| ሴቶችን የሚመለከቱ ህጎች ላይ... |
|
|
| Sunday, 09 March 2008 | |
![]() ወ/ሮ ማህደረ ጳውሎስን የካቲት 29 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም. (ማርች 8) ፣ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ትናንትና ተከብሯል፡፡ ለፆታዊ እኩልነት እንታገላለን የሚሉ ተቋማት በተለይ ለበዓሉ ልዩ ትኩረት ሰጥተውታል፡፡ ለፆታዊ እኩልነት እንታገላለን በሚል ከተቋቋሙ ማህበራትና ተቋማት መካከል የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አንዱ ነው፡፡ ከበዓሉ ጋር በማያያዝ ተቋሙ ባከናወናቸው ሥራዎች የመጡ ለውጦች፣ በሴቶች እኩልነት ላይ እንቅፋት በሚፈጥሩ የህግ ክፍተቶች ላይ የማህበሩን ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ወ/ሮ ማህደረ ጳውሎስን አነጋግረናቸዋል፡፡ በየዓመቱ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ማህበሩ የተለያዩ ኘሮግራሞችን የሚያቅድ ሲሆን ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከል የሚንቀሳቀስ ጥምረት አባል ስለሆነና ያቀዷቸው ነገሮች በጥምረቱ ዘመቻ የታቀዱ ሆነው ስላገኘቸው አንድ ላይ አክብረዋቸዋል፡፡ በተናጠል ደግሞ ተደማጭና ተነባቢ በሆኑ ሚዲያዎች ስለሴቶች የተለያዩ መልእክቶችን ማስተላለፍ የኘሮግራማቸው አካል ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ መልእክቶችን ሊያስተላልፉ የሚችሉ አጭር አጭር ነገሮች ታሳቢ በማድረግ ስፖቶችን አዘጋጅተው በሶኒክ ስክሪንና በቴሌቪዥን ለህብረተሰቡ እንደሚያስተላልፉ ገልፀዋል፡፡ ይህም በዚህ አጋጣሚ ህብረተሰቡ ስለሴቶች መብትና እየደረሰባቸው ስላሉ በደሎች እንዲያውቅ ይረዳዋል ተብሎ የታቀደ መሆኑን ገልፀውናል፡፡ ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሴቶችን ፆታዊ በደል ለማስቀረት ያደረጋችሁት አስተዋፅኦ ምን ይመስላል? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ማህበሩ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በተቻለ መጠን የሴቶችን ችግር ለመቅረፍ ቀደም ሲል ነድፎት በነበረው ሦስት ዓላማዎች መሠረት ይሠራል፡፡ ዓላማዎቹን ለማስፈፀም ይረዳሉ ተብለው የተቀመጡ ኘሮግራሞችም አሉ፡፡ በአገሪቱ ስድስት ክልላዊ ቢሮዎች ውስጥ ቢሮዎች ከፍተው በተጨማሪም ከነሱ ሥር በሚገኙ ማዕከሎች በአገር አቀፍ ደረጃ ላሉ ሴቶች አገልግሎት ለመስጠት መሞከሩን ወ/ሮ ማህደረ አስረድተዋል፡፡ በዞንና ወረዳ ደረጃ አገልግሎት በሚሰጡባቸው ማዕከላት ለሴቶች ያደረጉትን አስተዋፅኦ አስመልክቶም ባለሙያዋ እንደገለፁት ድርጅቱ የተመሰረተው ህገ መንግሥቱ ፀድቆ ከወጣ በኋላ በመሆኑ ህጉ ከሴቶች ፆታዊ እኩልነት ያለውን ጠቀሜታ መፈተሽ ዋናው ሥራ ሆኗል፡፡ “ህገ መንግሥቱ ሴቶችን በሚመለከት የተለያዩ በጣም ጠቀሜታ ያላቸው አንቀፆች አስቀምጧል፡፡ ዓለም አቀፍ ህጎችንም የሃገሪቱ የህግ አካል ናቸው ብሎ አፅድቋል፡፡ መጀመሪያ ድርጅቱ የተንቀሳቀሰበት ሥራ አድሏዊ የሆኑ ህጎች፣ ልማዶችና ወጎች የተከለከሉ ናቸው በሚለው ነው፡፡ በህግ ረገድ የትኞቹ ናቸው አድሏዊ የሆኑት የሚለውን ማጣራትና መፈተሽ የመጀመሪያው ዓላማ ነበር፡፡” በቀጥታ ከሴቶች ህይወት ጋር ተያያዥነት ያለው በቤተሰብ፣ በትምህርት በሥራ እና በዜግነት ዙሪያ ያሉትን ህጎች መፈተሽ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በመምረጥ ጥናት ሲያደርጉ የቆዩ መሆናቸውንም ወ/ሮ ማህደረ ገልፀዋል፡፡ የተደረገው ጥናትም አድሏዊ ህጎቹ የትኞቹ እንደሆኑ በግልፅ ማሳየቱን ይናገራሉ፡፡ ከጥናቶቹ ግኝቶች በመነሳትም መሻሻል ያለባቸው ህጎች፣ ለአፈፃፀም የሚያስቸግሩ ክፍተቶች መኖራቸውን በማንሳት ህጎቹ እንዲሻሻሉ ግፊት የመፍጠር ሥራ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ እንደባለሙያዋ አባባል ከሆነ በቤተሰብ ሽምግልና ጉባኤ፣ በቀለብ ረገድ ባጠቃላይ በትዳር ውስጥ ወንዶችና ሴቶች ያላቸው ሚናና መብትን በሚመለከት ፍፁም አድሏዊ የሆኑ ነገሮችን ለማየት ስለተቻለ ማህበሩ ህጎቹ በምን መልኩ መሻሻል አለባቸው ለሚለው የራሱ የሆነ አስተያየት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም ለሴቶች የህግ ምክር አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ችግሮችን በተግባር ለማየትም የህግ ምክር አገልግሎት መስጫ ተቋሞቹ ዋና ምንጭ እንደነበሩ ወ/ሮ ማህደረ ገልፀውልናል፡፡ ሲጀመር በቀን አንድ ሰው ይስተናገድባቸው የነበሩ የምክር አገልግሎት መስጫ ተቋማቱም ዛሬ በዓመት ነባርና አዲስ ከ16 ሺህ ሰው በላይ የተስተናገደበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በርካታ ሴቶች የህግ ምክር አገልግሎት ማግኘታቸውን አስረድተው በተጨማሪም “ጥብቅና ቆመንላቸው ከፍቺ በኋላ በትዳር ወቅት ያፈሩትን ንብረታቸውን የተካፈሉና መብታቸው የተጠበቀላቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡ ዋናው ግን እ.ኤ.አ በ2ዐዐዐ የቤተሰብ ህጉ ተሻሽሎ በመውጣቱ ትልቅ ለውጥ ነው” ብለዋል፡፡ ተሻሻለ ሲባልም ከዘጠና በመቶ በላይ በድርጅቱ ሲጠየቅ የነበረው ነገር ተፈፃሚ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ህግም በግልፅ አድሏዊ የነበሩ ህጎች ተወግደዋል፡፡ ባልና ሚስት በሁሉም ረገድ፣ ጋብቻ ከመፈፀማቸው በፊት፣ በጋብቻ ወቅትና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት እንዳላቸው አረጋግጧል፡፡ የሴቶች መብት እንዲጠበቅ የቤተሰብ ህጉ ብቻ ሳይሆን የወንጀል ህጉ መሻሻሉም ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ወ/ሮ ማህደረ ይናገራሉ፡፡ በወንጀል ህጉ በኩልም በርካታ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ፡፡ ቀደም ሲል የነበረው የወንጀል ህግ በሴቶች ላይ የሚደርሱ የኃይል ጥቃቶች የሀይል ጥቃት ስለመሆናቸው እውቅና አይሰጥም ነበር፡፡ ይህም ማለት ጠለፋም አስገድዶ መደፈርም ወንጀል መሆናቸው ተቀምጦ እያለ ልጅቷ የጠለፋትን ወይም አስገድዶ የደፈራትን ወንድ እንደምታገባው ከተስማማች የተጀመረ ክስም ቢኖር እንደሚነሳ ያስረዳል፡፡ እዚሁ ላይ ማህበራቸው አቋሙን ሲያሰማ መቆየቱን ወ/ሮ ማህደር አስረድተዋል፡፡ ጋብቻ በስምምነት ላይ የተመሰረተ እስከሆነ ድረስ አስገድዶ መድፈሩም ሆነ ጠለፋው ፈፅሞ መጋባት አይቻልም ነበር፡፡ ከጠለፋና አስገድዶ መድፈር በኋላ የሚፈፀም ጋብቻ ከማስፈራራትና ከዛቻ ወይም ከኃይል ጋር የተያያዘ ስለሆነ ወንጀል ነው ስንል ቆይተናል፡፡” በተጨማሪም በወንጀል ህጉ ግርዛትና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር (በህገ ወጥ መልኩ ሴቶችን ለሥራ በግል ወደ ውጭ የሚልኩትን ጨምሮ) በስፋት የተካተተው በተሻሻለው የወንጀል ህግ ላይ ነው፡፡ የቤት ውስጥ ጥቃትና ወሲባዊ ትንኮሳም ሴቶችን ሙሉ በሙሉ የህግ ጥበቃ እንዲያገኙ በሚያደርግ መልኩ ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ተካቷል፡፡ በአጠቃላይ የተሻሻሉ ህጎች የብዙ ሴቶችን ህይወት ታድገዋል ማለት እንደሚቻል ነው ወ/ሮ ማህደረ የገለፁት፡፡ ለህጎቹ መሻሻልም የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር አስተዋፅኦ ከፍ ያለ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ “እነዚህ የተሻሻሉ ህጎች ማህበራችን በተለያዩ መድረኮች እንዲሻሻሉ ግፊት ሲያደርግባቸው የቆዩ ናቸው፡፡ ህጉ ከመሻሻሉ በፊትም ማህበሩ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ አቋሙን እንዲገልፅ የተደረገበት ሁኔታ ነበ፡፡” ህጉ ከተሻሻለስ በኋላ የሴቶች ፆታዊ እኩልነት እንዳይከበር ምክንያት የሚሆኑ የህግ ክፍተቶች የሉም ወይ የሚል ጥያቄም አንስተንላቸው ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ በተለይ አተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ጠቅሰው አንድም በዳኞች አተረጓጎም ምክንያት የተፈጠረ ክፍተት እንዲሁም ህጉ በግልፅ ባለመቀመጡ ምክንያት ለትርጉም ክፍት ሆኖ ያስቸገረበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ አንዳንድ ጉዳዮች በሌላው ይሸፈናሉ ወይም ጠቅለል ባለ መልኩ በመቀመጣቸው ምክንያት ዘርዘር ብለው ሲመጡ ለመተግበር ያስቸግራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ልዩ የሆነ አንቀፅ የሚያስፈልጋቸውና ከሌላው ጋር ተደርበው በቁንፅል የተቀመጡ አሉ፡፡ ለአተገባበር ከሚያስቸግሩ ህጎች መካከል አንዱ የካሳ ጉዳይ ነው፡፡ ካሳ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ የሚሰጥ ነው፡፡ ሆኖም በትዳር ውስጥ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈፀም ሚካሰው እንዴት ነው? መጠኑስ ምን ያህል ነው? ለሚለው በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ የድሮው የፍትሐብሔር ህግ ላይ የሞራልን ካሳ 1ዐዐዐ ብር ብሎ አስቀምጦታል፡፡ ሌላውን ግን በደረሰው ጉዳት መጠን ይላል፡፡ አሁን የቤተሰብ ህጉ ተሻሽሎ ሲወጣ የካሳ መጠኑን በድሮው የፍትሐብሔር ህግ መሠረት ነው የሚመዝነው? ወይስ እንዴት ነው? እንዲህ ዓይነት ተጨባጭ የታዩ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን ነው ባለመያዋ የሚያስረዱት፡፡ በህጉ ጭራሽ ያልተካተቱ ነገሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ከፍቺ መለስ ያለ የቀለብ ጥያቄ አንዱ ነው፡፡ ትዳራቸው ሲፈርስ በተለይ የዕለት ገቢ የሌላቸው ሴቶች መጨረሻ ላይ ባዶ እጃቸውን የመቅረት ነገር መኖሩን ወደ ማህበራቸው ከሚመጡ አብዛኞቹ ሴቶች ተሞክሮ ያገኙት ነው፡፡ ይህ በሌሎች ሃገሮች ቢያንስ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ እንድትቋቋም የቀለብ ይሰጣል፡፡ መንግሥትም በሚደጉምበት ሁኔታ ባደረጉት ሃገራት ለቀለብ ተጠቃሚ የሚሆኑት ወንዶችም ጭምር ናቸው፡፡ ምክንያቱም አንዳንዴ በኢኮኖሚ አቅማቸው ሴቶች የተሻሉ የሚሆኑበት አጋጣሚ ስላለ፡፡ በእኛ ሃገር ግን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የገቢ ችግር ያለባቸው ሴቶች በመሆናቸው ጥያቄው ሴቶችን ይመለከታል፡፡ በመሆኑም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የቀለብ ጉዳይ በህጉ እንዲካተት ግፊት የመፍጠር ሥራ ማህበሩ መጀመሩን ወ/ሮ ማህደረ ገልፀዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን በሃገራችን መከበር ከጀመረ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሆኗል፡፡ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለ የአመለካከት ለውጥና እየደረሱ ያሉ ፆታዊ በደሎች ሲታዩ ግን በደሉ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስቸገረውም እንደ ወ/ሮ ማህደረ “በእርግጥ ለውጡ በጣም ዘገምተኛ ነው፡፡ ለውጥ የለም ብለን ግን ባንደመድምም በተለይ ያልተማረውን ክፍል መለወጥ አስቸጋሪ ቢሆንም የአመለካከት ችግር ስለሆነ በተማረውም ላይ ይስተዋላል፡፡ በመማር ብቻ አንዳንድ ጊዜ አመለካከት የማይለወጥበት ሁኔታ አለ፡፡ በርግጥ ትምህርት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ አመለካከት ግን ውስጥን የማሳመን ጉዳይ ነው፡፡ ማስመሰል ሳይሆን ከውስጥ ለውጥን ይጠይቃል፡፡ ስናድግ እንደ ባህል ሆኖ አብሮን ያደገ ነገር ነው፡፡ በተለይ የሴቶች ችግር ብዙ ጊዜ ከባህል ጋር የተሳሰረ ስለሆነ የአመለካከት ለውጥ በጣም አዝጋሚ ነው፡፡” “በፆታ እኩልነት ደህና ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚባሉ ሃገራትን ስናይ እኛ ያለፍንበትን ሂደት አልፈው ነው እዛ የደረሱት፡፡ ስለዚህ እኛም እዛ ደረጃ ላይ የማንደርስበት ምንም ምክንያት የለም” ብለዋል፡፡ ጊዜው ሊረዝም ቢችልም ያሉት ሁኔታዎች ተስፋ ሰጭዎች በመሆናቸው ሴቶች መቼ ከፆታዊ አድልዎ ይላቀቃሉ ብሎ መገመቱ ከባድ ቢሆንም ብዙ ሩቅ ላይሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ ከሁሉም የሚጠበቅ ነገር መኖሩን አሳስበዋል፡፡ ወላጅ ለውጡን ለልጆቹ ማሳየትና የአስተዳደግ ለውጥ ማድረግ እንዳለበትም መክረዋል፡፡ ከህብረተሰቡም የሚጠበቅ ነገር ቢኖርም በህብረተሰቡ በኩል ያለው ጥበቃ እንደሚያሰጋ ይናገራሉ፡፡ “ድሮ አንድ ሰው መንገድ ላይ ቢደበደብ ህዝብ ተረባርቦ ያገላግላል፡፡ አሁን ግን አይቶ እንዳላየ እኔን አይመለከተኝም በሚል ስሜት ማለፍ በጣም ይስተዋላል፡፡ ሴቶችም ላይ በመንገድ አንድ ችግር ሲፈፀም አይቶ እንዳላየ የመሆን ነገር አለ፡፡ ነገር ግን እሱ ልጅ ላይ ተመሳሳይ ነገር ቢደርስ እንዴት ሰው ዝም አለ ብሎ የሚቆጨውን ዓይነት ቁጭት መቆጨት አለበት፡፡ አንዱ ለአንዱ ተቆርቋሪ መሆን አለበት፡፡ ቢያንስ አይተን ልናስጥል የምንችለውን ነገር ማዳን እንችላለን፡፡ ምክንያቱም የሴቶች ጥያቄ የሴቶች ብቻ አይደለም” ብለዋል፡፡ መንግሥት ህግ አውጭ ነው፣ ህግ አስፈፃሚ በመሆኑ በሴቶች ፆታዊ እኩልነት ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ በመሆኑም የወጡ ህጎችን ተግባራዊነትንና ወኪሎቹ በአግባቡ ህጉን እየተረጎሙት ስለመሆናቸው የመከታተል ኃላፊነት አለበት፡፡ በተቻለ መጠን በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለማስወገድ የሚቻልበትን ማናቸውም ዓይነት መንገድ የመቀየስ ኃላፊነት እና በኃላፊነት ያስቀመጣቸው ሰዎች በአግባቡ ሥራቸውን እየተወጡ መሆኑን መቆጣጠርና መከታተል እንደሚጠበቅበት ጠቅሰው መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም አካላት የድርሻቸውን ከተወጡ በሴቶች ላይ የሚደርሰው በደል የማይቀርበት ምክንያት እንደሌለ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ በትዕግሥት ዘሪሁን |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |