| ጥቃቅን ችግር ፈላጊ ትልቁን አይመለከትም |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
|
ከሰሞኑ የተሰማው የወርቅ ማጭበርበር ዜና ለእያንዳንዱ ዜጋ ህመም ይፈጥራል፡፡ ህዝቡ በኑሮ ውድነት ችግር ውስጥ ባለበት ጊዜ እንዲህ አይነት በአገር ሀብት ላይ የሚቀልዱ እንደ ዜጋ ሳይሆን እንደ ባዕድ የሚያስቡ አጭበርባሪዎች ባቋራጭ ለመክበር ሲጣደፉ ማየት ያሳዝናል፡፡
ብሔራዊ ባንክም የሌሎችን ጥቃቅን ችግር ለመልቀም የሚያባክነውን ጊዜ እና ገንዘብ ጠርቀም አድርጎ በራሱ ላይ የወደቀበትን ችግር እንዳይደገም ቢሰራ መልካም ነው፡፡ አገሪቷን እና ሐብቷን ከመሸጥ ወደ ኋላ በማይሉ ራስ ወዳጆች አደጋ ላይ እንዳንወድቅ አሰራሩ ይፈተሽ፡፡ (ኃይለሚካኤል ታረቀኝ፣ ከአዲስ አበባ) ሁሉም ነገር በድርድርና በንግግር ይሰራ አገራችን ካሉባት ችግሮች አንዱና ዋነኛው የፍትህ ስርዓት ችግር ነው፡፡ ይህን ችግር ለመቀነስ ታስቦ በፌዴራል ደረጃ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡትን የሕግ የዲግሪና የዲፕሎማ ባለሙያዎች መደበኛ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የሁለት ዓመት ተጨማሪ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ አካሄድ ውጤታማ እንዲሆን ግን በአተገባበሩ ላይ ጥንቃቄ የሚያሻው ይመስለኛል፡፡ በመጀመሪያ መነሳት ያለበት ነጥብ ክልሎች የየራሳቸውን የተለያየ አሰራር ከተከተሉ በፌዴራል መንግሥት የሚኖራቸውን ውክልና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ይሆናል፡፡ በዚህ አሰራር ትልቅ ችግር እየታየበት ያለው የትግራይ ክልል የፍትሕ አካላት አሰለጣጠን ወደር የሌለው መሆኑ ነው፡፡ በትግራይ ከሌሎች ክልሎች ለየት ባለ መልኩ የሁለት ዓመቱን ስልጠና የምትወስዱት ሳትቀጠሩ ለምግብ ብቻ ብር እየተሰጣችሁ ነው፤ አለበለዚያ መልቀቅ ትችላላችሁ ተብለናል፡፡ የሌሎች ክልሎች ግን ተቀጥረው ወደ ስልጠናው እየገቡ ነው፡፡ የትግራይ ሰልጣኞች ጥያቄ ደግሞ ሁለት ዓመት ያለ ሥራ ልምድ በመቆየታችን በቀጣይ ክልላችንን ወክለን በፌዴራል መንግሥት የመስራት እድላችን ጠባብ ይሆናል፡፡ በተቋሙ እኛን ለማስተዳደር የተወከሉትም ከካድሬነት አልፈው የሚገባቸውን ሥራ ለመስራት ባለመቻላቸው ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ለመገናኘት አልቻልንም፡፡ (የተቋሙ ሠልጣኞች) ትኩረት ለትምህርቱ ጥራት እኔ በምማርበት ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ አብዛኞቹ የኢህአዴግ አባል መምህራን በስብሰባ ሰበብ የትምህርት ክፍለ ጊዜያቸውን በአግባቡ ስለማይጠቀሙ እና ተማሪዎቻቸውንም ስለማይቆጣጠሩ በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ የግሬድ አሰጣጣቸውም አብዛኛው ኤ እና ቢ ስለሆነ ተማሪው ሰራም አልሰራም ጥሩ ውጤት ማግኘቱ ስለማይቀር ለእነዚህ መምህራን ትምህርት ብዙም ትኩረት አይሰጥም፡፡ ስለሆነም እንደ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት መንግሥት የኢህአዴግ አባል የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ለትምህርት ጥራት ትኩረት እንዲሰጡ ያድርግ፡፡ (ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ) ትግል እስከ መቼ? ባለፈው ረቡዕ ሪፖርተር ጋዜጣ ፖለቲካ ገጽ ላይ በአዲስ አበባ ነዋሪ በሆኑ የትግራይ ተወላጆችና በክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል የተደረገው ውይይት አስመልክቶ የወጣውን ጽሁፍ አንብቤዋለሁ፡፡ ነዋሪዎቹ ያነሱዋቸው ጥያቄዎች መሰረታዊ ናቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የውሃ አቅርቦትናመንገድ የመሳሰሉ ችግሮች መፈታት አለባቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች በተገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ለበርካታ ጊዜያት ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ የክልሉ ባለሥልጣናት ግን ሁልጊዜ ተስፋ በመስጠትና ሰበቦችን በመደርደር ተገቢ እርምጃ ሳይወስዱ እስከዛሬ ቆይተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው ውይይትም የክልሉ ፕሬዚዳንት ጥያቄዎችን በማድበስበስ፣ በማስተባበል አልፈዋቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን “ብቃት ያላቸው አካላት ወደ አመራር አልመጡም” የሚለው የሕዝብ ቅሬታ አመራሮቹን የሚመለከት በመሆኑ የብዙዎች ቀልብ ሳይስብ አልቀረም፡፡ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “ብቃት የሌለው ሰው ስልጣን ላይ ካለ ታግላችሁ ማውረድ ትችላላችሁ” ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወደ ራሳቸውና በዙሪያቸው ወዳሉት ሰዎች ቢመለከቱ መልካም ነው፡፡ ሕዝቡማ እስከ መቼ ይታገል? (ከስብሰባው ተሳታፊዎች) ኃይሌ ዘግይቷል ኃይሌ ገብረስላሴ በአየር ብክለት ምክንያት በቤጂንግ ኦሊምፒክ በማራቶን ውድድር ላይ እንደማይሳተፍ ገል..ል፡፡ የአለማችን የበለፀጉ ሀገሮች በአየር ኡደት ላይ የሚያስከትሉትን ተፅዕኖ መቃወም ያስፈልጋል፡፡ የአየር ፖሊሲያቸውን እንዲለውጡ ከማድረግ አንፃር የኃይሌ እርምጃ ይበረታታል፡፡ ነገር ግን በአለማቀፍ ደረጃ የአየር ብከለትን ለማስቆም የሚደረጉ ስምምነቶች ባለመፈረም አሜሪካና ቻይና ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአትላንታ ግዛት 66 ከመቶ የኢንዱስትሪ መንደር ሲሆን የቤጂንግ የኢንዱስትሪ ይዞታ ግን 43 ከመቶ ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ መረጃዎች አንፃር ኃይሌ በአትላንታው ኦሊምፒክ ያላነሳውን ጥያቄ በቤጂንግ ማንሳቱ ዘግይቷል ያሰኛል፡፡ በተጨማሪም አትሌቶቻችን ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት በሚያስገኙ ሆኖም በኢንዱስትሪ ብክለት የታወቁ በምዕራባዊያን ከተሞች በሚደረጉ ውድድሮች ላይ በተደጋጋሚ ተወዳድረዋል፡፡ ያኔ ይህ የአየር ብክለት ጥያቄ ለምን አልተነሳም? (አቡሽ ከበደ፣ ከሳሪስ) ሸማቹም ይረጋጋ ባለፈው ረቡዕ በወጣው ጋዜጣ በማህበራዊ ገፅ ላይ የጨው ዋጋ መጨመርን ተከትሎ የተፃፈውን ጽሁፍ አንብቤዋለሁ፡፡ የሕብረተሰቡ አለመረጋጋት ለነጋዴዎች መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረ አመላካች ነው፡፡ ነዋሪው ባለፈው አርብ የጨው ዋጋ ጨመረ ሲባል በየሱቁ ተሰልፎ 10 እና 15 ኪሎ ሲገዛ ውሏል፡ የሸማቹ መረጋጋት ገበያውን ለማረጋጋት የሚኖረው ሚና ጉልህ በመሆኑ የሚፈጠሩ የዋጋ ለውጦችን ቀስ ብሎ ማጤን ይኖርበታል፡፡ (ሩት አዳነ፣ ከሳሪስ) አሳማኝ አይደለም በቅርቡ ከተበታተኑት የቀድሞ ቅንጅት አባላት መካከል በእነ ወ/ት ብርቱካን የሚመራው ቡድን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋምና ስያሜውንም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ማለታቸውን ከሪፖርተር ጋዜጣ አነበብኩ፡፡ እነዚህ ሰዎች አንድነት፣ ቅንጅት፣ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ የሚባሉትን በተግባር ያውቋቸዋል ለማለት አልደፍርም፡፡ በራሳቸው ውስጥ የተፈጠሩ ልዩነቶችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማስተናገድና መፍታት ተስኗቸው እየተበታተኑ እያየን እንደገና ለፍትህና ለዴሞክራሲ እንታገላለን እያሉ መናገራቸው አሳማኝ አይደለም፡፡ (በየነ ፍቅሬ፣ ከፍቼ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |