| “ዲያስፖራው ከሚሰራው በላይ እየተጠቀመ ነው” |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
|
አቶ ኃይለሚካኤል ገ/አናኒያ
<“ከውጭ የመጡ ኢትዮጵያውያን በአገልግሎት ደረጃ ለአገር የሚጠቅሙ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ ሆኖም አንዳንድ በኢትዮጵያ ጥሩ የሠሩ ዲያስፖራዎች ቢኖሩም በጅምላ ሁሉም ዲያስፖራ ከሚገባውና ከሚጫወተው ሚና በላይ እየተጋነነ ይነገርለታል፣ ጥቅማጥቅሞችንም ያገኛል፡፡ በመንግሥትም፣ በሚዲያውም፣ በግል ዘርፍም ከልዩ ዓይነት ቦታ እንደመጣ ተደርጐ ከሚገባው በላይ እየተነገረለት ነው፡፡ ይህ መልኩ ቢቀየር ጥሩ ነው" ነዋሪነታቸውን በኒውዮርክ አድርገው በልማቱ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ኃይለሚካኤል ገ/አናኒያ ዲያስፖራ ብሎ በጥቅሉ ሳይሆን በተለያዩ አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን ምን ምን መሥራት ይችላሉ? አቅማቸው ምንድን ነው? በያሉበት ምን እየሰሩ ነው? ምን ትምህርት አላቸው? በሚለው ጉዳይ ጥናት መደረግ አለበት የሚል እምነት አላቸው፡፡ መንግሥት ለዲያስፖራ ብሎ የተለየ ፖሊሲ ማውጣት ያለበት አይመስለኝም የሚሉት አቶ ኃይለሚካኤል፣ ለልማት፣ ለእድገትና ለኢንቨስትመንት ተብሎ አገር ቤት ያሉትን ኢትዮጵያዊያውያን፣ የግል ኮርፖሬሽን፣ የሌላ አገር ተቋሟትን ጨምሮ ሁሉን የሚያቀርብ አመቺ የኢንቨስትመንት ድባብ መፈጠር እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ አንድ ባለሃብት ወደ አገር ቤት ሲመጣ የሚጠይቀው መሠረታዊ ጥያቄዎች የደህንነት፣ የመልካም አስተዳደርና የመሠረተ ልማት መመቻቸትን ነው፡፡ ለዲያስፖራውም ሆነ አገር ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውያን እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች መሟላት አለባቸው፡፡ በመሠረተ ልማት በመንግሥት በኩል የተጀመረው ሥራ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው፡፡ አቶ ኃይለሚካኤል እንደሚሉት መልካም አስተዳደርን በሚመለከት ችግር አለ፡፡ አንዳንድ ቢሮዎች ተሄዶ ውጤት አይገኝም፡፡ መዘግየት፣ መጓተትና መመላለስ የተለመደ ነው፡፡ ይህ ዲያስፖራውንም ሆነ አገር ውስጥ ያሉትን ተስፋ አስቆርጦ ከልማቱ የሚያስወጣ ነው፡፡ ተበሳጭቶም ወደመጣበት የተመለሰ ዲያስፖራ ሞልቷል፡፡ ዲያስፖራው አገሩን ለማልማት መጥቶ በመልካም አስተዳደር እጦት ተመልሶ መሄዱ ደግሞ ውድቀት ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለዲያስፖራ ብሎ መሬትና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ከመስጠት ይልቅ መልካም አስተዳደር ላይ ቢያተኩር የተሻለ ይሆናል ይላሉ፡፡ “ጉምሩክ አላግባብ እቃዬን ይዞብኝ የነበረው ለሰባት ወራት ያህል ነው፡፡ ይህን ያህል ጊዜ ሲቆይ ሰዎች ለምን ሰው የሚያደርገውን አታደርግም ይሉኝ ነበር፡፡ እኔ ግን አላደርግም ብዬ ሰባት ወር ታገልኳቸው፡፡ በኋላም ጋዜጣ ላይ ጉዳዩ ሲወጣ የገቢዎች ሚኒስቴር ባለስልጣናት ጉዳዩን ጋዜጣ ላይ አይተው