| ከኢትዮጵያ ኬንያ የሚዘረጋው የኤሌክትሪክ... |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
![]() አቶ ምህረት ደበበ ከግልገል ጊቤ ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እስከ ኬንያ ድረስ ለሚዘረጋው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ከ500 ሚሊዮን ዩሮ በላይ እንደሚፈጅ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምህረት ደበበ መጋቢት 4 ቀን 2000 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በተደረገ የልማት አጋሮች ስብሰባ ላይ ገለፁ፡፡ ለኢትዮ ኬንያ ትራንስሚሽን ፕሮጀክት በአጋርነትና ብድር በመስጠት ከሚተባበሩ አገሮችና ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመነጋገር በሚል በተደረገው ስብሰባ ላይ ኢትዮ-ኢታሊ፣ ኢትዮ- ቻይና፣ ኢትዮ-ጀርመን፣ ኢትዮ ፈረንሣይ፣ ዓለም ባንክ፣ የፈረንሳይ የልማት ባንክና ፒቲኤ ባንክ ተወካዮች የተገኙ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ምህረት፣ "ዛሬ የተገኙትን የጉዳዩ ባለቤቶች ስናይ ሥራችን በጣም የተሳካ ነው ማለት ይቻላል"ብለዋል፡፡ የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ በጊቤ ሦስትና በኢትዮ ኬንያ መስመር መዘርጋት ሥራ ላይ ያተኮረ መሆኑን፣ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ፍላጎት፣ በተለይ ለኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት፣ እንዲሁም የአካባቢን ጠቀሜታ ከማሟላት ባሻገር፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚክ ስትራቴጂክ አቅም የመገንባት እድል ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡ “የልማት አጋሮቻችን ሊረዱን በሚያስችል መልክ ዝርዝር የሆነ አቀራረብና የፋይናንስ ምንጭን ዋስትና ማግኘት፣ አገር አቀፋዊና ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ፕሮጀክቶች፣ አንዳንድ ተቀናቃኞች የፕሮጀክቶቹን ትክክለኛ ገጽታ ከማንፀባረቅ ይልቅ አዛብቶ የማስተላለፍን ሁኔታ ለማስወገድ በስብሰባ ላይ ግልጽ ውይይት ማድረግ ጠቃሚነቱ የጎላ ነው” በማለት አቶ ምህረት አብራርተዋል፡፡ ሁሉም አጋሮቻቸው መገኘታቸውን ፋይናንስ የመልቀቅ እምነታቸውን አጠናክረው ይሄዳሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ምህረት ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች (የኢትዮ - ኬንያ) ኃይል ማስተላለፍ ፕሮጀክት ጥናት በሚያዚያ ወር 2000 እንደሚደርስ፣ ሁሉም የጉዳዩ ባለቤቶች አስተያየት ከተካተተበት በኋላ ለስምምነት ፊርማ እንደሚቀርብ አቶ ምህረት ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ ለአገር አቀፍና ለዓለም አቀፍ ተጫራቾች ጨረታ በማውጣት እንዲሳተፉ ተደርጎ፣ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ግንባታው እንደሚጀመር ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ግዙፍነትና በቴክኖሎጂው ውስብስብነት፣ ግንባታው በ2010 (እ.ኤ.አ) እንደሚጠናቀቅ የገለፁት አቶ ምህረት፣ የቶፓግራፊንግና ዲዛይን ሥራው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |