| "ብቃት ያላቸው ሰዎች ወደ... |
|
|
| Wednesday, 12 March 2008 | |
![]() አቶ ፀጋይ በርሀ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች "ብቃት የሌለው ባለሥልጣን ካለ ታግላችሁ ማውረድ ትችላላችሁ" የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋይ በርሀ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ጸጋይ በርሀ ጨምሮ በአዲስ አበባ ነዋሪ ከሆኑት የትግራይ ክልል ተወላጆች ጋር የፓናል ውይይት አካሂደዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበው መልስ የተሰጠ ሲሆን በክልሉ እየተካሄደ ስላለው የልማት እንቅስቃሴ፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ተሳታፊዎች ክልሉ ወደ ኋላ እየተጎተተ እንደሆነ የጠቆሙ ሲሆን፣ ባለሥልጣናቱ በበኩላቸው የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ቀውስ በትግራይ ክልል ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ይህ የተገለፀው ባለፈው እሁድ የካቲት 30/ 2000 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚሌንየም አዳራሽ በትግራይ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በትግራይ ተወላጆች መካከል ሕውሓት የተመሰረተበት የካቲት 11ን አስመልክቶ በተደረገው የፓናል ውይይት ነው፡፡ ውይይቱ የተጀመረው በክልሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ አቶ የማነ ዮሴፍ ባቀረቡት የአፈፃፀም ሪፖርት ነው፡፡ አቶ የማነ ባቀረቡት ሪፖርት ክልሉ በተለይ ከተሃድሶ በኋላ ግልፅ የሆነ ስትራቴጂ በመቅረፅ ድህነት በመቀነስና የትምህርትና የጤና ሽፋን በማስፋፋት ትልቅ ሥራ እንደተሰራ ነው፡፡ "ከተሃድሶ በፊት የነበረው አካሄድ በተለምዶና ግልፅ ባልሆነው ስትራቴጂ ነው" ያሉት አቶ የማነ፣ በድህረ ተሃድሶ በተለይ በገጠር ልማት በብሄራዊ ደረጃ የተቀረፀው ስትራቴጂ መሰረት በቤተሰባዊ፣ በአካባቢያዊና በአግሮ ኢንዱስትሪ ደረጃ ፓኬጆች ተዘጋጅተው ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ለወደፊቱም ካለፈው ብዙም የማይለይ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ በመቅረፅ "ዕድገት" ላይ ትኩረት ያደረገ ጉዞ እንደጀመሩ ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡ የአቶ የማነ ሪፖርት ተከትሎ ከውይይቱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ የጥያቄዎቹ ይዘት አብዛኛው ከመልካም አስተዳደር ማስፈን፣ ከመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ ብቁ አመራሮች ወደ ስልጣን ከማምጣት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ተሳታፊዎቹ ካነሱዋቸው ጥያቄዎች መካከል የሕዝቡ ስሜት በከፍተኛ ደረጃ የቀሰቀሰና ትኩረት የተሰጠው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው፡፡ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት ይህንን ሥርዓት ለማምጣት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ ሕዝብ እንዴት በፍትህ ማጣት ይስተጓጎላል? የሚል ነው፡፡ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከሁሉም ክልሎች የባሰ ሁኔታ እንዳለ ጠያቂዎች ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ከተሳታፊዎች ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ "እንደተፈለገው ባይሄድም" ከሌሎች ክልሎች የባሰ ነው የሚለውን ግን አስተባብለዋል፡፡ በቅርቡ በሁሉም ከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች የነበረው አደረጃጀት አፍርሰው በአዲስ መልክ ማዋቀራቸውና ይህ እርምጃ ጥሩ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አባዲ ዘሞ በበኩላቸው በሰጡት መልስ፣ ስብሰባው ከመካሄዱ ቀደም ብሎ ከመቀሌ የንግድ ማህበረሰብና ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ለመጀመሪያ ጊዜ "እናመሰግናለን" የሚል የሕዝብ ምላሽ ማግኘታቸው ተናግረዋል፡፡ "ሕዝቡ በዚህ ቀጥሉበት ብሎናል" ያሉት አቶ አባዲ፣ የክልሉ መንግሥት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሕዝቡ ወቅታዊ ችግር መሆኑን ተገንዝቦ ብቁ የሰው ኃይል በመፍጠርና ስልጠና በመስጠት የተጀመረው አዲስ ስትራቴጂ ውጤት እያስገኘላቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ለሪፖርተር ጋዜጣ፣ እንደገለፁት በቅርቡ ወደ ክልሉ መጓዛቸውና ችግሩ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ነው፡፡ በውይይቱ የቀረበው ሌላው ጥያቄ የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም መንገድ በመከተል እስካሁን ቢቆይም በኤርትራ መንግሥት በኩል ተመሳሳይ ዝግጁነት ባለመኖሩ "እንዲህ የምንኖረው እስከ መቼ ነው?" በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የኤርትራ ችግር በተለይ በትግራይ ክልል እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት አቶ አባዲ፣ "ጦርነትን ግን አይታሰብም" ብለዋል፡፡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የድንበር ውሳኔው ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ መንግሥት ሌላ መፍትሄ እንዲያይ ጠይቀዋል፡፡ በክልሉ እየተካሄደ ያለው የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴ ተሣታፊዎች ያደነቁ ቢሆንም በሌላ በኩል ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ እየተደረገ እንደሆነና በቂ የደን ጥበቃ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋየ በርሀ፣ ክልሉ ባለፉት መንግሥታት በቂ ትኩረት በማጣቱ ተፈጥሯዊ ደኑ ሙሉ በሙሉ መውደሙን እስታውቀዋል፡፡ አሁን በተደረገው የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴ የማገገም ለውጥ መታየቱንም ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት የመቀሌ ዩኒቨርሲቲና የኖርዌይ ዩኒቨርሰቲ በቅንጅት ላለፉት ሁለት ዓመታት ባካሄዱት ጥናት የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው ክልሉ ከ30 ዓመት በፊት ወደነበረበት የመመለስ አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ወገን የማልማት በሌላ በኩል የደን ጭፍጨፋ እየተደረገ ስለሆነ ከውይይቱ ተሳታፊዎች የቀረበው ቅሬታ ተገቢ መሆኑን አምነውበታል፡፡ አቶ ፀጋይ ችግሩን ለማቃለል ነዳጅ ቆጣቢ ምድጃ እያከፋፈሉ እንደሆነና ለወደፊቱ በቂ ትኩረት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡ አንድ ተሳታፊ በቅርቡ መኪና ይዘው ወደ ክልሉ ሲሄዱ ከፍተኛ የመንገድ ችግር እንዳለ ገልፀዋል፡፡ ጥያቄ አቅራቢው በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በጣም ከፍተኛ የመንገድ ችግር በመኖሩ አማረዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው የዓለም አቀፍ ባንክና ሌሎች ተቋሞች ከዓባይ ፖለቲካ ጋር በተያያዘና በሌሎች ምክንያቶች ተይዘው የነበሩ የመንገድ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች መቋረጣቸውን ጠቁመው፣ "ልማት መምጣት ከውስጣችን እንጂ ከውጭ መሆን የለበትም" በማለት መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ በክልሉ የሥራ አጥነት ችግር መስፋፋቱን አስመልክተው ጥያቄ ያቀረቡት ተሳታፊዎች፣ በቅርቡ በዚህ ችግር ምክንያት ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በፌዴራል ፖሊስ ተደብድበው መበተናቸውንና ለእስር መዳረጋቸው አግባብ እንዳልሆነ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው የቀረበው ወቀሳ በማስተባበል፣ ክልሉ የሚፈልገው ሙያና በተጨባጭ ያለው የሰው ኃይል እንዳልተጣጣመ ገልፀዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ስራ ፈላጊዎች የሶሻል ሳይንስ ምሩቃን ሲሆኑ፣ ክልሉ የሚፈልገው የሰው ኃይል ግን የጤናና የኢንጅነሪንግ ባለሙያ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ የስራ አጥነት ችግር መከሰቱን ያመኑት ፕሬዚዳንቱ፣ ችግሩን ለማቃለል መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎችን ዘርዝረዋል፡፡ በከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ ብቃት ያላቸው ሰዎች እንዲቀመጡ በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄዎች ቢነሱም እስካሁን ምንም ለውጥ አለመደረጉ እንዳአሳዘናቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ አቶ ፀጋዬ በበኩላቸው አዲስ ምሩቃንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አባል የማድረግና እነዚህን ወደ አመራር ለማምጣት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፓርቲያቸውን በርካታ ወጣቶች እያፈራ ቢሆንም፣ እነዚህ አዲስ አባላት ከድርጅቱ ሳይዋሃዱ ስልጣን ማስረከብ ካብ ሆኖ ይፈርሳል ብለዋል፡፡ በመዋቅሩ ውስጥ "እንክርዳዶች" እንዳሉ ጠቅሰው፣ የድርጅቱ ዓላማ ሕዝብን ማገልገል እስከሆነ ድረስ እነዚህን ነቅሎ በአዲስ ብቃት ባላቸው ሰዎች የመተካት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በማከልም "ብቃት የለውም የምትሉት ባለሥልጣን በአግባቡ ታግላችሁ ማውረድ መብታችሁ ነው" ብለዋል አቶ ጸጋይ፡፡ አቶ አባዲ ዘሙ በበኩላቸው ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ አንድ ሰው ቀጥታ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የሚታየው ማገልገልን ሳይሆን መገልገልን ስለሆነ፣ አዲስ አመራሮችን ለመፍጠር ከፍተኛ እቅስቃሴ እየተደረገ ቢሆንም ቀስ በቀስ የሚመጣ ለውጥ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶች በተለያዩ ክልሎች በልማትም ሆነ በዴሞክራሲ ዙሪያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ወደ ትግራይ ክልል የማይሄዱበት ምክንያት በክልሉ መንግሥት ክልከላ ወይስ ከእነሱ ፍላጎት ማጣት ምክንያት ነው የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አባዲ ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ድርጅቶቹ ወደ ክልሉ እንዳይገቡ በክልሉ መንግሥት ወይም በትግራይ ልማት ማህበርና በትግራይ ረድኤት ማህበር ምክንያት መሆኑን የሚወራው በፍፁም ውሸት መሆኑን፣ "እነዚህ ድርጅቶች አብዛኛዎቹ ሌላ የተለየ አጀንዳ ያላቸው ናቸው" በማለት የድርጅቶቹ አመራሮች ዓላማ ጥያቄ ውስጥ አስገብተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የድርጅቱ አመራሮች ቂም በቀል ተሸክመው እየተንቀሳቀሱ ናቸው በማለት ወቅሰዋቸዋል፡፡ ትግራይን ከማልማት ይልቅ በክልሉ ላይ አሉታዊ ወሬዎችን በመንዛት ቱሪስቶች ወደ አካባቢው እንዳይመጡ አድርገዋል በማለት ወቅሰዋቸዋል፡፡ የትግራይ ክልል ረአብዛኛዎቹሪ የኢትዮጵያ ጦርነቶች ተጀምረው ያለቁበት በመሆኑ በአካባቢው በርካታ ታሪክ እንደተፈፀመና የክልሉ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ለዘመናት ያደረገው ተጋድሎና የከፈለው መስዋዕትነት ከፍተኛ ሆኖ እያለ የአገሪቱ አንዳንድ ታሪክ ፀሐፊዎች ታሪኩን እያዛቡት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ ለወደፊቱ በሕዝቡ ባህልና ታሪክ ላይ ጥናት ማካሄድ ለሚፈልግ ምሁር ድጋፍ እንዲደረግ ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል፡፡ በትምህርት ጥራት፣ በጤና፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቦታ አሰጣጥና ውሃ አቅርቦት ዙሪያ ችግሮች እንዳሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ ክልሉ በፌዴራል መንግሥትም ይሁን በሌላ ትኩረት እንደተነፈገው በበርካታ ተሳታፊዎች የቀረበውን ቅሬታ ያስተባበሉት አቶ ፀጋዬ፣ "አጥፍተን ከሆነ ይቅርታ" በማለት እንደሚፈለገው ባይሆንም የክልሉ ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በውይይቱ ከአስራ ስድስት ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በተለይ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ፍቃደኞች ከሆኑ በክልሉ ችግሮች ዙሪያ ቀጣይነት ያለው ተመሳሳይ ውይይት ለማድረግ ፍላጎታቸው እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |