Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow በዳርፉር የምግብ ዕርዳታ...
በዳርፉር የምግብ ዕርዳታ... Print E-mail
Wednesday, 12 March 2008
በዳርፉር የምግብ ዕርዳታ በዘራፊዎች ተስተጓጐለ

በዳርፉር ለሚገኙ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች የሚቀርበውን የምግብ እርዳታ በዘራፊዎች መስተጓጐሉን የተመድ ዜና አገልግሎት አስታወቀ፡፡
በአካባቢው በእርዳታ ሥራ ላይ የተሰማሩ የረድኤት ሠራተኞች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚደርስ ዘገባው አመልክቷል፡፡ በዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ፕሮግራም ለአካባቢው ሊያቀርበው ካቀደው የምግብ አቅርቦት ሀምሳ በመቶ እንደሚቀንስ አስታውቋል፡፡

በዘገባው መሠረት በአካባቢው በሚገኝ ዘራፊዎች ምክንያት የእርዳታ አቅርቦት ማከናወን አልተቻለም፡፡ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሀያ ሶስት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እንዲሁም ሰላሳ ሰባት የምግብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች መጥፋታቸውን አስታውቋል፡፡

በሱዳን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ተወካይ ኬንሮ ኦሺዳሪ በዘራፊዎች ምክንያት የአየር ትራንስፖርት መጠቀም ግድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ተወካዩ የእርዳታ አቅርቦቱን በአየር ትራንስፖርት ብቻ ለማከናወን የሚከብድ መሆኑን አክለው አስታውቀዋል፡፡

ሞዛምቢክ በአውሎ ነፋስ ተመታች

በሞዛምቢክ ሰሞኑን በደረሰ የአውሎ ነፋስ አደጋ ሰባት ሰዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡

በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በደረሰው በዚሁ አደጋ በርካታ መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች መውደማቸው ታውቋል፡፡ በአካባቢው የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ተቋርጧል፡፡

በሰዓት ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ፍጥነት ባለው በዚሁ አውሎ ነፋስ የሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ በቅርቡ በሀገሪቱ የደረሰው የጐርፍ አደጋ ጋር የአውሎ ነፋሱ አደጋ ሁኔታውን አሳሳቢ ማድረጉን የዕርዳታ ሠራተኞች ገልፀዋል፡፡

የሀገሪቱ የአደጋ መከላከል ተቋም ዳይሬክተር ፓል ዙኩላ በአካባቢው ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ውጊያ አቋረጠች

እስራኤል ሰሞኑን በጋዛ የከፈተችውን ውጊያ ማቋረጧን አሶሲየትድ ፕሬስ ከጋዛ ያሰራጨው ዘገባ አመለከተ፡፡

በዘገባው መሠረት እስራኤል ከጋዛ የሚሰነዘረውን የሮኬት ጥቃት ሙሉ በሙሉ በማስቆሟ ዘመቻውን አቋርጣለች፡፡ በዘመቻው አራት የእስራኤል ወታደሮች እንዲሁም ከአንድ መቶ ሀያ በላይ ፍልስጤማውያን መሞታቸው ታውቋል፡፡

ግብፅ የእስራኤልና የሀማስ ባለስልጣናትን ለማደራደር ጥረት እያደረገች ሲሆን የእስራኤል ባለስልጣናት ሀማስ ለእስራኤል ህልውና እውቅና እስካልሰጠ ድረስ በቀጥታ ከሀማስ ተጠሪዎች ጋር እንደማይደራደሩ አሳውቀዋል፡፡

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ኦልመርት ከፕሬዚዳንት መሀመድ አባስ ጋር የተጀመረው የሰላም ድርድር እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ “በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ዘላቂ ሰላም ለመመስረት ጥረት እናደርጋለን በዚህም ተስፋ አንቆርጥም” ሲሉ ኦልመርት አስታውቀዋል፡፡ እስራኤል በጋዛ የከፈተችውን ጥቃት ተከትሎ፤ አባስ ከእስራኤል ጋር  የተጀመረው ድርድር እንደማይካሄድ አሳውቀዋል፡፡

በሰርቢያ ምርጫ ሊካሄድ ነው

የሰርቢያ መንግሥት ፕሬዚዳንት በሪስ ታዲክ ፓርላማውን በትነው ምርጫ እንዲያካሂዱ በጠየቀው መሠረት በቅርቡ በሀገሪቱ ምርጫ እንደሚካሄዱ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ፡፡

በዘገባው መሠረት የአውሮፓ ህብረት ለኮሶቮ እውቅና መስጠቱን ተከትሎ በሀገሪቱ የፓርላማ አባላት መካከል በህብረቱ ላይ ባላቸው አቋም ክፍፍል ተፈጥሯል፡፡ በዚህም የፕሬዚዳንት ታዲክ ፓርቲ የአውሮፖ ህብረት አባልነትን ሲደግፍ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ሰርቢያ ከህብረቱ አባልነት እንድትወጣ ይፈልጋሉ፡፡

የሰሎቬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሜትሪጂ ሩፔል “ሰርቢያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ሌላ ምርጫ የላትም” በማለት ለፕሬዚዳንት ታዲክ ፓርቲ ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል፡፡

አብዛኛው የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ለኮሶቮ እውቅና ሲሰጡ ሰርቢያና ሩሲያ የኮሶቮን ነፃነት እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡
 
< Prev   Next >