Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Friday
Nov 21st
Home arrow Sections arrow ዝክረ ገና - 2000
ዝክረ ገና - 2000 E-mail
Tuesday, 08 January 2008
ነገ ታኅሣሥ 28 ቀን 2000 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ምእመናን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት /ገና/ በዓል ያከብራሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በምሥራቁ ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያንም ነገን በጁሊያን አቆጣጠር /ካሌንደር/ ዲሴምበር 25 በማለት ዕለቱን ያከብራሉ፡፡

የጎርጎርዮሳዊውን አቆጣጠር የሚከተሉት ምዕራባውያን ከሁለት ሳምንት በፊት ዲሴምበር 25 /ታኅሣሥ 15/ ማክበራቸው ይታወሳል፡፡

ገና በኢትዮጵያ በታላቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበር ዐቢይ በዓል ነው፡፡ ሦስት ዓመት በተከታታይ ታኅሣሥ 29 ቀን ውሎ በአራተኛው ዓመት፣ ጳጉሜን 6 ስለምትሆን በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ 28 ይውላል፡፡ ዘንድሮ የሆነው ይህ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳውያኑ ከ43 ቀናት ጾም በኋላ ልደትን የሚያከብሩት በዋዜማው ዛሬ በየአብያተ ክርስቲያናቱ በመገኘት በጸሎተ ቅዳሴ ነው፡፡ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ ስጦታ ካበረከቱት ሰብአ ሰገሎች መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሌሊቱን ማሕሌት ተቁሞ ቅዳሴ እንዳበቃ የበዓል ፍጻሜ ቢሆንም በላሊበላ ግን ከዚህ በተጨማሪ ታኅሣሥ 29 ቀን ጧት ላይ ቤዛ ኩሉ የተሰኘው ክብረ በዓል ከአለት ከተፈለፈሉት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በአንዱ በቤተማርያም ካህናቱ ጋራና መሬት ላይ ሆነው ያከብሩታል፡፡

ስለ አከባበሩ ያጠናችው መሶበ ወርቅ ቅጣው በጥናቷ እንደገለፀችው፣ በላሊበላ ያለው የገና በዓል አከባበር የካህናቱ ረባዳ መሬትና ጋራ ላይ መሆን ትርጉም አለው፡፡

መሬት ላይ ያሉት የእረኞችና ማሜ ጋራ ላይ ያሉት ደግሞ የመላዕክት ምሳሌዎች መሆናቸውን ያሳያል፡፡ የኢየሱስን መወለድ መጀመሪያ ያወቁ እረኞች በመሆናቸው በአገር ቤት በተለይ እረኞች በጣም ያከብሩታል፡፡

በቤዛ ኩሉ ዝማሬ ትርዒት ላይ የሚሳተፉት ካህናት የሚለብሷቸው አልባሳትና የሚይዟቸው ንዋያተ ቅድሳት ከወትሮው ለየት ያሉ ናቸው፡፡

መምህር ዓለሙ ኃይሌ ስለዚሁ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፡፡ ..የወርቅ፣ የብር፣ የሐር፣ ወዘተ. ንዋያተ ቅድሳት የያዙና ልብስ ተክህኖ የለበሱ ካህናት ከማሜ ጋራው ላይ ተሰልፈው ይቆማሉ፡፡ በውስጥ ጥንግ ድርብ የታጠቁ፣ ከላይ ካባ የደረቡ አለቃ ወዳሾች፣ ርዕሰ ደብሮች፣ ቀኝና ግራ ጌቶች፣ ከውስጥ የሐር ቀሚስ ያጠለቁ፣ ከላይ ቀይ ጃኖ /ሸማ/ ያሸረጡ ልጅ እግር ደብተሮች መደዳውን ይደረደራሉ፡፡ በግራ እጅ የብር መቋሚያ በተጌጠ መሐረብ ተይዞ ትከሻ ላይ ያርፋል፡፡ በቀኝ እጅ የብር ጸናጽል ይያዝና በሰልፍ ይቆማል፡፡ ሌሎች መዘምራንና ደባትራን ደግሞ በዚሁ ዓይነት ከታች ከማሜ ጋራው ሥር ክብ ሰርተው ይቆማሉ፡፡ ከዚያ እየተቀባበሉ ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ /ዛሬ የዓለም መድኅን ተወለደ/ እያሉ ያዜማሉ፡፡ ይህ የማይለወጥ ሁሌም ያለ ሥርዓት ነው፡፡ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የገናን በዓል በላሊበላ ለማክበር የሚጓዙት ምዕመናንና ከዓለም ዙሪያ የሚመጡት ዑደተኞች /ቱሪስቶች/ ብዛት ከፍ ያለ ነው፡፡

በላሊበላ በገና ዕለት ከሚሰሙት የታቦት ዘፈኖች የሙገሳ ቃል ግጥሞች ይገኙበታል፡፡

ማር ይዘንባል ማር
ከእመቤቴ በር
ማር ይዘንባል ማር
አልጋ ባልጋ ነው መንገዱ
ቅዱስ ላሊበላ ወዳንተ ሲሄዱ
ቀና ነው አሉ መንገዱ
ታየኝ ክብርሽ
እመቤቴ ያሉሽ
ከቶ እንዴት አድርጎ አነፀው? እያሉ ነጋሪት /ከበሮ/ እየመቱ ምስጋና በዜማ በልደት ቀን እያቀረቡ እያጨበጨቡ እልል እያሉ ይጨፍራሉ፡፡

ሁሌ እንደሚዘመረው ምእመኑ ኪነ ሕንፃውን እያወደሱ የሚዘምሩት ቃል ግጥም አላቸው፡፡

..ቅዱስ ላሊበላ የላስታው ደብር
ውስጡ አረንጓዴ ነው ባሕር
ቅዱስ ላሊበላ የመጥረቢያው እንኳ እጀታ የለው
ከቶ እንዴት አድርጎ ሠራው?

