| ገበያ ተኮር የግብርና ኤክስቴንሽን... |
|
|
| Wednesday, 12 March 2008 | |
ገበያ ተኮር የግብርና ኤክስቴንሽን መዘርጋት ያስፈልጋልገበያ ተኮር የግብርና ኤክስቴንሽን ስርዓት መዘርጋት ከሕዝብ ቁጥር እድገት ጋር እያነሰ የመጣውን የተፈጥሮ ሐብት በተሻለ ሁኔታ የመጠቀም አቅም እንደሚፈጥር ይህም በገበያ ላይ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች እንዲመረቱ በማድረግ የዋጋ መናርን የማረጋጋት ሚና እንደሚኖረው ተገለፀ፡፡ የኤክስቴንሽን ስርዓቱ የገበሬውን የገበያ ችግር የመፍታት አቅም ሊኖረውም ይገባል ተብሏል፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ገብረ መድን በዓለም አቀፍ የከብቶች ምርምር ተቋም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራ ምርትን እያሳደጉ ገበያውን ማሳካት በሚል ፕሮጀክት ከፍተኛ ሳይንቲስት ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ እስከ አሁን የነበረው ግብርና በምግብ እህል ራስን ከመቻል የዘለለ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ገበያ ተኰር ግብርና መዘርጋት በዘላቂነት ከድህነት ለመውጣትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መፍትሄ ይሆናል፡፡ የሕዝብ ቁጥር መጨመር በተፈጥሮ ሀብት ላይ ጫና ስለሚፈጥር ያለውን ሀብት የተሻለ አንፃራዊ ተጠቃሚነት ወዳለበት ምርት ማዞር ምርታማነትን የመጨመር አቅም እንደሚኖረው ጠቁመው የተሻለ አቅም ያላቸውን ምርቶች ማምረት ስፔሻላይዜሽንና ልውውጥን እንደሚያዳብር ይህም የሕብረተሰቡን ኑሮ እንደሚያሻሽል ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ ገበያ ተኰር የሆነ እርሻ ለመመስረት በመንቀሳቀስ ላይ ቢሆንም ገበያ ተኰር ግብርና ምን እንደሆነ በግልፅ አለመቀመጡንና የአርሶ አደሩም ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ዶ/ር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ የገበያ መረጃ ማግኘት ዋጋን፣ አቅም ያላቸውን ሸማቾች፣ የሚያከማቹበትን ቦታና፣ ምን ማምረት እንዳለባቸው እንዲያውቁ ሲረዳ መረጃው የገበሬውን የመደራደር አቅም የመጨመር፣ የግብይት ዋጋ የመቀነስና በገበያ ውስጥ ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች ብሎም ያለውን ሃብት የተሻለ አዋጪ በሚሆንበት ሁኔታ ለመጠቀም የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡ በገበያ ተኮር ግብርና ገበያው እርሻውን የመምራት አቅም መፍጠር ሲሆን አሁን ባለው ሁኔታ ምርት ስለተመረተ ብቻ ወደ ገበያ እንደሚሄድ ስለሆነም ገበያ ተኮር የሆነ ግብርና ለመመስረት ገበያው ምን ይፈልጋል የሚለውን መረዳት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በገበያ ተኮር ግብርና "ያመረትከውን ለመሸጥ ሞክር ሳይሆን ለመሸጥ የምትችለውን አምርት" መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከግብርና ምርቶች ዋጋ የግብይት ወጪ ያለው ድርሻ ከሌሎች አገሮች አንፃር ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት ዶ/ር ብርሃኑ የግብይት ወጪ መቀነስ በምርት ዋጋ ላይ ለውጥ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የመሸጫ ጊዜ፣ የማከማቻ፣ የትራንስፖርት፣ የማዘጋጃ የምርት መሸጫና ማውረጃ ዋጋን በመቀነስ ሂደት ላይ ትኩረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ በእሴት ሰንሰለት፣ ምርት ከመመረቱ በፊት ያለው የግብዓት አቅርቦት፣ የማምረት፣ ከምርት በኋላ ያለው ሂደት፣ ትራንስፖርት፣ ነጋዴና ሸማች እርስ በርስ የተያያዙ በመሆናቸው ከግብዓት እስከ ሸማች የሚያገናኘው ሰንሰለት ለማሻሻል ያለበትን ደረጃ ማወቅ ገበያውን ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አነስተኛ አቅም ባላቸው ገበሬዎች የገበያ መረጃ ውሱንነት የማከማቻ ቦታ፣ የትራንስፖርት ወጪ፣ ምርቱን የመለያየት፣ ደረጃ የማውጣት አቅም፣ የሚመረተው ምርት አናሳ መሆኑና የምርት ጥራት አናሳ መሆን የግብይት ወጪ ከፍተኛ እንዲሆን እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡ የገበያ መሠረተ ልማት አለመኖርና የገበሬዎች የመደራደር አቅም አነስተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ገበሬውን ገበያ ተኮር ለማድረግ ያሉበትን ችግሮች መፍታት ማስፈለጉን የኤክስቴንሽን ሥርዓቱም የገበሬውን የገበያ ችግር የመፍታት አቅም ሊኖረው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በአብዛኛው የነበረው የኤክስቴንሽን ሥርዓት ምግብ እንዲያድግ በምግብ እህል ራስን የመቻልን አቅጣጫ ብቻ ይዞ የተጓዘ እንደሆነ ጠቅሰው ገበያ ተኰር ግብርናን ተግባራዊ ለማድረግ የኤክስቴንሽን ስርዓቱን በዚያ መልኩ መቃኘት አስፈላጊ መሆኑንም አሳስበዋል፡፡ ገበያ ተኮር የኤክስቴሽን ስርዓት መዘርጋት ለገበሬው ገበያ ነክ የሆኑ መረጃዎችን ለማድረስ፣ በገበሬውና ገዢ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲጠናከር መርዳት፣ የገበሬውን የግብይት አቅም ለመፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ገበያ ተኮር ወደሆነ እርሻ ለመረማመድ ሁሉም ምርት በተወሰነ መልኩ ገበያን መሠረት ያደረገ ይሆናል ያሉት ዶ/ር ብርሃኑ በገበያ ተኮር ግብርና የገበያ ወይም የምግብ እህል ብቻ የሚል ክፍፍል እንደሌለ ምርቱ የአካባቢው አየር ንብረትና የተፈጥሮ ሀብት መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ የሕብረተሰቡን የመግዛት አቅም መጨመሩ ጠቅላላ ፍላጐት ላይ ግፊት ማሳደሩ ከጠቅላላ አቅርቦት ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ አሁን የተፈጠረው የዋጋ ንረት እንዲፈጠር አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንፃራዊ ተጠቃሚነት የሚኖራቸውን ምርቶች ማምረት ጠቅላላ አቅርቦትን የመጨመር አቅም ሲኖረው በመካከል ያለውን ልውውጥ ለማሳደግ መሥራት አስፈላጊነት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የእህል ምርቶችም ሆነ አትክልት አቅርቦት መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ ገበያ ተኮር የሆነ የኤክስቴንሽን ፕሮግራም ከምርት ግብዓት የሚጀምር ሲሆን ገበሬው ምን ማምረት አለበት? ምን ያስፈልገዋል? የሌሎች አካባቢዎችን ልምድ ማሳየት ማስተማር ተግባራዊ ስልጠናዎችን ወርክሾፖችን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ገበሬው ብቻውን እየመጣ ከሚሸጥ በማህበር በቡድን ተደራጅቶ መምጣቱ የግብይት ዋጋን የመቀነስ አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በምርት ዋጋ የትራንስፖርት የማስጫኛና የማውረጃ ዋጋ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ይህም ከሌሎች አገሮች አንፃር ከፍተኛ እንደሆነ ገበያው እንዳያድግ ምክንያት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ ገበያ ተኮር የኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት የገበሬውን ማነቆ መፍታት እንደሚገባውም ጠቁመው የምርት ገበያ አገልግሎት መጀመሩ ለገበሬው የገበያ መረጃ በመስጠት በኩል የተቀላጠፈ እንዲሆን አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በየገጠሩ የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች የገበያ ተኮር ኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲሰጡ እገዛና ስልጠና እንደሚፈልጉ የጠቆሙት ዶ/ር ብርሃኑ የምርምር ማዕከሉ በሚሰራባቸው የደቡብ፣ አማራ፣ ትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች ለስልጠና አገልግሎት የሚውሉ መመሪያዎችን (ማኑዋል) ማዘጋጀታቸውን በዚሁ መሠረት በአንዳንድ አካባቢዎች ተግባራዊ ተደርጎ አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ የኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን ታች ድረስ ለማድረስ የግብርና ባለሙያዎችን አቅም በማጠናከር በኩል የሚሠራው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡ የገበያ ተኮር የኤክስቴንሽን ፕሮግራምን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት የአርሶ አደሩ የተቆራረጠና አንድ ሄክታር የማይሞላ መሬት መኖሩ እንቅፋት አይፈጥርም ብለን ለጠየቅናቸው ሲመልሱ በከፍተኛ ቦታዎች ላይ ያለው መሬት አነስተኛ መሆኑን ተናግረው በአነስተኛ መሬቶች ላይ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻልና በዚህም የምሥራቅ እስያ አገሮች ለውጥ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በአነስተኛና ትላልቅ እርሻዎች ተግባራዊ በሚደረገው የኤክስቴንሽን ፕሮግራም፣ መሠረተ ልማት፣ ገበያ ትራንስፖርት ልዩነት ቢኖርም ገበያ ተኮር ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ እርሻው ገበያ ተኮር መሆኑ የገጠርና የከተማ ኢኮኖሚ ትስስርን ተግባራዊ ለማድረግ ሲረዳ በገጠር ያለውን ሕዝብ ቁጥር በተነፃፃሪነት የመቀነስ፣ በከተማና ኢንዱስትሪ የሚኖረው ሕዝብ የመጨመር አቅም እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ በግብዓት አቅርቦትና ፍላጐት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ዋጋው እንዲጨምር እንዳደረገው፣ የምርት ዋጋ እንዲጨምር አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በገበያ ተኮር ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በግብዓት፣ ብድር አቅራቢዎች፣ ገዢዎች አጓጓዦች መካከል ያለውን ትስስር ፈጣን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ገበሬዎች በማህበር ተደራጅተው የሚያቋቁሙት ማህበር የገበሬዎችን የመደራደር አቅም ለማሳደግ፣ የባለሙያዎች እገዛ ለማግኘት የግብይት ዋጋን በመቀነስ የሚኖረው ሚና ጉልህ መሆኑንም ጠቁመው የምርቶችን ደረጃ በማውጣት የተወሰነ ክብደትና አስተሻሸግ እንዲኖራቸው እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ በቤዛዊት ሥዩም |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |