Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow የጨው ገበያ ውሎ
የጨው ገበያ ውሎ Print E-mail
Wednesday, 12 March 2008
Imageባለፈው ሳምንት ማብቂያ በተወሰኑ ነጋዴዎች ያልተገባ ድርጊት የጨው ዋጋ መጨመርን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ ስለነበረው ግርግር የተለያዩ ሰዎችን ለማነጋገር መነን ትምህርት ቤት አካባቢ ዘጠኝ ቁጥር በግ ተራ ገበያ ተገኘን፡፡ ከበግ ተራው ወደ ላይ በሚወስደው ኮረኮንች መንገድ በግራና በቀኝ በርካታ ጉሊቶች አሉ፡፡ ጥቂት ጉሊቶችን እንዳለፍን ሌላ ጉሊት ጋር ቆመው በዓይናቸው የራሳቸውን ጉሊት ሲጠብቁ የተመለከትናቸውን እናት አነጋገርናቸው፡፡
ወ/ሮ አሰለፈች ገብሬ የሚኖሩት ቁስቋም አካባቢ የግለሰብ ቤት ተከራይተው ነው፡፡ ሦስት ልጆች ያሏቸው ሲሆን የመጀመሪያ ልጃቸው ትዳር ይዛ እንደምትኖር፣ ሌላዋ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ በመስተንግዶ ሥራ ላይ መሰማራቷንና የመጨረሻ ልጃቸው ደግሞ ገና ተማሪ መሆኑን ገለፁልን፡፡ እዚህ ገበያ ውስጥ መሥራት የጀመሩት መቼ ነው ስንል ጠየቅናቸው? “ከአስር ዓመት በላይ ይሆነኛል፡፡ በፊት እዚሁ አካባቢ ነበር ተከራይቼ የምኖረው፡፡ ቀደም ሲል በተለያየ አጋጣሚ መሀበር፣ ለቅሶና ምርቃት ሲኖር እየተዘዋወርኩ ወጥ እሠራ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ሰዎች ቤት በቋሚነት ልብስ አጥብ ነበር፡፡ እነዚህን ሥራዎች በመሥራት ነበር ልጆቼን ለማስተማር የምሞክረው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የጤና ችግር ገጠመኝ፣ አቅሜም እየደከመ መጣ” በማለት እዚያ ገበያ ውስጥ የተለያዩ ነገሮች መቸርቸር መጀመራቸውን ነግረውናል፡፡ ልጆቻቸውን ማስተማር ቢችሉም ዛሬም ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት የእሳቸው ብቻ ነው፡፡ ለዚህ የሚያስቀምጡት ምክንያት ደግሞ ትዳር የያዘችውም ሆነ በመስተንግዶ ሥራ ላይ የተሰማራችው ልጃቸው የሚያገኙት ገንዘብ ከራሳቸው አልፎ እሳቸውን ለመደገፍ የማይበቃ በመሆኑ ነው፡፡ የጨው ዋጋ ጨምሮ የነበረ እለት እዚያ አካባቢ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ሲገልፁ፣ ወደ እዚያ ገበያ የመጡት ከወትሮ ይመጡ ከነበረበት ሰዓት ቀደም ብለው እንደነበርና ወደ አራት ሰዓት ገደማ ግርግር ተፈጥሮ እንደነበር ነግረውናል፡፡ ወ/ሮ አሰለፈች እንደገለፁት አብዛኛውን ጊዜ እዚያ አካባቢ ባሉ ጉሊቶች ጨው በኪሎ አይሸጥም፡፡ እዚያ ገበያ ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች ምግባቸውንም እዚያው አብስለው ስለሚመገቡ አልፎ አልፎ ጨው በችርቻሮ የሚሸጡ አሉ፡፡ አንዳንዶች ተወደደ ብለው በአቅራቢያ ወደሚገኙ ሱቆች ሲሯሯጡ ቢመለከቱም ከዚህ ቀደም ጨው ተወዶ የዚያ ዓይነት ግርግር ተፈጥሮ ስለማያውቅ እውነት አልመሰላቸውም፡፡ ወደ መንገድ ወጣ ብለው በሱቆች ደጃፍ በርካታ ሰዎች ተሰልፈው ሲመለከቱ ሰዎች የተጣደፉበት ምክንያት ይኖራል ብለው ስለጉዳዩ አጠገባቸው ካሉ መደቦች ላይ ከሚሠሩ ጓደኞቻቸው ጋር ተነጋግረው እርሳቸውም ጨው ለመግዛት ወደ አንድ ሱቅ ሄደው ነበር፡፡

አንድ መደብር ለተወሰኑ ደቂቃዎች በአንድ ብር ከሀምሳ ጨው ሲሸጥ እንደነበር አስታውሰው የነበረው ሰልፍም በጣም ብዙ ስለነበር ቢያልቅስ፣ ባለሱቁ አልሸጥም ብሎ ቢያቆምስ በሚል ፍራቻ መጠነኛ ሰልፍ ወደ ነበረበትና ኪሎ ጨው አምስት ብር ይሸጥ ከነበረበት ሱቅ ሦስት ኬሎ ጨው መግዛታቸውን አልደበቁም፡፡ ጉሊታቸውን ለጓደኞቻቸው አስጠብቀው ጨው ለመግዛት ነበር የሄዱት፡፡ እሳቸው ገዝተው ሲመለሱ ደግሞ ጓደኞቻቸው ሄደው ገዝተዋል፡፡ አብዛኛው ሰው ይገዛ የነበረው ከአምስት ኪሎ ጨው በላይ እንደነበርና የዚያን እለት በዚያ ገበያ የተፈጠረው ግርግር ገበያውን የዓመት በዓል ገበያ አስመስሎት እንደነበር ከወ/ሮ አሰለፈች ለመረዳት ችለናል፡፡ የጨው ዋጋ መጨመር ያስከተለው ግርግር እንዳለ ሆኖ አንዳንዶች ጋዝም ይጠፋል በሚል ፍራቻ ጋዝ ለመግዛት ወደ ነዳጅ ማደያ ሲሄዱ ተመልክተዋል፡፡

በዚያ እለት የተለያዩ ሰዎች ለጨው መወደድ ምክንያት ያሉትን የተለያየ ነገር ይናገሩ ነበር፡፡ አንዳንዶች ይሰጡ የነበረው ምክንያት አሳማኝ ባይሆንም ተከስቶ የነበረው ድንገተኛ የጨው ዋጋ ጭማሪና ግርግር ከፍተኛ አለመረጋጋት ፈጥሮ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ሸቀጦች መወደድን ተከትሎ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት ሕገወጥ ነጋዴዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሕብረተሰቡ እንዲሸበር ያደርጋል ብለዋል፡፡ “አንድ ወቅት ላይ በርበሬም ከፍተኛ የዋጋ መወደድ አሳይቶ ነበር፡፡ ስኳር፣ ዘይት ጋዝም በቅርቡ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ በተለያየ ጊዜያት ሸቀጣ ሸቀጦች ሲጨምሩ ጨው ለረዥም ጊዜያት ይህ ነው የሚባል የዋጋ ጭማሪ አሳይቶ አያውቅም፡፡ ጨው ሊጠፋ ወይም ሊወደድ ይችላል የሚል ስጋት ያለው ሰውም አለ ብዬ አላስብም” በማለት የጨው ዋጋ ላይ የተደረገው አላአግባብ ጭማሪ ያስከተለው ግርግር እጅግ እንዳስገረማቸው ገልፀዋል፡፡

የጨው ዋጋ ላይ የተደረገውን አላግባብ ጭማሪ ተከትሎ ምሽት ላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሕገወጥ ነጋዴዎች ከሕገወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግሥት ያስተላለፈው መልዕክት ቅፅበታዊውን የጨው ዋጋ ንረት በፍጥነት ቀድሞ ይሸጥ ወደ ነበረበት ዋጋ እንዲመለስ አድርጓል፡፡ ይህ የመንግሥት እርምጃ የጨው ዋጋ መጨመርን ተከትሎ የተፈጠረውን የገበያ ግርግር በቀላሉ ቢያረጋጋውም በተለያዩ ሸቀጦች ላይ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረው በቀላሉ መክበር የሚፈልጉ ነጋዴዎችን በመከታተል ጠንካራ እርምጃ እስካልወሰደ ነጋዴዎች በተለያየ ጊዜ በሚፈጥሩት ግርግር ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሕብረተሰቡ መጐዳቱ አይቀርም፡፡

በዚያ እለት እዚያው በግ ተራ ዘጠኝ ቁጥር ማዞሪያ ውለው ምሽት ላይ ወደ ቤታቸው እስከሄዱበት ሰዓት ድረስ የጨው ዋጋ ከአንድ ብር ከሀምሳ እስከ አስራ ሁለት ብር መድረሱን የሚናገሩት ወ/ሮ አሰለፈች የጨው ዋጋ የዚያን እለት ይሸጥ ከነበረበት ዋጋ ይበልጥ ይጨምራል ብለው በማሰብ ጨው እያላቸው የለንም አንሸጥም ያሉ ባለሱቆችም እንደበሩ አልሸሸጉም፡፡ እንደዚህ ዓይነት የገበያ ግርግር ሲፈጠር በሸቀጦች ላይ ከተደረገው አላግባብ ጭማሪ ባሻገር ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው የተፈጠረውን አጋጣሚ ጠብቀው በሚነሱ ዘራፊዎች ሕብረተሰቡ እንደሚጐዳ አስረድተዋል፡፡

በተለያየ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ሕገወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር መንግሥት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ባሻገር አላግባብ ዋጋ በመጨመር የገበያ ግርግር ለመፍጠር የሚሞክሩ ነጋዴዎችን ለሚመለከተው አካል መጠቆምን ጨምሮ የዚህ ዓይነት አጋጣሚዎችን ተረጋግቶ የማጤንና የማሳለፍ ልማድን ሕብረተሰቡ ሊያዳብር ይገባል፡፡

በምሕረት አስቻለው
 
< Prev   Next >