Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow በአንድ ራስ ሁለት ምላስ
በአንድ ራስ ሁለት ምላስ Print E-mail
Wednesday, 12 March 2008
(በአብዱር ቃድር ሁሴን፣ ከጅማ)

አቶ በድሩ አደም የካቲት 26 ቀን 2000 ዓ.ም “ከኢንጅነር ኃይሉ ተለይቻለሁ” በሚል ርዕስ በሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡትን አስተያየት ተመለከትኩና ስለ ተለዋዋጭ ባህሪያቸው ትንሽ መጣጥፍ ለመጻፍ ተነሳሳሁ፡፡
አቶ በድሩ እስከ 1997 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በፓርላማ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩና በኋላም እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የመሠረቱት የቀስተ ደመና አባል በመሆን ቅንጅትን በመወከል ለፓርላማ የተመረጡ ናቸው፡፡ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ታስረው ሲወጡም እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋንና እነ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ማውገዝን የመጀመሪያ ሥራቸው አደረጉት፡፡ እውነተኛ የፓርቲው መሪም ኢንጅነር ኃይሉ መሆናቸውን እያረጋገጡ ለአገር ውስጥ የግል ጋዜጦች፣ እንዲሁም በውጭ አገር ላሉ ፖልቶክና ሬዲዮ ጣቢያዎች ገለፃ ያደርጉ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ቀደም ያሞገሷቸውን የፓርቲውን መሪ ማውገዝን ተያያዙት፡፡ ይህ አቋማቸው የአቶ በድሩን አቋም እንድጠራጠር አስገደደኝ፡፡ እስቲ በወቅቱ ይሰጡት ከነበረው ቃል ምልልስ እየወሰድን እንመልከት፡፡

ኢንጅነር ራሱን ጠብቆ ፓርቲውን ሲመራ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ሌላ ቀርቶ ፓርቲዎቹ ሲዋሃዱ መስከረም 14 ቀን 1998 ዓ.ም ከአራቱ ፓርቲዎች ሂሣቡን በሕጋዊ ኦዲተር ኦዲት አድርጎ ያቀረበው ኢንጅነር ነው፡፡  ስለዚህ ከማንኛውም አምባገነናዊ ባህርይ ቀርቶ እውነቱን ለመናገር በምንም ዓይነት ምንም ውስጥ ላለመግባት ወይም የፓርቲውን ሕገ ደንብ ላለመጣስ ተሸክሞ የሚሄድበት ሁኔታ ነው እስካሁን የነበረው፡፡
 
አቶ በድሩ አደም ለአንድ ጋዜጣ ቀደም ሲል ከሰጡት አስተያየት የተወሰደ ነው፡፡

ማንኛውም ሰው በፖለቲካ ሕይወቱ ቋሚ አቋም እንዲኖረው የግድ ይላል፡፡ እንኳንስ በፖለቲካ ሕይወት በግል ኑሮም በመርህ መመራት ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ስሜታቸው የነበራቸውን ሁሉ እንደ ወረደ ተቀብለው በጭፍኑ መክነፍ የለባቸውም፡፡ ንግግሮችም ሆኑ ድርጊቶች በተጠየቅ መርህ ሊገዙ ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ለሌሎች አንዳችም ትምህርት ወይም መረጃ የማይሰጡ ይሆናሉ፡፡

አቶ በድሩ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ለቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ብቁና ተገቢ መሪ መሆናቸው ሳይመሰክሩ ያለፉበት መድረክ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ጊዜ አሞግሰዋቸዋል፡፡ ቀንጭበን ያስቀመጥነውም ከአንደበታቸው የተገኘ የምስክርነት ቃል መሆኑ እንዳይዘነጋ፡፡ ታዲያ ከመቅፅበት ለምንድነው የተለወጡት? አሳማኝና ተጨባጭ መነሻ ሊያሳዩን ይገባል፡፡

በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ካቀረቡት አስተያየት እየመዘዝን እንመልከት፡፡ እርግጥ ነው ጋዜጣው ሃሳባቸውን ቃል በቃል ባያስቀመጠውም ሃሳባቸውን በመረጠው ቅርፅ አደራጅቶታል፡፡ ይዘቱም ግልጽ ነው፡፡

እንደ ጋዜጣው አዘጋገብ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በቅርቡ አዲስ አበባ መጥተው በሚጠሩት ጠቅላላ ጉባኤ የቅንጅትን እውነተኛ አባላት ማግኘት እንደማይችሉ አቶ በድሩ ተናግረዋል፡፡

አቶ በድሩ ምን ለማለት ፈልገዋል? “... እውነተኛ አባላት...” ማለት እርስዎና መሰሎችዎ ይሆኑ እንዴ? የእርስዎን አተረጓጎም ለእርስዎ እንተወው፡፡ በእኛ ምልከታ ግን እውነተኛ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት ሞልተዋል፡፡ እንዲያውም እልፍ አዕላፋት ናቸው፡፡ ይህ ጉዳይ አስጨንቆዎት ከሆነ ከባዶ መነሻ የሰረፀ የመንፈስ ጭንቀት ስለሆነ ባያሳስብዎ መልካም ነው፡፡ ትናንት ፓርላማ ውስጥ ለአሥር ዓመታት ሙሉ የፖለቲካ ጉዳዮችን ሳይነኩ ቁንፅል ማኅበራዊ ጉዳዮችን እያነሱ “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር” የአፈፃፀም ችግር እንጂ የሕግና የፖሊሲ ችግር በአገራችን የለም..” ሲሉ ከርመው ለአገዛዙ ያለዎትን ታማኝነት አውልቀው በመጣል ከቅንጅት ጋር ተቀላቀሉ፡፡ የፖለቲካ አቋምዎ ምንድነው?

በመቀጠል ደግሞ አቶ በድሩ “ፓርቲው የጀመራቸውን አጀንዳዎች መንግሥት ቀጥሎበታል” ብለዋል፡፡ ግለሰቡ የሚናገሩትን በውል የሚያውቁም አይመስለንም፡፡ መንግሥት እንዴት አድርጎ ነው የቀጠለበት? የፓርቲው አጀንዳዎች ከመንግሥት ጋር ምን ያዛምዳቸዋል? ይህ አባባል የጤንነት ይሆን?

አቶ በድሩ በማያያዝም “ቅንጅት ከጅምሩ አልተቀናጀም፡፡ እስከ መጨረሻውም ቢሆን ሊቀናጅ አልቻለም፡፡ ነገር ግን ሕዝብና መንግሥት ጠንካራ ፓርቲ መስሏቸው ተሳስተዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባንድ ራስ ሁለት ምላስ ይሏል ይሄ ነው፡፡ አቶ በድሩ ከማንም በፊት የቅንጅትን ጥንካሬና ድል አድራጊነት ለሕዝብ ያበሰሩት እርስዎ መሆንዎን ከምኔው ዘነጉት? ሚያዚያ 30 ቀን 1997 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰበው በሚሊዮኖች በሚቆጠር ሕዝብ ፊት “ኢሕአዴግን ወደ መጣበት እንመልሰዋለን” በማለት አልተናገሩም? ይህ አባባልዎ ቅንጅት ደካማ ፓርቲ መሆኑን እንደሚያሳይ እንዴት ሊያረጋግጡልን ይችላሉ? ደካማና ያልተቀናጀ ፓርቲ ደግሞ እንዴት ገዥውን ቡድን ሊያባርር ይችላል? ምን ዓይነት ነቢይነት ነው?

በአሉታዊ ይዘት አዎንታዊ ውጤት የሚያስመዘግብ የፖለቲካ ጨዋታ አይገባንም፡፡ የቅንጅት ድክመት የታየዎት “እርስዎ የቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት አባል ነን” ሲሉ ኢንጅነር ኃይሉ ደግሞ “የቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት አባል አይደሉም፡፡ በውህደቱ ወቅት ቀስተ ዳመና ለላዕላይ ምክር ቤት አባልነት ስምዎን አላስተላለፈልንም” በማለት በመመለሳቸው ይሆን እንዴ? የራስዎን ምክንያት ራስዎ ያውቃሉ፡፡ እኛ በበኩላችን ግን የቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት አባል እንዳልሆኑ እናውቃለን፡፡ እንመሰክራለንም፡፡

አቶ በድሩ አደም ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገበው መሰረት ኢንጅነር ኃይሉ፣ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያትን ሐምሌ 20 ቀን 1999 ዓ.ም የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት ሰብሳቢ አድርገው መሾማቸውን፣ እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ የጉብኝት ጉዞ አባልና አስተባባሪ ማድረጋቸውን በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡

ከላይ ቀንጭበን ያስቀመጥነው አይዘንጋ፡፡ ዶ/ር ታዬ የቅንጅት ዓለም አቀፍ አመራር ሊቀመንበር ሆነው በምክር ቤቱ አባላት የተመረጡት የቅንጅቱ አመራር ከእስር ቤት ሳይፈቱ በፊት ሰኔ 1999 ዓ.ም መሆኑን ደግሞ አንርሳ፡፡ ረአቶ በድሩ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሐምሌ 20 በኢንጅነር ደብዳቤ የቅንጅት ዓለም አቀፍ ምክር ቤት መፍረሱንና ከዚያ በኋላ ግን ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት እንዳልፈረሰ አድርገው መናገራቸውን ነውሪ አቶ በድሩ ምን ማለትዎት ነው? መስከረም 18 ቀን 2000 ዓ.ም ከአንድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህን ጉዳይ ለምን አላነሱትም? እያደር ነው የሚያንገበግብዎት? ዶክተር ታዬን ለመቃወምስ ምን በቂ ምክንያት አለዎት? በደመ ነፍስ መናገር ያስገምታል፡፡ ያስንቃልም፡፡ በዚህ አባባልዎ የእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ዓላማ ለማስፈፀም የተቀጠሩ ይመስላሉ፡፡ ያለጥርጥር ቅንጅትን የማፍረስ ተልዕኮ ይዘው ተነስተዋል፡፡

ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር መሆናቸውን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ እርስዎም አያጡትም፡፡ የረዥም ዓመታት የትግል ልምድ እንዳላቸውም ይታወቃል፡፡ ምሁሩ የዓላማ ቁርጠኝነትንም ታጥቀዋል፡፡ ብሄራዊ ስሜት የተላበሱና በሕዝባዊ ወገናዊነት ባህርያቸውም ጎልተው ይታወቃሉ፡፡ የአንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ሊቀመንበር ሆነው በማገልገል ወያኔን ለብዙ ዓመታት መታገላቸውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡ ከእሳቸው የተሻለ ማን ይምጣ? በጭፍን ጥላቻ አገር ነፃ አይወጣም፡፡ ወደዱም ጠሉም ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት አሁን ለያዙት ኃላፊነት ተገቢም አስፈላጊም ሰው ናቸው፡፡ ፓርቲው የግል ስሜትዎን አያስተናግድም፡፡ ፓርቲው ግለሰቦችን የሚመዝነውም ለሕዝባዊ ዓላማ ካላቸው ቁርጠኝነት አኳያ መሆኑን ይግባዎት፡፡ ዶክተር ታዬም በዚህ መልኩ ለኃላፊነት በቅተዋል፡፡ ኃላፊነታቸውንም እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ ይበልጥ እንዲተጉም ልናበረታታቸው ይገባል፡፡

አምስቱን ሰዎች ከፓርቲ መታገዳቸውንም አቶ በድሩ ተቃውመዋል፡፡ እንዲሁም የአቶ አባይነህ ብርሃኑን ውክልና በማስመልከት በተቃራኒ አቋም ተሰልፈዋል፡፡ በምን ምክንያት ይህን አቋም እንደወሰዱ ግን የነገሩን ነገር የለም፡፡

እውን ከዚህ ቀደም አምስቱ የአመራር አባላት ጊዜያዊ እገዳ በተጣለባቸው ወቅት በዲያስፖራ ፓል ቶክ አስተያየት ተጠይቀው የሰጡትን መልስ ረስተውት ወይም አድማጭ ይረሳዋል ብለው አስበው ይሆን?   

አቶ በድሩ በሰብዓዊ ተፈጥሮ እንከን ከሌለብዎት በስተቀር ከዚህ ቀደም በአማካይ በጤነኛ አዕምሮ የተናገሩትን ዛሬ የሚረሱበት በቂ ምክንያት አይታየኝም፡፡ ፓል-ቶክ በገቡበት ወቅት ስለአምስቱ ሰዎች መታገድ አስተያየት ተጠይቀው “እንዲያውም የተወሰደው የማገድ እርምጃው ዘግይቷል፤ ቀደም ሲል መሆን ነበረበት” ነበር ያሉት፡፡ አሁን ለምን ሃሳብዎን ቀየሩ? የአቶ አባይነህ ብርሃኑን ውክልና ለመቃወምስ ምን መነሻ ምክንያት ያቀርባሉ? ፓርቲው ያለ መሪ እንዴት ሥራውን ሊያከናውን ይችላል? ኢንጅነር ኃይሉ ከአገር ውጭ በሕክምና ላይ ናቸው፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሯ ከፓርቲው ሕገ ደንብ አፈንግጣለች፡፡ ዋና ፀሐፊውም ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ወግኗል፡፡ ፓርቲውን ማን ይምራው? እርስዎ ለቦታው ጓጉተው ነበር ይሆን እንዴ? ምን ይደረግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ሆነ የላዕላይ ምክር ቤት አባል አይደሉ፡፡ ፓርቲውን ለማዳንና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ለማስተባበር የግድ መሪ ያስፈልጋል፡፡ ኢንጅነር ኃይሉ አቶ አባይነህን ወከሏቸው፡፡ ይሄ ወንጀል ነውን? የፓርቲው ሕገ ደንብ ሊቀመንበሩ ለተቀላጠፈ አሰራር የሥራ አስፈፃሚ አባላትን በተለያዩ ኃላፊነቶች መመደብ እንደሚችሉ ይገልፃል፡፡ ሕግን አክብረው ግዴታቸውን መወጣታቸው እርስዎን ለምን ያንገበግብዎታል?

በአሁኑ ወቅት አቶ በድሩ ያለ ጥርጥር ከፀረ-ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ቡድኖች ጋር ተሰልፈዋል፡፡ መስመራቸውን ከእነሱ ጋር አስተካክለዋል፡፡ ቅንጅትን ለማጥፋት የበኩልዎን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ መንፈሰ ልል በመሆንዎ የማንም መሣሪያ ሆነዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ቅንጅትን ለማፍረስ አይቻልም፡፡
 
< Prev   Next >