Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ግላውኮማ
ግላውኮማ Print E-mail
Sunday, 09 March 2008
Image
አቶ ዘገየ ኃይሌ
Image
ዶክተር አበባ ተክለጊዮርጊስ
Image
ዶክተር ባየህ ዓለሙ
Image
ግላውኮማ ቀስ በቀስ ዓይነስውርነትን የሚያመጣ ነው፡፡ ስለሆነም ለኅብረተሰቡና ለዓይን ሕሙማን ስለ በሽታው ያላሰለሰ፣ ቀጣይነት ያለው፣ በተለያየ ዘዴና መንገድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት እንደሚጠበቅ ተገለፀ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና አጋሮቹ ህሙማን በተቻለ መጠን በአካባቢያቸው እንደ አቅማቸው የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ ቀስ በቀስ ማመቻቸት እንደሚኖርበት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሌሎች በሽታዎች መከላከያ ቡድን መሪና የብሔራዊ ዓይነስውርነት መከላከያ ኮሚቴ ሊቀመንበር አስታወቁ፡፡
 
የኢትዮጵያ የአይን ሕክምና ማኅበር የዓለም የዓይን ግፊት ህመም (ግላውኮማ) ቀን ምክንያት በማድረግ የካቲት 27 ቀን 2000 ባካሄደው ስብሰባ ላይ ሊቀመንበሩ አቶ ዘገየ ኃይሌ እንዳመለከቱት ሕሙማኑ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ብቻ ሳይሆን በብቃትና በብዛት ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ አስፈላጊ ግብአቶችን ማሟላትና ተቋማትን መገንባት የግድ ይላል፡፡

በአገሪቱ በቅርቡ በተደረገው ጥናት 1.6 በመቶ ወይም ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ማየት የተሳናቸው እንዳሉና ከእነዚህም መካከል 5.2 ከመቶ ያህሉ ግላውኮማ መሆኑን አቶ ዘገየ አስረድተዋል፡፡

ዶክተር አበባ ተክለጊዮርጊስ የማኅበሩ ምክትል ሊቀመንበር በበኩላቸው እንዳመለከቱት ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት ትኩረት ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ዋነኛ ተግባራት አንዱ የዓለም ጤና ድርጅትና ተባባሪዎቹ የጀመሩትን ቪዥን 2020 "ዘ ራይት ቱ ሳይት" በሚል መርህ የጀመሩትን መርሃ ግብር በአገራችን በሥራ መተግበር ነው፡፡ የዚህም መርሃ ግብር ዋነኛ ግብ መከላከልና በሕክምና መዳን የሚችሉትን ዓይነ ስውርነትን የሚያስከትሉ በሽታዎችን እ.ኤ.አ እስከ 2020 ማጥፋት ነው፡፡ ከእነዚህም በሽታዎች ዋና ዋናዎቹ የሞራ ግርዶሽ፣ ትራኮማ፣ የቫይታሚን ኤ እጥረት፣ የሳይት ችግር እና ግላውኮማ ናቸው፡፡

በዓለም ከ105 በላይ የዓይን ግፊት ህመም (ግላውኮማ) ተጠቂዎች አሉ፡፡ 9.1 ሚሊዮን ደግሞ በሕመሙ ምክንያት ለዓይነ ስውርነት ተዳርገዋል፡፡ ግላውኮማ በአብዛኛው በአፍሪካ አገራት አይነ ስውርነትን በማስከተል በሁለተኛ ደረጃ ይፈረጃል፡፡ በአገራችንም በቅርቡ በተደረገው አገር አቀፍ ጥናት ግላውኮማ ዓይነስውርነትን ከሚያስከትሉ ዋና ዋና መንስኤዎች አንዱ ሆኗል፡፡ የዓይን ግፊት ሕመም ከሌሎች ለየት የሚያደርገው የዓይን ብርሃን አንዴ ከታጣ በሕክምና የማይመለስ መሆኑን ነው፡፡

በአደጉ አገሮች 50 ከመቶ፣ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች 90 ከመቶ የሚሆኑ ተጠቂዎች ሕመሙ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ ምክንያቱም የሕመሙ ባህሪይ በአብዛኛው የሕመም ስሜት ሳይኖረው ቀስ በቀስ የእይታ አድማስን እያጠበበ በመጨረሻም የዓይንን ብርሃን ሙሉ በሙሉ የሚያሳጣ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ስለ ሕመሙ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለ ግንዛቤ አናሳ መሆን ነው፡፡

ዶክተር ባየህ ዓለሙ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓይን ሕክምና ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር "የዓይን ሕክምና በዩኒቨርሲቲው ስር ሆኖ ከተቋቋመ 28 ዓመታትን አሳልፏል፡፡ እስካሁንም ባለፈባቸው ዓመታት ወደ 80 የሚሆኑ የዓይን ሐኪሞችን አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡ ከምሩቃኑ ውስጥ አስሩ ተመርጠው የማስተማሩን ሂደት በጥራትና በብቃት እያካሄዱ ነው" ብለዋል፡፡

በዓለም ውስጥ በበሽታው ከተጠቁት ሕዝቦች መካከል አብዛኛው የሚገኘው በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች መሆኑን በዚህም ላይ የሕክምና ተቋማት ማነስ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እና የሚያስፈልጉ መድሃኒቶች አለመገኘት ቢገኙም ዋጋቸው ከፍተኛ እና ከኅብረተሰቡ የመግዛት አቅም በላይ መሆን ሕክምናውን ውስብስብ እንዳደረገው ዶክተር ባየህ አስረድተዋል፡፡

በሽታው አጣዳፊ ምልክት ስለሌለው፣ ሕመምተኛው የታዘዘለትን መድሃኒት ሲያቋርጥ ወይም በመርሳት ችግሩን እንዲያባብስ ያደርገዋል፡፡

የግላውኮማ በሽታ ታማሚ የሆነው ወጣት ሰለሞን አሊ በበኩሉ "አይኖቼ ለረጅም ዓመታት በጣም ይቀሉ ነበር፡፡ አልፎ አልፎም የማሳከክ ስሜት ነበራቸው፡፡  ወደ ሕክምና መስጫ በመሄድ ምንም አይነት ምክርም ሆነ ምርመራ ሳላደርግ ለረጅም ዓመታት ቆየሁ፡፡ በአይኖቼ ላይ የህመም ስሜት ስለማይሰማኝ ነበር ያልሄድኩት" ብሏል፡፡ በመካከሉ የአይኖቹ ነርቭ ክፉኛ ተጎዱ፡፡ አልፎ ተርፎም የእይታ አድማሱ  ያነሰ ሆኖ ተገኘ፡፡ በዚህም የተነሳ ሁለቱንም አይኖቹን ቀዶ ሕክምና ማድረግ ግድ ሆነበት፡፡ ምክንያቱም የአይኑ ግፊት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ በቅርብ ጊዜ አይኑን ሊያጠፋው ስለሚችል ነበር፡፡ ከቀዶ ሕክምና በኋላ የእይታ አድማሱን መጨመር ባይቻልም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡

ወይዘሮ አዲስዓለም ወልደአረጋይ በበኩላቸው የ11 ወር ሕፃን ልጃቸው በግላውኮማ በሽታ ተይዞ እንደነበር ይህም በሽታ ያደረባት ገና በዘጠኝ ወሯ እንደሆነና ሲጀምራት ዓይኖቿ ጉም እንደለበሱ አስረድተዋል፡፡ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ተቋም በመወሰድ በቀዶ ሕክምና ከበሽታዋ ልትገላገል እንደቻለችና በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡

በታደሰ ገብረማርያም
 
< Prev   Next >