መረመሩና እቃው ያለአግባብ ለሰባት ወር መያዙን አረጋገጡ፡፡ በሳምንት ጊዜ ውስጥም እቃዬን አውጥቻለሁ” የሚሉት አቶ ኃይለሚካኤል የኢትዮጵያ ሕዝብ መማር ያለበት ይህንን ነው፣ ሲቸግረው ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ ለሚመለከተው አካል መናገር፣ በሚድያ ማውጣት፡፡ ይህ ሲሆን ቢሮክራሲ ውስጥ ያሉ ይጠነቀቃሉ፣ ስማቸውን ይጠብቃሉ፣ ሥራቸውን ይዘው መቆየት ይፈልጋሉና በንቃት ይሰራሉ በማለት ገልፀዋል፡፡ “ገንዘብ ከመስጠት ትንሽ ተናደን፣ ተበሳጭተንና ጊዜያችንን አጥፍተን መልካም አስተዳደር ሊመጣ የሚችልበት መንገድ ላይ መታገል አለብን” በማለትም አሳስበዋል፡፡ የደህንነት ጉዳይን በተመለከተ የኤርትራ መንግሥት ከሚፈጥረው ችግር አንፃር መልካም የደህንነት ዋስትና እንዳለ ለመናገር ይቻላል፡፡ ለኢንቨስትመንትም የሚያሰጋ ችግር የለም፡፡ ገንዘብ ያላቸው ዲያስፖራዎች አገራቸው ገብተው በልማት እንዲሰማሩ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ቢቆይም የደህንነት ዋስትና የለም ብለው ይፈራሉ፡፡ በውጭው ያለው አመለካከት ኢትዮጵያ ውስጥ የደህንነት ዋስትና እንደሌለ ነው፡፡ በውጪ ተጋኖ የሚነገረው በአገር ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር ተመጣጥኖ የተነገረ አይደለም፡፡ ፍርሃትም ቢኖር ለኢንቨስትመንት የሚያሰጋ የደህንነት ችግር የለም፡፡ ይህንን ለዲያስፖራው ማስገንዘብ ይገባል፡፡ የትኞቹ ዲያስፖራዎች ለአገር ይጠቅማሉ፣ ራሳቸውን ጠቅመው ለኢትዮጵያ እድገት ምን ያበረክታሉ የሚለው መጠናት አለበት፡፡ ለሁሉም በጅምላ የሚደረገው ጥቅማጥቅም አግባብ አይደለም ይላሉ፡፡ በደርግ ጊዜ ወደ ውጭ የሄዱ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ዘርፍ ተምረው ትላልቅ ቦታ የሚሠሩ አሉ፡፡ እነዚህ አሁን ጡረታ የሚወጡበት ጊዜ ነው፡፡ በ60 ዓመት ጡረታ ወጥተው እስከ 70 ዓመት ድረስ መሥራት የሚችሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ጡረታ ስላላቸው ለአገራቸው በበጐ ፈቃኝነት መሥራት ይችላሉ፡፡ ስለሆነም መንግሥት እነዚህን ለመሳብ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ ለኢትዮጵያ ኤምባሲዎችም እነዚህን የተማሩ ዲያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሰሩ ለማስቻል ትዕዛዝ ቢሰጣቸው ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ ያላቸውን ሰዎች አምጥቶ በአገሪቱ በትላልቅ የትምህርት ተቋማትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ፣ ለተወሰኑ ጊዜያት አገልግሎት እንዲሰጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡ “በተባበሩት መንግሥታትና በተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች ይሠሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ይመጣሉ፡፡ የመጡም አሉ፡፡ በሰላም ማስከበርም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መሥራትና በየዩኒቨርሲቲው ማስተማር ይችላሉ፡፡ እነዚህን መንግሥት መፈለግ አለበት፡፡ ጥረት ማድረግ ያለበትም ይህንን የተማረና ትልቅ አቅም ያለው ዲያስፖራ አቀናጅቶ እንዲሠራ ማደረጉ ላይ ነው” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደሃ እንዳለ ሁሉ ከአገር ውጪም ደሃ የሆነ ኢትዮጵያዊ አለ፡፡ እዚያም ቢሆን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ያላቸው ብዙ ናቸው፡፡ በሌላ አንፃር ደግሞ ለዲያስፖራ ተብሎ የተለየ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ወጥቷል፡፡ ይህ መሆን የለበትም፡፡ ሊሠራ የሚችለውና የማይችለው መለየት አለበት፡፡ አገር ውስጥ ያለውም ኢትዮጵያዊ መጠቀም ይኖርበታል፡፡ “እኔ ለምሳሌ ቤት የነበረበትን ቦታ ከግለሰብ ገዝቼ ነው ወደ ልማት የገባሁት፡፡ መንግሥትንም መሬት አልጠየኩም፡፡ በዚህ መልኩ የሠሩ ዲያስፖራዎች አሉ፡፡ ዲያስፖራ ተብለው መሬት ተሰጥቷቸው ሊያበረክቱ ከሚችሉት በላይ የተጠቀሙ አሉ፡፡ መሬት ተቀብለው ወደ ሥራ ያልገቡ አሉ፡፡ ለመሬትም ሆነ ለሌላ ለዲያስፖራ ተብሎ የተለየ ፖሊሲ መኖር የለበትም፡፡ በአገር ላለውም ሆነ ለዲያስፖራው አመቺ የሆነ የኢንቨስትመንት ድባብ ነው የሚያስፈልገው” ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትንሽ ገንዘብም ይዘው መጥተው ቤት መሥራት ይችላሉ፡፡ እዚያም ቢሆን መኖር የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ችግር ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ነው የሚሉት አቶ ኃይለሚካኤል፣ በኢትዮጵያ የተማሩና የዩኒቨርሲቲ መምህራን ወጪያቸውና ገቢያቸው አይመጣጠንም፣ በመሆኑም አገር ጥለው ይሄዳሉ፡፡ እነዚህ አገር ጥለው እንዳይሄዱ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ዲያስፖራውን ብቻ ለማምጣት ጊዜ ከማጥፋት እዚህ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን የኢኮኖሚ ሁኔታ ማስተካከል፣ ገቢያቸውን ከሚሠሩት ሥራ ማመጣጠን፣ ኢትዮጵያን እንዲወዱና ኑሮዋቸውን እያሻሻሉ እንዲቆዩ ማድረግ ተመራጭ መሆኑንና አገር ውስጥ ባለውና በዲያስፖራው ልዩነት መፈጠር እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ ዲያስፖራው እንደ ልዩ የልማት አጋር ተቆጥሮ እንዲመጣ ይደረግና መሬት ይሰጣል፡፡ ከአንድ በላይ የሚያገኝም አለ፡፡ ነገር ግን ምን እየሠራበት እንደሆነ እንኳን ጥናት አይካሄድም፡፡ ከሚያገኘው ጥቅማጥቅም አንፃር የሚሠራው ሥራ አይታይም፡፡ መሬት አግኝተው ገንዘብ ስለሚያጥራቸው አይሠሩበትም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን መሬት አጥቶ ቤት ሰርቶ ለመኖር የተቸገረ አለ፡፡ መንግሥት ማድረግ ያለበት ከውጭ የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ያለባቸውን የመረጃ ችግር መፍታት ነው፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያለውንም የዲያስፖራ ቢሮ ሕዝቡ በቅጡ አያውቀውም፡፡ “እኔ አገሬ ገብቼ ከዓመት በኋላ ነው መኖሩን ያወቅሁት.. ይላሉ፡፡ ለዲያስፖራው ማበረታቻ ከማድረግ ይልቅ በአገራቸው ገብተው ምን መሥራትና ከምን መጠንቀቅ እንዳለባቸወም መረጃ መስጠት ይገባል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የተለወጡ ሁኔታዎች አሉ፡፡ “እኔ በመጣሁበት በ1993 ዓ.ም ገደማ ከውጭ የመጣነው የተሻለ ገንዘብ ነበረን፡፡ በአሁኑ ደረጃ ሲታይ አገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያውያን የበለጠ ሃብታም ናቸው፡፡ ከውጭ የሚመጣው ከጥቂቱ በስተቀር አገር ውስጥ ካሉት ጋር የመወዳደር አቅም የለውም፡፡ ከዚያ መጥተው አገር ውስጥ ካለው ኢትዮጵያዊ ይወዳደሩ፡፡ አገር ውስጥ ያሉትም ይበረታቱ” የሚል እምነት አላቸው፡፡ ዲያስፖራው ከአቅሙ፣ ከሚያስፈልገውና ከሚገባው በላይ እየተጠቀመ አገር ውስጥ ያለው መጐዳት የለበትም፡፡ ይህንንም ያህል ከሌላው ኢትዮጵያዊ ተለይቶ ክብደት ማግኘት አይገባውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቤት የሌለው ብዙ ደሃ አለ፡፡ ጠግቦ የማያድረው ብዙ ነው፡፡ በመሆኑም ዲያስፖራው ላይ ማተኮር ትቶ አገር ውስጥ ላለው ቅድሚያ መሰጠት አለበት፡፡ መጠለያ አጥቶ በየላስቲኩ የሚያድርና መግቢያ የሌለው ኢትዮጵያዊ ሞልቷል፡፡ ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ በአንፃሩ አቅሙ የፈቀደለት መጥቶ ገዝቶም መኖርም ሆነ መሥራት ይችላል፡፡ አቅም የሌለው ደግሞ ባለበት መኖር ይችላል፡፡ ኑሮውም አገር ውስጥ ካለው የተሻለ ነው፡፡ ፆሙን የሚያድር የለም፡፡ በተለያየ መልኩ ድጐማ ማግኘት የሚችል ነው፡፡ አገር ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ ግን ይህ እድል የለውም፡፡ በመሆኑም ትኩረት ለአገር ውስጥ ነዋሪዎችም መሰጠት አለበት ባይ ናቸው፡፡ ዲያስፖራው ከሪል ስቴት ባሻገርም በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች መሰማራት አለባት፡፡ ይህንን ለማድረግ በግለሰብ ደረጃ ከባድ በመሆኑ ተደራጅቶ መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ለመሰማራት ገንዘብ ያላቸው ጥቂት ሰዎች ቢኖሩም የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በመፍራት ገንዘባቸውን ኢንቨስት ማድረግ አይፈልጉም፡፡ እዚህ ላይ መንግሥት የበኩሉን መሥራት አለበት፡፡ ዲያስፖራዎች ከሪል ስቴትና ከአገልግሎት መስጠት ባሻገር በኢንዱስትሪዎች መሰማራት ካልቻሉ አገር ውስጥ ላለው ኢትዮጵያዊ የሚያበረክቱት ዘላቂ የሥራ መስክ አይኖርም፡፡ ህንፃዎችም ተገንብተው ያልቃሉ፡፡ በግንባታ ሥራ የነበሩት መልሰው ሥራ አጥ ይሆናሉ፡፡ ፋብሪካዎች ቢከፈቱ ግን ኢትዮጵያዊውም ለዘለቄታው ሰርቶ ራሱን የሚያሻሽልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለዲያስፖራው ጥቅማጥቅሙን ከማስከበር በዘለለ ለአገሪቱ ዘላቂ ልማት እንዲያመጣ የሚደራጅበትን መንገድ ማመቻቸት ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡ በምሕረት ሞገስ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |