Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow በሕግ ከነገዱ ቀና ነው መንገዱ!
በሕግ ከነገዱ ቀና ነው መንገዱ! Print E-mail
Sunday, 16 March 2008
Image
ማጭበርበር ከወደዱ ጥልቅ ነው ጉድጓዱ!

በርዕሱ ላይ የተቀመጡት ሁለት ነጥቦች ተግባራዊ ሆነው የሚታዩ ናቸው? እውነት ሕግን ተከትሎ፣ ሃቀኛ ሆኖ፣ አገርንና ሕዝብን ወድዶና አክብሮ የሚነግድ ሰው መንገዱ ቀና ይሆንለታል? እውነት አጭበርብሮ ሰርቆና አታሎ የሚነግድ ነጋዴ እየተያዘ ችግር ውስጥ የሚገባ፣ ሥራውም ገደላማና ጥልቅ ጉድጓድ የሞላበት ነው?

ሰሞኑን እየታየ ባለው መንገድ መንግሥት ጥብቅ መሆን ከቀጠለ እውነትም በሕግ ከነገዱ ቀና ነው መንገዱ ያሰኝ ይሆናል፡፡ ማጭበርበር ሲወዱ ጥልቅ ነው ጉድጓዱ የሚባልበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም፡፡

በሕግ ለመስራት የሚንቀሳቀስ፣ የሚነግድ እየተጎዳና እየተገፋ የሚሄድበት፣ አጭበርብሮና አታሎ ሰርቆ የሚሄደው ነጋዴ ግን ሲካስ፣ ሲጠቀም፣ ሲያተርፍና አይዞህ ሲባል የታየበት ሁኔታ ነው የተስተዋለው፡፡

ሰሞኑን እየታየ ያለው የወርቅ ማጭበርበርና የሃሰት ብር የማሳተም ወንጀል የሚያረጋግጠው ተሰርቶና ተለፍቶ የተገኘ ሃብት አለመሆኑን ነው፡፡ ንጹህ ነጋዴ የለም ማለት ነው? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ ባለሥልጣናት በዚህ ተግባር ተባባሪ አልሆኑም? የሚል አጀንዳም እየተከፈተ ነው፡፡ የሚሰማን አጥተን ነው እንጂ ብለን ነበር የሚሉም ብዙ ናቸው፡፡

ሃቀኛው የሚጨነቅበት፣ አጭበርባሪው የሚፈነጥዝበት መድረክ ለመኖሩ ጥናትና ምርምር አያስፈልገውም፡፡ ገሃድ የወጣና ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነውና፡፡ አንዱ እቁብ ገብቶ፣ አራጣ ተበድሮ፣ የቤተሰቡና የጓደኛው ንብረት አስይዞ፣ ተፍጨርጭሮ ቢዝነሱን ለማሳካት መከራውን ያያል፡፡ ሌላው ትንሽዬ ኪዮስክ ከፍቶ በጥቁር ገበያ ዶላርና ዩሮ እየመነዘረ ሕጋዊ ፍቃድ ሳይዝና ግብር ሳይከፍል ሚሊየነር ሆኖ ፎቅ ሲሰራ ይታያል፡፡

አንዱ በሪል ስቴት ሥራ ውስጥ ገብቶ ቤት ለመግዛት ከወሰኑት ቅድሚያ ክፍያ ተቀብሎ ለራሱ ምንም ሳይዝ በቅድሚያ ክፍያ ሃያ ሰላሳ ሚሊዮን ብር ግብር ለመንግሥት በሃቀኝነት አስረክቦ ሥራ ይጀምራል፡፡ በመሃልም ዓያሌ መንገላታት ያጋጥመዋል፡፡ ትቼው ልውጣ ወይ ብሎ እስከማወላወል ይደርሳል፡፡ ሌላኛው ብልጣ ብልጥ ደግሞ ለሪል ስቴት ብሎ በወሰደው ቦታ ላይ ከአሥር ካሬ ሜትር ያልበለጠ ..ሰርቪስ.. ሰርቶ መሬቱን ይሸጠዋል፡፡ ቤት ሳይሆን መሬት ሽያጭ ውስጥ ይገባል፡፡ ሚሊየነር ይሆናል፡፡ ሃቀኛው ይጎዳል አጭበርባሪው ይጠቀማል፡፡

አንዱ ያመጣው ባሌስትራ ወርቅ ነው ተብሎ ይታመንለታል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት እምነት አይባል “ተባባሪነት”፣ አገር ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ይከስራል፣ መሳቂያ መሣለቂያም ይሆናል፡፡ አንዱ ደግሞ ያመረተውን ምርት ብቻ ሳይሆን ምርቱን ለማምረት የተሰማራው ሠራተኛ ታስሮ የማያውቅ፣ እብድ አለመሆኑን ማስረጃ አምጣ ተብሎ ይወጠራል፡፡

