Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow በምርጫው ከወዲሁ ተስፋ....
በምርጫው ከወዲሁ ተስፋ.... Print E-mail
Wednesday, 12 March 2008
Image
ዶ/ር መረራ ጉዲና
Image
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ
በምርጫው ከወዲሁ ተስፋ የቆረጡ ፓርቲዎች


በሚያዚያ ወር የሚደረገውን የተወካዮች ምክር ቤት የማሟያ እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ ምርጫን በሚመለከት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከህብረት፣ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከኦፍዴን እና አቶ ልደቱ አያሌው ከኢዴፓ-መድን አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡
 
ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ዶ/ር መረራ ሲናገሩ "ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከምርጫ ቦርድ ጋር ተነጋግሬያለሁ፣ ሌሎች አባሎቻችንም እንዲሁ ለመነጋገር ሞክረዋል፡፡ ነገር ግን መነጋገሩ እንዳለ ሆኖ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ጨርሶ መቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ ላይ እንዳለ ነው ሁኔታዎች የሚያሳዩት" ብለዋል፡፡ በአብዛኛዎቹ የእሳቸው ፓርቲ በሚሳተፉባቸው አካባቢዎች የምርጫውን ሂደት እየተቆጣጠረ ያለው የአካባቢው አስተዳደር እንጂ የምርጫ ቦርድ ምርጫ አስፈፃሚ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ ዶክተሩ አባባል የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚ ተብለው የተመደቡትም ቢሆኑ በእርሳቸው ፓርቲ መረጃ መሠረት ከገዢው ፓርቲ ጋር በተለያዩ መንገዶች ቁርኝት ያላቸውና በካድሬነት፣ በአባልነት ወይም በደጋፊነት በግልጽ የሚታወቁ ናቸው፡፡ "በዚህም ምክንያት" አሉ ዶ/ር መረራ "በዕጩነት ለመመዝገብ የሚሄዱ አባሎቻችን ላይ ከፍተኛ የማዋከብ፣ የእስር እና የማስፍራራት ተግባራት እየተፈፀመባቸው ከመሆኑም በላይ ያቀረብናቸው እጩዎች እንዳይመዘገቡ ተደርገውብናል" ብለዋል፡፡

ለአብነት ያህል በሰበታ አካባቢ ያቀረቡዋቸውን እጩዎች እንዲያስተባብሩ ወደዚያው የሄዱት የፓርላማ አባል አቶ አሰፋ አንጋሶ በካድሬዎች ተደብድበው ሥራቸውን እንዳያከናውኑ መደረጋቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ የምርጫ አስፈፃሚዎች እያዩ መሆኑ ይበልጥ የምርጫ ቦርድ አቅምና ገለልተኛነት ምን ያህል እንደሆነ በትክክል የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡

"ምርጫ ቦርድ እኛ ያሰብነው የምርጫ ቦርድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ምርጫ ቦርድ ኢሕዴግ ብቻውን የመረጠው ነው" የሚሉት ደግሞ አቶ ቡልቻ ናቸው፡፡

"በሌላ አገር ምርጫ ቦርድ የተቃዋሚዎችንም አመለካከት ያንፀባርቃል፡፡ የእኛ ግን በፍፁም የተቃዋሚዎችን አመለካከት የማያሳይ ነው፡ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም የሚያንፀባርቀው የሾመውን ሃይል ፍላጎት ብቻ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በደብዳቤ ጭምር አድሏዊ መሆናቸውን ደጋግመን ብናሳውቃቸውም ያገኘነው መልስ የለም" ይላሉ አቶ ቡልቻ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ በኦፍዴን በኩል የነበረው አስተሳሰብ ቦርዱ አዲስ ነውና ምንም ቢሆን ከድሮው ቦርድ ይሻላል የሚል የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን አንጻራዊ ለውጥ ቢኖርም ብዙ የተለየ ነገር እንዳልታየ አቶ ቡልቻ አመልክተዋል፡፡

አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ምርጫ ቦርድንና ሌሎች የምርጫ አስፈፃሚዎችን ለይቶ ማየቱ ተገቢ እንደሆነ ያሳስባሉ፡፡ "እጩዎቻችንን ማዋከብ፣  ያልተገቡ ጥያቄዎችን ማቅረብ፣ አልፎ ተርፎም የሀገሪቱ ችግሮች ስላልተቀረፉ የእናንተ ዕጩነት አያስፈልግም" የመሣሰሉ ተገቢ ያልሆኑ አባባሎች እየተሰነዘረባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማለት ዘጠኝ አባላት ያሉት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ የተሾመ ሕጋዊ አካል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሌሎች የምርጫ አስፈፃሚዎችን ከምርጫ ቦርድ ጋር ማመሳሰል ተገቢ አይመስለኝም፡፡ የምርጫ ቦርድ አንዳንድ መግለጫዎችም ከዚህ የተሳሳተ አረዳድ የመነጩ ናቸው፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች እየበደሉን ነው ብሎ መክሰስ ምርጫ ቦርድን ከመክሰስ ጋር ምን አገናኘው? በማለት ይጠይቃሉ አቶ ልደቱ፡፡

ለምሳሌ በቅርቡ የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ኃላፊ የሰጡት መግለጫ አስገርሞኛል ያሉት አቶ ልደቱ "እኛ ያልነው የኢሕአዴግ አባላት ዕጩዎቻችንን እያዋከቡብን ነው፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ቢሮ ጥለው ይጠፋሉ የሚል ሲሆን ሃላፊው የሰጡን ምላሽ ከጥያቄያችን ወይም ከክሳችን ጋር የማይገናኝ ነው፡፡ ለመሆኑ ማነው እሳቸውን ስለእኛ ፓርቲ እጩ ማነስ ወይም መብዛት እንዲነግሩን ስልጣን የሰጣቸው፡፡ ክሳችንን በአግባቡ ተመልክተው መልስ መስጠት ሲገባቸው እንዲህ ያለው ገለልተኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ተግባር ነው" በማለት በምርጫ እና ከታች ባሉት የምርጫ አስፈፃሚዎች መካከል ስላለው ልዩነት እና አረዳድ አብራርተዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ለምርጫ ቦርድ የሚቀርቡ አቤቱታዎችና ክሶች አስመልክተው ሲናገሩ፣ "መረጃዎችን ይዘን አቤቱታዎቻችንን እናቀርባለን፡፡ ምርጫ ቦርድ ግን አይኑን በጨው አጥቦ አላውቅም ይለናል፡፡ አስገድደን እንዲቀበለን ማድረግ አንችልም፡፡ ለአባሎቻችን የምንላቸው አቤቱታ ስታቀርቡ ምስክር ይዛችሁ መሆን አለበት ነው፡፡ ከሰው ምስክር በላይ ማቅረብ አይቻልም፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የሰው ምስክር የማይገኝበት ሁኔታ ሁሉ አለ፡፡ የታሰሩ፣ የተደበደቡ፣ እንዳይመዘገቡ የተደረጉ ሰዎች አሉ፡፡ መረጃ እናቀርባለን፡፡ ምርጫ ቦርድ አልቀበልም ካለ ምን ማድረግ ይቻላል?" በማለት ይጠይቃሉ፡፡

ስለዕጩዎቻቸውና ስለሕዝቡ ተሳትፎ አስመልክተው አቶ ቡልቻ በበኩላቸው "ሕዝቡን ለምርጫ ተመዝገቡ በመብታችሁ ተጠቀሙ ብለናል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ሕዝቡ እንዲመዘገብ ቅስቀሳ አድርገናል፡፡ ተመዝገቡ የሚለውን ቅስቀሳ ስንጀምርና ዕጩ ለማድረግ ያሰብናቸው ሰዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ስንቀሰቅስ ፈሩ፡፡ ሕዝቡም ፈራ" ብለዋል፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ ሰዎች ፍርሃት ይታይባቸው እንደነበር፣ ለምርጫ ያለው ጉጉታቸውም አንደቀነሰ ገልፀዋል፡፡ አቶ ቡልቻ እንደሚሉት ፍራቻቸው ሊከሰት የቻለው ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ነው፡፡

"በዚያን ወቅት ሕዝቡ ተቀጠቀጠ፣ ታሰረ፣ ተሰቃየ፣ ስለዚህ ፈራ፡፡ ማግለል በመኖሩ ሕዝቡ ለእኛ ዕጩ ሆኖ ሊመዘገብ አልቻለም፡፡ ለመመረጥ የሚቀርበው አብዛኛው እጩ የኢሕአዴግ ብቻ በመሆኑ ቀጣዩ ምርጫ የኢሕአዴግ ብቻ ነው" ብለዋል አቶ ቡልቻ፡፡

አቶ ልደቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ "ከመጀመሪያ ጀምሮ እንዳስታወቅነው በዚህ ምርጫ ሚናችን የተሳትፎ ነው፡፡ በተወሰኑ የተመረጡ ቦታዎች እጩዎችን አቅርበን ማሳተፍ ነው፡፡ በዚህ ምርጫ ለፉክክር የሚያበቃ የእጩዎች ቁጥር ማቅረብ አንችልም" በማለት ፓርቲያቸው ካለበት የአቅም ውስንነት አንጻር የሚኖሩት ዕጩዎች በጣም አነስተኛ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ "ኢዴአፓ-መድህን ለምርጫ መርህ ያለውን ታማኝነት ለማሳየት ብቻ ሲል ነው ወደ ምርጫ የሚገባው" በማለት ፓርቲያቸው በዚህ ምርጫ የሚኖረውን ሚና አመልክተዋል፡፡ "በእኛ እምነት" አሉ አቶ ልደቱ "የምርጫው ሂደትና ተሳትፎ በራሱ ዋጋ አለው፡፡ በምርጫው የማሸነፍና የመሸነፍ ጉዳይ ሌላ ነገር ነው" ብለዋል፡፡ በምርጫው ላይ የሚኖራቸው ሚና ከተሳትፎ ያልዘለለበት ምክንያት ነው ያሉት የ97ቱን ምርጫ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን ባላቸው አቅም ለፉክክር የሚያበቃ ድርጅታዊ ብቃት የላቸውም፡፡ እንደሳቸው አባባል በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዙሪያ ያለው ደጋፊ የ97ቱን ምርጫ ተከትሎ የሞራል ድቀት ደርሶበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በምርጫና በሰላማዊ ትግል የመሳተፍ፣ ዕጩ ሆኖ የመቅረብ ፍላጎት የለውም፡፡ በተጨማሪም ፓርቲያቸው ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ችግር እንደገጠመው አስታውቀዋል፡፡

ዶ/ር መረራ የአሁኑ ምርጫ በየትኛውም መመዘኛ ከ97ቱ አይነፃፀርም ይላሉ፡፡ ልዩነቱን ሲያብራሩም በዚያ ምርጫ ኢሕአዴግ ዴሞክራት ለመሆን ይዳዳው ስለነበርና ገበሬውን ይዣለሁ፣ የገበሬው ድጋፍ አለኝ፣ ተቃዋሚው ደካማ ነው ብሎ ዘና ብሎ ሚዲያውን ከፍቶልን አንዳንድ ነገር ስናደርግ ነበር፡፡ የአሁኑ ምርጫ ግን በየትኛውም ሚዛን ጨርሶ ምርጫ አይመስልም፡፡ በዕጩዎች ብዛትም ሆነ በምንሸፍናቸው የአካባቢዎች ስፋት አንፃርም ቢሆን፡፡ የምርጫ ቦታ ሽፋንን አስመልክተው ከምርጫ 97 በኋላ የቀበሌ ምክር ቤት አባላት ቁጥር በፊት ከነበረበት በፍጥነት ወደ ሶስት መቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ቁጥር መሠረት  "በኦሮሚያ ደረጃ በሁሉም ቀበሌዎች እንወደዳደር ብንል ወደ 1.7 ሚሊዮን እጮዎችን ማቅረብ አለብን ማለት ነው፡፡ እንደሳቸው አባባል በኢትዮጵያ ደረጃ ወደ አምስት ሚሊዮን አካባቢ ዕጩዎች ማለት ነው፡፡ ይህ የተደረገው ሆን ተብሎ ተቃዋሚዎች እጩ ማቅረብ እንዳይችሉ ነው" ብለዋል፡፡ ዶ/ር መረራ እንዳሉት ለምሳሌ በኦሮሚያ አካባቢ የአንድ ቀበሌ አማካኝ የቤተሰብ ቁጥር ከአራት መቶ እስከ አምስት መቶ ነው፡፡ ከዚህ ሶስት መቶ ተወዳዳሪ ለማቅረብ ከአንድ ቤት ውስጥ የተለያዩ ፓርቲ አባላትን ካላቀረብን ፈፅሞ የማይሆን ነገር ነው" ይላሉ፡፡

ከገዢው ፓርቲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክተው፣ "ገዢው ፓርቲ በሩን ዘግቷል፡፡ ከእናንተ ጋር አልነጋገርም፣ አልደራደርም ብሎ ካቆመ ወደ ዓመት ሊሆን ነው፡፡ የ97ቱ ምርጫ ላይ ግን እየተነጋገርንም፣ እየተከራከርንም ነበር፡፡ ያ ሁሉ አሁን የለም" በማለት ተቃዋሚዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እየተባባሰ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

ከሌሎች ፓርቲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አስመልክተው፣ "ከኢሕአዴግ ጋር ባደረግነው ስምምነት ከውጪ አገር ካሉት ጋር ምንም ዓይነት ቁርኝት እንዳይኖረን ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ፓርላማ በመግባታችን ከነሱ ያለን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፡፡ አንዳንዶቻችን አሜሪካና አውሮፓ ለሥራ ጉዳይ ስንሄድ የእግዚአብሄር ሰላምታ እንለዋወጣለን፣ ከአንዳንዶቹ ጋር ደግሞ ጭራሽኑ አንጋገርም" ብለዋል ዶ/ር መረራ፡፡ "ሀገር ውስጥ ደግሞ መንግሥት ቅንጅትን ገፍቶ ከሜዳው አስወጥቶታል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በአብዛኛው ያሉት በኢሕአዴግ ጎራ ናቸው፣ በተቃዋሚ ጎራ ብዙ የሉም፡፡ በተወሰነ መልኩ ከኦፍዴን በስተቀር ከሌሎች ጋር ይህ ነው የሚባል ግንኙነት የለንም" ብለዋል፡፡

በዚህ ምርጫ እያደረጉት ስላለው ተሳትፎ ሲናገሩ "ሕዝቡን በሁለት በኩል ነው የማየው፡፡ ለምሳሌ ሕዝብ ያኮረፈባቸው እንደ አዲስ አበባ ያሉ አካባቢዎች አሉ፡፡ በእኔ እምነት አብዛኛው የአዲስ አበባ ሕዝብ ለመምረጥ የተመዘገበ አይመስለኝም፡፡ በሌላ በኩል ለምሳሌ እኛ በስፋት በምንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ ጭራሽ ምርጫው ውስጥ እንዳለንም አያውቅም፡፡ ለመመዝገብ ብዙም ፍላጎት አልነበረውም" ብለዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በእነሱ በኩል አንድ ሀሳብ አቅርበው እንደነበረ ጠቁመው ይህም በየጊዜው መራጭ ከሚመዘገብ ቋሚ መዝገብ ይኑርና ከዚያ ውስጥ አካባቢውን የለቀቀ፣ የሞተና አዲስ ሰው ወዘተ ሲኖር የቀበሌ አስተዳደሩ እያስተካከለ እንዲሄድ የሚል ሲሆን ሃሳቡ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡

አቶ ቡልቻ በበኩላቸው ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ምንም ዓይነት የምክክርና የጋራ መድረክ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት በተለይ ከሕብረት ጋር የተሻለ ግንኙነት እንደነበራቸውና አንዳንድ ቅሬታዎች ለምርጫ ቦርድ ዘርዝረው ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ተቃዋሚዎች በመካከላቸው ይህ ነው የሚባል ግንኙነት እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡

ከኢሕአዴግ ጋርም ከአንድ ዓመት በፊት በፓርላማ የሕብረት፣ ቅንጅትና ኦፌዴንን ጨምሮ የውይይት መድረክ መክፈታቸው በማስታወስ፣ በተወሰኑ ነጥቦች መስማማት ባለመቻላቸው ተቃውመው እንደወጡና ከዝያ በኋላ ኢሕአዴግ ለውይይት ፍቃደኛ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ነገሩ ካልተሰማማህ መውጣት በየትም አገር የተለመደ ነው፣ የትግልም ዘዴ ነው" ያሉት አቶ ቡልቻ፣ "ወጥተህ መመለስ ግን ትችላለህ" በማለት ተቃዋሚዎች ከኢሕአዴግ ጋር እንደ በፊቱ ለምርጫና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ለመነጋገር ፍላጎት ቢያሳዩም፣ ኢሕአዴግ "ይቅርታ ካልጠየቃችሁ ሁለተኛ እናንተ ጋር አልነጋገርም" በማለት መድረኩን ዝግ ማድረጉ አግባብ አይደለም በማለት ወቅሰዋል፡፡

አቶ ልደቱም በበኩላቸው የእርስ በርስ ተባብሮ መስራትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አጠቃላይ ግንኙነት አስመለክተው፣ "በአሁኑ ሰዓት አብረን እየሰራን አይደለም" ብለዋል፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሉበት ሁኔታ መጥፎ እንደሆነ ገልፀው፣ ኢዴፓ መድህን ከአሁን በኋላ አብሯቸው ሊሰሩ የሚችሉት ፓርቲዎች (ነገ በታሪክ አጋጣሚ) ስልጣን ሲይዙ ከኢሕአዴግ የተሻለ ነገር ይዘው ሊመጡ የሚችሉ መሆናቸውን ሲያረጋግጥ ብቻ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ እንደ አቶ ልደቱ አባባል ይህ ፓርቲያቸው ከ97 ምርጫ የተማረው ትልቅ ትምህርት ነው፡፡

አቶ ልደቱ አክለው ሲናገሩ "ይህንን መዝነን ካላረጋገጥን በስመ ተቃዋሚ አብረን የምንሰራበት ሁኔታ አይኖርም" ብለዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ከሌሎች ፓርቲዎች ሊኖራቸው የሚችል ሽርክና በጥንቃቄ የተጠና ብቻ ሊሆን እንደሚችል አክለው ገልፀዋል፡፡

የአሁኑ ምርጫ ተወዳድረህ የመንግሥት ስልጣን የሚያዝበት ጉዳይ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ የፓርቲያቸው አጠቃላይ የምርጫ ዘመቻ የገዢውን ፓርቲ ፕሮግራም በተሻለ ሁኔታ እናስፈፅማለን በሚል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
 
ስለዚህ ፓርቲዎቹ ከምርጫው ምን ይጠብቃሉ?

"ጨዋታው አልቋል" የሚሉን ዶ/ር መረራ "ፎርፊ ላለመውጠት እንጂ ጨዋታውን ማን እንደሚያሸንፍ ግልጽ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚለውን ጨዋታ ባንሳተፍ ሕዝቡም አያውቅልንም ዓለም አቀፍና ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡም አይረዳንም ብለን እንጂ ብዙም የምንጠብቀው ነገር የለንም" በማለት ከአንዳንድ ዲፕሎማቶችና ከተለያዩ ሰዎች እንደሚሰሙት ያሁኑ ምርጫ ጨዋታው አልቋል እስቲ ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ ለሚኖረው ምርጫ ምን እንደሚሆን እናያለን የሚል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አቶ ልደቱ በበኩላቸው ደጋግመው እንደሚሉት በአሁኑ ምርጫ ከተሳትፎ የዘለለ ነገር እንደማይጠብቁና አላማቸውም የዴሞክራሲውን ሂደት ለማገዝ እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ምርጫ እናሸንፋለን የሚል ምንም ግምት የላቸውም፡፡ "በግልፅ ለመናገር ምርጫውን ለማሸነፍ የሚያስችል ብቃት በአሁኑ ሰዓት የለንም" ብለዋል፡፡ "በእርግጥ  "አናሸንፍም" ብሎ እውነታውን በግልፅ መናገር በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተለመደ አይደለም ግን እናሸንፋለን ብለን ስለማናሸንፍ የተሳሳተ ግምት መስጠት አንፈልግም" ይላሉ፡፡

እንደ አቶ ቡልቻ ገለፃ የኢሕአዴግን ያህል እጮዎቸን ያቀረበ ተቃዋሚ ፓርቲ ስለሌለ በቀጥታ የምርጫው አሸናፊ ኢሕአዴግ ነው፡፡ "በኦፌዴን በኩል ያቀረብናቸው ዕጩዎች ብዛት አሸናፊ እንድንሆን የሚያደርገን አይደለምና" በማለት ተቃዋሚዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር መፎካከር የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡

በሄኖክ ስዩም
 
< Prev   Next >