|
Wednesday, 12 March 2008 |
|
“እናቶች ብዙ ጊዜ ለልጆቻቸው ያነባሉ፡፡ አባቶች ጣጣቸውን ቢሮ ውስጥ ጨርሰው ይመጣሉ፡፡ ቤት ውስጥ ከልጆች ጋር የማንበብ ነገር የጎላ አይደለም፡፡ አንድ አስቸኳይ ሥራ ነበረብኝና የማነበውን ነገር ይዤ መጥቼ ቁጭ ስል የእናቴን መጽሐፍ ቁጭ አድርግ፣ ያንተ አይደለም አለኝ፡፡ ለካ ይሄ ልጄ ማይም አድርጎኛል፡፡”
ይህ በሕፃናት የንባብ ልምድ ውስጥ ከወላጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያሳይ ገጠመኝ የቀረበው ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል አዳራሽ ነበር፡፡ ወላጆች በተቻለ መጠን ሁለቱም አባትና እናት ምሳሌ መሆን አለባቸው የሚለውን መሠረተ ሐሳብ ለማሳየት የአንዱን እሙናዊ ገጠመኝ ያቀረቡት የሕፃናት መጻሕፍት በማዘጋጀት የሚታወቁት ረዳት ኘሮፌሰር ዓለም እሸቱ ናቸው፡፡ “ንባብ የሕፃናትን የወደፊት ሕይወት በጽኑ መሠረት ላይ የሚያውል ሁነኛ መሳሪያ ነው” በሚል መሪ መልእክት በተዘጋጀው መድረክ ላይ በሕፃናት መጻሕፍት ደራሲው የተደረሱና የተተረጐሙ አስራ አምስት አዳዲስና ነባር የሕፃናትና የታዳጊዎች መጻሕፍት ታትመው ለእይታ ቀርበዋል፡፡ ሕፃናት፣ ወላጆች፣ ከተለያዩ የከተማው ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ መምህራንና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተገኙበት በቀረበው የረዳት ኘሮፌሰር ዓለም ማብራሪያ በልጆች ንባብ ልምድ ውስጥ የወላጆችን ሚና አብራርተዋል፡፡ በልጆች ንባብ ልምድ ውስጥ ወላጆች የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ምንድን ነው? ወላጆች ለልጆች ምን ጊዜ ማንበብ ይኖርባቸዋል፡፡ ብዙ ወላጅ ሕፃናት ማንበብ ያለባቸው ትምህርት ቤት መሄድ ሲጀምሩ ነው ብሎ ነው፡፡ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት ንባብ ፊታቸውን ሊመታ አይገባም ብሎ ያስባል፡፡ “ነገር ግን ሕፃናት ገና አፍ ባልፈቱበት፣ ወላጆች ጭን ላይ በሚቀመጡበት ጊዜ ነው ልናነብላቸው የሚገባው፡፡ የሕፃናት መጻሕፍት በባሕሪያቸው ድግግሞሽ፣ ዜማዊነት አላቸው፡፡ ሕፃናትም ያንን ባሕሪ የመከተል ነገር አላቸው፤” ብለዋል፡፡ ትምህርት ቤት እስኪሄዱ መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ አንዳንድ ወላጆች ሕፃናት መጻሕፍትን እንዲያውቁ ድምፅን ከፍ አድርጎ የማንበብ ሁኔታ ማንበብ ከቻሉ በኋላ አያስፈልግም ይላሉ፡፡ ልጆቹ ግን ይፈልጉታል፡፡ ለሕፃናት የሚነበቡ ጽሑፎች አንዴ ተነበው የሚያበቁ አይደሉም፡፡ ሁሌም ተደጋግሞ እንዲነበብላቸው የሚፈልጉት ነገር አላቸው፡፡ ለሕፃናት ምን እናንብብ? ተረት ብቻ የሚያስቡ አሉ፡፡ ግን ተራኪ የሆኑ አጫጭር ግጥሞችና እንቆቅልሾች ልናነብላቸው እንችላለን፡፡ የልጆች ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ በራሪ አስገራሚ ጽሑፎች ማንበብ እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ዓለም፣ በተቻለ መጠን ሕፃናት በግልጽ መጽሐፉን ሊያዩት በሚችሉበት መንገድ ማንበብ እንደሚገባ፣ ስናነብላቸው መጽሐፉን ጠጋ ብለው እንዲያዩና ሥዕሎቹን እንዲመለከቱ ዕድል በመስጠት አብረው በጋራ የሚያነቡበት መንገድ እንደሚያስፈልግ፣ በዝግታ ስናነብም በተቻለ መጠን ድራማዊ በሆነ መልክ ማንበብ ሕፃናቱን የበለጠ እንደሚስባቸው አመልክተዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ለሕፃናት ስናነብ ሕፃናት እንድናቆም የሚጠይቁበት ጊዜ አለ፡፡ ጥያቄ ይጠይቃሉ፣ አንዳንድ ወላጆች “ዝም በል እስክጨርስ ምን ያቅለበልብሃል?” ይላሉ፡፡ እንደዚያ መሆን እንደሌለበትና ጥያቄ ካለ ምላሽ ሰጥቶ ወደቀጣዩ መሄድ እንጂ አታቋርጠኝ ብሎ ለሕፃናቱ ጥያቄ ምላሽ አለመስጠት ትክክለኛ አካሄድ አይደለም፡፡ ተራክቦ መፍጠር ጥሩ ነው፡፡ እንደ አቶ ዓለም አተያይ ወላጆች በሕፃናት ዘንድ የንባብ ልምድን ለማስረጽ፣ በተቻለ መጠን ለንባብ ከፍተኛ ግምት የሚሰጡ መሆኑን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ለልጆች ማሳየት ይገባል፡፡ እኛ ለንባብ ትኩረት ከሰጠን ልጆችም ይከተላሉ፡፡ አዘውትሮ መጽሐፍን መያዝ ልጆችን እንዲሳቡ ያደርጋል፡፡ የንባብ ጊዜ መወሰንና እንዲከበር ማድረግ፣ ሁልጊዜ በትምህርት ዓይነቶች ላይ ችክ ማለት እንደሌለባቸውና ጊዜ ማሳለፊያ ንባቦችን ከታች ጀምሮ እንዲተዋወቁ ማድረጉም ተገቢ ነው፡፡ የሕፃናት መጻሕፍት ገበያ የሚመጣው ክረምት ሲመጣ ቢሆንም “ትምህርታችሁን አጥኑ” በማለት ወላጆች የሚከለክሉበት ሁኔታ መታረም እንዳለበትና በሕፃንነት የሚጀመር የንባብ ልምድ መጻሕፍት አስተማሪ መሆናቸውን መዘንጋት እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡ የማንበብ፣ የመጻፍ፣ የማዳመጥና የመናገር ክሂልን ያዳብራል፡፡ በተጨማሪ አስተዋይና ሒሳዊ አስተሳሰብን ያዳበሩ ሕፃናት እንዲሆኑ ትልቅ ድጋፍ ስለሚያደርግ ዓመቱን ሙሉ መጻሕፍቱን በኘሮግራም መከታተል እንደሚገባቸውና ካነበቡ በኋላ ጊዜ ወስደው መወያየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ዓለም ትንተና አንዳንድ ወላጆች ጥሩ ገዢዎች ናቸው፡፡ መጻሕፍት ይዋሳሉም፡፡ ሆኖም መግዛትና መዋስ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ ብዙዎቹ ማንበባቸውን መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ልጆቻችን ወደ ቤተ መጻሕፍት ወይም ወደ መጻሕፍት መደብር መውሰድና ማሳየት ከመጻሕፍት ጋር ያላቸውን ቀረቤታ የጠበቀ ሆኖ እንዲመጣ ያደርጋል፡፡ አንብበው ሲጨርሱ ማበረታቻ ሽልማት መስጠት ከከረሜላ ጀምሮ ሊለመድ ይገባል፡፡ በውስጣቸው የሚፈጥረው ትልቅ ነገር የሕፃናት የዘወትር ተግባራቸው መማር፣ መማር መማር እንደሆነ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገር ይገባል፡፡ አንድ መነኩሴ በየገዳማቱ እየዞሩ ..እንዴት ዋላችሁ፤ ደህና ናችሁ፣ እንዳትረሱ ሞት አለ፤ እያለ እያስታወሱ ይሄዳሉ፡፡ እኛም ለሕፃናት ሁልጊዜ ማድረግ የሚገባን ምንድነው የተሻለ ሕይወት ሊገጥመን የሚችለው የተሻለ ደረጃ ልንደርስ የምንችለው ትምህርታችንን አጥብቀን ስንይዝ ብቻ ነው፡፡ ካለ ትምህርት ሊገኝ የሚችል ምንም ነገር የለም ብለን ልንነግራቸው ይገባል.. ብለዋል፡፡ ወደኋላ የቀረውን የሕፃናት መጻሕፍት ንባብ ጉዳይ አንስቶ መነጋገሪያ መድረክ መፈጠሩን ያወደሱት የዩኒቨርሲቲው መምህር ዶክተር ብርሃኑ ማቴዎስ የንባብ ትምህርት ከሙዓለ ሕፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሰጥበት ሁኔታ መመቻቸት እንደሚገባው አስታውሰዋል፡፡ አያይዘውም “ከረምት ኮርስ ተማሪዎች ጋር ሥነ ጽሑፍን በቋንቋ ማስተማር ዙሪያ ባለው አገልግሎት ድምፅን ከፍ አድርጎ ማንበብ ያለውን ፋይዳ አስመልክቼ ስጠይቅ “ይሄ በፖሊሲ ተከልክሏል ሲሉኝ ገርሞኝ የሚመለከታቸውን ሁሉ ጠይቄያለሁ” ብለዋል፡፡ ከመምህራኑ ሥልጠና በላይ የሚያሳስበው ለተማሪዎቻችን የሚያነቡት ነገር አቅርበናል ወይ ብለው የጠየቁት አቶ ዓለም፣ ችግሩ ከሁለተኛ ደረጃ በላይ የዘለለ በመሆኑ የንባብ ትምህርት መስጠት እንደሚያስፈልግና መምህራን ከዘመናዊ የንባብ ማስተማሪያ ሥነ ዘዴ ጋር የሚተዋወቁበትን መንገድ መቀየስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሕፃናት መጻሕፍት የአማርኛ እትሞች ታሪክ ዙሪያ ዳሰሳ ያቀረቡት አቶ አስፋው ዳምጤ እንደገለጹት፣ የመጀመሪያው “የፍቅር መላእክት ለኢትዮጵያ ልጆች” በሚል ርእስ በ1916 ዓ.ም. የታተመው መሆኑን የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “ስኳርና ወተት” የእንግሊዝኛ ተረት መጽሐፍ በ1922 ተተርጉሞ መታተሙ፣ ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ በከበደ ሚካኤል በሦስት ቅጽ የተዘጋጁት “ታሪክና ምሳሌ”፣ በ194ዐዎቹ በገብሬ ወዳጆ የተደረሱት “ለማና ዘመዶቹ”፣ “ለማ በትምህርት ቤት”፣ “ለማ በገበያ” ከቀዳሚ ሥራዎች እንደሚጠቀሱና በ197ዐዎቹ የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት አስተዋጽኦ ዓይነተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በአቶ ዓለም 15ቱ መጻሕፍት ኪነ ትረካ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ መምህር የሻነው ተሰማ ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሥራዎች በሐሳብ ውስጥ የሚቀሩ መናፍስትና አማልክት ዓይነት ባሕርያትን ይጠቀሙ እንደነበርና ቀስ በቀስ ወደ ሰብዓዊ ባሕርያት ማተኮራቸው፣ ተረቶቹ አጫጭሮችና ሕፃናቱ ተረቱን በቃል ለመተረክ የሚያስችላቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የአሁኖቹ ታሪኮች ለሥዕሎች ግብአት ትኩረትና ጥንቃቄ መሰጠቱንና ሥዕሎቹና ትረካዎቹ በአቻነት የቀረቡበት በአመዛኙ መልካም መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በመሰናዶው ላይ ከጥሩ አንባቢነታቸውና ሌላ ለደራሲው ግብረ መልስ (ፊድባክ) በመስጠት አስተዋጽኦ ላደረጉ አምስት ሕፃናት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የውይይቱ መሪ የነበሩት አቶ ደረጀ ገብሬ ወላጆች በእኩል ለልጆቻቸው ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው አንድ ገጠመኝ በማንሳት ተናግረዋል፡፡ “በ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ጊዜ የሰዓት እላፊ በአንድ ሰዓት በመሆኑ አባወራ በጊዜ እቤቱ ይገባል፡፡ ልጆቹ ለእናታቸው አንድ እንግዳ ሰው ሳሎን ተቀምጧል ይላሉ፡፡ እናት ሄዳ ስታይ አባታችሁ እኮ ነው ስትላቸው፣ አባታችን ያ ነው በማለት ፎቶ ግራፍ ላይ ያለውን የቀድሞ ምስል ያሳያሉ፡፡ እነሱ የድሮ መልኩን ያስታውሳሉ፡፡ በተለያየ ምክንያት አምሽቶ ስለሚገባ አነጋግሯቸው፣ አጫውቷቸውና አስነብቧቸው አያውቅም፡፡” |