Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow "ጭቅጭቅን በመፍራት 'ቅንጅት'...
"ጭቅጭቅን በመፍራት 'ቅንጅት'... Print E-mail
Wednesday, 12 March 2008
Image
ዶ/ር ኃይሉ አርአያ
"ጭቅጭቅን በመፍራት 'ቅንጅት' የሚለውን ቃል አልተጠቀምንም"

ዶ/ር ኃይሉ አርአያ

ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በስም እንጂ በመንፈስ የተለወጠ አለመሆኑን፣ ጭቅጭቅን በመፍራት "ቅንጅት" የሚለውን ቃል ከመጠቀም መቆጠባቸውን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የካናዳ ቪዛ ተከለከሉ፡፡
 
የቅንጅት ስምና ምልክት በሌላ አካል ከተሰጠ በኋላ በቅንጅት ስም መንቀሳቀስ እንደማይቻል በመረዳት በአዲስ ስያሜ ፓርቲ ለማቋቋም መግባባት ላይ መደረሱን የጠቆሙት ዶ/ር ኃይሉ በቀድሞ የቅንጅት አባላት የተቋቋመው የአዲሱ ፓርቲ አላማና መንፈስ መስከረም 14 ቀን 1998 ዓ.ም የተመሰረተውን ቅንጅት መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለቀድሞ የቅንጅት አባላት፣ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ለሚገኙ ደጋፊዎች የአዲሱን ፓርቲ ስም በማውጣት ሂደት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ለአዲሱ ፓርቲ ስያሜ ከመቶ በላይ ሀሳቦች መቅረባቸውን የገለፁት ዶ/ር ኃይሉ የስያሜ ዝርዝሩ ለሥራ አስፈፃሚ ከቀረበ በኋላ ተጣርቶ የመጨረሻ ተጨማሪ የሆነው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ የሚለው ስያሜ መጽደቁን ተናግረዋል፡፡

ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የሚለውን ሃሳብ አሻሽሎ በማቅረብ "ቅንጅት" የሚለውን ቃል የያዘ ፓርቲ ይቋቋም የሚልና ፓርቲው በአዲስ ስም መተካት አለበት የሚሉ የተለያዩ ሃሳቦች ቀርበው ውይይት እንደተካሄደባቸው የጠቆሙት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው "ቅንጅት" የሚለው ቃል ከገባ ውዝግብና ጭቅጭቅ ሊያስነሳ ይችላል የሚል እምነት ስላሳደረ አዲስ ስም ቢሰየም ይሻላል የሚለው ሀሳብ እንዳመዘነና ተቀባይነት እንዳገኘ ገልፀዋል፡፡

"በአዲስ ስያሜ ፓርቲ ማቋቋማችሁ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንድታገኙ ያስችላችኋል?" ለሚለው ዶ/ር ኃይሉ ሲመልሱ "ፓርቲው አዲስ ነው ማለት አይቻልም የመስከረም 14/1998ቱን የቅንጅት ውህደት መንፈስና አላማ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ፓርቲው ለኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ አይሆንበትም፤ የስም ለውጥ እንደሚመጣም ህዝቡ አስቀድሞ አውቆታል" ብለዋል፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የአሁኑ አወቃቀር የቀድሞውን ቅንጅት አወቃቀር የተከተለ መሆኑን፣ ስልሳ የላዕላይ ምክር ቤት እና ሀያ ሥራ አስፈፃሚ አባላት እንዳሉት ዶ/ር ኃይሉ ገልፀዋል፡፡ የፓርቲው ዘላቂ አወቃቀር ግን ወደፊት በጠቅላላ ጉባኤው እንደሚወሰን ተናግረዋል፡፡ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ ዋና ፀሐፊ አቶ ሙሉነህ ኢዩኤል ሆነው መመረጣቸው ምንጮቻችን ያረጋገጡ ቢሆንም ዶ/ር ኃይሉ ግን "ምርጫው ወደፊት በጠቅላላ ጉባኤ የሚከናወን ነው" ብለዋል፡፡ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ተፈላጊውን የፓርቲ ምሥረታ መስፈርት ካሟላ በኋላ ዕውቅና ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡   

በሌላ ዜና የቀድሞ የቅንጅት የኢትዮጵያ የባህልና ርዳታ ድርጅት በቶሮንቶ የቅንጅት ድጋፍ ሰጭ ጽ/ቤት ሊያካሂደው በነበረው ስብሰባ ላይ ተጋብዘው የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የካናዳ መግቢያ ቪዛ መከልከላቸውን የካናዳ ኤምባሲን በመኮነን የአዲስ አበባ ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡

"የካናዳ ኤምባሲ የጸረ አንድነት ቡድኑን እየደገፈ የአንድነት ኃይሉን በማዳከም የሚሰራው ሥራ የሲ አይ ኤ እጅ አለበት የሚል ጥርጣሬ አለኝ" ሲሉ የቀድሞ የቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት አባል ወ/ሪት መሶበወርቅ ቅጣው ተናግረዋል፡፡

በቶሮንቶ ሳይካሄደ የቀረው ስብሰባ በሌላ ጊዜ ተካሂዷል፡፡ ከአዲስ አበባ በቴሌ ኮንፈረንስ፣ ከአሜሪካ በቪዲዮ ኮንፈረንስና በፓል ቶክ የተካሄደው ስብሰባ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ታክስ ከፋዮች የፈለጉትን እንዳይደግፉ የሚደረገው ተጽዕኖን መንቀፋቸውን ወ/ሪት መሶበ ወርቅ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም "ቀደም ሲል የካናዳ ኤምባሲ ለወ/ሪት ብርቱካንና ለአቶ ደበበ እሸቱ ቪዛ ሲሰጥ በተመሳሳይ ለኢንጂነር ኃይሉ ሻውልና ለአቶ ማሙሸት ከልክሏል፡፡ ይህ ፖለቲካዊ አጀንዳ አለው" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡  

በኃይሌ ሙሉ
 
< Prev   Next >