| ክቡር ሚኒስትር |
|
|
| Wednesday, 12 March 2008 | |
|
- ሃሎ.. - አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡ - የለም እንዴ ሰውየው? - አለ እንጂ ... መጥፎ ወሬም እየተወራ ነው፡፡ - ምን መጥፎ ወሬ? - የሃሰት ብር ታትሞ ሊገባ ሲል ተይዟል፡፡ ሊያስገባ የሞከረው እሱ ነው የሚል ወሬ አለ፡፡ ሁላችንም ተረብሸናል፡፡ - ቻቻቻቻ .... ው... ው... (ክቡር ሚኒስትሩ ስልኩን ዘጉትና ብቻቸውን ቢሯቸውን ዘግተው ተቀመጡ፡፡ ፀሐፊዋ ገባች) - ልግባ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ማን ነው እሱ? - የእርስዎ ጓደኛ ወንድም ነው፡፡ - ማን ነው የእኔ ጓደኛ? የምታውቂው ጓደኛ አለ? - ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ራስዎ ታመው ጀርመን ሲሄዱ ተባበረኝ ብለው የነገሩኝ ነዋ.. - ታዲያ እሱ ድሮ ነው፡፡ - እና ይግባ ወይስ? - ግባ በይው ግን የካቢኔ ስብሰባ ስላላቸው ለአንድ ደቂቃ ብቻ በይው፡፡ - እሺ፡፡ (ሰውየው ገባ) - ደህና ነዎት ክቡር ሚኒስትር? - ደህና ነኝ ምን ልርዳህ? - ወንድሜ የተፈረመ ደብዳቤ ይሰጡሃል ብሎ ነግሮኝ ለዛ ነው የመጣሁት፡፡ - ገና አልተፈረመም፡፡ - ተፈርሞ ተዘጋጅቷልና ሰው ላክ ብለውኝ ነው ብሎ ነበር የላከኝ፡፡ - መቼ ነው እንደዛ ያለህ? - ትናንት ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ታዲያ ዛሬኮ ብደውል ብደውል አጣሁት፡፡ - ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ነው፡፡ - ለምን? - እንጃ በወርቅ ይሁን በታተመ ብር ብቻ ባንዱ ጠርጥረውት ሊጠይቁት ፈልገው ነው መሰለኝ፡፡ ብቻ እሱን ይጠይቁት፡፡ ማታ ያገኙት የለ የእራት ግብዣ አለ እንዳይረሱ፡፡ - ፖሊሶች ይለቁታል ብለህ ነው? - እሱ ይችልበታል፡፡ ይሰጣቸዋል፣ ይለቁታል፡፡ - ገንዘብ አሳትሟል የሚባለውስ? - ቢሆንም ግማሽ፣ ግማሽ እንካፈለው ይላቸዋል፡፡ ይለቁታል፡፡ እሱ አክቲቭ ነው፡፡ - ፖሊሶችም ዘንድሮ ጠንከር ያሉ ይመስላሉ፡፡ - አንድ የመጣሁበት ምክንያትም ፖሊሶቹ ሲወስዱት ለእርስዎ እንድነግር ስለነገረኝ ነው፡፡ - እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ? - መርማሪዎቹን አያውቋቸውም? - አውቃቸዋለሁ ብለህ ነው? - ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ይሞክሩ፡፡ በነገራችን ላይ ምንጣፍ ከውጭ ገብቷል፡፡ ዛሬ ውሰድላቸው ስላለ ቤት ልውሰደው? - ቤ... ትት... ቤት አትውሰደው፡፡ የእህቴን ቤት ታውቀው የለ፡፡ እዛ ውሰደው፡፡ ደብዳቤውንም ለካ ፈርሜዋለሁ፡፡ እንካ ይኸውልህ፡፡ - አመሰግናለሁ ቻው፡፡ (ማታ ወደ ተጋበዙት ግብዣ አልሄዱም ሰውየው አልተለቀቀምና፡፡ የሄዱት ሌላ ቦታ ነበር) - ቢመጡልን ጥሩ ነበር ስንል መጡ አይደል ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ነገሩን ለማወቅ ስለፈለግሁ ነው እንጂ በዚህ ሰዓት እዚህ ቦታ መገኘት አልነበረብኝም፡፡ - ክቡር ሚኒስትር የኒውዮርክ ገዢ ከሴተኛ አዳሪዎች ጋር ይገናኝ እንደነበር ዛሬ ይፋ ተደረገ፡፡ ይቅርታ ጠየቁ፣ በቃ፡፡ እርስዎ ከእኛ ለአገርና ለወገን ከሚያስቡ ባለሃብቶች ጋር መገናኘትም ምን የሚያሳፍር ነገር አለው ያኮራል እንጂ፡፡ - እኔ ያሳፍራል አላልኩም፡፡ መሽቷል ነው ያልኩት፡፡ - ብቻ ወደቁም ነገሩ እንግባ ክቡር ሚኒስትር፡፡ በጥሞና ያዳምጡን ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እሺ አዳምጣለሁ፡፡ - ይኸውልዎት እርስዎን እንደ አባት፣ እንደወንድም ነው የምናይዎት፡፡ እንደ ባለስልጣን አይደለም፡፡ ባለሃብቱን ለማሸሽ ወርቅ፣ ባንክ እየተባለ መወንጀል ተጀምሯል፡፡ እኛ እንኳን ልንሰርቅ ያለንን ተካፍለን እንደምንበላ ከእርስዎ በላይ ምስክር የለም፡፡ - አውቃለሁ፡፡ - የእርስዎን ቤት የሰራነውና መኪና ለባለቤትዎ የሰጠነው ሃብትና ገንዘብ ተርፎን አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ያላችሁን ተካፍላችሁ ብሉ ስላለ ነው፡፡ - አውቃለሁ፡፡ ይህን ስለማውቅ አይደለም ወይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ ሲሄዱ አብራችሁ እንድትሄዱ ለማድረግ የምወተውተው፡፡ በቀደም ሽልማት ሲሰጥ ለሚወስኑት ሰዎች የእናንተ ስም እንዲገባ ያደረግሁት እኔ አይደለሁም ወይ? ጥሩ ለሰራልህ ጥሩ ስራ ብሏል ፈጣሪ፡፡ - ተብሏል ግን አሁን እንደምንም ብለው ይህ የተጀመረ ምርመራ እንዲቆም ያድርጉት ክቡር ሚኒስትር፡፡ - እ? - ለመርማሪውም ለአዛዡም ለሌላም ለሌላም የሚሸፈን ወጪ በእኛ ይተውት፡፡ ሌላ ሰው የለንም አሁን በቃ ቅበሩን ክቡር ሚኒስትር መረጋጋት ከሌላ ኢንቨስትመንት የለም ማለት ነው፡፡ ለዚህም ለዛም የሚያስፈልግ ወጪ ይኸውልዎት፡፡ - እኔ ምንም ወጪ የለብኝም፡፡ ገንዘብ አያስፈልገኝም፡፡ ምናልባት ለነዳጅ ይሆናል እሺ፡፡ - በቃ የራሳችን የቤተሰባችን ሕይወት በእርስዎ እጅ ነው፡፡ ሌላ የምንለው የለንም፡፡ - እሺ ቻው፡፡ (ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ገቡ፡፡ ከሚስታቸው ጋር ያወራሉ፡፡ ነገር ግን ሃሳባቸው ሌላ ጋር ነው) - ስማኝ እንጂ ምን እያሰብህ ነው? ልብህ እኔ ጋር የለም፡፡ - እየሰማሁ ነኝ፡፡ እሺ የጥሎሽ ነገር እያወራሽ ነው አይደል፡፡ - አዎን እኮ ልጨርስልህ ለጥሎሽ ወርቅ ይዘው መጡ፡፡ - እሺ፡፡ - ቤተሰቧ የተደሰተ መሰለህ? - ወርቅ ሲመጣ እንዴት አልተደሰቱም? - የዘመኑ በሽታ ነዋ.. - ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ደግሞ ከጥሎሽ ጋር ምን አገናኘው? - ኤድስ ማን አለህ? - የዘመኑ በሽታ ብለሽ የለ፡፡ - ባሌስትራ ማለት ነው፡፡ የጥሎሽ ወርቅ ባሌስትራ ቢሆንስ ብለው አልጠረጠሩም መሰለህ፡፡ - ስትስቂ ነዋ የዋልሽው? - በእናትህ የዛ ወዳጃችን አባት ሞተውኮ ቀብርም ሄጀ ነበር፡፡ እየሰማኸኝ ነው? - ኧረ እየሰማሁ ነው ስለቀብር አይደል የምታወሪ ያለሽው፡፡ - አዎን ስለቀብር ነው፡፡ - ቀብር እንዴት ነበር? - ምን ልበልህ... ቀብር ብሎ ዝም ነው፡፡ - አስፕሪን አለሽ ራሴን አመመኝ፡፡ - የሚዋጠውን ላምጣልህ የሚበጠበጠውን? - ካልበጠበጠኝ የተበጠበጠውን አምጭልኝ፡፡ - ሆስፒታል ልውሰድህ? - ለምን? - በጭራሽ ደህና አትመስልም? - ሥራ በዝቶብኝ ነው፡፡ - የራስህ ጥፋት ነዋ.. - ምን ጥፋት አለኝ? - እነዛ ወዳጆችህ ገንዘብ ማቋቋሚያ እንሰጥሃለን የግል ሥራ ትጀምራለህ ብለውህ የለ ለምን እሺ አትላቸውም? - አልገባኝም? - መንግሥት ካባረረህ እናግዝሃለን ነው ያሉት እንጂ አሁን ከወጣሁማ ምንስ እጠቅማቸዋለሁ፡፡ እዛ ሆነህ ጥቀመን እኛም እንጠቅምሃለን ነው የሚሉት፡፡ ከቦታየ ከተነሳሁ ዞር ብለውም አያዩኝም፡፡ ብር ከሌለኝ ብወጣ ምን ዋጋ አለው? - ኧረ ይህ ብር የሚባል ነገር የውሸት ብር ያሳተሙ ተያዙ አሉ፡፡ መረሸን ነበር የት አባታቸውንስ፡፡ - ኧረ ተው ሆስፒታል እንሂድ ፊትህ ጥሩ አይደለም፡፡ - በቃ ልተኛ አሁን፡፡ (ጧት ተነስተው የሄዱት ሆስፒታል አይደለም፡፡ ቢሮም አይደለም) - ክቡር ሚኒስትር በጧት መጡ አይደል፡፡ - አዎን ላነጋግርህ ብዬ ነው፡፡ - ምን ችግር አለ? - በወርቅ ጉዳይ፣ በልማት ባንኩ ጉዳይ፣ በብሄራዊ ባንክ ጉዳይ፣ ብር ያሳትማሉ፣ የሚል ወሬ አለ፡፡ ልማታችንን ለማደናቀፍ ሆን ተብሎ የሚሰራ አሻጥር እንዳይሆን ብዬ ነው፡፡ ጥርጣሬ ነው፡፡ - ውሸት አይመስለኝም፡፡ መዓት ማስረጃ እየተያዘ ነው፡፡ እኔም እንደርስዎ እንዳይሆን ሰግቼ ነበር፡፡ ግን የተረጋገጠ ነው፡፡ - እንደዚህ ዓይነት ሰዎች እንዳናጣቸው ብዬ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ግብር በመክፈል የታወቁ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ተሸላሚዎች ናቸው፡፡ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ዓለምን ይዞራሉ፡፡ ጥሩዎች ባይሆኑ ይህን ሁሉ ያደርጉ ነበር ወይ? - ብቻ ነገሩ ብዙ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ ሰዎቹ አደገኞች ናቸው፡፡ - አደገኞች ከሆኑ አደጋ እንዳያደርሱ በትዕግሥትና በጥበብ መያዝ ነዋ.. - እኮ በትዕግሥትና በጥበብ ስለያዝነው እንጂ አንዳንድ የሚተባበሩዋቸው ባለሥልጣኖች እንዳሉ ጥቆማ ደርሶንም ነበር፡፡ ለመያዝ አልፈለግንም፡፡ በትዕግሥት ነው የያዝነው፡፡ - ሻይ ወይስ ቡና? ክቡር ሚኒስትር፡፡ የዚህን ሆቴል ቡና እወደዋለሁ፡፡ - እሺ ቡና ጥቁር ቡና እነማን ናቸው እነዚህ ባለሥልጣናት? - ስማቸው እስካሁን አልተነገረም፡፡ ነገር ግን ማታ ማታም ቢሆን ይገናኛሉ ነው የሚባለው፡፡ - ባለሥልጣናት ካሉ በፍላጎታቸው አግባብቶ ስልጣን እንዲለቁ ማድረግ ነው፡፡ በሀገር ቀልድ የለም፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ባለሥልጣን ካሉማ መረሸን ነው እንጂ የምን ስልጣን እንዲለቁ ማድረግ፡፡ በሚሊዮን ሰርተው ስልጣን ቢለቁ ምን ይጎዳል? ለሌላው ትምህርት እንዲሆን መቀጣጫ መሆን አለባቸው፡፡ - እንግዲህ በዚህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ ስብሰባ ይጠሩ ይሆናል፡፡ - ትናንትና ማታኮ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ነበር፡፡ እሱማ ግማሽ ሌሊት ነበር ስብሰባው አሉ፡፡ - የአንድ ወዳጃችን አባት ሞተው ሌሊቱን እዛ ነበርኩ፡፡ ቀን ቀብር ነበር፡፡ ሃዘን ስለሆነ ሞባይሌን አጥፍቸው ነበር፡፡ የምረዳው ካለ እንድትነግረኝ ነው፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ካለ እናገራለሁ፡፡ አሁን ልሂድ የሚያዙ ተጨማሪ ሰዎች አሉ፡፡ - በጥዋቱ ነው የምታስሩት? - ክቡር ሚኒስትር ትናንት ልንይዛቸው ነበር፡፡ ማታ አካባቢ አንድ ባር ውስጥ ተሰብስበው ነበር፡፡ ምክንያቱን አላውቅም እንዳትይዙዋቸው ተባልን፡፡ - ለምን? - ምናልባት በመሃላቸው ሊያዝ ያልተፈለገ ሰው አለ ወይም እሱ እያለ ግርግር መፍጠር አልተፈለገም መሰለኝ፡፡ - ማን ነው እሱ? - ክቡር ሚኒስትር አለቆቻችን ናቸው የሚያውቁት እኛ አናውቀውም፡፡ - እነማን እንደሆኑ ስታውቅ ትነገረኛለህ? - ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር አንድ የሬዲዮ መልዕክት መጣብኝ፡፡ (ሰውየው ለ45 ደቂቃ የሚሆን በሬዲዮ ይነጋገራል፣ ይጨቃጨቃል፡፡ ስሜታዊ ሆኗል፡፡ ይቆጣል፡፡ ከ45 ደቂቃ በኋላ ወደ ክቡር ሚኒስትሩ መጣ) - አልሰማኸኝም መሰለኝ እነማን እንደሆኑ ስታውቅ ትነግረኛለህ? - ምን እነማን እንደሆኑ? - የሚፈለጉት ባለሥልጣናት እነማን እንደሆኑ ስታውቅ ትነግረኛለህ፡፡ - አወቅኩ እኮ አሁን በሬዲዮ መልዕክት ነገሩኝ፡፡ - ንገረኛ እነማን ናቸው? - እንሂድ እዛ ወንጀል ምርመራ ክፍል ይነገርዎታል፡፡ - ምን? - እንሂድ!! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |