| የፎቶ ግራፍ አመጣጥ |
|
|
| Wednesday, 12 March 2008 | |
|
ምኒልክ የውጭ አማካሪያቸውን ጠሩትና እየሳቁ “አንድ ነገር ሰማሁ፡፡ ይህም የሰማሁት ነገር ፍፁም ውሸት መሆኑን አውቄአለሁ፡፡ ይህ የሰማሁት ነገር እኔን ትንሽ ያደርግና ከነቤተመንግሥቴ ሌላውን ቤት ሁሉ ሕዝቡ በቅሎና ፈረሱ ሁሉ ሳይቀር እትንሽ ጥቁር ሳጥን ውስጥ ይጨምረናል አሉ፡፡ ይህ ነገር ፈፅሞ የማይቻል ነገር ነው፡፡ እውነት ነው ካልክ እንዴት ሊሆን ይችላል” አሉት፡፡ አማካሪውም እውነት መሆኑን ቢነግራቸው “እንዴት ሊሆን ይችላል፡፡ ደግሞ እኮ እዚያች ትንሽ ሳጥን ውስጥ የሚጨምረን እየዘቀዘቀን ነው አሉ፡፡
አሁን እኔን ከዚህ አንስቶ ራሴን ቁልቁል፣ እግሬን ሽቅብ የሚያደርገኝ ነገር እንዴት ይኖራል፡፡ ያውም ሰው ሳያግዘው ነው" አሉት፡፡ ከዚያ በኋላ ካሜራ እንዲመጣ ታዞ ካሜራው ከነፎቶግራፍ አንሺው በ1875 ዓ.ም መጣ፡፡ (አዲስ ኢንቨስትመንት፣ ነሐሴ 1999) በማደግ ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ቻይና በቀጥታ የስልክ አገልግሎት ዓለምን በመምራት ላይ ትገኛለች፡፡ ቻይና ያሏት ቀጥታ (አውቶማቲክ ቴሌፎን) ጥሪ ማድረግ የሚችሉ ደንበኞች ቁጥር በአንድ ዓመት ውስጥ በእጥፍ በማደግ 13 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ይህም ቻይና በዓለም ከፍተኛ ቀጥታ የቴሌፎን ጥሪ ማድረግ የሚችሉ ደንበኞች ያሉባት አገር እንዳዳረጋት በአንድ ጉባኤ ላይ የቀረበ ሪፖርት ይገልፃል፡፡ ይኸው ሪፖርት እንዳመለከተው የቀጥታ ቴሌፎን ጥሪ በሌሎች አገሮችም እድገት በማሳየት ላይ እንደሆነ ገልፆ የዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎች ጠቅላላ ቁጥር እስከ ታህሳስ ወር ድረስ 100 ሚሊዮን እንደሚደርስ ያስረዳል፡፡ (ቴሌ ነጋሪት፣ መስከረም-ታህሳስ 1994) ጋንዲ ጋንዲ እንደማንኛውም ተራ ሰው መኖርን ይመርጣል፡፡ ሩስኪና ቶልስቶይም በመጽሐፎቻቸው ይህንኑ ነበር ይፅፉ የነበረው፡፡ እነዚህ ደራሲዎች የሰው ልጅ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ራሱ መፈፀም አለበት ብለው ያምናሉ፡፡ ለምሣሌ ሰው ለራሱ የሚያስፈልገውን ምግብ ራሱ ማብሰል አለበት፡፡ የራሱን ቤት ራሱ መሥራት አለበት፡፡ የሰው ልጅ ሥራዎቹን በራሱ ካከናወነ ህይወት ቀላል ትሆናለች ይላሉ፡፡ ጋንዲም ይህንን ሀሳብ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት የራሱን ልብስ የሚያጥበው ራሱ ነበር፡፡ ፀጉሩን የሚያስተካክለው እሱው ነበር፡፡ ጋንዲ ፀጉር አስተካካይ ቤት ሄዶ አላስተካክልህም ብሎ ከመለሰው በኋላ ነበር፡፡ በነጩ ፀጉር አስተካካይ እምቢታ ጋንዲ አልተበሳጨም፡፡ ምክንያቱም ይህ ነጭ ፀጉር አስተካካይ ጋንዲን አላስተካክልህም ያለው እዚህ ፀጉር ማስተካከያ ቤት ፀጉራቸውን የሚስተካከሉት ሁሉም ነጮች በመሆናቸው ጋንዲ ፀጉሩን ሲስተካከል ቢያዩት ደንበኞቹ እንዳይሸሹት ካለው ፍርሃት የመነጨ መሆኑን ያውቅ ነበር፡፡ ጋንዲ ብዙ ጊዜ የሌሎች ሰዎችን ችግር መገንዘብ የሚችል ሰው ነበር፡፡ (ሰለሞን ኃይለማርያም፣ የታላላቅ ሰዎች እውነተኛ የፍቅር ታሪኮች፣ 1980) በሴቶች ላይ ተፅዕኖ የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ገበያዎች ከክልል ውጭ ካሉ ሀገሮች እየመጡ በሚራገፉ ርካሽ ጨርቃጨርቆችና “ነፍስ ይማር” ልብሶች ከአፍ እስከገደፋቸው የተሞሉ ስለሆኑ፣ የአካባቢው ሴቶች የሚሠሯቸው የእደ ጥበብ ውጤቶች የሚያስገኙት ገቢ ትንሽ ነው፡፡ ድንበሮችን እያቆራረጡ በንግድ ከሚሰማሩትና ወደሌሎች ሀገሮች እየፈለሱ ተቀጥረው ከሚሠሩት ወንዶች ይልቅ ሴቶች ሲሆኑ፣ ፍልሰቱ በአብዛኛው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች ነው፡፡ ወደሌሎች ሀገሮች እየፈለሱ ተቀጥሮ የመሥራቱ ነገር የሰብዓዊ መብቶችን መረገጥ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል፡፡ የመንግሥት የልማትና የንግድ ተቋማት ለግል ባለሀብቶች ሲሸጡ፣ ኢኮኖሚው በነፃ ገበያና በኢ-ማዕከላዊነት መርህ በመመራቱ የተነሳ በመደበኛው የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው በነበሩት ሴት ሠራተኞች የሥራና የማኅበራዊ ዋስትና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አድርጓል (ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያ ፋብሪካዎች ወደግል ይዞታነት ሲለወጡ የሥራ እና የማኅበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩት ሴቶች ለችግር ተጋልጠዋል)፡፡ የገጠር ሴቶችም ለቤተሰቦቻቸው ኑሮ የሚያስፈልገውን ገቢ ለማግኘት ላይ ታች ለማለት ተገደዋል፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ውስጥ፣ በግብርናው ዘርፍ ይደረግ የነበረው የድጎማ ፕሮግራም በመቋረጡና በአንድ ምርት ወይም ሸቀጥ (ለምሳሌ ቡና፣ ከብት፣ ወዘተ". ይመካ የነበረው ኢኮኖሚ በማቆልቆሉ፣ ወንዶች ገበሬዎች ቤተሰቦቻቸውን እየጣሉ ሌላ ሥራ ፍለጋ ወደ ከተሞች ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተዳምረው፣ ሴቶች ልጆቻቸውንና ራሳቸውን ለመደገፍ ያላቸውን ጊዜና ችሎታ ስለሚጫናቸው፣ አሁን የተንሰራፋው የዓለም አቀፋዊነት መርህ በከፈታቸው ዕድሎች ወደ መጠቀሙ አማራጭ እንዲያዘነብሉ ይገደዳሉ፡፡ (የሥነ-ጾታ ጉባኤ የጾታ እኩልነትና የለውጥ ስልቶች በአፍሪካ ቀንድ፣ህዳር 1996) አባይ ፊት ለፊትህን ስትጋልብ አባይ አባይ አባባይ መሶባችን ተራቁቶ ሲዘምም አንገትህን አዙረህ ላታይ ፍርፋሪያቸውን ላናይ ፈትፍቶ ለባዕድ አቀባይ ጠኔ ጌጥ ነው ያገርህ ታሪክ ይኸው ልንገርህ በአደባባይ ቤተኛ ነኝ አይበል ድርሳንህ ዋሾ ቀጣፊ ነህ አባይ ግን ደሞ አንተ ምን ታረግ? እኛው ነን አንተን የእኛ ባይ አባይ፡፡ (ቴሌ ነጋሪት መስከረም-ህዳር 1997) ካዛንቺስ ከታላቁ ቤተ መንግሥት ወደታች እስከ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ድረስ የተዘረጋው ቦታ “ካዛንቺስ” እየተባለ ፋሺስት ጣሊያኖች ባወጡለት ስም እስከ ዛሬ ድረስ ይጠራል፡፡ ወራሪዎቹ ጣሊያኖች አዲስ አበባ ከተማን ለ200,000 ያህል የጣሊያን ተወላጆች መኖሪያና ዋና ከተማ ለማድረግ በነበራቸው ፖሊሲ መሠረት ኢትዮጵያውያንን ከማዕከል ወደ አዲስ ከተማ አፈናቅለው ለራሳቸው መኖሪያነት ምሥራቃዊውንና ደቡባዊውን የከተማዋን ክፍል መርጠው ነበር፡፡ በዚሁ መሠረት ምሥራቃዊውን የከተማዋን ክፍል የፋሺስት ጣሊያን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣኖች መኖሪያ ለማድረግ ስለታሰበ፣ መኖሪያ ቤቶችን ሠርቶ የሚያስረክብ አንድ መንግሥታዊ የቤት ግንባታ ድርጅት (ፕሮጀክት) ተቋቁሞ ነበር፡፡ የድርጅቱ ስያሜ በምሕፃረ ቃል ካዛንቺስ (I.N.C.I.S) ይባል ስለነበር አካባቢው በዚሁ ቃል መጠራት ጀመረ፡፡ አሁንም የሚታወቀው በዚሁ ስሙ ነው፡፡ ምሕፃረ ቃሉ ሲዘረዘር “ኢስቲቱቶ ናሲዮናሌ ፔር ሌ ካዜ ዴሉ ኢምፒየጋቲ ዴሎ ስታቶ” ነው፡፡ ትርጉሙም “የመንግሥት ሠራተኞችን መኖሪያ ቤቶች የሚገነባ ብሔራዊ ተቋም” እንደማለት ይሆናል፡፡ የፋሺስት ጣሊያን መንግሥት በተጠቀሰው ድርጅት አማካይነት ለኃላፊዎቹ ካሠራቸው ቤቶች የተወሰኑት አሁንም “ካዛንቺስ” ውስጥ ይገኛሉ፡፡ (ቱሪዝም አዲስ፣ ህዳር 2000) የጊዜ አጠቃቀም ጊዜ ሃብት ነው፡፡ “ጊዜ ወርቅ ነው” የሚለው አባባል ጊዜ ከምንም ነገር በላይ ውድ የሆነ የሰው ልጆች ጥሬ ሀብት (Resource) እንደሆነ ያረጋግጥልናል፡፡ ከአደጉ አገሮች ልምድ በመነሳት ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ብልጽግናን ያመጣል፡፡ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ትርፍ እቃ፣ ንብረት፣ እና ጥሬ ሀብት (Resource) ሆኖ የሚያዘው ጊዜ ነው፡፡ ሌሎች ያደጉ አገሮች ደግሞ የሌላቸው ጊዜ ነው፡፡ ኢንተርፕረነሮች ለትልልቅ ራዕይ የተወለዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ኢንተርፕረነሮች የሕዝብን አመለካከትና በራሳቸው አኗኗር የሚቀይሩ የፈጠራ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ኢንተርፕረነሮች ችግርን የሚቋቋሙ፤ ከችግሩ በመነሳት መፍትሄና ቢዝነስ የሚፈጥሩ፤ በዚያም በሚፈጥሩት ቢዝነስ የሀገራቸውን ኢኮኖሚ የሚቀይሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ለእነዚህ ሰዎች ጊዜ ከምንም ነገር በላይ ውድ ይሆንባቸዋል፡፡ ይህን ውድ የሆነ ጥሬ ሀብት (Resource) በአግባቡ መጠቀምና አለመጠቀም ለኋላቀርነት ወይም ለእድገት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ ከማንኛውም ነገር በላይ በየትኛውም አገር ለሁሉም ሰው እኩል የተሰጠው ነገር ቢኖር ጊዜ ነው፡፡ ምናልባት በሌሎች ጥሬ ሀብቶች (Resource) ላይ ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ ጊዜ ግን እኩል ታድሎናል፡፡ ልዩነቱ ጊዜን በአግባቡ የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች የእቅድ አፈፃፀማቸውን ሲገመግሙ በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ፣ ይህን ያህል ፐርሰንት እቅዴን እውን አድርጌአለሁ፤ ብለው ሲያቀርቡ፤ ከነበረኝ ጊዜ ይህን ያህል ተጠቅሜአለሁ፣ ይህን ያህል ግን ባክኖብኛል ብለው ሪፖርት አቅርበው አያውቁም፡፡ ይህም ጊዜ ዋጋ እንዳልተሰጠው ያሳየናል፡፡ ጊዜ የሚለካ ጥሬ ሀብት (Resource) ነው፡፡ በምንሠራው ሥራ፣ በምናከናወናቸው ተግባራት፣ በአጠቃላይ በምንደርስበት እድገት ይለካል፡፡ ጊዜ በምንም የማንተካው ጥሬ ሀብት (Resource) ነው፡፡ ሌሎች ጥሬ ሀብቶችን (Resource) መለወጥ ይቻላል፡፡ ጊዜ ግን አንዴ ካለፈ የማይመለስ፣ እንደገና ልናገኝ የማንችለው ትልቅ ሀብታችን ነው፡፡ (አትርሳው ጣሰው እና ብርሃነ ሰሙ የብልፅግና ቁልፍ፣ 1999) ገራገር ረዥሙ የጆሮ ውስጥ ፀጉር ተመዘገበ አንድ ሕንዳዊ የሸቀጣሸቀጥ ነጋዴ በጆሮአቸው ውስጥ ያለው ፀጉር ረዥምነት በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ መስፈሩ ተገለፀ፡፡ ረድሃንካንት ባጃፓይ የተባሉት የ580 ዓመት አዛውንት በጆሮአቸው ውስጥ ያለው ፀጉር 9.8 ኢንች ርዝመት እንዳለው ዘ ሰን የተሰኘው ጋዜጣ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ባጃፓይን የጆሯቸውን ፀጉር ለማፅዳት የተለየ ሻምፖ ይጠቀማሉ፡፡ የጆሮ ፀጉራቸውን ደህንነት ለመጠበቅ የጆሮም ሆነ የአንገት ጌጣጌጥ እንደማያደርጉ ተጠቁሟል፡፡ በሰሜናዊ ሕንድ ኡታር ጃራዴሽ ናይ ጋንጂ የሚገኙት አዛውንቱ ሰዎች የተለየ ተፈጥሮአችን ከቁም ነገር እንዲቆጥሩት ጠይቀዋል፡፡ “በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ” ላይ ለመመዝገብ በመቻሉ ለእኔም ሆነ ለቤተሰቦቼ መልካም እድል ነው ብለዋል፡፡ ገነት የተላከው ደብዳቤ ተመላሽ ሆነ አንዲት ፈረንሳይዊት ታዳጊ ከሁለት ዓመት በፊት በሞት ለተለየቻት እናቷ የፃፈችው ደብዳቤ ተመላሽ በመሆኑ ለዚህም ተገቢውን ክፍያ እንድትከፍል ተጠየቀች፡፡ የ13 ዓመቷ ታዳጊ አነየስ ደብዳቤውን ሔቨን ከተማ ፓራዳይዝ ጎዳና ብላ መላኳ ተመልክቷል፡፡ ሕፃኗ የፃፈችው እናቷን ዛሬም ቢሆን እንደምትወዳት የሚገልፅ ደብዳቤ ሲሆን ከሞተች ሁለት ዓመት የሆናትን እናቷን ዘወትር በማሰብ እንደምትጨነቅ ተጠቁሟል፡፡ የፈረንሳይ የፖስታ ቢሮ በሁኔታው ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን የቢሮው ቃል አቀባይ “ሲየል” በፈረንሳይኛ ሔቨን የተሰኘ ከተማ በመኖሩ ፖስታው እንደተላከና ፓራዳይዝ የሚባል ጎዳና ባለመኖሩ መመለሱን አስረድቷል፡፡ ለስንፈተ ወሲብ ተዳርጌያለሁ ያለው የኪሣራ ክፍያ ጠየቀ አንድ ጣሊያናዊ ከሚስቱ የ14,000 ፓውንድ የኪሳራ ክፍያ ጠይቋል፡፡ ምክንያቱም በጭቅጭቅ ለስንፈተ ወሲብ ዳርጋኛለች የሚል ነው፡፡ በፓርማ ከተማ ኗሪ የሆነው ሰርጂዮ ቪኑቺ ጥያቄውን የሚደግፍ የሕክምና ማስረጃ ለፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን ይህም ሚስቱ በጭቅጭቅ ጭንቀት በመፍጠር በመጨረሻ ስንፈተ ወሲብ እንዲፈጠርበት እንዳደረገችው ያስረዳል፡፡ ቪኑቺ “ሚስቴ ሁሌም ቢሆን ቅሬታ እንዳሰማችና እንደተጨቃጨቀች ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ ጭንቀት ላይ የሚጥል ስለሆነ የወንድነት ስሜቴ እንዳይመጣ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተወሰነ ካሳ ያስፈልገኛል” ብሏል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |