Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የአይ.ኤስ.ኦ 9001 የጥራት ሥራ አመራር...
የአይ.ኤስ.ኦ 9001 የጥራት ሥራ አመራር... Print E-mail
Sunday, 09 March 2008
የአይ.ኤስ.ኦ 9001 የጥራት ሥራ አመራር ደረጃ የምርት ጥራት ማረጋገጫ ዋነኛ መሣሪያ ነው

(ከኢትዮጵያ የጥራትና የደረጃዎች ባለሥልጣን)

በሪፖርተር ጋዜጣ ጥር 18 ቀን 2000 ዓ.ም በቢዝነስና ኢኮኖሚ ገጽ ላይ "የአይ.ኤስ.ኦ ሠርተፊኬት የምርት ጥራት ማረጋገጫ አይደለም" በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ብዙ ሰዎች ወደ መሥሪያ ቤታችን ስልክ በመደወል “የአይ.ኤስ.ኦ 2000 ሠርተፊኬት” የጥራት ማረጋገጫ ካልሆነ ጥቅሙ ምንድን ነው? በሌሎች ከሚሰጡት ሽልማቶችስ በምን ይለያል የሚሉና ሌሎችም ተዛማጅ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ የጥራትና የደረጃዎች ባለሥልጣን የሚከተለውን ጽሁፍ ያቀርባል፡፡

ወደ የአይ.ኤስ.ኦ 9000 የጥራት ሥራ አመራር በቀጥታ ከመግባታችን በፊት ጥራትን ለማምጣት የሚያስችሉና አንድን ምርት ወይም አገልግሎት በስምምነት የተዘጋጀለትን ደረጃ ወይም ተፈላጊውን መሥፈርት እንዲያሟላ የተዘጋጁ ደረጃዎችን ለመተግበር የሚያስችሉ የተለያዩ የሥራ አመራር ሥርዓቶች መኖራቸውን ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ ከእነዚህ የሥራ አመራር ሥርዓቶች መካከል የተወሰኑትን ብንጠቅስ፡-

. የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት
. በኦዲት ላይ የተመሰረተ የሥራ አመራር ሥርዓት
. የምግብ አያያዝና ደህንነት ሥራ አመራር ሥርዓት
. የላቦራቶር ሥራ አመራር ሥርዓት
. የአካባቢ ሥራ አመራር ሥርዓት
. የአለካክ ሥርዓት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

አንድ ደረጃ ከተዘጋጀ በኋላ እጅግ ቢዘገይ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ መከለስ ይኖበታል፡፡ የአይ.ኤስ.ኦ 9000 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን የተመለከቱት ዓለም አቀፍ ደረጃዎችም አንድ ጊዜ ታትመው እንደወጡ በዚያው ፀድቀው የቀሩ አይደሉም፡፡ በየጊዜው የተለያዩ ለውጦችና ማሻሻያዎች ተደርጎባቸዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ታትመው የወጡት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1987 ዓ.ም ሲሆን በርካታ ማሻሻያዎች ተደርጎባቸው እንደገና እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም ታትመው በሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ክለሳው በዚሁ ሳያቆም አሁንም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትንና ተጠቃሚዎችን እንዲሁም በአሰራር ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በአቀራረብና በይዘት ካለፈው የተለዩ ደረጃዎች እ.ኤ.አ በ2000 ታትመው ወጥተው እስካሁን እየተሰራባቸው ይገኛል፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ሥራ ላይ በማዋል የአሠራር ቅልጥፍና እና ውጤታማነትን ያመጡ በርካታ ተቋማት የአሠራር ሥርዓቱን በመተግበር ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተዋል፡፡

የጥራት ሥራ አመራር ደረጃዎችን ስናነሳ ወደ ዝርዝሩ ከመሄዳችን በፊት አሁንም በተለያዩ የአይ.ኤስ.ኦ 9000፣ 2000 ደረጃዎች ማዕቀፍ (Family of standards) የሚካተቱትን ሦስት ዘርፎች በመጠኑ ማሳየቱ ደረጃዎቹ ያላቸውን ተያያዥነትና ልዩነት በግልጽ ለመረዳት ያስችላል፡፡ በነገራችን ላይ 9000 የሚለው ቁጥር የሚያመለክተው የደረጃውን ቁጥር ሲሆን 2000 የሚያመለክተው ደረጃው ፀድቆ የታተመበትን ዓ.ም ነው፡፡   

1. አይ.ኤስ.ኦ 9000 2000 - ይህ ደረጃ በውስጡ ያካተታቸው ዋነኛ ነገሮች የደረጃው መሠረታዊ ይዘትና የቃላት ፍቺ ሲሆኑ ስለ ጥራት ሥራ አመራር ፅንሰ ሃሳብና በሌሎቹ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓቶች ውስጥ የተገለጹ ደረጃዎች የሚጠቀሙባቸውን ቃላት በተመለከተ መረጃ ይሰጣል፡፡

2. አይ.ኤስ.ኦ 9001 2000 - ይህ ደረጃ በውስጡ ያካተታቸው ዋነኛ ነገሮች ተፈላጊ ዝርዝር መሥፈርቶች ሲሆኑ ድርጅቶች በምርትና አገልግሎት ውስጥ ጥራትን በማስረፅ የጥራት ሰርተፊኬት ለማግኘት ማሟላት የሚገባቸውን ተፈላጊ መሥፈርቶችን በዝርዝር ይገልጻል፡፡

3. አይ.ኤስ.ኦ 9004 2000 - ይህ ደረጃ ለሥራ አፈፃፀም መሻሻል የሚረዱ የአሠራር መመሪያዎችን አካትቷል፡፡

የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓቱ ምርትንና አገልግሎት በተመለከተ ኩባንያዎች/ ድርጅቶች ወደ ተግባር ሲተረጉሙት ምን ምን ነገሮችን ይይዛል? እንዴትስ ይገለፃል? የሚለውን ለመመልከት እንድንችል አይ.ኤስ.ኦ 9000 2000 የጥራት ሥራ አመራር ላይ የተመሠረተውንና የጥራት ሥራ አመራር መርሆዎችን መነሻ ያደረገ አሠራር ለመፍጠር ስለ ደረጃዎቹ ፅንሰ ሐሳብ መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡

በአይ.ኤስ.ኦ 9000 2000 የጥራት ሥራ አመራር የተካተቱት ስምንት የጥራት ሥራ አመራር መርሆዎች፡-
1. ደንበኛ ተኮር ምርት ማምረት አገልግሎት መስጠት (Customer Fouces)
2. መሪነት (Leadership)
3. የሠራተኞች ተሣትፎ (Involvement of people)
4. በሥራ ሂደት ላይ ያተኮረ አቅጣጫ (Process approach)
5. በአሰራር ሥርዓት ላይ ያተኮረ አመራር (System approach to management)
6. ቀጣይት ያለው መሻሻል (Continual improvements)
7. በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ የውሳኔ አሰጣጥ (Factual approach making of decision)
8. በአቅራቢያዎችና በደንበኞች የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት (Mutually beneficial supplier relationship)

ስለ ጥራት ሥራ አመራር መርሆዎች ይህን ያህል ካልን የአይ.ኤስ.ኦ 9000 የጥራት ሥራ አመራር መሥፈርት በማሟላት የሚሰጥ ሰርተፊኬት የምርት ጥራት ማረጋገጫ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ማረጋገጥ እንድንችል ተፈላጊ መሥፈርቶችን የያዘው የአይ.ኤስ.ኦ 9000 2000 የጥራት ሥራ አመራር ደረጃ ይዘትን በመመልከት ስለጉዳዩ ይበልጥ እንድናውቅ ይረዳናል፡፡ የዚህ የጥራት ሥራ አመራር ደረጃ ምርትን በተመለከተ የደንበኞችን ፍላጎት መነሻ ከማድረግ ጀምሮ ምርቱ ተጠቃሚው ዘንድ እስከሚደርስ ድረስ መደረግ የሚገባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ይተነትናል፡፡

በደረጃው ውስጥ በግልጽ እንደተቀመጠው የአይ.ኤስ.ኦ 9000 2000 የጥራት ሥራ አመራር አንድን ምርት ለማምረት ሲታቀድ ድርጅቱ የሚከተሉትን እንደአግባብነቱ መወሰን እንዳለበት ይጠቅሳል፡፡ እነዚህም፡-

ሀ/ የሚመረተውን ምርት በተመለከተ የጥራት ግቦችና ተፈላጊ መሥፈርቶችን
ለ/ ምርቱን ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ የሥራ ሂደቶችን፣ ሰነዶችን፣ ማዘጋጀትና ለምርቱ የተለዩ ግብዓቶች ማቅረብን
ሐ/ ምርቱ ተፈላጊ የሆነውን መሥፈርት ስለማሟላቱ ክትትል ማድረግን፣ የሚመረተውን ምርት በተመለከተ የሚያስፈልገውን ቁጥጥር የፍተሻ ተግባራት ማካሄድንና ምርቱ ተቀባይነት ለማግኘት የሚያስችለውን መመዘኛ ማሟላቱን ማረጋገጥን፣
መ/ ምርቱን ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ የአሰራር ሂደቶችና የተመረተው ምርት ተፈላጊውን መስፈርቶች ማሟላት መቻሉን የሚያረጋግጡ ተፈላጊ ማስረጃዎችን ማቀድና ማዘጋጀት የሚሉት መሆናቸውን ይገልጻል፡፡

የአይ.ኤስ.ኦ 9000 2000 የጥራት ሥራ አመራር ደረጃ ምርቱ ተፈላጊውን መሥፈርት ማሟላቱን በተመለከተ ከደንበኛ ጋር ያለው የግንኙነት ሂደትም ሲገልጽ ከሚዘረዝራቸው መስፈርቶች አንዱ ምርቱ ከሕግና ከደንብ አንፃር ያለውን ተፈፃሚነት ነው፡፡

በደረጃው ውስጥ እንደተጠቀሰው የተሻሻለው የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ድግግሞሽ ያላቸውን መሥፈርቶች አስወግዶ ከሸቀጥ ጋር በተለይ የሚገናኙትን ተፈላጊ ዝርዝር መሥፈርቶች አሁንም በመሥፈርትነት እንደሚጠቀምባቸው ያሳያል፡፡ ደረጃው በዚህ ብቻ አያቆምም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግድፈቶችን መከላከልንና ወጥነት የሌለው የማምረት ሂደትንና ብክነትን ማስወገድ ላይም ትኩረት ያደርጋል፡፡

የምርቱን ደህንነት መጠበቅን በሚመለከት የአይ.ኤስ.ኦ 9000 2000 የጥራት ሥራ አመራር ደረጃ፣ አንድ ድርጅት ከውስጥ ጀምሮ ምርቱ በመጨረሻ እንዲደርስ እስኪታቀድበት መዳረሻ ድረስ ሳይበላሽ ተገቢውን የአሰራር ሂደት የተከተለ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት ይገልጻል፡፡ ይህም የምርቱ መለያ አያያዝ፣ አስተሻሸግ፣ በመጋዘን ውስጥ ያለውን አቀማመጥ እና ከበካይ ነገሮች መከላከልን ያጠቃልላል፡፡ የእነዚህ ምርቶች ደህንነት እንዲጠበቅ ምርቶቹ እንዳይበላሹ ወይም በተጠቃሚው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የመቆጣጠሪያ ስልቶቹ በጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ውስጥ ተዘጋጅተዋል፡፡

ይህንን የአይ.ኤስ.ኦ የጥራት ሥራ አመራር በሚያሟላ መልኩ የተዘጋጀን ምርት በሚመለከት የሚሰጥ ሰርተፊኬት የምርት ጥራት ማረጋገጫ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ጥያቄ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡
ከዚህ በላይ በዝርዝር እንደተመለከትነው የአይ.ኤስ.ኦ የጥራት ሥራ አመራር ደረጃ ምርትን በተመለከተ የዘረዘራቸው መሥፈርቶች ሁሉ የጥራት ማረጋገጫ ዋነኛ መሣሪያ ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸው ነው፡፡ ይህም ሌሎች በጥራት ስም የሚሰጡ ሽልማቶችና የአይ.ኤስ.ኦ የጥራት ሥራ አመራር መሥፈርት አሟልተው ለተገኙ ድርጅቶች የሚሰጡ ማረጋገጫዎች በይዘታቸውም የተለያዩ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ ሌሎቹ በጥራት ስም የጥራት ማረጋገጫ እየተባሉ የሚሰጡ ሽልማቶች አንድም በገንዘብ የሚገዙ አሊያም በማበረታቻነት የሚሰጡ ናቸው፡፡

የአይ.ኤስ.ኦ 9000 2000 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን በተመለከተ ምርቱ/አገልግሎቱ በጥራት ለመመረቱ/ለመዘጋጀቱ የሚመሰከርበት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ያሟላና እንደስሙ ሁሉ ተገቢ የሆነ የጥራት ማረጋገጫ ነው፡፡ የአይ.ኤስ.ኦ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ዋነኛ ግብና አላማም ኅብረተሰቡ ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ በመሆኑም የደረጃዎቹ ተፈላጊ መስፈርቶች ተጨባጭነት ያላቸው፣ የሚለኩ እና በኦዲትም የሚረጋገጡ በመሆናቸው አይ.ኤስ.ኦ 9001 ከምርት ጥራት ማረጋገጫ በተጨማሪ የምርትና አገልግሎት ጥራት ቀጣይነት (Sustainability) ባለው መንገድ ምርቱና አገልግሎቱ ውስጥ ለመስረፃቸው አስተማማኝ መሆናቸውንም ያረጋግጣል፡፡
 
< Prev   Next >