Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow "ስንዴ እየጠበቁ እንዲኖሩ ሳይሆን...
"ስንዴ እየጠበቁ እንዲኖሩ ሳይሆን... Print E-mail
Sunday, 09 March 2008
Image"ስንዴ እየጠበቁ እንዲኖሩ ሳይሆን ረተረጂዎችሪ ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ነው የሚፈለገው"
ዶ/ር ዘላለም ደመቀ፣
የአዲስ አበባ ኤች.አይ.ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ

ዶ/ር ዘላለም ደመቀ ከዩክሬን ክሪኒያ ሜዲካል ኢንስቲትዩት የሕክምና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ1988 ዓ.ም አግኝተዋል፡፡ በደቡብ ክልል ለአምስት ዓመታት፣ በኦሮሚያ ለአንድ ዓመት አገልግለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች፤ በመሿለኪያ ጤና ጣቢያ በሜዲካል ዳይሬክተርነት፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊነት በመቀጠልም በክፍለ ከተማው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊነት የሰሩ ሲሆን ከህዳር ወር 2000 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አበባ ኤች.አይ.ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት በኃላፊነት  እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
 
የአዲስ አበባ ኤች.አይ.ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት በአለማቀፉ የምግብ ፕሮግራም፣ በኤምሳፕና የበጀት መዘግየትን አስመልክቶ በሚቀርቡ ጥያቄዎች ዙሪያ ዶ/ር ዘላለም ደመቀ የአዲስ አበባ ኤች.አይ.ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ኃላፊን ምህረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ለኤድስ ህሙማንና ወላጅ ላጡ ህፃናት ከአለማቀፉ የምግብ ፕሮግራም ይሰጥ የነበረው የምግብ ድጋፍ ለምን ተቋረጠ?

ዶ/ር ዘላለም፡-
የምግብ ፕሮግራሙ አልተቋረጠም፡፡ የተወሰኑ ችግሮች አሉት፡፡ ሆኖም በቅርቡ የሚፈቱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሮቹ ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ዘላለም፡-
ከውል ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ አለማቀፉ የምግብ ፕሮግራም (ደብሊው.ኤፍ.ፒ) ከገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር ውል ይገባል፡፡ በመቀጠልም ከክልሎች ፈፃሚ አካላት ጋር ይዋዋላል፡፡ የምንንቀሳቀሰው በዚህ ውል መሠረት ነው፡፡ የፕሮግራሙ ውል ያለቀው ታህሳስ 21 ላይ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ውሉ በጊዜው ስላልተፈረመ ለተወሰነ ጊዜ ያክል ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ችግሩ ተፈጠረ ማለት ግን ፕሮግራሙ ቆመ ማለት አይደለም፡፡ ችግሩን ከደብሊው.ኤፍ.ፒ ጋር በመነጋገር በቢሮ ደረጃ እየፈታነው ነው፡፡ ለዚህም የሁለት ወር የማራዘሚያ ጊዜ አግኝተን እስከ የካቲት መገባደጃ የምግብ እደላውም ሆነ ሌላው ሥራ እየተሠራ ነበር፡፡ አስተዳደራዊ የሆኑ ችግሮችም ነበሩት፡፡ እንዴት ይፈታ በሚለው ከፕሮግራሙ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረን ጉዳዩን ለጊዜው ፈትተናል፡፡ የሁለት ወር ፕሮግራሙ በማለቁ በመጪው ሣምንት ውይይት ይኖረናል፡፡ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር ስምምነቱን እንደጨረሱ በቀጣይ ከእኛ ጋር እንፈራረማለን፡፡ ያሉ ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸውም እንወያያለን፡፡

ሪፖርተር፡- ውሉ ለስንት ዓመት የሚቆይ ይሆናል?

ዶ/ር ዘላለም፡-
በየአንድ አንድ ዓመቱ ነው የምንዋዋለው፡፡ አዲስ ውል እስክንዋዋል ውሉ ሲያልቅ ይቆማል፡፡ ይህ ሲቆም ግን ሥራዎች ቀጣይነት ስላላቸው እንዴት እናስተካክል በሚል የውል ማራዘሚያ ጊዜዎችን እንወስዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞው ውል ታህሳስ 21/2000 እንደሚያልቅ እየታወቀ ለምንድን ነው ቅድመ ዝግጅት ተደርጐ ውሉ በወቅቱ ያልተፈረመው?

ዶ/ር ዘላለም፡-
ይህ በእኛ በኩል አይደለም የሚያልቀው፡፡ በደብሊው.ኤፍ.ፒ እና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በኩል ነው፡፡ እነሱ ውሉን ካልተፈራረሙ መሆን የሚችል ነገር የለም፡፡ ከእኛ ጋር ወጥተውም መፈራረም አይችሉም፡፡ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጨርሰው ነው ወደ ጽህፈት ቤታችን የሚመጡት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት አብዛኞቹ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በኩል ነው የሚያልፉት፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለት ወር የማራዘሚያ ጊዜ ብታደርጉም ክፍለ ከተሞች የስድስት ወራት ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በላይ የምግብ ድጋፍ ያገኙ የነበሩ የኤድስ ህመማን ድጋፉ እንደተቋረጠባቸው ሲገልፁ ነበር፤

ዶ/ር ዘላለም፡-
እሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ መቋረጥ ሳይሆን በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የነበሩት ለተወሰነ ጊዜ ያክል በፕሮግራሙ ውስጥ ይካተታሉ፤ ጊዜያቸውን ሲጨርሱ ይወጣሉ፡፡ ጤንነታቸው ጥሩ ሲሆንና መሥራት ሲችሉ፣ ማህበራዊና ጤናዊ መስፈርቶችን ማሟላታቸውን ከሆስፒታልና ከየክፍለ ከተማው ካሉ አስፈፃሚ አካላት ለመሥራት ብቁ የሚያደርጋቸውን ማረጋገጫ ሲያገኙ ከፕሮግራሙ እንዲወጡ ይደረጋሉ፡፡ አሁን የማራዘሚያ ውሉን ስንዋዋል ያደረግነው በፕሮግራሙ ውስጥ ያሉ በሙሉ እንዲወጡ፣ ከወጡ በኋላ እንደ ሁኔታው የጤንነታቸው ሁኔታ እየታየ መግባት ያለባቸው እንዲገቡ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በምግብ ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ ይውጡ ነው ያልነው፡፡ ሆኖም ሁሉም አይደሉም የሚወጡት፡፡ እናቶች አይወጡም፡፡ ይውጡ ሲባልም ደግሞ እንደ አዲስ የሚገቡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ የምግብ ተጠቃሚዎችን መስፈርትና የቆይታ ጊዜ አስመልክቶ ከፕሮግራሙ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ይኖረናል፡፡ ፕሮግራሙ በተያዘለት አላማ ተከትለን ነው የምንሰራው፡፡ አዲሱን ውል ስንፈራረም የሚመጡ እርዳታዎች አሉ፡፡ እነዚያን እርዳታዎች እንዴት ያገኛሉ ሲባልም መስፈርቱን ካሟሉ የወጡት ሰዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ መስፈርቱን የማያሟሉ ከሆነ ደግሞ ሌሎች ፕሮግራሞች ውስጥ እንዲታቀፉ ነው የምናደርጋቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች ፕሮግራሞች ሲባል፤

ዶ/ር ዘላለም፡-
ሰርተው እንዲበሉ ነው የሚፈለገው፡፡ የተረጂነት ስሜት እንዲጠፋ ነው የሚፈለገው፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛው የደብሊው.ኤፍ.ፒ ተጠቃሚዎች ችግረኞችና ህመምተኞች ናቸው፤

ዶ/ር ዘላለም፡
- አዎ ችግረኞች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት ሊቋረጥ እንደሚችል አሳውቃችኋቸዋል?

ዶ/ር ዘላለም፡-
ያውቃሉ፡፡ በየክፍለ ከተማው ባሉ አጋር አስፈፃሚ አካላት በኩል ተነግሯቸዋል፡፡ መጀመሪያ ሲገቡ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ ተነግሯቸዋል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ችግሮች አሉ፡፡ ምግብ ተጠቃሚውም ቢሆን እንደ ገቢ አይቶት ለምን ከፕሮግራሙ እንወጣለን የሚል አለ፡፡ ቀድመው ካስረዷቸው የማይቀበሉበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የእነሱ ከፕሮግራሙ መውጣት ለሌሎች ተጠቃሚዎችም ቦታውን እንደመልቀቅ ማለት ነው፡፡ ሲጠቀምና ጤናውን ሲያሻሽል የቆየ ሰው መሥራት እንደሚችል ይታመናል፡፡ መሥራት ከቻለ ደግሞ ሌሎች መሥራት የማይችሉት የምግብ ተጠቃሚ እንዲሆኑና እሱ የደረሰበት ቦታ እንዲደርሱ ቦታ መልቀቅ አለበት፡፡ ያለው የምግብ ክምችት ውሱን ስለሆነ ለሁሉም ማዳረስ አለብን፡፡ የፕሮግራሙ አቋምም ይኸው ነው፡፡ የምግብ ፕሮግራሙ ምግቡ ለሚገባው ሰው እንዲደርስ ነው፡፡

ከፕሮግራሙ የሚወጡ ሰዎችም ውጡ ተብሎ እንደማባረር አይደለም አካሄዳችን፡፡ ከደብሊው.ኤፍ.ፒ ውጭ ሌሎች ፕሮግራሞች አሉ፡፡ በእነዚህ ፕሮግራሞች የሚታቀፉበትን መንገድ እያመቻቸን ነው፡፡ የገቢ ማስገኛ እድሎች፣ የሙያ ስልጠናና የመሳሰሉት አሉ፡፡ በእነዚህ ተጠቃሚ ሆነው በራሳቸው ወደ ሥራ ሊገቡ የሚችሉበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው ያለነው፡፡ በየክፍለ ከተማው ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትንም ሆነ ወላጅ ያጡትን በፕሮግራሙ እየገቡና እየሰለጠኑ ነው፡፡ ለዚህም መስፈርት አስቀምጠን ከጥቃቅንና አነስተኛ ኤጀንሲ ጋር በመሆን በየክፍለ ከተማው ምቹ የሆኑ የሥራ ዘርፎችን በመምረጥ በዚህ እንዲገቡና ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ቤተሰባቸውንም እንዲረዱ ማድረግ ነው፡፡ በነፃ ይሰጣቸዋል፡፡ እንደ ብድርና ቁጠባ አይደለም፡፡ ራሳቸውን እንዲያቋቁሙ ስልጠና ወስደው ገንዘብ በነፃ ይሰጣቸዋል፡፡ ሁል ጊዜ እድሜ ልካቸውን ስንዴ እየጠበቁ እንዲኖሩ ሳይሆን ህይወታቸውን እንዲለውጡ ነው የሚፈለገው፡፡ መድሃኒትና ምግብ ይሰጣል፡፡ እየተሻላቸው ሲመጣ ደግሞ እንደማንኛውም ሰው መሥራት ይችላሉ፡፡ ማበረታታት የሚያስፈልገውም ይህንኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በእናንተ በኩል ይህ አመለካከት ቢኖርም ተጠቃሚዎቹ እየገለፁ ያሉት ምግብ ካልተሰጠ መድሃኒት እስከማቆም እንደሚደርሱ ነው፡፡ በእናንተ በኩል መድሃኒት ካልጀመራችሁ ምግብ አታገኙም ተብለውም ነበር፡፡ ምግቡን ተስፋ አድርገው መድሃኒት የጀመሩት ሲቋረጥ መቀበል አልቻሉም፤

ዶ/ር ዘላለም፡-
ይሄ እኮ የጥገኝነት ወይም በአንድ ነገር ላይ የመመርኮዝና የተረጂነት ባህሪ ነው፡፡ ይህንን ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ሥራ ጥናት ተደርጎ ነው የገባንበት፡፡ ከምግብ ፕሮግራም ይውጡ ሲባል እንዲሰሩም ለማበረታታት ነው፡፡ መሥራት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ከደረሱ እንዲሰሩ ነው፡፡ መሥራት የማይችሉና የጤንነታቸው የተሟላ ካልሆነ የሚረዱት በምግብ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡ ብዙ እርዳታዎችን ነው የምናደርገው፡፡ የቤት ለቤት ተንከባካቢዎች ይረዱዋቸዋል፣ ምግብ ይሰጣቸዋል፣ የስነልቦና ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ሁሌ ምግብ መጠበቅ ጥሩ አይሆንም፡፡ ዛሬ ደህና ተሁኖ ነገ ላይኮን ይችላል፡፡ ሆኖም ሊሠሩ የሚችሉበት ደረጃ ከደረሱ እንዲሰሩ ነው የሚፈለገው፡፡ ሁል ጊዜ ተረጂ ከሚሆኑ ከእርዳታ እንዲወጡ እንርዳቸው ነው የምንለው፡፡ ለሌላውም ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ፡፡ መድሃኒት እየወሰዱ በደማቸው ያለው የቫይረስ ሁኔታ እየቀነሰና የጤንነታቸው ሁኔታ እየተሻሻለ ነው፡፡ እንደማንኛውም ሰው መኖር እንደሚችሉ ማመን ይኖርባቸዋል፡፡ የግዴታ ስንዴ ወይም ምግብ ስለቆመ መድሃኒት አቆማለሁ ማለት የዋህነት ነው፡፡ እኛ እየሰራን ያለነው ከዚህ ህይወት ውስጥ እንዲወጡ ነው፡፡ መድሃኒቱ የሚጠቅመው ቫይረሱን ለመቀነስ እንጂ በራሱ ምግብ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ሰርተው ቤታቸው ሲገቡ ነው ለአእምሯቸውም ጥሩ የሚሆነው፡፡ ይህንን እንዲያዳብሩ ነው የሚፈለገው፡፡

ሪፖርተር፡- ዝግጅት ተደርጓል?

ዶ/ር ዘላለም፡-
አዎ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ያሉ አስፈፃሚ አካላት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁና ወደ ሥራ እንዲመጡ ቀድመው እየነገሯቸው ነው፡፡  አማራጭም ተቀምጧል፡፡ ያለአማራጭ አይደለም የተተውት፡፡ አማራጩን ይጠቀሙበት ነው የምንለው፡፡ ለወደፊቱም አመለካከታቸው ከተረጂነት ወደ መሥራት ቢቀየር ጥሩ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የቤት ለቤት ተንከባካቢዎችን በተመለከተ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ቁሳቁስ (ኪት) እጥረት አለባቸው የሚሉ አስተያየቶች አሉ፤

ዶ/ር ዘላለም፡
- ኪቶችን በተመለከተ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ችግሮች ይነሳሉ፡፡ የኪቶችን ሁኔታ ከመጀመሪያውም ያደረግነው ኪቶችን በየክፍለ ከተሞች ባሉ ጤና ጣቢያዎች እንዲቀመጡና የቤት ለቤት ተንከባካቢዎች ከዚያ እንዲወስዱ ነው፡፡ ይህን ስናደርግ መጀመሪያ ኪቱን የሚያሟሉ ነገሮች አቅርበናል፡፡ ከዚህ በኋላ አስፈላጊና ጥቃቅን የሆኑ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ጤናን የተመለከተ፣ የቤት ለቤት እንክብካቤም ስለሆነና ቁስልን የማከምም ሊኖር ስለሚችል ኪቱን መጀመሪያ ከወሰዱባቸው ጤና ጣቢያዎች ውስጥ መረከብ ይችላሉ፡፡ ጤና ጣቢያው ካለው ኪቱን ይሰጣል፡፡ እኔ እዚህ ቦታ ከመጣሁ ጀምሮ ኪቶች ላይ ችግር አለ ሲባል አልሰማሁም፡፡ የትኞቹ ላይ ክፍተት እንዳለ እኛ ጋ ቢደርሰን ለየጤና ድርጅቶቹ የቻልነውን ልናደርግ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ከየጤና ድርጅቱ ሄደው እንዲረከቡ ስለተደረገ፡፡

ሪፖርተር፡- ቫዝሊንና አልኮል የለም ሲባል ነበር፤

ዶ/ር ዘላለም፡
- ኪቶቹን የሰጠነው ለጤና ድርጅቶች ነው፡፡ አልኮልና ቫዝሊን የሌለው ጤና ድርጅት የለም፡፡ የቤት ለቤት ተንከባካቢዎች ያለቀባቸው ጊዜ አካባቢያቸው ወደሚገኘው ጤና ድርጅት ሄደው ቢጠይቁ አይከለከሉም፡፡ ገፍቶም በጤና ጣቢያዎቹ ችግር አለ ከተባለ ወደ ጽህፈት ቤቱ መምጣት ይቻላል፡፡ እኛ ካወቅነው ከድርጅቶች ጋር ተነጋግረንም ልናሟላው እንችላለን፡፡ ጥቃቅን ነገሮች ናቸው፡፡ አንድ ወቅት ላይ ጓንት የለም ተብሎ ነበር፡፡ በወቅቱ ጤና ጣቢያዎች ላይም እጥረት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ችግር አልሰማሁም፡፡ የከፋ ነገር ካለ ቢገልፁልን መፍትሄ መፈለግ እንችላለን፡፡ ፕሮግራሙን የሚረዱ ብዙ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነሱን ማስተባበር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የኤምሳፕ ፈንድ አላማው ምን ነበር?

ዶ/ር ዘላለም፡-
ኤምሳፕ ወይም ኢትዮጵያን መልቲ ሴክተራል ፕላን ኦፍ አክሽን ፎር ዩኒቨርሳል አክሰስ ኤንድ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ትሪትመንት ኤንድ ኬር ሳፖርት ኢትዮጵያ ፕሮግራም የተጀመረው ቀደም ብሎ ሲሆን አሁን ሁለተኛው ዙር ላይ ነው ያለው፡፡ ኤምሳፕ አንድ (ማፕ አንድ) በሚል ነበር መጀመሪያ የሚታወቀው፤ በዚህ ፕሮግራሙ በየክፍለ ከተሞች ውስጥ የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር እናውቃለን፡፡ በዚህ ስር የተያዘ በጀት ተከፋፍሎ ሥራዎቹ እያለቁ ነው፡፡ በሁለተኛው ፕሮግራም ላይ ግን የተለያዩ ችግሮች ስለነበሩ የተሠራው ሥራ ብዙም አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሮቹ ምን ነበሩ?

ዶ/ር ዘላለም፡-
በከተማ ደረጃ ጽህፈት ቤቱ የራሱ የአወቃቀር ሁኔታና እንዲሁም በየክፍለ ከተሞቹ ያለው አወቃቀር ሥራዎችን ማሰራት የሚችል አልነበረም፡፡ ይህ ፕሮግራም የሚያዛቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ ጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባም ይሁን በየክፍለ ከተማ ደረጃ የአስተዳደርና የገምጋሚ ቦርድ ማቋቋም እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ፕሮጀክቶች ሲመጡ በገምጋሚና በአስተዳደር ቦርድ ታይቶ ሥራዎች መሥራት እንዳለበት ነው የሚገልፀው፡፡ ነገር ግን ይህ ባለመኖሩ በከተማም ሆነ በክፍለ ከተማ  ደረጃ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም የክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚቀርቡትን ፕሮጀክቶች አይቶና አፅድቆ አስፈፃሚ እንዲመርጥና ወደ ሥራ ለሚገቡት እንዲያስተላልፍ ከሚል ስምምነት ተደርሶ ተጀምሮ ነበር፡፡ አሁን ችግሮች በሙሉ እየተቀረፉ ናቸው፡፡ በከተማም በክፍለ ከተማም ደረጃ የአስተዳደርና የገምጋሚ ቦርዱ ተቋቁሞ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ፕሮግራሞቹን እያስተላለፍን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኤምሳፕ ዙር ሁለት ተላልፋል ማለት ነው? ሥራ ተጀምሯል?

ዶ/ር ዘላለም፡-
የተላለፈ አለ፡፡ አስቸኳይ የሆኑ ሥራዎችም አልቆሙም፡፡ በክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እየፀደቀ ወደ ሥራ የተገባበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ቦርዱ በአስሩም ክፍለ ከተሞች ተቋቁሟል፡፡ በከተማም ደረጃ እንዲሁ፡፡ አሁን ፕሮጀክቶችን ወደመቀበል እየመጣን ነው፡፡ የተቀሩትን ሥራዎች ለመሥራት ዝግጅት ላይ ነን፡፡ የአስተዳደር ቦርዱ ሶስት፣ የገምጋሚው ደግሞ ሁለት ስብሰባዎችን አካሂዷል፡፡ የትኞቹ የፕሮጀክት ዓይነቶች በከተማ ደረጃ እንዲሁም የትኞቹ በክፍለ ከተማ ደረጃ እንደሚታዩ ዝርዝር እየተቀመጠ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል ድርጅቶች ፕሮጀክቶቻቸውን እንዲያቀርቡ ይገለፃል፡፡ ለዚህም ረቂቁ እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክት ማቅረቢያ ጊዜው መቼ ይገለፃል ብላችሁ ታስባላችሁ?

ዶ/ር ዘላለም፡-
የገምጋሚ ቦርዱ ነው ይህንን የያዘው፡፡ ረቂቁን ጨርሰዋል፡፡ በቅርብ ቀናት ውስጥም ይሰበሰባሉ፡፡ ወደ ሥራም ልንገባ ነው፡፡ የሥራ መቆም ሳይሆን የገንዘቦች አለቃቀቅ መዘግየት ነው ያለው፡፡ የዘገየውም ቦርድ ባለመኖሩ ምክንያት ነበር፡፡ ወደየክፍለ ከተማውም የበጀት ዓይነቱ ተለይቶ እየተላከላቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የበጀት ዘግይቶ መለቀቅ ክፍለ ከተሞች እንደ ችግር ያነሱታል፤

ዶ/ር ዘላለም፡-
የበጀት መዘግየቱ የተፈጠረው የአስተዳደርና የገምጋሚ ቦርድ ባለመኖሩ ምክንያት ነበር፡፡ ይሄ በሌለበት በጀት መልቀቅ አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል በየክፍለ ከተማ ያሉ ድርጅቶችም ይሁኑ በየክፍለ ከተማው ያለው አሰራርም የሚይዝ ነገር አለው፡፡ የተላኩ ፈንዶች በየጊዜው እየተወራረዱ አይደለም፡፡ በጊዜው ቶሎ እንዲወራረዱ ይፈለጋል፡፡ አንዱ ሳይወራረድ ተጨማሪ መስጠት አንችልም፡፡ የማወራረድ አቅማቸውን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በሰው ሀይል መጠናከር አለባቸው፡፡ ይህንንም ጀምረናል፡፡ አሰራሩን የሚያፋጥኑ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ በእኛ በኩል ቦርዱ ስላልነበረ የተወሰኑትን ነገሮች ብቻ ነበር ወደ ክፍለ ከተማ የምንልከው፡፡ የአስተዳደርና የገምጋሚ ቦርድ ስላልነበር የመጣውን ሁሉ ማውረድ አይቻልም ነበር፡፡  አሁን ቦርዱ ስለተቋቋመ መውረድ የሚገባው ይወርዳል፡፡ ተጀምሯልም፡፡ ከእነሱ የሚጠበቀው የተሰጠውን ገንዘብ በየጊዜው ማወራረድ፣ ያሸነፉ ፕሮጀክቶችን መከታተልና በቅርበት ስራዎችን ማገዝና ማስተካከል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በክፍለ ከተማ ክፍተት መኖሩ ታውቋል፡፡ በእናንተስ በኩል ያለው ችግር፤

ዶ/ር ዘላለም፡-
ያለውን ችግር አውቀናል፡፡ በሰው ሀይል በኩል በሁላችንም ጋ ችግሮች አሉ፡፡ እሱን ወደመፍታት እየሄድን ነው፡፡ የአዲስ አበባ ኤች.አይ.ቪ. መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት መዋቅርን ሙሉውን እየቀየርን ነው፡፡ ቦርድ ማቋቋም አንዱ ነው፡፡ የጽህፈት ቤቱን መዋቅር በአዲስ መልክ ለማዋቀር አስፈላጊ ጉዳዮች በአዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ፀድቀው መጥተዋል፡፡ በቀጣይም የሚፀድቁ ይኖራሉ፡፡ የእኛን መዋቅር ስንጨርስ በየክፍለ ከተማው ያለውን መዋቅር የምናይበትና የምንቀይርበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ የምንሰራው የሰው ሀይልና ድባብ የሚፈጥር ነው፡፡ ጥሩ ጅምሮችም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡-  የፕሮጀክት ተለዋዋጭነት የሚባለውስ?

ዶ/ር ዘላለም፡-
  ይህ ከደብሊው.ኤፍ.ፒ ጋር ይያያዛል፡፡ ዛሬ አንዱ ተብሎ ነገ ሌላ ይባላል ነው፡፡ ይህ ከበጀትና ከውል ሁኔታ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ እስኪስተካከሉ ጊዜያዊ የሆነ የፕሮጀክት ተለዋዋጭነት ይኖራል፡፡ ሆኖም ፕሮጀክቱ ተለውጧል ማለት አይደለም፡፡ ድንገት በሚፈጠሩ ጉዳዮች የሚመጣ የአሰራር ሂደት እንጂ ተለዋዋጭነት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከእናንተ ለትምህርት ቢሮ የተለቀቀ ገንዘብ ወደ ክፍለ ከተሞች አለመውረዱ በስድስት ወር ሪፖርት ላይ ሲቀርብ ነበር፡፡ የሥራ ሂደቱን የምትቆጣጠሩበት ስልት የለም?

ዶ/ር ዘላለም፡-
የምንቆጣጠርበት መንገድ አለ፡፡ እንደ አንድ አጋር አካል በትምህርት ቢሮ በኩል የምንለቀው ገንዘብ ይኖራል፡፡ ለሌሎች ቢሮዎችም የምንሰጠው ይኖራል፡፡ ትምህርት ቢሮ ያንን ወስዶ በራሱ ነው የሚሰራው፡፡ ትምህርት ቢሮ በየክፍለ ከተማው በትምህርት መምሪያ ደረጃ የራሱ መዋቅር አለው፡፡ እነሱ በራሳቸው መንገድ ይሄዳሉ፡፡ ዋናው ችግር የሪፖርት ማድረግና አለመነጋገር ነው፡፡ የተሠሩ ስራዎችን ከዴስኩ ጋር ተቀናጅቶ አለመስራት ነው የሚታየው፡፡ በትምህርት ቤቶች የተሠሩ ሥራዎች በትምህርት ቢሮ በኩል ቀርቧል፡፡ ክፍተቱ መረጃ ያለማግኘትና ተቀናጅቶ ያለመሥራቱ ላይ ነው፡፡ ትምህርት ቢሮው በራሱ በኩል ሥራውን ሰርቷል፡፡ ሆኖም የሰው ሃይል እጥረት አንዱ ችግር ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የተሠሩ ሥራዎችን አስመልክቶ ከክፍለ ከተሞች ጋር መለዋወጥ እንደሚያስፈልግ ተነጋግረንበታል፡፡ ጤና ላይም የዚሁ ዓይነት ችግር ነበር፡፡ ጤና ጣቢያዎች ተጠሪነታቸው ለጤና ጽህፈት ቤት ነው፡፡ ዴስኩ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ሥራዎች ግን ተሰርተዋል፡፡ ሪፖርቱ ሲቀርብ ለመረዳት እንደተቻለው የነበረው ክፍተት ተቀናጅቶ ባለመሥራት የመጣ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሰፊ ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የጽህፈት ቤታችሁ መዋቅር እስከታች አብረዋችሁ የሚሰሩትን በአንድ ስር የሚያስገባ ይሆናል?

ዶ/ር ዘላለም፡-
እንደዚያ ነው የማስበው፡፡ እዚህ የሰው ሃይል ይጨመራል፡፡ አንድ ሰው ሶስት አራት ቦታ ላይ ደርቦ እንዲሰራ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ ይህንን መበተን ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የሚችለውን መሥራት አለበት፡፡ ይህንን ስናደርግ ነው በየቢሮዎች ክትትሉ የሚጠናከረው፡፡
 
< Prev   Next >