አንዱ መከራውን አይቶ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ያቋቁማል፡፡ ሌላው በኮንትሮባንድ ልብስ ያመጣል፡፡ አምራች ተብሎ ፋብሪካ አቋቁሞ ገዥ ያጣል፡፡ ዋጋው ውድ ነው ተብሎ ይቀራል፡፡ በኮንትሮባንድ የሚያመጣው ቀረጥ ስለማይከፍል በርካሽ ይሸጣል፡፡ ግብር ከፋይ ይጎዳል፤ ኮንትሮባንዲስቱ ይጠቀማል፡፡

አንዱ በስንት መከራ የመድሃኒት ፋብሪካ ያቋቁማል፡፡ ሌላው መድሃኒቱን በኮንትሮባንድ ያመጣዋል፡፡ በርካሽ የሚሸጠው ኮንትሮባንዲስቱ ነው፡፡ ቀኑ ያለፈበት፣ በረሃ ዱርና ገደል አቋርጦ የመጣ የተበላሸ መድሃኒት ይሸጣል፡፡ አጭበርባሪው ይጠቀማል፣ ሃቀኛው ይጎዳል፡፡

ብዙ ምሣሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ገሃድ የሆነ ሃቅ ስለሆነ ይህ ይብቃንና እንደዚህ ሆኖ መቀጠል አለበት ወይ? የሚለውን ጥያቄ እናንሳ፡፡

አጭበርባሪን የሚክስና ሃቀኛን የሚጎዳ አሰራር በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ መንግሥት ሰሞኑን በጨው ነጋዴዎች፣ በወርቅ አጭበርባሪዎችና በሕገወጥ ዶላር መንዛሪዎች ላይ የወሰዳቸው እርምጃዎች ዓይነት በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አለባቸው፡፡

አጭበርባሪና ሕገወጥ ነጋዴዎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለአደጋና ለውርደት የሚዳርጉ መሆናቸውን በሚወሰደው ሕጋዊ እርምጃ በግልፅ ሊነገራቸው ይገባል፡፡ መቀመቅ የሚወርዱበት ጥልቅ ጉድጓድ እንደሚጠብቃቸው ሊታያቸውና ሊነገራቸው ይገባል፡፡

በሃቅ የሚሰራው ወገን ደግሞ ሊበረታታና የመንግሥትን ድጋፍ ሊያገኝ ይገባል፡፡ በሃቅ የሰራ ይጠቀማል፣ አጭበርባሪ ይጎዳል የሚል ግልፅ መልዕክት በማያሻማ መንገድ መተግበር አለበት፡፡ የመንግሥት እርምጃም ጊዜያዊና እያደር የሚጠፋ እንቅስቃሴ መሆን የለበትም፡፡ ምንጊዜም በአጭበርባሪዎች ላይ ምህረት እንደሌለው ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ ይኖርበታል፡፡ ምንጊዜም ከሃቀኞች ጋር እንደሚቆም በተግባር ማረጋገጥ አለበት፡፡

ሃቀኛን የማበረታታትና አጭበርባሪን የመቅጣት እርምጃ ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከሕዝብም ሊመጣ ይገባል፡፡ ሕዝብ ከአጭበርባሪ ጋር አልሰራም ብሎ መነሳት አለበት፡፡ የሸማቾች ማኅበርን እያቋቋመ ሊታገል ይገባል ብቻ ሳይሆን አጭበርባሪዎችን ማጋለጥና መጠቆም አለበት፡፡ መንግሥትም ወንጀለኛን ለሚጠቁሙ የማበረታቻ ከፍያ ሊከፍል ይገባል፡፡ ይህ ማበረታቻ ወንጀለኞችና አጭበርባሪዎች በሕዝብ እንዲታደኑ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ሕዝቡም፣ መንግሥትም፣ ሃቀኛ ነጋዴዎችም በጋራ ቃል ይግቡ፡፡ በሕግ ከነገዱ ቀና ነው መንገዱ የሚል መልዕክትና አሠራር በግልጽ ይስፈን፡፡ ማጭበርበርን ከወደዱ ጥልቅ ነው ጉድጓዱ የሚል ተግባራዊ መፈክርም ይስተጋባ፡፡ ያኔ ነው “አገር እንዴት ነው?” ስንባል በልበ ሙሉነት “ሰላም ነው” የምንለው፡፡
 
< Prev   Next >