| “የድህነት ቅነሣ ኘሮግራም ቢኖርም... |
|
|
| Wednesday, 12 March 2008 | |
“የድህነት ቅነሣ ኘሮግራም ቢኖርም ታች ያለው ኀብረተሰብ እውቀት ዝቅተኛ ነው”አቶ አበጀ ተፈራ አቶ አበጀ፣ በፖቨርቲ አክሽን ኔትወርክ ኦፍ ሲቪል ሶሳይቲ ኢን ኢትዮጵያ የኘሮግራም አስተባባሪ ናቸው፡፡ በድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ዙሪያ ብርሃነ ዓለሙ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ድህነት ቅነሳ ሲባል ድህነት እስከምን ደረጃ ነው የሚቀንሰው? የት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው ድህነት ተቀነሰ የሚባለው? አቶ አበጀ፡- በጥቅሉ ስናየው መለኪያዎች አሉ፡፡ በመቶኛ ወስደን ከዚህ ዓመት እስከዚህ ዓመት ይህን ያህል ነበር፤ አሁን ደግሞ በዚህን ያህል መቶኛ ቀንሷል ብለን የምናስቀምጥበት መስፈርት አለን፡፡ ወደታች ወርደን ስናየው አንድ ሰው ማግኘት አለበት የሚባሉ መሠረታዊ ነገሮች አሉ፡፡ በእኛ አገር ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ የሚበላው፣ የሚጠጣውና የሚለብሰው እንዲያጣ አያስፈልግም፡፡ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች ሊያጣ አይገባም፡፡ እነዚህን የማዳረስ ሥራ ነው፡፡ ሁለተኛው በገቢ መካከል ያለው ክፍተት እየጠበበ የሚሄድበትን መንገድ የመፍጠር ነው፡፡ ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ ጥቂት ሃብታሞች ወደ ላይ ከፍ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ታች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ መካከል ያለውን ክፍተት የማጥበብ ሥራም አንዱ ድህነትን የምትቀንስበት ነው፡፡ የድህነት ቅነሳው ተሻሽሏል አልተሻሻለም ለሚለው መልስ የሚሆነው በድህነት ወለል በመቶኛ ከሚገኘው ምን ያህሉ ከፍ ብሏል የሚለው ነው፡፡ ካለፈው የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ጋር የአሁኑ ድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ሲነፃፀር የተፈለገውን ያህል ባይሆንም ሁለት በመቶ ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡ ድህነትን በዚህ መጠን ማሻሻል (መቀነስ) ተችሏል ማለት ነው፡፡ የምናልመው በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መጨረሻ ላይ መድረስ የሚገባን የድህነት ወለል አለ፡፡ ከዚያ ላይ መድረስ መቻላችን ነው፡፡ ገና ብዙ የሚቀረን ነገር አለ፡፡ መንግሥት ከሚለውም አንፃር ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ኘሮግራሞች አሉ፡፡ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሚቀረፁትም አንፃር ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችል እድገት ይፈጠራል ተብሎ ይገመታል፡፡ ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ በድህነት ላይ ምን ሠራ? ምንስ ውጤት አገኘ? አቶ አበጀ፡- ፖቨርቲ አክሽን ኔትወርክ ኦፍ ሲቪል ሶሳይቲ ኢን ኢትዮጵያ (ፓኒ) የሚሠራው በድህነትና በምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ላይ ነው፡፡ ከሁለቱ የድህነት ቅነሳ ኘሮግራሞች አንዱን ጨርሰን በሁለተኛው ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ፓኒ መንግሥት ባወጣው ኘሮግራም ላይ ሲቪል ማኀበረሰቡ፣ ኀብረተሰቡ የሚሰጠውን አስተያየት በማሰባሰብ ይህ ኘሮግራም የተሻለ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በሁለተኛው የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም (አሁን ባለንበት) ላይ ጉልህ ሥራዎች ለመሥራት ተሞክሯል፡፡ ከተሠሩት መካከል አንዱ ዜጎች በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ረክተዋል አልረኩም የሚለው ነው፡፡ መንግሥት የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ወዘተ. አስፋፍቻለሁ ይላል፡፡ ሲቪል ማኀበረሰቡ ይህን ይህን አደረግኩ ይላል፡፡ ኀብረተሰቡስ ምን ይላል ለሚለው ጥናት ያስፈልጋል፡፡ በጥናቱ መሠረት ኀብረተሰቡ በድህነት ቅነሳ ኘሮግራሙ ላይ ጎደለ ያለውን አስተያየት ይሰጥበታል፡፡ ይህን የጥናት መረጃ ለመንግሥት አቅርበን ተቀባይነት አግኝቶ በድህነት ቅነሳ ሁለተኛው ኘሮግራም ላይ ተካትቷል፡፡ ሌላው የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ቢኖርም ታች ያለው ኀብረተሰብ እውቀት ዝቅተኛ ነው፡፡ ይኼ ለምን አልሆነም ከሚለው ይልቅ የጎደለውን መሙላት ስላለብን ለኀብረተሰቡ፣ ለመንግሥት፣ ለመንግሥት አካላት፣ ለሲቪል ማኀበረሰቡ ከወረዳ ጀምረን እስከ ክልል ድረስ የማስተዋወቅ ሥልጠናዎችን ሰጥተናል፡፡ ካስተዋወቅን በኋላ ነው በኘሮግራሙ ላይ አስተያየት መስጠት የሚቻለው፡፡ በድህነት ቅነሳ ጉዳይ ላይ የኀብረተሰቡ እውቀት ዝቅተኛ ስለነበር እስካሁን ድረስ እያስተዋወቅን ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ድህነት የሚቀነስበትን ስልት ነው የምታስተዋውቁት? አቶ አበጀ፡- መጀመሪያ ኘሮግራሙን ማወቅ አለበት፡፡ መንግሥት የቀረፀው የአምስት ዓመት ኘሮግራም ምንድነው? ኀብረተሰቡ ገብቶታል ወይ? እንዳየነው ስለድህነት ቅነሳ ኘሮግራሙ ብዙ ሰው እውቀት የለውም፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በድህነት ቅነሳ ኘሮግራሙ ምን ተሠርቷል የሚለውንም እናያለን፡፡ መንግሥትንና ሲቪል ማኀበረሰቡን እናነጋግራለን፡፡ አሁን ያለው ኘሮግራም በትክክል ለውጥ ሊያመጣ የሚችልና ድሆች ላይ ያተኮረ ኘሮግራም ነው ወይ? የሚለውንም እንገመግማለን፡፡ አቅምን እንገነባለን፡፡ ኘሮግራሙን እናስተዋውቃለን፡፡ በሚቀርቡ አስተያየቶች መሠረት የሚሻሻሉት ተሻሽለው በሚቀጥለው ኘሮግራም ይቀጥላሉ፡፡ የምናስተዋውቀው በተለያዩ ቋንቋዎች ነው፡፡ ለኀብረተሰቡ በሚገባው መልኩ በአጭር በአጭሩ ቀለል ባለ መንገድ ይቀርብለታል፡፡ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ከድህነት ቅነሳው ጋር ምን ያህል ተጣጥመዋል የሚለውን ደግሞ በሦስት ወረዳዎች ላይ እንሞክረዋለን፡፡ የዓለም መንግሥታት የተስማሙበት የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር መሳካቱንና አለመሳካቱን ለመገምገም ሦስት ወረዳዎችን መርጠናል፡፡ ሪፖርተር፡- ወረዳዎቹን እንዴት መረጣችኋቸው? አቶ አበጀ፡- መመዘኛዎች አሉን፡፡ በዚያ መሠረት መርጠን ሦስቱ ወረዳዎች ከምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች አንፃር የት ናቸው? ምን ይጎድላቸዋል እንላለን፡፡ በወረዳው ያሉ ሴክቶሪያል የመንግሥት ቢሮ ኃላፊዎችን አምጥተን ነው አንድ ላይ የምንሠራው፡፡ ከእነርሱ ጋር ሆነን ኘላን እናወጣለን፣ ሪፖርት እናዘጋጃለን፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ድህነት ጥልቅ ነው፡፡ ስለሆነም የድህነት ቅነሳ ኘሮግራሙን ለማስተዋወቅ በተወሰኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይዘለቃል? አቶ አበጀ፡- ፖቨርቲ አክሽን ኔትወርክ የምንለው 8ዐ ድርጅቶችን ያቀፈ ነው፡፡ በየክፍሎቹ ቻኘተሮች የምንላቸው አሉ፡፡ ቅርንጫፎች እንደማለት ነው፡፡ ነገር ግን ነፃ የሆኑ ናቸው፡፡ ከሶማሌ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች አሉ፡፡ አባሎቻችን በእነዚህ የተደራጁ ናቸው፡፡ አባሎቻችን ወደ ወረዳዎችና ወደ ተለያዩ ክፍሎች እንዲያስተላልፉልን፣ በድህነት ቅነሳው ጉዳይ ላይ የሚሰሩበት አደረጃጀት አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ በምርምር፣ አንዳንዶቹ በቅስቀሳ፣ አንዳንዶቹ በቁጥጥርና ግምገማ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በበጀት ጉዳይ ላይ ይሠራሉ፡፡ ለድህነት ቅነሳ የተመደበው በጀት ድህነትን ለመቀነስ በሚያስችል መንገድ የተበጀተ ነው ወይ የሚለውን ለማየት ነው፡፡ ለወደፊቱ ግን ዘጠኙ ክልሎች ላይ ብቻ ሣይሆን ወረዳዎችም ላይ ይኖረናል፡፡ ምክንያቱም የአሁኑ የመንግሥት የድህነት ቅነሳ አደረጃጀት ወረዳ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ እኛም በወረዳ ደረጃ ሲኖረን ነው ጥሩ ሥራ ልንሠራ የምንችለው፡፡ ሪፖርተር፡- እስካሁን የድህነት ቅነሳ ኘሮግራምን በማስተዋወቅ ሥራ ላይ ነው ያላችሁት ማለት ነው? አቶ አበጀ፡- ከማስተዋወቅ አልፈን ጎን ለጎን የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ ከኘሮግራሙ ጋር የሚሄድ ጥናት እናካሂዳለን፡፡ ኀብረተሰቡ ምን ይላል የሚለውን እናጠናለን፡፡ ከዚህ የሚገኙ ውጤቶችን ተመልክተን ኘሮግራሙ በዚህ መልኩ ይሂድ እንላለን፡፡ ለኘሮግራሙ የሚሆኑ አስፈላጊ ማሻሻያዎችን እናቀርባለን፡፡ አንዳንዴ የቁጥጥርና የግምገማ ብቻ ሳይሆን የማስተዋወቅና አቅም የመገንባት ሥራንም አብሮ መሥራት ስላለብን ነው የምንሠራው፡፡ ሪፖርተር፡- የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ለማሳካት በጊዜ ተቀንብቧል፡፡ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይሳካል? አቶ አበጀ፡- የመጀመሪያ የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ጨርሰን ሁለተኛው ላይ ነው ያለነው፡፡ በሁለተኛውም ስድስት ወር ያህል ሰርተናል፡፡ የሚቀጥለው ሦስተኛው የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ከምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ጋር በ2015 ነው የሚያልቀው፡፡ በትክክል የድህነት ቅነሳ ኘሮግራማችን፣ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ግቡን መትቷል ወይስ አልመታም የምንለው የወደፊቱ የአምስት ዓመት ኘሮግራም ሲጠናቀቅ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ያሉት