የልደት ወር የሆነው ታኅሣሥ የመፀው /የአበባ ወቅት - ከመስከረም 26 - ታኅሣሥ 25/ የመጨረሻዋ ወር ነው፡፡ ታኅሣሥ የሚለው ስም ..ኅሠሠ.. ከሚል ግስ የወጣ ሲሆን ትርጓሜውም ከጥጋብና አዝመራ በተጨማሪ ፈለገ፣ አሠሠ፣ ከጀለ፣ ተመኘ ማለት እንደሆነ መምህር ካህሣይ ገ/እግዚአብሔር ያብራራሉ፡፡ በ6ኛው ምእት ዓመት የኖረው ታላቁ ኢትዮጵያዊ ማሕሌታይ ያሬድ ታኅሣሥን የኖላዊ፣ የስብከት የብርሃን ዘመን እንደሚለው በድጓው ተመዝግቧል፡፡

የልደት ባህላዊ መገለጫው የገና ጨዋታ ነው፡፡ ጥንግና ሩር ተይዞ አዋቂዎችና ልጆች በየፊናቸው የሚጫወቱበት ነው፡፡ በገና ጨዋታ ወቅት አልፎ አልፎ የአካል ጉዳት የሚደርስ ቢሆንም ተጫዋቾቹ በዚህ የተነሣ ቂም አይዙም፡፡ በዕለቱ ከጨዋታ ጋር በተያያዘ ለሚደረደሩ የስድብ ግጥሞች ከቻሉ አጸፋዊ ምላሽ መስጠት እንጂ እገሌ እንዲህ አለኝ ብሎ ማኩረፍና መጣላት አይኖርም፡፡ ከነብሂሉ ..በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ.. ነው የሚባለው፡፡

የገና ጨዋታ ግጥሞች በአብዛኛው ..የውረፋ.. ግጥሞች ናቸው፡፡ አንዱ በነገር
እየው መለል ብሎ
የወንዝ ዳር ጉሎ
ቂል ነው የዝም ብሎ ብሎ ሲጐንጠው የተወረፈው ወገን ደግሞ
ሳይነኩኝ አልነካም
እኮማጠጣለሁ እንደቃሪያ ኮሽም እያለ ምላሽ መስጠት ይጀምራል፡፡
አሽከርና ጌታ እኩል መብትና ድርሻ የሚኖራቸው በገና ጨዋታ ወቅት ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በኅብረ ብዕር እንደተጻፈው ከገና ጨዋታ ሌላ በልደት ሰሞን እረኞች በተለይ በግ ጠባቂዎች ከእምበስ ዛፍ ሽምልምል በትር አዘጋጅተው ይይዛሉ፡፡ በትግራይ እረኞች ሽምልምል በትር ይዘው በየቤቱ እየዞሩ ይጨፍራሉ፡፡ ይህም ከጌታ ልደት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገራል፡፡ እናቶችም ለእረኞች የተለያዩ ምግቦች ይሰጡዋቸዋል፡፡ በተለይ እርጉዝ ከሆነች ግን ሙሉ ዶሮ ወጥ ሠርታ ነው የምትሰጣቸው፤ ዐዋቂዎች ደግሞ በልደት ገንፎ አገንፍተው ይበላሉ፡፡

በሁሉም አክባሪዎች እንደየአቅሙ የሚያቀርበው የገና ማዕድ ከዘወትሩ የተለየ ነው፡፡ ዶሮ ወጥ፣ ኅብስት፣ ድፎ ዳቦ፣ ክትፎ፣ ቆጮ፣ ጠላና ጠጅ ይቀርባል፡፡ የበሬ ቅርጫ፣ የበግ/ፍየል እርድ ሁሉ ይፈጸማል፡፡

ታኅሣሥ፣ ገበሬው በግንቦትና በሰኔ ከአእላፍ የወፍ አፍ አትርፈህ አብላኝ ብሎ የዘራውን አጭዶ የሚከምርበት፣ ይልቁንም እየወቃ ወደ ጎተራ የሚያስገባበት ወር በመሆኑ የፍላጎት የምኞት ወርም እንደሚባል መምህር ካህሣይ ይገልጻሉ፡፡

የገና በዓል የሚከበርበትን ባለጸጋዋን ታኅሣሥ ከሌሎች ወራት አብልጠው ያወድሱታል፡፡ እንዲህ እያሉ፤

ነሐሴ እግር ብረቱ
መስከረም ዳገቱ
ጥቅምት አቀበቱ
ኅዳር ቁልቁለቱ
ታኅሣሥ ሆይ ቀብራሬ ጀብራሬ
ይህን ሁሉ ይዘህ ምነው እስከዛሬ ተጠቃሽ ቃል ግጥም ነው፡፡
የታኅሣሡን የገና በዓል ሁሉም አክብሮ ሲለያይ የመሰነባበቻ ዜማ ያሰማል፡፡ እንዲህ እያለ፤

..ከርሞ እንገናኝ ላመት
እናንተም ሳትሞቱ፣ እኛም ሳንሞት፣
እንዲህ እንዳለን ከእናታችን ቤት
ከመካከላችን ማንም ሳይሞት
ከርሞ እንገናኝ ላመት..
ሠናይ ልደት፡፡

በሔኖክ ያሬድ

 
< Prev   Next >