| ከአውሮፓ ጋር እንዲፈረም በሚፈለገው... |
|
|
| Sunday, 09 March 2008 | |
ከአውሮፓ ጋር እንዲፈረም በሚፈለገው የንግድ ስምምነት ኢትዮጵያ የተለየ አቋም ያዘችበአውሮፓና በአፍሪካ አገሮች መካከል በአዲስ መልክ እንዲፈረም የተፈለገው የኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነትን (Economic Partnership Agreement) ኢትዮጵያ ጠንካራ ተከራካሪ ሆና መቅረቧ ተገለፀ፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገራትም ስምምነቱን እየፈረሙ ነው፡፡ ይህ የተገለፀው በአዲሱ የአውሮፓና የአፍሪካ የኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነት (ኢፒኤ) ዙሪያ የካቲት 27 ቀን 2000 ዓ.ም በግሎባል ሆቴል በተደረገ ውይይት ላይ ነው፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሙያዎች አቶ ገረመው አያሌውና አቶ መንገሻ ታደሰ በውይይቱ ላይ ባቀረቡት ፅሑፍ እ.ኤ.አ ከ2008 መግቢያ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ተፈልጐ የነበረው ይህ ስምምነት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ተከራካሪዎች ባቀረቡት ሃሳብ ምክንያት ስምምነቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊተገበር ሳይችል ቀርቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢፒኤን ለመደራደር ሲወስን የኢፒኤን አላማና መርሆ ካስቀመጠው የልማት ስትራቴጂ በተለይም "በኮተኑ" ስምምነት ላይ የኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነቱ ዓላማዎች ተብለው የተቀመጡት የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ከማሳካት አኳያ ሊጫወት የሚችለውን ሚና በመገምገም እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በዚህ መሠረት ከመጀመሪያው ጀምሮ ተሳትፎ የተደረገበት ሲሆን በተለይ የኢፒኤ ስምምነት "በቀጣይ እድገት ላይ የተመሠረተና በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ የንግድ የኢንዱስትሪ ዘርፍ መፍጠር" ከሚለው የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ራዕይ ጋር በተያያዘ መልኩ ከልማት ስትራቴጂያችን ጋር የተጣጣመ የድርድር ሃሳብ በማፍለቅና የኢትዮጵያ አቋም የክልል አቋም ሆኖ ለድርድር እንዲቀርብ በማድረግ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና መጫወቷ ተጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበትና 16 አገራት የተካተቱበት ቡድን ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የመከራከሪያ ነጥብ እስከመጨረሻው የገፉበት ቢሆንም ኢኮኖሚያችንን ሊጐዳ ይችላል ያሉ አገራት ግን ኢትዮጵያ እየወሰደች ካለው አቋሟ አፈንግጠው ጊዜያዊ ስምምነት አድርገዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ዋነኛ መደራደሪያ እና መከራከሪያ ሃሳቦች ውስጥም ልማት የማያመጣ ከአውሮፓ ጋር የሚደረግ የኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነት (ኢፒኤ) አንፈልግም፣ የገበያ በራችንን የምንከፍተው የልማታችንን ደረጃ እያየን ነው፣ ልማታችንን የሚያግዝና ለኢፒኤ መሳካት የሚረዱ ለክልላዊ ውህደትና የንግድ መስፋፋት ለሚረዱ ፕሮጀክቶች የገንዘብ እገዛ ይኑር የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ አውሮፓ ይህ ስምምነት እንዲፈረም ባደረገችው ጠንካራ ጫና እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አድርጓል፡፡ በተለይ ኬንያ ስምምነቱን ባትፈርም በአውሮፓ 3 በመቶ ይከፈልበት የነበረው የአበባ ምርቷ ቀረጥ ዘጠኝ በመቶ ስለሚደርስባት ስምምነቱን በችኮላ ልትፈርም መገደዷን ከባለሙያዎቹ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በመደራደሪያ ሃሳቡ መሠረት አስራ ስድስቱ አገሮች ከአውሮፓ ህብረት ጋር እስከ ኦክቶበር 2007 በመጨረሻ ድረስ ተከታታይ ድርድሮች ቢደረጉም የኢትዮጵያ አቋም እንደታሰበው የስምምነቱ አካል ሊሆን አልቻለም፡፡ ከዚህ በኋላም ሌላ የድርድር መድረክ የሚዘጋጅ በመሆኑ የኢትዮጵያን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል ተጨማሪ መደራደሪያዎችን ይዛ ትቀርባለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ በአፍሪካ በአውሮፓ አገራት መካከል እንዲፈረም የሚፈለገው ስምምነት የአፍሪካ አገሮች በአራት ምድብ ተመድበው ሲደራደሩበት የቆዩ ሲሆን ስምምነት ይበልጥ ለአውሮፓውያኑ የሚጠቅም በመሆኑ በተከፋፈለ መንገድ ከመደራደር ይልቅ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲሆን ኢትየጵያ ያቀረበችው ተጨማሪ ሃሳብ በአውሮፓ ህብረት በኩል ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በዚህ ስምምነት ዙሪያ የአኮር ኢትዮጵያ ኤርያ ማናጀር የአብወርቅ ኃይሉ እንደገለፁት፣ አውሮፓውያኑ ይህንን ግትር አቋም የወሰዱት አፍሪካውያን በአፍሪካ ህብረት በኩል ከመጡ የምንፈልገውን ልናሳካ አንችልም ከሚልና በቡድን ከፋፍሎ ማናገሩ ጠቃሚ መሆኑን በመረዳታቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹን የአፍሪካ አገሮች ስምምነቱን እያስፈረሙዋቸው ሲሆን ጠንካራ ተከራካሪ የሆኑትን እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ደግሞ ቀስ ብለን እናገኛቸዋለን የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ስምምነቱን መፈረም ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት በድጋሚ መታየት ይኖርበታል ያሉት አብወርቅ "የሚመለከተው ክፍል ሁሉ በስምምነቱ ዙሪያ ግንዛቤ ኖሮት ኢትዮጵያ ይዛ ልትቀርብ የሚገባትን ተጨማሪ ሃሳቦች በማስጠናት ኢትዮጵያን ወክሎ ለሚደራደረው መንግሥታዊ አካል በማቅረብ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል፡፡ እንደባለሙያዎች ገለፃ፣ ይህ ስምምነት በአመዛኙ አውሮፓን የሚጠቅም ስለሆነ እንደምንም ብሎ ሁለቱንም ወገኖች በሚጠቅም መልኩ ሰነዱ መፈረም ሊኖርበት ይችላል ያሉት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ስምምነቱን በግድ እንድትፈርም የሚደነግግ ሕግ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ ስምምነቱን በመፈረም ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለው ጥቅም ሊኖር ስለሚችል ይህንን ጥቅም መሠረት በማድረግና ተጨማሪ መደራደሪያዎችን በማቅረብ ተጠቃሚ የምትሆንበት መንገድ ማመቻቸት ይገባል ባይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን በዚህ የኢፒኤ ድርድር ወቅት ከተደራዳሪ ሀገሮች በኩል ይቀርብ የነበረው የድርድር ሀሳብ የኢፒኤ ከዓለም የንግድ ድርጅቶች ሕጐችና ደንቦች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በረጅም ግቡ የአፍሪካ ካረቢያንና ፓስፊክ (ኢካፖ) ሀገሮች በአብዛኛው ገቢያቸውን (Substantially all trade) ለሕብረቱ ክፍት እንዲያደርጉ፤ የንግድ እንቅፋቶችን እንዲያስወግዱ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ይህም የአፍሪካ ሀገሮች ለተጨማሪ ግዴታና ጫና የሚዳርጋቸው፣ ታዳጊ ኢንዱስትሪዎቻቸውን ለውድድር የሚያጋልጥ በመሆኑ እነዚህን ታዳጊ ኢንዱስትሪዎች ለሚጠብቃቸው ውድድር ለማብቃትና በአካፖ ሀገሮች ኢኮኖሚ ውስጥ የሚስተዋለውን የመሠረተ ልማትና የአቅርቦት ችግር ለማስወገድ የአውሮፓ ህብረት ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ እስካሁን በነበረው ድርድር የአውሮፓ ኅብረት በቂ በጀት የመደብኩ ስለሆነ ተጨማሪ በጀት መመደብ አልችልም የሚል አቋም ይዟል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ጉዳይ ሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች በጋራ ተጨማሪ በጀት እንደሚያፈላልጉና "እርዳታ ለንግድ "ሽሳ for ማቈሮሳስ" በሚለው ማዕቀፍ ኅብረቱ ከሚመድበው በጀት ከፍተኛው ድርሻ ለአፍሪካ ሀገሮች እንደሚመደብ በሕብረቱ ቃል እየተገባ ስለሆነ ከኢፒኤ ስምምነት ውጭ መሆን ከዚህ ከተጠቀሰው የልማት በጀት ተጠቃሚነትን እንዲያሳጣ ስጋት መኖሩንም በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡ ዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |