Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow ከቡና ዓይነቶች ጥራትና ጣዕም...
ከቡና ዓይነቶች ጥራትና ጣዕም... Print E-mail
Wednesday, 12 March 2008
ከቡና ዓይነቶች ጥራትና ጣዕም አንፃር የሚገኘው ገቢ አነስተኛ ነው

ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡት የተለያዩ የቡና ዓይነቶች ጥራትና ጣዕም አንፃር የሚገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ በአሜሪካ በሲዳሞና በይርጋ ጨፌ የተገኘው የንግድ ምልክት ባለቤትነት ሰርተፊኬት ቡናዎቹ የተለየ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡
 
በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የንግድ ምልክት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወንድወሰን በለጠ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የኢትዮጵያ የተለያዩ የቡና ዓይነቶች የተሻለ ጥራትና ጣዕም ቢኖራቸውም ገቢው ከሌሎች አገሮች አንፃር አነስተኛ ነው፡፡

የቡናዎቹን የአዕምሯዊ ንብረት ይዘት በማየት የተሻለ ገበያ የሚያገኙበትን መንገድ ለመፍጠር የንግድ ምልክት ጥበቃ የተሻለ አዋጪ ስለሆነ የቡና ስሞችን በንግድ ምልክትነት በማስመዝገብ የተደራዳሪነት አቅም ለመፍጠር ሥራ መጀመሩን በዚህም የንግድ ምልክት ባለቤትነት ሰርተፊኬት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት ብዙ የቡና ዓይነቶች ቢኖሩም ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው በመጀመሪያ ኘሮጀክት ውስጥ የሚታቀፉት የትኞቹ ይሁኑ የሚለው ላይ ጥናት ተደርጐ በቀዳሚነት በዓለም አቀፍ ገበያ ሁለም እውቅና ያላቸው ቢሆኑም የተሻሉ ሆነው የተቀመጡትን የይርጋ ጨፌ የሐረርና የሲዳሞ ቡናዎች የበለጠ ተቀባይነትና በዓለም አቀፍ ቡና ገዥዎች ዘንድም ጥሩ አስተያየት የሚሰጣቸው ስለሆነ ለድርድር እንደተመረጡ ጠቁመዋል፡፡

የቡና ስሞችን በተለያዩ ቡና ገዥ አገሮች በንግድ ምልክትነት አስመዝግቦ የንግድ ምልክት ምስክር ወረቀት ማግኘት ኢትዮጵያ የስሞቹ ባለቤት ስለምትሆን እነዚያን ስሞችን የሚጠቀሙ የቡና ኩባንያዎች ከአገሪቱ ጋር የላይሰንስ ስምምነት እንዲፈራረሙና ስሞቹን እንዲጠቀሙ ለማድረግ እንደሚያስችልም አስረድተዋል፡፡

ይህን መሠረት አድርጎ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች፣ በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በእስያ የንግድ ምልክትነት ምዝገባ ማመልከቻ እንዲቀርብ መደረጉን በብዙዎቹ ዘንድም ማመልከቻዎቹ ተቀባይነት አግኝተው ሁሉም ባይሆኑም የተወሰኑት በአጭር ጊዜ ጥበቃ ሊያገኙ እንደቻሉ አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡

በአውሮፓ ከሲዳሞ ውጭ የሐረርና የይርጋ ጨፌ ቡናዎች ጥበቃ ማግኘታቸውንና የሲዳሞ ቡና ሌላ የአውሮፓ ኩባንያ ከሲዳሞ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሴፋ ሞኖ የሚል የንግድ ምልክት በባለቤትነት የያዘ ኩባንያ በመኖሩ መዘግየቱን ተናግረዋል፡፡ የኩባንያው የንግድ ምልክትና ኢትዮጵያ ጥበቃ ለማግኘት ያመለከተችው የንግድ ምልክት ተጠቃሚውን ሊያምታቱ ስለሚችሉ እንዳይመዘገብብኝ ብሎ እንዳገደው፣ ባለሙያዎች ጉዳዩን ሲያጤኑት የእነዚያ ምልክት በሌላ ምርት ላይ በመሆኑና ከተለያዩ አቅጣጫዎች በቀረቡበት ግፊት ተቃውሞውን (ጥያቄውን) ማንሳቱንም ተናግረዋል፡፡

ትኩረት አግኝቶ የነበረው አሜሪካ ውስጥ በኢትዮጵያ ንግድ ምልክት ማመልከቻዎች ላይ ቀርቦ የነበረው ተቃውሞ በሁለት ደረጃ የሚታይ እንደሆነ ገልፀው፡፡ ጥበቃእንዲያገኙ ማመልከቻ ሲቀርብ ከስታር ባክስ ተነስቶ የነበረው ተቃውሞና ለአሜሪካ ለፓተንትና ንግድ ምልክት ጽ/ቤት በስታር ባክስ የቀረበው የንግድ ምልክት ማመልከቻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ስታርባክስ በሰኔ 2004፣ ሰን ድራይ ሲዳሞ በሚል የንግድ ምልክት በሽርክና ይሰጠኝ በሚል ማመልከቻ አቀርቦ ስለነበር ቀዳሚ ባለመብት ስለሆንኩ የኢትዮጵያ ውድቅ ይሁን በሚል ክርክር አንስቶ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ሲዳሞ የሚመረተው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ስታርባክስ ከዚያ ገዝቶ የሚሸጥ በመሆኑ ስያሜው ለኢትዮጵያ ይገባል የሚል ተቃውሞ በመቅረቡና ክርክሩም ሰፊ ትኩረት በማግኘቱ በሰኔ 2006 ቅሬታውን ውድቅ መደረጉን አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡

ስታር ባክስ ተቃውሞ ሲያነሳ ስታርባክስ አባል የሆነበት የአሜሪካ ብሔራዊ የቡና ማህበር ሲዳሞ፣ ሐረር፣ ይርጋ ጨፌ የሚል የቡና ስያሜ ሁሉን አቀፍ ስያሜ (ጄነቲክ) ስለሆነ አያገለግልም የሚል ተቃውሞ አንስቶ እንደነበርም ገልፀዋል፡፡ የቡና ገላጭ በመሆኑ ለተወሰነ ቡና መጠሪያ አይሆንም የሚለውን ተቃውሞ እንዳይመዘገብ ላደረገው እገዳ ያለንን መከላከያ እንድናቀርብ ተጠይቀን በመረጃው መሠረት የይርጋ ጨፌ ቶሎ ውሳኔ እንዳገኘ በሲዳሞና የሐረር ረዥም ጊዜ መውሰዱን ጠቁመዋል፡፡

በሲዳሞና በሐረር የንግድ ምልክት የተላኩትን ቡናዎች በማቅረብ ሲደራደሩ መቆየታቸውን ምርመራ ከተካሄደ በኋላ ሰርትፊኬት ለማግኘት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የሲዳሞ ቡና የንግድ ምልክት ሰርቲፊኬት ለማግኘት ሦስት ዓመት እንደወሰደ ጠቁመው የሐረር ቡና የምስክር ወረቀት በቅርቡ ለማግኘት የሚያስችል በቂ መረጃ ማቅረባቸውን ጥሩ ተስፋ እንዳለውም አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል፡፡

የቡና ስሞችን በማግኘት የኢትየጵያ መሆኑ መታወቁ በማስተዋወቅ ሥራ ላይ የተሻለ ስም ለማግኘትና ምርቶች የተሻለ ገበያ እንዲያገኙ እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡


የኢትዮጵያ ቡና የተሻለ የጥራት ደረጃ እያለው በቡናው የሚመጥን የማስተዋወቅ ሥራ ባለመሠራቱ ተራ ቡና በሚሸጥበት ዋጋ እየተሸጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና የሚወዳዳራቸው የኬንያና የጃማይካ ቡናዎች የተለየ ዋጋ እንደሚያገኙ ጠቁመው የንግድ ምልክት ሰርቲፊኬቱ የተለየ ዋጋእንድናገኝ እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡

የንግድ ምልክት መኖሩ በተጠቃሚው ዘንድ እንዲታወቅ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ እንደሚያስችልና በማስተዋወቅም በረዥም ጊዜ ገበያው እንዲያድግ እንደሚያደርግም ጠቁሟል፡፡

ከስታርባክስ ጋር የነበረው ውዝግብ በቡና ዋጋ ላይ ለውጥ እንደፈጠረና በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያን የተደራዳሪነት አቅም እንዳሳደገ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ስታርባክስ ተቃዋሚነቱን ሰርዞ ድጋፍ በመስጠት የገበሬዎች አጋዥ ማዕከል ለማቋቋም በስሙ እንደተስማሙ በሌሎች ዘርፎችም ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ውይይት አዲስ አበባ ውስጥ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

በአሜሪካ ካቀረብነው ማመልከቻ በሲዳሞና የይርጋ ጨፌ ተቀባይነት የገኘ ሲሆን የሐረር በቅርቡ እንደሚያገኝና በአውሮፓም በሲዳሞ ቡና ላይ ተቃውሞ ያነሳ ድርጅት ቢኖርም ተቃውሞውን በማንሳቱ ሦስቱም ቡናዎች በቅርቡ ጥበቃ እንዲያገኙም ተናግረዋል፡፡

በጃፓን የሲዳሞና የይርጋ ጨፌ ቡናዎች የንግድ ስያሜ የምስክር ወረቀት ያገኙ ሲሆን የሐረር ቡና ስያሜን ቀደም ብሎ ያስመዘገበው ድርጅት ተቃውሞ እንዳነሳና በአሁኑ ጊዜ ተቃውሞው በመተው በቅርቡ ለማግኘት የሚያስችል ተስፋ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በአብዛኛው አገሮች ለሦስቱም ተቀባይነት ተገኝቷል፡፡

የንግድ ምልክት መገኘቱ የቡና ዋጋና ወደ ወጪ የሚቀርበውን ቡና መጠን ለመጨመር እንደሚያስችል ጠቁመው ተመሳሳይ ጥራት ያላቸውን ቡናዎችን በስፋት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡
 
በሐረር የቡና እርሻ የነበሩት በጫት የተተኩበትን ሁኔታ አስታውሰው የቡና ዋጋ መጨመር የገበሬውን የማምረት ተነሳሽነት እንደሚጨምረውም ያላቸው እምነት ገልፀዋል፡፡   

 በቤዛዊት ሥዩም
 
< Prev   Next >