Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 11th
Home arrow Sections arrow ያሰቡትን ለማሳካት የመጀመሪያ እርምጃ
ያሰቡትን ለማሳካት የመጀመሪያ እርምጃ Print E-mail
Wednesday, 12 March 2008
Imageታጠቅ ኃ/ማርያም ይባላል፡፡ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ሲነርጂ ሀበሻ ፊልም ኘሮዳክሽን የሚባል ድርጅት በማቋቋም ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ጥናታዊ ፊልሞችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከጥናታዊ ፊልሞች ዝግጅት ባሻገር የተለያዩ ፖስተሮችንና ቢል ቦርዶችን ይሠራሉ፡፡ ማንኛውንም ዓይነት ዝግጅት (በግለሰብ ደረጃም ሆነ በተቋም) ኃላፊነት ወስደው ያስፈፅማሉ፡፡
ሦስቱም ጓደኛማቾች ትምህርታቸውን በተለያየ መስክ ያጠኑ ሲሆን የተለያየ ትምህርት አጥንተው የተለያየ ሥራ ላይ መሰማራታቸው አሁን በጋራ ለሚያከናውኗቸው እንቅስቃሴዎች ስኬታማነት ጠቀሜታ እንዳለው ታጠቅ ገልጿል፡፡ ሦስቱም የተለያዩ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡

አንደኛው በፊልም ኤዲቲንግ ሌላኛው ደግሞ በሶሻል ወርክ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን እሱ ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪውን በኮምፒውተር ሳይንስ ይዟል፡፡ ከግል ሥራቸው ጐን ለጐን የጋራ እንቅስቃሴያቸውን ከጀመሩ ሁለት ዓመት  እንደሆናቸው የሚናገረው ታጠቅ በእነዚህ ጊዜያት ያዘጋጇቸውን ጥናታዊ ፊልሞች በአብዛኛው መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የሠሩ መሆኑን ገልፆልናል፡፡ ጥናታዊ ፊልሞችን ለመሥራት ሁለት ዓይነት መንገዶችን ይከተላሉ፡፡ የመጀመሪያው መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች በሚመለከት ጥናታዊ ፊልም ለማሠራት ጨረታ ሲያወጡ ተከታትሎ ኘሮፖዛል በማስገባትና በቀጣይ ሁኔታዎች ላይ በመነጋገር የሚሰሩበት ሁኔታ ነው፡፡ ሌላው የተለያዩ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በማጥናትና ከነዚያ ተቋማት ጋር ተያያዥነት ያሏቸውን ጥናታዊ ፊልሞች ለመሥራት የሚያስችል ኘሮፖዛል ቀርፆ ለድርጅቶቹ በማስገባት ነው፡፡

ታጠቅ እንደገለፀው፣ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በጥናታዊ ፊልም ዙሪያ መሥራታቸወ ስለተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የአኗኗር ዘዬ የተወሰነ እውቀት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ አንድ ልማታዊ ድርጅት ከከተማ ውጭ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያተኩር ፊልም ለመሥራት ድርጅቱ የሚንቀሳቀስበት አካባቢ ላይ በመገኘት፣ በዚያ ያለውን ሁኔታ በመረዳትና የአካባቢን ነዋሪዎች በማነጋገር የጥናታዊ ፊልሙን ፅሁፍ የማዘጋጀት ሥራ ይሠራል፡፡

“እያንዳንዳችን በቋሚነት የምንሰራው ሥራ አለን፡፡ ከሥራችን ጐን ለጐን ጥናታዊ ፊልም እንሰራለን፡፡ ዌብ ሳይት ዲዛይን እናደርጋለን፡፡ በብዛትም ባይሆን የተለያዩ ዝግጅቶች አጠቃላይ ክንውንን እናስፈፅማለን፡፡ ይህ በሌሎች ሥራዎቻችን ያገኘናቸውን መረጃዎች በመጠቀም የምንሰራው በመሆኑ ብዙም ከባድ አይደለም፡፡ እንደመዝናኛም የምናደርገው እንቅስቃሴ ነው” በማለት በቅርቡ ከናዝሬት አሠላ ሲኖ ሀይድሮ በተባለ የቻይና ኩባንያ የተሠራው መንገድ ምርቃትን ማዘጋጀታቸውን አመልክቷል፡፡

እስከ አሁን የሰሯቸው ጥናትዊ ፊልሞች በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ ሲሆኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር እያከናወኑ ባሉት የጥናታዊ ፊልም ሥራ የተቋሞች ቀደም ሲል ያከናወኗቸው (በተወሰነ መልኩ ከጥናታዊ ፊልሙ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው) እንቅስቃሴዎች እንዲካተቱ መፈለግ፣ ኢንተርቪው ሊሰጡ የሚገባቸው ግለሰቦች በሠዓት አለመገኘትና ስክሪኘቶችን በሚመለከት አፋጣኝ ምላሽ አለማግኘት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡ ጥናታዊ ፊልሞችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን በሚሠሩበት ወቅት በተቋማቱ በኩል በሚኖር የሥራ ውጥረት ፊልሞቹ ያልቃሉ ተብሎ በተገመተበት ጊዜ ላይጠናቀቁ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን ታጠቅ አልደበቀም፡፡

ጥናታዊ ፊልሞችን ሲሰሩ የሚያሠሯቸው ተቋማት በፊልሙ ውስጥ ያላቸው ድርሻ እስከ ምን መሆኑን አስመልክቶም፡፡ “ጥናታዊ ፊልም መሥራት ከመጀመራችን በፊት ከሚመለከተው ተቋም ጋር የተቋሙን አጠቃላይ እንቅስቃሴና ሊሰራ የታሰበው ጥናታዊ ፊልም የትኛው የተቋሙ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚያተኩር እንነጋገራለን፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በመካከላችን በቂ ትውውቅን ይፈጥራሉ፡፡ የጥናታዊ ፊልሙን ኘሮፖዛልና ስክሪኘቶችን እስከመገምገም የሚሳተፉበት ሁኔታ ይኖራል” በማለት መልሶልናል፡፡

ሦስቱም ወጣቶች ይህን ሥራ የሚሠሩት ከመደበኛ ሥራቸው ጐን ለጐን መሆኑን ጠቅሶ አቅምና እድል እስካለ ወጣቱ አንድ ሥራ ብቻ ሠርቼ ሕይወቴን እመራለሁ የሚል አቋም ሊኖረው አይገባም ብሏል፡፡ ታጠቅ እንዳለው የተለያዩ ሥራዎችን እድል ለማግኘት ደግሞ ወጣቱ የግድ አጋጣሚዎችን ወይም ሌሎች ሰዎችን መጠበቅ አይኖርበትም፡፡ “እያንዳንዱ ወጣት የተለያዩ ነገሮችን የመሥራት ፍላጐትና አቅም አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ደፍረው ያሰቡትን ነገር ለመጀመር እርምጃ የመውሰድ ሁኔታ ብዙ ጊዜ አይስተዋልም” ብሏል፡፡

በምሕረት አስቻለው
 
< Prev   Next >