ግን እየተነበይናቸው ነው፡፡ በትምህርት በኩል ያሉ ጥረቶች፣ በመንገድ ጉዳይ ላይ ያሉ ሥራዎች ከምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ጋር የሚሄዱ ናቸው የሚል ሃሳብ አለ፡፡ ነገር ግን እነዚህም አንዳንዶቹ ጉድለት የለባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የትምህርት የጥራት ደረጃ መሻሻል እንዳለበት የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ፡፡ የትምህርት ማስፋፋት ሲኖር የጥራት ደረጃውም ከፍ የሚልበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ እነዚህ በጥሩ ሁኔታ የሄድንባቸው ሲሆኑ ሌሎችም የበለጠ ሊመዘኑ የሚችሉበትና ሊያልፉ የሚችሉበት ሦስተኛው የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ከምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ጋር በ2015 ሲነፃፀር ነው፡፡ አሁን ግን የት ላይ ነን ለሚለው መንግሥት ያስቀመጣቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከመንግሥት ጋር ሆነን ያወጣነው ነው፡፡ ያለንበትን ደረጃ ያሳያል፡፡ ወደ ኋላ የቀረንበትንም ጭምር፡፡ ወደ ኋላ የቀረንባቸውም ነገሮች አሉ፡፡ እንደ አገር ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ነው፡፡ ነጥለን ሦስት ወረዳዎችን ወስደን የት ነው ያሉት ብለን ገጠሮችን ለማየት የሞከርንበት ጥናት አለን፡፡ የጥናት ውጤታችንን በሚቀጥለው ወር እናወጣዋለን ብለን እናስባለን፡፡ ሌሎችም ወረዳዎች በዚህ ደረጃ እንዴት ሊሄዱ ይችላሉ የሚለውን የሚያመላክተን ነው፡፡ አሁን ያለንበት ይሄ ነው፡፡ ወደፊት መራመድ እንድንችል ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ያሳዩናል፡፡ እነዚያን ወረዳዎች እንደ ኘሮጀክት አናያቸውም፡፡ እንደ ምሳሌ ሆነውን ለወደፊቱ በአገሪቱ ደረጃ ከመንግሥት ጋር ተመካክረን ምን መሥራት አለብን የሚለውን ሃሳብ ለማቅረብ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ሦስቱ ወረዳዎች ለማሳያ በቂ ናቸው? የምትጠብቁትን ነገር እያገኛችሁ ነው? አቶ አበጀ፡- በትልቅ አገር ውስጥ ሦስቱ ወረዳዎች በቂ አይደሉም፡፡ መንግሥት ለብቻው፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለብቻቸው ኘላን ያደርጋሉ፡፡ ሃሳባችን በአንድ ወረዳ ውስጥ ያለ ሐብት (ሪሶርስ) መንግሥትም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ለልማት የሚሠራበትን መንገድ የማሰብ ጭምርም ነው፡፡ በተናጠል እያንዳንዱ ከሚሠራው ይልቅ በጋራ በመሥራት የዚያን ወረዳ ልማት ማፋጠን ይቻላል፡፡ በዚያ ወረዳ ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በዚያ ወረዳ ያሉ የመንግሥት አካላት አንድ ላይ ሆነን ነው እየሠራን ያለነው፡፡ የድህነቱ ጉዳይ በዚህ ወረዳ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ወደፊት በጋራ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ይነግረናል፡፡ ሪፖርተር፡- የምዕተ ዓመቱን የልማት ዓላማዎች በማሳካቱ ረገድ ገንዘብ፣ የአየር ፀባይ፣ መልካም አስተዳደር ወዘተ. ተፅዕኖ አያደርጉም? አቶ አበጀ፡- መንግሥት ባወጣው የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ላይ አስጊ የሆኑ ነገሮች ተጠቁመዋል፡፡ አንደኛው የፋይናንስ ችግር ነው፡፡ ይህን ኘሮግራም ማሳካት የሚቻለው በመንግሥትና በኀብረተሰቡ በኩል ያለው፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በኩል ያለው አቅምና ከውጭ ደግሞ ሊገኝ የሚችለው ተገምቶ ነው፡፡ ከውጭ ሊገኝ የሚችለው ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ ይህ አንዱ ችግር ሲሆን ሌሎች ችግሮችም አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ሲኖሩ እንዴት ልንቀርፋቸው እንችላለን የሚል ሃሳብም እዚያው ውስጥ አለ፡፡ ሊቀረፉ የሚችሉበት ስልት፡፡ ችግሮች አይመጡም ተብሎ አይደለም የተዘጋጀው፡፡ ችግሮች ቢያጋጥሙ ምን መፍትሄ ይኖራቸዋል የሚልም አለ፡፡ ሪፖርተር፡- የድህነት ቅነሳ ኘሮግራሙን እንዴት ማስኬድ ይቻላል? ሲቀረፅ በደቡብ ያለው የድህነት መንስዔ ከሰሜኑ፣ የሰሜኑ ከምዕራቡ ጋር አንድ ዓይነት ነው ተብሎ ታሳቢ ተደርጎ ነው ወይስ ሌላ መንገድ አለው? ኘሮግራሙን እንዴት ማጣጣም ይቻላል? አቶ አበጀ፡- ኘሮግራሙ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣ ነው፡፡ ይህን ኘሮግራም ወስዶ የኦሮሚያ ክልል ከኦሮሚያ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ የአምስት ዓመት ኘሮግራም ይቀርፃል፡፡ የአገር አቀፍ ኘሮግራም እንዲወጣ ኦሮሚያም የአምስት ዓመት የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ያወጣል፡፡ ሌሎችም ክልሎች እንደዚሁ ናቸው፡፡ ግን ደረጃቸው ይለያያል፡፡ አዲስ አበባ የአምስት ዓመት የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም አልቀረፀችም፡፡ ሌሎች ክልሎች ከክልላቸው ሁኔታ ጋር አጣጥመው ቀርፀው ተግባር ላይ እያዋሉ ነው፡፡ ሁሉም ቦታ ላይ ሄደን አይተናቸዋል፡፡ አፋር ክልል ብትሄድ ከአርብቶ አደሩ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ነው ኘሮግራሙ የተቀረፀው፡፡ ከአርብቶ አደሩ ጋር አያይዞ በአምስት ዓመት ምን መደረግ እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ እኛ ምን እንደጎደላቸው አይተን ሃሳብ እንሰጣለን፡፡ አቅም እንገነባለን፡፡ ለመንግሥት ያቀረቡትን ኘሮግራም እንዲፈፅሙት ብቃታቸውን እናሳድጋለን፡፡ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ችግሩ ግን ያላቸው አቅም ዝቅተኛ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ የድህነት ቅነሳ ኘሮግራምን ለምን አልቀረፀችም? አቶ አበጀ፡- አዲስ አበባ በባለአደራ አስተዳደር የምትደዳደር ነች፡፡ ስትራቴጂክ ኘላን በቅርቡ ተቀርጿል፡፡ ይህ ስትራቴጂ ኘላን ከድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ጋር ምን ያህል ይጣጣማል በሚል ለውይይት አቅርበውት ነበር፡፡ ባቀረቡበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተናል፡፡ ከድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ጋር የተዋሃደ እስካሁን አልቀረፁም፡፡ ለተወሰነ ዕድሜ ስለሚቆዩ ከዚያ ጋር ላለማያያዝ ይመስለኛል፡፡ ለሚቀጥለው የማስረከብ ስትራቴጂክ ኘላን በሚል አስቀምጠውታል፡፡ ሪፖርተር፡- በይበልጥ የምታተኩሩት ከተማ ላይ ነው ወይስ ገጠር? አቶ አበጀ፡- ከተማ ላይ የምንሰራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ቅርንጫፎች አሉን፡፡ ባሉን አባላት አማካይነት እስከ ወረዳና ገጠር ወርደን እናያለን፡፡ እስከቀበሌ ድረስ ወርደን እናጠናለን፡፡ ለአገር አቀፉ የድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ሊጠቅሙ የሚችሉ ሃሳቦችን ነው በብዛት የምናወጣው፡፡ ታች ወርደው በድህነት ቅነሳ ኘሮግራም ላይ የሚሠሩ የእኛ አባል ድርጅቶች ብዙ አሉ፡፡ ሪፖርተር፡- የድህነቱ ጥልቀት ላይስ ታተኩራላችሁ? ከክልል ክልል፣ ከወረዳ ወረዳ ወዘተ. እያላችሁ ደረጃ ለማውጣትስ ሞክራችሁ ታውቃላችሁ? አቶ አበጀ፡- እኛ ብዙውን ጊዜ የምንወስደው የውጭ መለኪያዎችን ነው፡፡ በአገራችን ደረጃ ድሃ ምንድነው? ሐብታም ምንድነው? የሚለው እያንዳንዱ ክልል የራሱ የሆነ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ ቀደም ሲል ድሃ የሚባለው ይህን ያህል ያለው ነው ተብሎ የተገመተው አሁን ያ ላይሆን ይችላል፡፡ እነዚህን ከአገራችን ሁኔታ አንፃር ለመተርጎም ሃሳቡ አለን፡፡ የኢኮኖሚው ሁኔታ እያደገ ነው፣ በመካከሉ ያለው ክፍተት እየሰፋ ነው ስለሚባል እነዚህን ለማጥናት ሃሳቡ አለን፡፡ በእያንዳንዱ ገጠር ሄደን ለድህነት ምላሾችን መስጠት ሳይሆን አባሎቻችን መሥራት ያለባቸውን፣ መንግሥት ሊያተኩርበት የሚገባውን እናመለክታለን፡፡ ብሔራዊ ኔት ወርክ ነን፡፡ ሪፖርተር፡- ከአገሪቱ ማኀበራዊ፤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ጋር በማያያዝ በድህነት ቅነሳው ኘሮግራም ላይ ተስፋ የሚቆርጡ ሰዎች አሉ፡፡ የኀብረተሰቡ ንቃተ ኀሊና ከፍ ያለማለት፤ የመልካም አስተዳደር አለመኖር፤ ከክልል ክልል ተዘዋውሮ በነፃነት ካለመሥራት ጋርም ያያይዙታል፤ አቶ አበጀ፡- ዋናው ቁም ነገሩ በድህነት ቅነሳ ኘሮግራሙ ላይ ሁሉም እንዲሳተፍበትና ሁሉም የእኔ ነው እንዲል ማድረግ ነው፡፡ ይህ ኘሮግራም እኔ ሃሳብ ሰጥቼበታለሁ፤ የእኔ ድምፅ አለበት ብሎ ሊያስብ የሚችልበት ደረጃ ከፈጠርን ድህነትን የማንቀርፍበት ምክንያት የለም፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ የፖሊሲ ሃሳቦች መሻሻል አለባችው፡፡ ድህነት አንድ ሴክተር ላይ ያለ ነገር አይደለም፡፡ ድህነት ከሰብዓዊ መብት ጋር፣ ከውሃ ጋር፣ ከትምህርት ቤት፣ ከሴቶች እኩልነት ወዘተ. ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ድህነት የአንድ አካል ወይም የአንድ ወገን ኃላፊነት አይደለም፡፡ የሁላችንም ነው፡፡ ኀብረተሰቡ የራሱ ኘሮግራም አድርጎ ከወሰደው ይተገብረዋል፡፡ እያንዳንዱ ክልልም በጋራ የሚመክርበት ይሆንና በአገር አቀፍ ደረጃ የጋራ ይሆናል፡፡ ኀብረተሰቡ ካመነበት ተግባራዊ ለማድረግ ይቀላል፡፡ ድህነት ሊወገድ የሚችለው ይህንን በመፍጠር ነው፡፡ ይህንን ለመፍጠር የሁሉንም ተሳትፎ ከፍ ማድረግ፣ በዚህ ዙሪያ ያሉ ፖሊሲዎችን ማሻሻል ወዘተ. ያስፈልጋል፡፡ ፖሊሲ የሚሸረሽሩ የውጭ ተፅእኖዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ከአገራችን ሁኔታ ጋር አጣጥመን ማስኬድ አለብን፡፡ ደረጃ በደረጃ እየተሻሻለ ይመጣል ብለን ነው የምንሰራው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |