Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Monday
Sep 08th
Home arrow Sections arrow “ሕዝቡ በእርግጠኝነት ይመርጠኛል”
“ሕዝቡ በእርግጠኝነት ይመርጠኛል” Print E-mail
Sunday, 16 March 2008
Imageዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ፣ የፓርላማ ዕጩ ተወዳዳሪ

በቀጣዩ ወር በሚካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ በግል ዕጩ ተወዳዳሪ በመሆን ከቀረቡት መካከል ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ አንዱ ናቸው፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ማሟያ ምርጫ ለ14 ያህል ወንበሮች በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 122 ያህል ዕጩዎች የቀረቡ ሲሆን ዶ/ር አሸብር በቀረቡበት ወረዳ 18 ለአንድ ወንበር እሳቸውን ጨምሮ ዘጠኝ ያህል ዕጩዎች ቀርበዋል፡፡ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ፍሬው አበበ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለፓርላማ ለመወዳደር እንዴት ተነሳሱ?

ዶ/ር አሸብር፡-
በተፈጥሮዬ በሕግ የበላይነት አምናለሁ፡፡ ፍትህ ፈልጌ ካላገኘሁ ዝም ብዬ የምኖር ሰው አይደለሁም፡፡ የሕግ የበላይነት የመኖር ወይም ያለመኖር ጉዳይ ከምተነፍሰው አየር፣ ከምበላው ምግብ፣ ከምጠጣው መጠጥ እኩል ወይም ከዚያ በላይ አስበልጨ ነው የማየው፡፡ ይኸንንም በራሴ ተሞክሮ አይቼዋለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ የሕግ የበላይነት እንዲከበር የመፈለግ ምኞቴን በመያዝ ወደሕግ አውጪው (ፓርላማ) ለመቀላቀል እንድነሳሳ አድርጎኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ለፓርላማ ለመወዳደር ዕጩ ሆነው መቅረብዎ ሲሰማ ለብዙዎች እንግዳ ነገር ሆኗል፤

ዶ/ር አሸብር፡-
እንግዳ ሊሆን አይገባም፡፡፡ እያንዳንዱ ሰው በውስጡ ምን እንደሚያስብ የሚያውቀው ባለቤቱ ብቻ ነው፡፡ ወዴት ማምራት፣ የቱጋ ራሱን ማግኘት እንደሚፈልግ የሚያውቀው ባለቤቱ ስለሆነ በዚህ ረገድ እንግዳ የሚሆን ነገር መኖር የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡-  ባለፉት ዓመታት በፖለቲካ ተሳትፍዎ አይታወቁም፡፡ አሁን በድንገት ነው በፖለቲካ ውስጥ ብቅ ያሉት፤

ዶ/ር አሸብር፡-
አዎን፡፡ እኔ በየትኛውም ሥርዓት፣ በየትኛው ሁኔታ በፖለቲካ ውስጥ ሰርቼ፣ ተሳትፌ አላውቅም፡፡ ከዚህ በመነሳት ይሆናል የእኔ ለፓርላማ መወዳደር ሲሰማ በብዙ ሰዎች ዘንድ አግራሞትን የፈጠረው፡፡

ሪፖርተር፡- ይኸኛው የመጀመሪያው ነው ማለት ነው?

ዶ/ር አሸብር፡- 
አዎን! ይኸ የመጀመሪያዬ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ሰዎች ዕጩ ሆነው መቅረብዎን በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ ከገጠምዎ ችግር ጋር ያያይዙታል፤

ዶ/ር አሸብር፡- 
ቢያያዙትም ስህተት ያለው አይመስለኝም፡፡ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት መኖር እንዳለበት በማመን ጠንክሬ መስራት የጀመርኩት ወደኳስ ሜዳ ከመጣሁ በኋላ ነው፡፡ ዋጋውንም ያወቅኩት ፌዴሬሽን ውስጥ ነው፡፡ በአንዳንድ መልካም አስተዳደር በሚጎድላቸው ባለሥልጣናትና የበላይ ኃላፊዎች አማካይነት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጣልቃ ገብነት፣ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ነገር ስመለከት፣ ይህንን ሕገወጥነት፣ በሕጋዊነት ለመመከት፣ ለማስተማር መድረክ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን አሳምኖኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ውስጥዎ ቁጭት አለ ማለት ነው?

ዶ/ር አሸብር፡
- ቁጭትም ባይሆን እንደ ኢትዮጵያዊ የመመረጥ ዕድሉን ባገኝ ስህተት ውስጥ ላሉ ባለሥልጣናት፣ ኃላፊዎች ድክመታቸውን ለመጠቆም፣ መልካም ጎናቸውን እንዲያጎለብቱ በጎ አስተዋፅኦ ለማድረግ እችላለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለፓርላማ ቢመረጡ ለወከለዎት ለወረዳ 18ና ለቀሪው ሕዝብ ምን ይሠራሉ?

ዶ/ር አሸብር፡-
  እኔ ፓርቲ አይደለሁም ወይም የፓርቲ መሪ አይደለሁም ወይም የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ አባልም አይደለሁምና የተስፋ ፕሮግራም ሊኖረኝ አይችልም፡፡ ነገር ግን ከአሸናፊውም ሆነ ከሌሎች ፓርላማ ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በአገሪቱ እየጠፋ ያለው የሕግ የበላይነት ለማስተካከል እንዲቻል፣ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ከኑሮ ውድነቱ ጋር በተያያዘ ዋስትና ያጣውን የሕዝብ ኑሮ ሁነኛ መፍትሔ ለማግኘት እንዲቻል እጥራለሁ፡፡ ወጣቱ ትውልድ በአብዛኛው ሥራ አጥ እየሆነ ነው፣ የሥራ ዋስትና፣ የመኖር ዋስትና፣ የማኅበራዊ ዋስትና አናሳ ነው፡፡ በነዚህ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ከሁሉም ወገኖቼ ጋር በጋራ ለመሥራት አስባለሁ፡፡ በአብዛኛው በትምህርት፣ በጤና ፖሊሲ መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች እንዲካተቱ፣ እንዲሁም የሚወክለኝን የወረዳ 18 ሕዝብ ፍላጎት በመጠየቅ የሕዝቡን አምባሳደር፣ ተወካይ በመሆን፣ የሕዝቡን ሃሳብ ወደመንግሥት፣ ወደፓርላማ ለማቅረብ፣ ድልድይ ለመሆን የሚያስችለኝን ሁኔታ እፈጥራለሁ፡፡ ሴቶች እህቶቻችን የጥቃት ሰላባ የማይሆኑበት፣ የጠነከረ ሕግ በአገር ደረጃ እንዲኖር፣ የወጣውንም የሚከበርበትን አግባብ ለመፍጠር የበኩሌን ለማድረግ ሃሳቡ አለኝ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የዘንድሮ ምርጫ ካለፈው ምርጫ 97 ጋር ሲነጻፀር በጣም የተቀዛቀዘ ይመስላል የሚሉ አሉ፤

ዶ/ር አሸብር፡
- ምርጫው አልተቀዛቀዘም ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሕዝቡ ከፖለቲካው ይልቅ በልቶ ማደር እያስቸገረው የመጣበት ሁኔታ መኖሩ በአንድ በኩል፤ ካለፈው ምርጫ ጋር በተያያዘ ፓርቲዎች በፈጠሩት ስህተት የሕዝቡ ፍላጎት ተጣጥሞ መሄድ የቻለበት ሁኔታ አለመኖሩ በሌላ በኩል ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ሕዝቡ ተጠናክሮ በምርጫው ለመሳተፍ የቻለበት ሁኔታ የታየ አልመሰለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ እንዲስተካከል በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በኩል (ለምሣሌ በምርጫ ቦርድ) ተገቢውን ጥረት ተደርጓል ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር አሸብር፡
- በምርጫ ቦርድ በኩል እኔ ባየሁትና በማውቀው መንገድ ስመዝነው ጥሩ ሁኔታ መኖሩን ነው የምረዳው፡፡ መደረግ የሚገባውን ያደርጋሉ፣ የተጠየቁትን ያሟላሉ፡፡ የዕጩዎች የምዝገባ ጊዜ ታህሳስ ሰባት ሊያልቅ ምርጫ ቦርድ የሄድኩት በአምስት ነበር፡፡ ከአንድ ሺህ በላይ ሕዝብ የድጋፍ ፊርማ ያሰባሰብኩት በግማሽ ቀን ጊዜ ነው፡፡ በዚህ አጭር ውስጥ የምርጫ ቦርድ ሰዎች ያሳዩት ትብብር ጥሩ ነበር፡፡ በተረፈ ግን እኔ ምርጫ ቦርድ ምን ሰርቷል፣ ምን አልሰራም የሚለውን አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- የምርጫ ቅስቀሳን በተመለከተ (ለምሣሌ የመገናኛ ብዙሃንን አጠቃቀም ጉዳይ) እንዴት አገኙት?

ዶ/ር አሸብር፡-
መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ላይ መቸኮል እንዳይሆንብኝ እንጂ ለግል ተወዳዳሪዎች እስካሁን የተደረገ ድጋፍ የለም፡፡ ወደፊት ታስቦ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ፓርቲዎች የቴሌቪዥን፣ የሬዲዮ የአየር ሰዓት ተመድቦላቸው ይጠቀማሉ፡፡ የግል ተወዳዳሪዎች ግን የተረሱ መሰለኝ፡፡ ከዚህ አንጻር ተገቢ የሆነ አሰራር አላየሁም፡፡ ፓርቲዎች ብቻ የሚወዳደሩ ቢሆን አሰራሩ ችግር አልነበረውም፡፡ ነገር ግን የግሎቹም ከፓርቲዎቹ ጋር ነው የምንወዳደረው፡፡ ቅስቀሳ ያደረገና ያላደረገ እኩል መወዳደራቸው ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ተረስቶም ከሆነ በፍጥነት መስተካከል ያለበት ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በወረዳ 18 እርስዎን ጨምሮ 9 ያህል ተወዳዳሪዎች ለፓርላማ ዕጩ ሆናችሁ ቀርባችኋል፡፡ ውድድሩ ጠንከር የሚል አይመስልዎትም?

ዶ/ር አሸብር፡-
በአንድ ምርጫ አሸነፍኩ ወይም ተሸነፍኩ ለማለት ጥሩ የሚሆነው ተወዳዳሪ ሲኖር ነው፡፡ የሰዎቹና የፓርቲዎቹ መኖር ጥሩ ነው፡፡ መራጩ ህብረተሰብ ማን ይመጥነኛል የሚለውን ለማየት አማራጭ ይኖረዋል፡፡ ለተመራጩም ቢሆን በሕዝብ አመኔታ ብቻ እንዲመረጥ ዕድል ይሰጠዋል፡፡

ሪፖርተር፡- መራጩን ሕዝብ ለምርጫ ቅስቀሳ እያገኙት ነው?

ዶ/ር አሸብር፡
- ከውጭ አገር ከተመለስኩ ጊዜ ጀምሮ ወደ 10 ዓመት አብሬው የኖርኩት ሕዝብ ነው፡፡ ራዕዬን፣ ዓላማዬን ለሕዝቡ ቀርቤ ለማስረዳት ሁኔታዎችን እያመቻቸሁ ነው፡፡ በቅርቡ ከመራጩ ሕዝብ ጋር ለመገናኘት እቅድ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ለፓርላማ ቢመረጡ በተለይ ከስፖርቱ አመራር ጋር በተያያዘ መለወጥ፣ መሻሻል አለበት የሚሉት ጉዳይ ይኖራል?

ዶ/ር አሸብር፡-
በስፖርቱ አካባቢ በአሁኑ ሰዓት ግራ የተጋባ ነገር ያለ ነው የሚመስለኝ፡፡ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማትና በየአገሩ ካሉ የፓርላማና የመንግሥት አካላት ጋር መግባባትን የማይፈጥሩ ሁኔታዎች እየታዩ ነው፡፡ ፓርላማ የስፖርቱ አጋዥ እንጂ የስፖርቱ መሪ አይደለም፡፡ መንግሥትም ስፖርቱን ብቻ ለማገዝ እንዲነሳሳ፣ ለስፖርቱ ዕድገት ተገቢውን በጀት በመመደብ፣ እገዛዎችን በማድረግ፣ የተፈራረምናቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ውሎችን ከማክበር አኳያ በፅናት የምንሰራበት ሁኔታ እንዲፈጠር ሃሳብ ለማቅረብ በጣም እፈልጋለሁ፡፡ ይኼ ዓይነት ችግር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙ ታዳጊ አገሮች ላይ ይታያል፡፡ በስፖርቱ ላይ መንግሥትም ፓርላማም ፍላጎት አለው፡፡ ያ ፍላጎት ግን በቀጥታ ተሿሚ በመመደብ የሚገለፅ ሳይሆን ቅስቀሳ (ካምፔይን) በማድረግ ሊገለፅ ይችላል፡፡ የፈለጉትን ሰው ቅስቀሳ በማድረግ እንዲመረጥ ማድረግ እንደ ግለሰብ፣ እንደ መንግሥት መሥራት ይቻላል፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገራትን ከፊፋ መሰል ተቋማት ጋር እያጣላ ያለው በስፖርቱ በቀጥታ እኔ አዛለሁ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥትም፣ አማተሩም፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ስፖርቱ እንዲያድግ ይፈልጋሉ፡፡ ግን በመካከላቸው ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ሕጋዊ መሰረት እንዲይዝ ጥረት ማድረግ አለብኝ ብዬ አምናለሁ፡፡   

ሪፖርተር፡- የስፖርቱን ከፍተኛ አመራር ቦታ በሹመት ሲሰጥ መኖሩ እንደ አንድ ችግር የሚያነሱ ሰዎች አሉ፡፡ አመራሩን ባለሙያዎች ቢይዙት የተሻለ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ?

ዶ/ር አሸብር፡-
ተሿሚዎች ማለትም ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንደአማተር ተሹመው ማገልገላቸው ክፋት የለውም፡፡ ግን ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡ የአትሌቲክስ ወይም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን መምራት ያለበት ሚኒስትር ስለሆነ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ተሿሚውንም፣ ባለሀብቱንም፣ ባለሙያውንም፣ ሌላውንም ያጠቃልላል፡፡ ይኼ ስብጥሩ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡  ከተሿሚውም፣ ከባለሀብቱም፣ ከባለሙያውም ወዘተ መሰባጠሩ ለዘርፉ ጥሩ ነገር ነው፣ ሁሉም ይፈለጋሉ፡፡ ያን ለማምጣት በሹመት ሳይሆን በምርጫ፣ በየፌዴሬሽኖቹ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ተወዳድሮ አሸንፎ መምጣት ግን የግድ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ምርጫው አንድ ወር ገደማ ቀርቶታል፡፡ ያለውን ሁኔታ በመገምገም “በእርግጠኝነት እመረጣለሁ” የሚሉበት ቅድመ ትንበያ ላይ ደርሰዋል?

ዶ/ር አሸብር፡-
በውድድር አሸናፊም ተሸናፊም ይኖራል፡፡ በእርግጠኝነት የምኖርበት ወረዳ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይመርጠኛል የሚል እምነት ግን አለኝ፡፡ ፓርላማ የምገባው ደመወዝ ወይም ሌላ ጥቅም ለማግኘት አይደለም፡፡ የምገባው ሕዝብን ለማገልገል ብቻ ነው፡፡ ጥሩ ዓላማ ይዤ፣ ሕዝብን ለማገልገል ጥሩ ራዕይ ይዤ በመነሳቴ እመረጣለሁ የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡
 
< Prev   Next >