Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ከሸራተን የተፈናቀሉ የአልታድ መንደር...
ከሸራተን የተፈናቀሉ የአልታድ መንደር... Print E-mail
Sunday, 16 March 2008
ከሸራተን የተፈናቀሉ የአልታድ መንደር ነዋሪዎች ካርታና ፕላን እንዲሰጣቸው ጠየቁ

በሸራተን ግንባታ ምክንያት ከፍል ውሃ ተፈናቅለው በሲ ኤም ሲ አካባቢ የሰፈሩ የአልታድ መንደር ነዋሪዎች በሼህ መሐመድ አል አሙዲን በነፃ ተሰርቶ ለተሰጣቸው ቤት ካርታና ፕላን አለማግኘታቸውን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገለፁ፡፡

ሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲን በገቡት ቃል መሰረት ምትክ ቤት ተሰርቶ እንደተሰጣቸው የሚገልጹት የአልታድ መንደር ነዋሪዎች፣ እስከአሁን ድረስ የቤት ባለቤትነት ማስረጃና የስም ይዛወርልን ጥያቄዎቻቸው እንዳልተመለሱላቸው ይናገራሉ፡፡

የአልታድ መንደር ነዋሪዎች እየደረሰባቸው ስላለው የመኖር ኅልውና ጥያቄ አስመልክተው ለከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ በፃፉት ደብዳቤ፣ ለመዝናኛና ለአረንጓዴ አካባቢ የተከለሉት ክፍት ቦታዎች በግለሰቦችና በጉልበተኞች እየተወሰዱባቸው መሆኑን፣ በጊዜያዊነት የተመደቡት የቀበሌ አመራሮች ነዋሪዎችን በመጥራትና በማስገደድ “የመንግሥት ቤት ነው” ብላችሁ ፈርሙ እንደሚሏቸው የቀበሌ መታወቂያም ሆነ ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችንም የተባላችሁትን እስከሚያሟሉ ድረስ ምንም አይነት የትብብር ደብዳቤ ከቀበሌ ጽ/ቤት እንደማያገኙ መገለፁ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው አብራርተዋል፡፡

በሸራተን አዲስ ሆቴል ፕሮጀክት ግንባታ ምክንያት በአልታድ መንደር የሰፈሩት ነዋሪዎች የቤት ይፈቀድልን ጥያቄም የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ያመለከቱት የአልታድ መንደር ነዋሪዎች ጉዳዩ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ በሜድሮክ ኩባንያ በአንድ መቶ ሰላሳ ሺህ ሜትር የተከለለላቸው ቦታ በሙሉ በሳይት ፕላኑ መሰረት ተከብሮ እንዲቆይ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

ከአስራ አምስት ዓመት በፊት የአልታድ መንደር ቤቶች ስምምነት በተካሄደበት ጊዜ የመሬት ማስተላለፍ እና መረካከብ ውል የተፈፀመው በገበሬዎችና በባለሃብቱ መካከል እንደነበር የሚጠቅሰው የአልታድ መንደር ነዋሪዎች ማኅበር፣ በጉዳዩ ላይ አስተዳደሩ እንዳልተሳተፈ ያስረዳል፡፡ የቤቶቹ አሰራር ለህዝቡ ተሰርተው በነፃ እንደሚሰጡ በተገባው ቃል መሰረት ከባለሃብቱ ካዝና በወጣ ሂሳብ የተሰሩና በስጦታ ውል መሰረት ችሮታና ዳረጎት ከመሆኑ ውጭ ሌላ የመንግሥት ካዝና የሌለበትና ከእዳ ነፃ መሆኑን ማኅበሩ ይገልፃል፡፡

የፈረሱ ቤቶች ግምት ዝርዝር ወጥቶ ተከፍሎባቸዋል፡፡ በቁ/ቦ/ክ/ከ/ ቀ14/15/4458/97 በተጠየቀው ደብዳቤ መሰረት ሠላሳ አምስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ዘጠና ሶስት ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ስምንት ብር ለመከፈሉ ማረጋገጫ እንዳለ ማኅበሩ ያስረዳል፡፡

ነባር ባለይዞታነትን በሚመለከት ከአስራ አምስት አመት በፊት ከፍልውሃ አካባቢ የተነሱ ነዋሪዎች የምትክ ቤቶች መስሪያ በ160 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ሲከለል የነበሩ ነባር ባለይዞታዎች 15 ገበሬዎች ብቻ እንደነበሩ የጠቀሰው የአልታድ መንደር ነዋሪዎች የሥራ ማኅበር የእነዚህ 15 ገበሬዎች ጥቅምና የሂሳብ ክፍያ በወቅቱ እንደተፈፀመላቸው አመልክቷል፡፡

በሕገ መንግሥት አንቀጽ 40(1) እና 43(1) መሰረት በሕግ አግባብ ያገኙትን ንብረት የማፍራትና የልማት ሥራ የመስራት መብታቸው በፍርድ ቤት ውሳኔ ካልሆነ በስተቀር በደንብ ማስከበር ሽፋን ሊነጠቁ እንደማይችሉ ነዋሪዎቹ ያብራራሉ፡፡

ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉት ወ/ሮ ሙሉዬ በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ በመሆናቸው ለማነጋገር አልቻልንም፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ውብሸት ብርሃኑም ስለተባለው ጉዳይ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልፀውልናል፡፡

በኃይሌ ሙሉ

 
< Prev   Next >