኢህአዴግም ፓርቲው ውስጡ ባዶ እንደሆነ ቢያውቅ አያስረንም ነበር፡፡ ህዝቡም ይሕን አያውቅም ነበር፡፡ ወደ ሚዲያ እንዳልወጣ ንፁሀን ዜጎችን በሽምግልና ይልኩ ነበር፡፡ እነዚህ ንፁሃን ሰዎች ውስጣችን የተጠናከረና አንድነቱ የተጠበቀ ለሀገር ፍፁም የሆነ አቋም ያለው አድርገው ይወስዱናል፡፡ ሕዝቡ አሁንም እውነታውን የሚያውቀው አልመሰለኝም፡፡ ሪፖርተር፡- የታሰራችሁት ፓርላማ የገቡትን ፣ከሀዲ፣ አድርጋችሁ ትቆጥሩ ነበር ይባላል፤ አቶ በድሩ፡- ይሄ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ፓርላማ ላለመግባት ሕዝብን በማነጋገር የተያዘ አቋም ነው፡፡ ማነጋገር የለብንም የሚል አቋም ነበረኝ፡፡ ፓርቲ የፖለቲካ መመሪያ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ህዝብን መመሪያ መጠየቅ የለበትም፡፡ ምርጫው ስለተጭበረበረ ህዝብን መጠየቅ አለበት ቢባል እንኳን አዲስ አበባ ስላልተጭበረበረ ተገቢ ቦታ አይሆንም፡፡ አንዴ ህዝቡ ፣ፓርላማ አትግቡ፣ ካለ በኋላ ፓርላማ ገብቼ ልሰራ አልችልም፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ የማቀርበውን ሪፖርት ህዝብ ሳላናግር ውክልናዬን ሳልፈፅም ማቅረብ አልችልም፡፡ በግሌ ፓርላማ የገባውን ፣ከሀዲ፣ ነው ብዬ አላምንም . . . . ሪፖርተር፡- በቁጥር ምን ያህሉ ይህ እምነት ነበረው? አቶ በድሩ፡- ብዙዎቹ ይህ እምነት ነበራቸው፡፡ ሪፖርተር፡- እስር ላይ የነበረው አመራር የፓርላማ አባላትን የቅንጅቱ አካል አድርጎ ይቆጥራቸው ነበር? አቶ በድሩ፡- እነሱን የመፈለግ ነገር ፈፅሞ አልነበረውም፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ ወልደማርያም ግን የተለየ አመለካከት ነበረው፡፡ ፓርላማ መግባታቸውን አይኮንንም ነበር፡፡ በተወሰነ መልኩ ኘሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተመሳሳይ ሀሳብ ነበረው፡፡ ሪፖርተር፡- ወ/ት ብርቱካን ከፓርላማው ቡድን ከአቶ ተመስገን ዘውዴ ጋር አብረው እየሰሩ ነው፡፡ በእስር ላይ የእሳቸው አመለካከትስ የተለየ አልነበረም? አቶ በድሩ፡- ወ/ት ብርቱካን ከእስር ሲፈቱ የፓርላማው ቡድን አይመለከተውም በማለት ነው ጥለዋቸው ወደ ውጭ የተጓዙት፡፡ እንደ ጠላት ነበር የምትቆጥራቸው፡፡ እኔ አቶ ተመስገን ዘውዴ በጣም ጥሩ ሰው እንደሆነ በፊትም እናገር ነበር፡፡ ሪፖርተር፡- ስለመጭው ጊዜ ምን ያስባሉ? አቶ በድሩ፡- ቅንጅት ዱሮም እንደ ድሪቶ የተሰፋ ነው እንጂ የተደራጀ አልነበረም፡፡ የሦስት ወር ደቦ ነበር፡፡ ልዩነቱ ከአመራር ነው፡፡ በእኩልነት እምነት አልነበረውም፡፡ ህዝቡ በዚህ አዝኗል፡፡ ነገር ግን እንደገና ማደራጀትና መደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ቺሊ የፒኖቼን ፓርቲ የጣለው የአራት ወር ፓርቲ ነበር፡፡ አርጀንቲና የዳንኤል ኦርቴጋ ፓርቲ የጣለው የስምንት ወር ፓርቲ ነበር፡፡ ለእኛም እድል ነበረን፡፡ አሁንም እርስ በርስ ከተጠናናንና ከተዋወቅን በቅርቡ በኬንያ የተገኘውን ዓይነት ድል ማስመዝገብ እንችላለን፡፡ ቅንጅት የጀመራቸውን ብዙ ነገሮች ኢህአዴግ ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ከኢንጅነር ቡድን ጋር ይቀጥላሉ? አቶ በድሩ፡- አልቀጥልም፡፡ አሰራሩ ሁሉ አላስደሰተኝም፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ አብሬ አልቀጥልም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |