Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow የመብትና ፍትሕ ፊልም ፌስቲቫል...
የመብትና ፍትሕ ፊልም ፌስቲቫል... Print E-mail
Sunday, 09 March 2008
የመብትና ፍትሕ ፊልም ፌስቲቫል ለሁለተኛ ጊዜ ይካሄዳል

አዲስ ዓለም አቀፍ የመብትና ፍትሕ ፊልም ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ ኢኒሼቲቭ አፍሪካ አስታወቀ፡፡ “ያልተደራጀውን ማደራጀት” በሚል መሪ መልእክት ዙሪያ የተሠሩ ዓለም አቀፍና የአትዮጵያ ረዥም ጥናታዊና አጫጭር ፊልሞች ከመጋቢት 12 እስከ 21 ባሉት ቀናት ይቀርባሉ፡፡

የኢኒሼቲቭ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና እንደገለጹት በፌስቲቫሉ የመክፈቻ ምሽት “ብላክ ጎልድ” የተሰኘው ጥናታዊ ፊልም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሴባስቶፖል ሲኒማ አዳራሽ ይቀርባል፡፡

በሁለተኛው አዲስ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል የሚቀርበው ..ብላክ ጎልድ.. በውጩ ዓለም የሽልማት አሸናፊ ሲሆን ፊልሙ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የኢትዮጵያን የቡና አብቃይ ገበሬዎች ሕይወት ያሳያል፡፡

በአሜሪካና በአውሮፓ ለአንድ ስኒ ቡና በወተት (ማኪያቶ) አሊያም ካፑችኖ የኢትዮጵያ 33 ብር ያህል ይከፈላል፡፡ የኢትዮጵያ የቡና አብቃይ ገበሬዎች ግን ልፋታቸውን የሚመጥን ክፍያ ማግኘት ባለመቻላቸው የቡና እርሻቸውን በመተው ከቀያቸው ለመፈናቀል ይገደዳሉ፡፡

ይህንኑ ሕይወት የሚያንፀባርቀው “ብላክ ጎልድ” ፊልም በመሪ ገፀ ባህርይነት የሚጫወቱት አቶ ታደሰ መስቀላ የኦሮሚያ ቡና አብቃይ ገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሊቀመንበር ናቸው፡፡

ከኪሳራ ለመዳን የሚጣጣሩ 74,000 የሚደርሱ የቡና አብቃይ ገበሬዎችን ህይወት የመታደግ ተልዕኮ ያነገበው ይኸው ፊልም መሪ ተዋናዩ፣ ባልደረቦቹና የቡና አብቃይ ገበሬዎች ለዓለም አቀፍ የቡና ገበያ የሚቀርብ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማምረት ሲጥሩ፣ አግባብነት ያለው ክፍያ በመክፈል ለመግዛት ፈቃደኛ የሆኑ ገዢዎችን ለማፈላለግ አቶ ታደሰ በመላው ዓለም ሲዟዟሩ ያሳያል፡፡

በኒክ ፍራንሲስ ዳይሬክተርነት የቀረበው “ብላክ ጎልድ” ፊልም በመላው ዓለም ለእይታ በቀረበበት ጊዜ ውዝግብ ያስነሳና የኢትዮጵያን የቡና አብቃይ ገበሬዎችን ሕይወት በማንፀባረቅ ግንዛቤ እንዲፈጠር ያስቻለ ነው፡፡

ኢኒሼቲቭ አፍሪካ መግለጫ እንዳመለከተው የፊልም ፌስቲቫሉ አምና ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ሲካሄድ ዋነኛ ግቡ የነበረው የሰብዓዊ መብትን ጉዳይ በፊልም አማካይነት ማስተላለፍና የዓለም፣ የአፍሪካንና የኢትዮጵያን ችግሮች ዓለም አቀፋዊ በሆነ መልኩ እንዲታይ በማስቻል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ ነው፡፡

በ”ያልተደራጀውን ማደራጀት” ዙሪያ የሚቀርቡት ፊልሞች በዓለም ዙሪያ በስፋት በመከናወን ላይ ያለውን የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታነት የመለወጥ ርእሰ ጉዳይ እንዲሁም በኢትዮጵያ የፌስቱላን ሕመም፣ በጦርነት ወቅት ሴቶች ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ የሠራተኛ ማኀበራትና ሌሎች ጭብጦች ላይ ያተኩራሉ፡፡

በዘመነ ደርግ ቀይ ሽብር ላይ ተመሥርቶ የተሠራውና የእንግሊዝኛ መግለጫ ያለው “ዘፋዘር” (አባትየው) የተሰኘው የታዋቂው ኤርምያስ ወልደ አምላክ ፊልም በፌስቲቫሉ ከሚቀርቡት ፊልሞች አንዱ ነው፡፡ “ዘፋዘር” በዓለም አቀፍ ፊልሞች መድረክ ተሳትፎ አድናቆትና ሽልማት ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

 
< Prev   Next >