| የሲሚንቶ እጥረት እንደገና |
|
|
| Sunday, 16 March 2008 | |
|
የሲሚንቶ እጥረትን ለመቅረፍ ከአንድ ዓመት በፊት ሕጋዊ የውጪ ምንዛሪ ያላቸው ባለሀብቶች ሲሚንቶ ከውጪ አስመጥተው እንዲሸጡ፣ የተሰጠው ፈቃድ ባለፈው ሐሙስ በድንገት እንዲነሳ መወሰኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሲያስታውቅ ለእርምጃው ትልቅ መነሻ ያደረገው ባለሀብቶቹ የውጪ ምንዛሪን ጤናማ ሂደት አውከዋል የሚል ነበር፡፡ በእርግጥም የአንድ ዶላር ምንዛሪ ዋጋ ወደ አስር ብር አሻቅቧል፡፡ ግን ምክንያቱ የሲሚንቶ አስመጪዎች የተፈጠረ ችግር ነበር የሚለው እራሱን የቻለ ጥናት ማድረግን እንደሚጠይቅ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
መንግሥት በሀገር ውስጥ የሲሚንቶ እጥረት የፈጠረውን ቀውስ ተገንዝቦ በይፋ ባለሀብቶች የራሳቸው የውጪ ምንዛሪ (በፍራንኮቫሉታ) ከውጪ ገዝተው እንዲያስገቡ በመፍቀድ ለመጀመሪያ ጊዜ የሼክ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ ኩባንያ ከሆነው ደርባ ሲሚንቶ ጋር ሰኔ 22 ቀን 1998 ዓ.ም በሸራተን ሆቴል ተፈራረመ፡፡ ይህ ስምምነት ወዲያውኑ “ለምን ደርባ ብቻ?” የሚል ጫጫታ በማስነሳቱ በ1999 ዓ.ም መግቢያ በውጪ ሀገር የውጪ ምንዛሪ እንዳላቸው ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ድርጅቶች በፍራንኮቫሉታ ሲሚንቶ እንዲያስመጡ ተፈቀደ፡፡ በወቅቱ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ከሼክ አልአሙዲ በስተቀር የውጪ ምንዛሪ አለኝ ብሎ የሚቀርብ ኢትዮጵያዊ ባለሀብት አይኖርም የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም በሚገርም ሁኔታ 15 ገደማ ነጋዴዎችና ኮንትራክተሮች መመዘኛውን አሟልተው ፈቃድ ለማግኘት የቻሉት በዚያው ሰሞን ነበር፡፡ በዚህ ወቅት አብዛኛው ሕዝብ የሚጠቀምበት ፒፒሲ የተሰኘው የሲሚንቶ ምርት ከብር 195 - 205 ብር በኩንታል በገበያ ላይ ይሸጥ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኮንስትራክሽን ፍላጎት ለማሟላት ከሙገር፣ ከድሬዳዋ ሲሚንቶ፣ ከመሰቦ ከሚገኙ ምርቶች በተጨማሪ ከአንድ ዓመት በፊት በዓመት ተጨማሪ ከ12 - 15 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ጉድለት መኖሩ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም የቱን ያህል የገዘፈ መሆኑን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ የሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ በዓመት እያመረተ ያለው 8.5 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን የመሰቦም ምርት እምብዛም የሚበልጥ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሥራ የጀመሩት ደርባ ሲሚንቶ ቁጥር አንድ፣ አቢሲኒያ እና አዲስ ቆቃ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች እጥረቱን ለማቃለል የራሳቸውን አስተዋፅኦ ቢኖራቸውም በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት አሁንም ሰፍቶ መቀጠሉን ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ አገሪቱ በትንሹ በዓመት 1.2 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ጉድለት እያለባት በፍራንኮቫሉታ ከውጪ እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው ነጋዴዎችና ኮንትራክተሮች ባለፉት 15 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ያስገቡት 965 ሺህ 351 ቶን ሲሚንቶ መሆኑ ሲታይ ከውጪ ሀገር ሲሚንቶ እይገባም ፍላጎቱንና አቅርቦቱ አለመጣጣሙን፣ አሁንም ትልቅ ጉድለት መኖሩን ያሳያል ይላሉ፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በፍራንኮቫሉታ ፈቃድ የወሰዱ ሲሚንቶ አስመጪዎች በገቡት ውል መሠረት የራሳቸውንና በውጪ ሀገር አለን ያሉትን የውጪ ምንዛሪ ከመጠቀም ይልቅ ከሀገር ውስጥ ጥቁር ገበያ በብዛት ወደመጠቀም ማድላታቸው የውጪ ምንዛሪ ጤናማ ሂደት ለማዛባት አንድ መንስኤ መሆናቸውን ባለሙያዎቹ ይስማማሉ፡፡ ሆኖም ሲሚንቶ እንዳይገባ አድርጎ እጥረት ከመፍጠር ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መንግሥት ማጥናት ነበረበት ይላሉ፡፡ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ዓለም አቀፍ ኮንትራክተሮችን አሁንም ከውጪ ሲሚንቶ እንዲገዙ የሚፈቀድበት ሁኔታ መኖሩን ፍንጭ መገኘቱ ጥሩ ነገር መሆኑን የሚገልፁት ባለሙያዎቹ ለሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮች፣ ለግል ተጠቃሚዎች ባሉት ጥቂት ፋብሪካዎች ብቻ እንዲራኮቱ ከማድረግ እንደ ጅንአድ ያሉ መንግሥታዊ ፋብሪካዎች በአቅርቦቱ ሥራ ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ መመቻቸት ነበረበት ይላሉ፡፡ ባለፈው ዓርብ ዕለት የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ ከ210 -220 የተሸጠ ሲሆን ምናልባትም ከውጪ ሀገር ሲሚንቶ እንዳይገባ ከመከልከሉ ጋር በተያያዘ ዋጋው ከዚህም በላይ እንዳያሻቅብ ባለሙያዎቹ ብርቱ ሥጋት አላቸው፡፡ በፍሬው አበበ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |